Saturday, 12 July 2014 12:27

“ሚሚ እንደ አዲስ እንደተፈጠረች ነው የሚቆጠረው”

Written by  ኤልሳቤት ዕቁባይ
Rate this item
(0 votes)

      ህፃን ሚሚ ጠባየ-ወርቅ ናት፡፡ ፎለፎል ናት። ሥራ ስትሰራ ጠንቃቃ ናት፡፡ ለመታዘዝ ዝግጁ ስለሆነች ለማዘዝ ቀለል ያለች ናት፡፡
ሚሚ ኃይሉ ከልጅነቷ ጀምሮ ወገቧና ትከሻዋ መካከል ባለ አኳላ ላይ የወጣው ትርፍ ጉባጭ  (Hunchback) በሰውነቷ ላይ ይታያል፡፡ ለግላጋ ቀይ ቆንጆ ልጅ ነች፡፡
ሚሚ ሀይሉን ልናነጋግራት እንደምንፈልግ ለአቶ ዓለምሰፋ ባለቤት ለወ/ሮ ገነት ስንጠይቃቸው “በደስታ! እጠራላችኋለሁ” ብለው ወደ ሚሚ ደወሉ። ሚሚ የ13 አመት ታዳጊ ህፃን ናት። የተወለደችው ጉራጌ ውስጥ ዶባ የሚባል ቦታ ነው። አዲስ አበባ የመጣችው በ2000 ዓ.ም ነው። ያኔ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላም ትምህርቷን ቀጥላለች፡፡ የአጎቷ በሆነውና ካዛንቺስ በሚገኘው “አለምሰፋ ሥጋ ቤት” ውስጥ ጊዜ ሲኖራት በመምጣት ስራ የምታግዘው ሚሚ፤ ሳታስበው ነው በዚያው ምግብ ቤት ህይወቷን የሚለውጥ አጋጣሚ የተፈጠረው፡፡
“ፈረንጆቹ ለወገቤ መድሀኒት እንዳለ ነገሩኝና ወገቤን ለመሰራት (ትርፍ አካሉን አስወግዶ ማስተካከል) ወደ ጋና ሄድኩ፡፡ በአውሮፕላን መሄድ ያስፈራል፤ ልቤ በጣም ፈራ፡፡” (ያም ሆኖ ሚሚ ጋና በሰላም ደረሰች፡፡)
“ሆስፒታል ገብቼ ህክምናው ከተካሄደልኝ በኋላ፤ “በጣም ደስ አለሽ ወይ?” አሉኝ፡፡ እኔም በጣም እንደተደሰትኩ ነገርኳቸው፡፡ ወገቤ ላይ ወጥቶብኝ የነበረውን ትርፍ ጉባጭ (Hunchback) አካል በማደንዘዣ ለማስወገድ ሲሰሩልኝ አልተሰማኝም ነበር፡፡ ስነቃ በጣም አመመኝ፡፡ ወገቤን ስለተሻለኝ ግን ደስ ብሎኛል፡፡ ወገቤ ያበጠ ስለነበር ጠፍቶ ሳየው በጣም ደስ አለኝ፡፡ ዶክተሩን አመሰግናለሁ” ስለው “ምንም ማለት አይደለም” አለኝ፡፡ እኔ ድሮም ቢሆን ከተማርኩ በኋላ ሀኪም መሆን እፈልጋለሁ ስል ነበር፡፡ እንደሌሎች ጤነኛ ሰዎች ስለሆንኩ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ወገቤን እንድታከም ያደረጉትን ሰዎች በሙሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በተለይ መንክርን (ባርቾን) በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡
ባርቾ (መንክር) ስለሚሚና ህክምናዋ ምን ይላል?
መንክር ይርጋ የሚሚ የአክስት ልጅ ነው፡፡ ወደ ጋና ለህክምና ስትሄድ ሀላፊነቱን በመውሰድ የፈረመውም እሱ ነበር፡፡ ሚሚ ስላገኘችው እድል የሚከተለውን አጫውቶናል፡፡
ሚሚ ሰው ስትንከባከብ እንደ እናት ናት፡፡ በትምህርቷም ጎበዝ ናት፡፡ ጀርባዋ ላይ በነበረው እብጠት ምክንያት ቶሎ ሆድ ይብሳት ነበር፡፡ እብጠቱ ከጊዜ በኋላ ቀስ እያለ እየጎላ የመጣ ሲሆን ከዚህ በፊት ምንም አይነት ህክምና አድርጋ አታውቅም።  ሚሚ እንደሁልጊዜው ስራ እያገዘችን ነበር፡፡ ለደንበኞች ትኬት እየሰጠች ገንዘብ ትቀበላለች። በዚህ መሀል የቤቱ ደንበኞች የሆኑ የውጪ አገር ዜጎች ያዘዙት ምግብ እስኪመጣ እየጠበቁ ባሉበት ሰአት ሚሚን አይዋትና በአስተርጓሚያቸው አማካኝነት “ስለዚህች ልጅ የምናነጋግረው ሰው ጥሩልን” አሉ፤ እሷም እኔን አስጠራችኝ፡፡ ሄጄ ሳናግራቸው ሚሚ የምትታከምበት እድል እንዳለና ፈቃደኛ እንደሆንን ጠየቁኝ፡፡ ያለምንም ማመንታት ተስማማሁ፡፡ ጀርባዋ ላይ ያለው እብጠት መንስኤ ከቲቢ ጋር የተያያዘ እንዳይሆን ተብሎ ስድስት ወር የቲቢ ህክምና አደረገችና የጋና ጉዞዋ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡  ከመሄዷ በፊት የሚፈረም ሰነድ ስለነበር፣ ፈርሙ ሲሉን ትንሽ ፈራን፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ሰዎች ይዘው ሄደው የሞተና ፓራላይዝድ የሆኑ እንዳሉ እንዲሁም በህክምና ላይ ድንገት ህይወቷ ቢያልፍ አስከሬኗ እዚህ እንደማይመጣ ስለነገሩን ሰግተን ነበር፡፡ በኋላ ግን አደራውን ለፈጣሪ ሰጥተን ላክናት፤ እሱም አላሳፈረንም፡፡ ሚሚ እንደ አዲስ እንደተፈጠረች ነው የሚቆጠረው፡፡
የፈረንጆቹ አስተርጓሚ ራሱ እንደ ሚሚ ትርፍ ጉባጭ (Hunchback) የነበረው ሲሆን ታክሞ ነው የዳነው፡፡ ዛሬ ከፈረንጆቹ ጋር ይሰራል፡፡
ስለልጆች ጨዋታ ስትጠየቅ፤ “ገመድ መዝለል በጣም የምወደው ጨዋታ ነው!፡፡” ትላለች፡፡ ስለአካላዊ ሁኔታዋ ስታስታውስም፤ “የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ምን ሆነሽ ነው ሲሉኝ በጣም አለቅስ ነበር፡፡ ሀኪሙ ረጅም መንገድ መሄድ ትችያለሽ ካለኝ በቅርቡ አገር ቤት እሄዳለሁ፡፡ እናት እና አባቴን በጣም ናፍቄያቸዋለሁ፡፡ እኔ በጣም መሄድ ፈልጌያለሁ፣ተሽሎኝ እንዲያዩኝም እፈልጋለሁ፡፡ በስልክ እንደታከምኩ ስነግራቸ፣ ለእግዚአብሄር ምን ይሳነዋል አሉ፡፡ ጓደኞቼም ሰምተዋል፤ በጣም ደስ ብሏቸዋል፡፡
ጋና ሳለች ምን ትመገብ እንደነበር ጠየቅናት “ጋና ምግቡ በብዛት ሩዝ ስለሆነ እንጀራ በጣም ናፍቆኝ ነበር፡፡ ዝላይ ከአመት በኋላ ስለሚፈቀድልኝ ያኔ እዘላለሁ፡፡ ኳስ መጫወትም እወዳለሁ፡፡ የብራዚል ደጋፊ ነኝ፡፡ ሲሸነፉ ላለቅስ ነበር፤ ከዚያ ተውኩት፡፡ ፑሽ-አፕ መስራትም እወዳለሁ፡፡” ስትል መለሰችልን።
የሚሚ ሀይሉ አሳዳጊ አቶ ዓለምሰፋ ኤርማቶ (የዓለምሰፋ ሥጋ ቤት ባለቤት) ሚሚ ወደ ጋና ስትላክ የመኖሪያ ቀበሌው ጽህፈት ቤት አስፈላጊውን የመሸኛ ደብዳቤ በመፃፍ ያደረገላትን ትብብር አድንቀዋል “ሁሉም ቀበሌዎች እንደሚሚ ዕድል ላገኙ ታማሚዎች ድጋፍ ማድረጋቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሚሚን ወስጄ ላሳያቸው እፈልጋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡  

Read 2686 times