Saturday, 12 July 2014 12:03

ዶ/ር አሸብር በቀጣዩ ምርጫ ለመወዳደር አልወሰኑም

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(5 votes)

የዛሬ አራት ዓመት በ2002 ዓ.ም ምርጫ ነው በከፋ ዞን ጊንቦ ቦንጋ ላይ ተወዳድረው በማሸነፍ ፓርላማ የገቡት፡፡ “የኢህአዴግ ደጋፊ፤ የግል ተወዳዳሪ” በሚል ራሳቸውን የሚገልፁት የፓርላማ አባሉ፤ በወቅቱ ከኢህአዴግ ጋር የተወዳደሩት በአካባቢው የቀርቡ ተፎካካሪያቸው ባደረሱባቸው በደል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን ባይወዳደሩ እንደሚመርጡም ገልፀዋል - ዶ/ር አሸብር፡፡ የግል ተመራጭ ቢሆኑም በአራት ዓመት የፓርላማ ቆይታቸው ኢህአዴግን በመደገፍ ከፓርቲው አባላት ባልተናነሰ የመንግስትን ዓላማና ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በመጪው ምርጫ ስለመወዳደራቸው ገና ያልወሰኑት ዶ/ር አሸብር፤ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በኢኳቶሪያል ጊኒ የተካሄደውን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ተሳትፈው የተመለሱት የፓርላማ አባሉ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ጋር ስለ ጉባኤው፣ ስለፓርላማ ቆይታቸው፣ በም/ቤት አባልነታቸው ስላበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ስለፀረ ሽብር ህጉና ሌሎች ጉዳዮች በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ:-


አሁን ደስ የሚለኝ ኢህአዴግን በድጋሚ ባልወዳደር ነው
ፓርላማ ትልቅ ዕውቀት ያገኘሁበት የፓለቲካ     ት/ቤት ነው


           የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ተካሂዶ ነበር፡፡ የጉባዔው ዓላማ ምን እንደነበርና ስለእርስዎ ተሳትፎ ይንገሩኝ..
የፓን አፍሪካ ፓርላማ እንደ አንድ የሕብረቱ አካል እንሳተፋለን፡፡ በስብሰባው ለአስር ቀን ያህል ተካፍለናል፡፡ የፓን አፍሪካ ፓርላማን ወደ ህግ አውጪነት ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት የሚል ውይይት ተካሂዷል፡፡ የአፍሪካ ህዝቦችን ሙሉ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚቻለው በህዝቦች የተመረጡ የፓርላማ አካላት ሲኖሩ እንደሆነ ታምኖበት፤ ከዚህም አኳያ ፓርላማው ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ (ሞዴል ሎው) ህጐችን እንዲያወጣ፣ በአህጉሪቱ ላይ ሊተረጎሙ ሊሰሩ የሚገቡ ህጎችን በራሱ ተነሳሽነትም ሰርቶ ለመሪዎች ውሳኔ እንዲያቀርብ..የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡ መሪዎች በወቅቱ አስፈላጊ ነው የሚለውን ህግ የማመንጨቱ ስራ የራሳቸው ሆኖ፤ ፓርላማው ደግሞ ያንን እነሱ በጠቆሙት መንገድ ህግ አውጥቶ ያቀርባል፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበረ ተጨማሪ ስልጣን ነው ለፓን አፍሪካ የተሰጠው፡፡
በሌላ በኩል በአጠቃላይ በአፍሪካ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ችግር ላይ ያሉ የአፍሪካ አገራት፡- ደቡብ ሱዳን፣ ሴንትራል አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ማሊ፣ ሊቢያ… በብዙ አገራት ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በአፍሪካ ኢንተግሬሽን በተለይም የአፍሪካ አገራት በንግድ፣ በኢንዱስትሪ የሚተሳሰሩበትን ሁኔታ ውይይት ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥሬ እቃ ያለው በአፍሪካ ነው፤ ነገር ግን ያለውን አውቆ ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ፣ የስራ ዕድል መፍጠር፤ ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ የሚቻለው ሀገራት በአንድ ላይ መስራት ሲችሉ እንደሆነ… በአንዱ አገር ላይ ያለ እውቀት በሌላ አገር ያለውን ጉልበት መጠቀም ሲችል፣ በአንዱ አገር ያለውን ገንዘብ በሌላው አገር ያለው ጉልበት መጠቀም ሲችል… በሚል የእርስ በእርስ ትስስሩ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የአፍሪካ ዳያስፖራዎች በአፍሪካ ጉዳይ መሳተፍ የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻች ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከአጋር አገራት የአውሮፓ ህብረት፣ የፓሲፊክ፣ የአሜሪካ፤ የሩሲያ ወኪሎቻቸው ተገኝተዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፀሃፊ ነበሩ፤ ሰፊ ውይይት ነበር የተካሄደው፡፡ እኔ በእጅጉ ደስ ያለኝ ነገር፣ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ፣ አብዛኛውን  ስብሰባ የመሩት ክቡር ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ አሁን እሳቸው የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ መሪ አይደሉም፡፡ አዲሱ የወቅቱ ሊቀመንበር ስብሰባውን እንዲመሩ ውክልና የሰጡት ለጠ/ሚኒስትሩ ነበር፡፡ የስብሰባ ተካፋዩም በደስታ ነበር የተቀበለው፡፡ ያ ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን ተቀባይነት የሚያሳይ ነው፡፡ እኔም በዚሁ ወቅት የጉባዔው አካል በመሆኔ በእጅጉ በሀገሬ ኮርቻለሁ፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተነሱ ነጥቦች ምን ነበሩ?
ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች በምሳሌነት ስትገለፅ ነበር። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሪዎችን ጨምሮ የአውሮፓ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአፍሪካ መሪ ከድህነት እንዴት መላቀቅ እንደሚቻል ከኢትዮጵያ ተማሩ፣ የኢትዮጵያን ፈለግ ተከተሉ እያሉ ሲናገሩ ነበር፡፡ አዳራሽ ውስጥ በመሆኔ በጣም እድለኛ ነበርኩ፤ የተለያዩ መሪዎች የኢትዮጵያን ምሳሌ ተከተሉ ሲሉ ስሰማ እጅግ ነው የተደነቅሁት፡፡ በሰላም፣ በእድገት እንደምሳሌ ትነሳ ነበር። ኢትዮጵያ ሲባል መሬቱን ብቻ አይደለም፤ ህዝቡን አመራሩን፣ ፖሊሲውንም ጭምር ነው፡፡ አፍሪካ ላይ የምግብ ዋስትና እንዴት ማረጋገጥ እንደተቻለ በምሳሌነት የተጠቀሱት ሁለት አገራት በቀዳሚነት ኢትዮጵያ ቀዳሚ ስትሆን ሩዋንዳ ትከተላታለች፡፡ የሰላም አስከባሪ ሃይል በአፍሪካ በማሰማራትም የትብብርና መልካም ግንኙነት ተምሳሌት መሆኗ ተገልጿል፡፡
ብዙ ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች በሙስና ይወነጀላሉ፤ ከዚህ አንፃርስ የተነሱ አጀንዳዎች ነበሩ?
በአፍሪካ ደረጃ የአፍሪካ የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ድርጅቱ ከአፍሪካ ህብረት ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ አገራትም ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ነው፡፡ ሙስና ለእድገት ጠንቅ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይቻልም መቀነስ እንደሚቻል፣ ሙስናን የቀነሱ አገራትም እድገት እንዳመጡ ተገልጿል። ሙስናን በመዋጋት እድገት ማምጣት እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡ በማንኛውም አገር ሙስናን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አይቻልም፤ ነገር ግን ቀንሶ ተቆጣጥሮ መስራት እንደሚቻል ከኢትዮጵያ መማር ያስፈልጋል በሚል ተጠቅሳለች፡፡ መልካም አስተዳደር በአፍሪካ አገራት መስፈን እንዳለበት በማስረገጥም በጥሩ መንፈስ ውይይቱ ተካሂዷል፡፡
የአፍሪካ አገራት በፓርላማ የስራ ሂደታቸው ከምርጫ ጋር በተገናኘ የታዘቡትና ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ የሚሉት አሠራር አይተዋል?
የፓን አፍሪካ ፓርላማ መሪና ምክትል ፕሬዚዳንት ስለሆንኩ የአፍሪካ ሀገራትን ባህሪ አውቀዋለሁ፡፡ በተለያዩ የስራ አጋጣሚዎች አገኛቸዋለሁ፤ አብረንም ነው የምንሰራው፡፡ እርስ በርስ እንተዋወቃለን፡፡ ምርጫ ላይም ዞረን እንታዘባለን፡፡ ከዚህ አኳያ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አለበት ብዬ የማስበው በዚምባብዌ የታዘብኩትን ነው። በዚምባብዌ ምርጫ ላይ ነበርኩኝ፡፡ በምርጫ ሂደት አንድ ድምፅ ወሳኝ የሚሆንበት ወቅት አለ፡፡ በአንዱ ድምፅ የበለጠ ተወዳዳሪ አሸንፎ ፓርላማ የሚገባበት ብዙ አጋጣሚ አለ፡፡
በኢትዮጵያ ደረጃ ከ40 እስከ 50ሺ የምርጫ ታዛቢዎች አሉ፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች ብዙ ጊዜ ድምፅ አይሰጡም፡፡ የዕለቱ ዕለት ለመታዘብ ሲወጡ፤ የሚታዘቡበት ቦታ ከምርጫ ጣቢያቸው የራቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ዚምባብዌ ላይ ያየሁት፣ በጥበቃ ላይ የሚሰማሩ ፖሊሶች፣ ተወዳዳሪዎች፣ ታዛቢዎች መከላከያዎች ከምርጫው ቀን በፊት ድምፅ እንዲሰጡ ይደረግና ድምፃቸው በምርጫ ቦርዱ በኩል ሳጥኑ ታሽጎ፤ በዕለቱ አብሮ ይቆጠራል፡፡ ይሄ ለኢትዮጵያም ይጠቅማል። ምርጫን በተመለከተ ኢትዮጵያም ላይ ጎደሎ ነገር የለም። የአገሪቱ አቅም በፈቀደ የምርጫ ቦርድ በየደረጃው የተዋቀሩ አካላት አሉ፡፡ ምርጫዎችም፤ የምርጫ ስርአቱ በፈቀደው መሰረት በእኩል ሜዳ ይከናወናሉ፡፡ አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከት የአፍሪካ አገራትም ከኢትዮጵያ ብዙ ሊማሩት የሚችሉት ነገር አለ፡፡
በአፍሪካ አገራት በዘር፣ በሃይማኖትና በብሄር በመከፋፈል ግጭቶችና ጦርነቶች እየተከሰቱ ነው፤ ከዚህ አንፃር በአገራቱ ላይ ምን አይነት ተፅእኖ ለመፍጠር ታስቧል?
በአፍሪካ ኢኮኖሚው በባዕዳን የተያዘ ነው፤ ሀብቱ ጉልበት እየሆነ የዘር ጥያቄ የሚመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ ወደ ስልጣን ስንመጣ ግን በአህጉራችን ዋናው ችግር ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግና ካለማድረግ የሚመጣ ነው፡፡ አንድ ስርዓት ወደ ስልጣን በሚመጣበት ጊዜ ህዝቡን ከማገልገል ይልቅ የራሱን ጎሳ ለመጥቀም የመሞከር ሁኔታ ይታያል፡፡ ብዙ ጊዜ አፍሪካ ላይ ለተነሱ ችግሮች ምክንያት ነው ተብሎ የሚታሰበው ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ አለመደረጉ ነው፡፡ ምርጫ ከተደረገ በኋላ የምርጫ ውጤትን ላለመቀበል የሚኬድበት ሁኔታ አለ። ቁልፍ የአፍሪካውያን ችግር የሚመስለኝ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች፤ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ስለቆዩ ስጋት አለባቸው፡፡
ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ እስር ቤት እንገባለን ብለው ይሰጋሉ፡፡ ይሄ ደግሞ  ልቀቅ አለቅም ግብግብ ይፈጥራል። አፍሪካውያን ለቅኝ ገዢዎች የሰጠነውን ዓይነት ምህረት ለእነዚህ አንጋፋ መሪዎች በመስጠትና ከእነክብራቸው የአዲሱ ጉዞ አካል እንዲሆኑ በእኛም ሆነ በህዝቡ በኩል ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡
ፓን አፍሪካ ከተመሰረተ በኋላ የተሠሩ ስራዎች ምንድን ናቸው?
የተመሰረተበት አስረኛ አመት ማርች ላይ ነው የተከበረው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. ነው የተመሠረተው። መንግስታቱ ሲያቋቁሙት ትልቅ አላማ ይዘው ነው። ለፓን አፍሪካ ፓርላማ የህግ አውጪነት ስልጣን ለመስጠት ነው፡፡
በአፍሪካ ችግር ያለባቸው አገራት አካባቢ ዞሮ ፋክት ፋያንዲንግ ሚሽን በመላክ፤ ምርጫዎችን በመታዘብ፤ ከሌሎች አቻ ድርጅቶች ከአውሮፓ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ ከካሪቢያን፣ ከእስያ ፓርላማ ጋር በመገናኘት በርካታ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ አፍሪካን ወክሎ ስለ አፍሪካ ተሟግቷል፡፡ ከዚህም በላይ የአፍሪካ ፓርላማዎች ልምድ እንዲለዋወጡ፤ አንዱ ለአንዱ መልካም ስራውን እንዲያጋራ ሰፊ እድል ፈጥሯል፡፡ የፓን አፍሪካ ፓርላማ አሁን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ህግ የማውጣት ስራ ውስጥ መግባት አለበት ብለው መንግስታት መልካም ፍቃዳቸውን ያሳዩት፡፡ ከዚህ በኋላ ፓርላማው ሞዴል ህጎችን ማውጣት ስራዬ ብሎ ይጀምራል፡፡
ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚ፣ ህግ አስፈፃሚ አለ፡፡ በአፍሪካ ህግ አስፈፃሚዎቹ የኮሚሽኑ ቋሚ ተወካዮችና እዛው ያለው አካል ነው፡፡ ህግ አውጪው የፓን አፍሪካ ፓርላማ ቢሆን፣ ህግ ተርጓሚው አፍሪካን ሂዩማን ራይት ኮርት ነው፡፡ እነዚህ ጥረታቸውን አሳክተው መሄድ ከቻሉ፣ ትልቅ ውጤት ነው የሚመጣው፡፡ የአፍሪካ ድርጅት ሆኖ አፍሪካውያን የማይሳተፉበት ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡
በፓርላማ የግል ተመራጭ ሆነው የቆዩበትን ዘመን እንዴት አገኙት?
ፓርላማው ለእኔ የፖለቲካ ት/ቤት፤ ትልቅ ዕውቀት ያገኘሁበት፤ ትልልቅ ሰዎችን ያወቅሁበት፤ አገሬን በአህጉር ደረጃ መወከል የቻልኩበት ትልቅ ልምድ መቅሰሚያ የሃላፊነት፣ የአደራ፣ የክብር ቦታ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ፓርላማው ለእኔ ብዙ ነገር ነው፡፡ እንደ ህዝብ እንደራሴነት፤ የመረጠኝን ህዝብ ጉዳይ በቀጥታ አምጥቼ በውክልናዬ መሰረት ለአገሪቱ መሪ፣ ለመንግስት ማቅረብ የቻልኩበት ትልቅ ቦታ ነው፡፡ በምክር ቤቱ በተሰጠኝ ኃላፊነት መሰረት በኮሚቴ ደረጃ አስፈፃሚውን አካል በእቅዱ መሰረት ሪፖርቱን እያደመጥኩ፣ መቆጣጠር መከታተል የቻልኩበት ነው፡፡ አዋጆችን ህጎችን ማውጣት የቻልንበት ቦታ ነው፡፡ የህዝብን የስልጣን ሉዓላዊነትና የበላይነት ማረጋገጥ የቻልኩበት ቦታ ነው ለእኔ፡፡ ፓርላማን መምራት፣ አፈ ጉባኤነት… ምን ማለት እንደሆነ ትልቅ ትምህርት ያገኘሁበት ነው፡፡
በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የመወዳደር ሃሳብ አለዎት?
ባለፈው ምርጫ ለውድድር የገባሁት ገዢውን ፓርቲ በመቃወም አይደለም፡፡ ነገር ግን ከእኔ ጋር በአንድ ምርጫ ክልል ውስጥ የነበሩ ግለሰብ ባደረሱብኝ በደል ተነሳስቼ ነው፡፡ በወቅቱ ድርጅቱ ሌላ ሰው ቀይሮ ቢሆን ኖሮ አልወዳደርም ነበር፡፡ ግለሰቡ መወዳደር አለብኝ ብለው ድርጅቱን አሳምነው ስለተወዳደሩ ነው፤ እኔም ለዚህ ደረጃ የደረስኩት፡፡ አሁንም ደስ የሚለኝ ኢህአዴግን በድጋሚ ባልወዳደር ነው፡፡
እኔ ፓርላማ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ዓላማቸውን፣ ፖሊሲያቸውን በሄድኩበት አገር ሁሉ ሳስፈጽም ነበር። የአገሬንና የተሰጠኝን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣሁ፣ ከድርጅቱ አባላት ያላነሰ ስራ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ ከኢህአዴግ ጋር ባልወዳደር ደስ ይለኛል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ቆይቼ የማስብበት ነው የሚሆነው፡፡
ባለፈው የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት “የኢህአዴግ ደጋፊ፤ የግል ተወዳዳሪ” ብለው ነበር ራስዎን የሚያስተዋውቁት፡፡ አሁንስ ይኼን አላማ ይዘው ነው የሚጓዙት? የመረጠዎት ህዝብ ስሜት እንዴት ይገለፃል?
የመረጠኝ ህዝብ እኔን በመምረጡ አልተከፋም። እንደ አጋጣሚ ደግሞ ብቸኛው የግል ተመራጭ ስለሆንኩ በምክር ቤቱም ሰፊ ሰዓት አለኝ፡፡ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የአካባቢውን ችግሮች ለጠ/ሚኒስትሩም፤ ለአፈጉባኤውም፣ ለምክር ቤቱም፣ ለሚኒስትሮችም በማቅረብ የህዝብ ውክልና ስራዬን በአግባቡ ተወጥቻለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ ህዝቡ ደስተኛ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ያጎደልኩት ነገር የለም፤ ቢኖር እንኳን ይነግሩኛል፡፡ “ለምን ተመልሰህ አትገባም፤ ተወዳደርልን” የሚሉ አሉ፡፡ ለእኔ ግን ቀላል አይደለም፡፡ የቤተሰብ ሃላፊ ነኝ፤ የልጆች አባት ነኝ፤ ስራዬም እኔን ይፈልጋል፡፡ እንደዚህ ስልሽ ስራዬን የሚያግዘኝ፣ ኃላፊነቱን የሚጋራኝ የለም ማለቴ አይደለም፡፡ ባለቤቴም እጅግ ጠንካራ ሴት ናት፤ ወንድም ሴትም ሆና ከጐኔ ያለች አጋዤ ናት፡፡ እንደዚህም ሆኖ ጎደሎ ሊኖር ይችላል፤ ሊፈልጉኝ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቆም ብዬ ማሰብና መወሰን ይኖርብኛል፡፡
ኢህአዴግ አገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም በሚል ተቃዋሚዎችን ይተቻል፡፡ እንደግል ተወዳዳሪ ደግሞ እርስዎ በቀጣይ ምርጫ “ልግባ፣ አልግባ” የሚል ውሳኔዎትን አላወቁም፡፡ ይህ ሁኔታ የፓርላማውን እንቅስቃሴ አይጎዳውም?
አሁን ባለው አኳኋን መቶ ፐርሰንት አንድ ፓርቲ ብቻ በፓርላማ ቢኖር ነውር የለውም፡፡ ምክንያቱም የሰራውን ነው የሚያገኘው፡፡ አጭበርብሮ ሳይሆን ሰርቶ ነው፤ ህዝቡ አምኖለት፣ መርጦት ያሸነፈው፡፡ የአንድ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ በፓርላማ መታየት በሌሎች አገራትም ያለ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ ለረዥም ዓመት በስልጣን ላይ መቆየት በህንድና ጃፓን የተለመደ ነው፡፡ ወደዚህ ስንመጣ ገዢው ፓርቲ ከሚፈልገው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አኳያ፤ ይሄን እንዴት ሊያስኬደው እንደሚችል ማሰብ  ይኖርበታል፡፡ የእኔን በተመለከተ ስለራሴ መናገሩ ብዙም ላይመች ይችላል፡፡ ስለ እኔ መናገር የሚችለውና መመዘን ያለበት ፓርቲው ነው፡፡ “እንደ እኔ አባል ሰርቷል ወይ? የዓላማ ሰው ነው? ጥንካሬ አለው፣ የለውም?” ብሎ መመዘንና ፈተናውን ማሳለፍና መጣል ያለበት ራሱ ገዢው ፓርቲ ነው፡፡  
በተረፈ ግን እንደ አንድ ዜጋ በምክር ቤት ውስጥ የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ብገባም ባልገባም የሚያጓጓኝ ነገር የለም፡፡ እስካሁን የደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ ያበቃኝ ገዢው ፓርቲን፣ መንግስትን፣ የመረጠኝን ህዝብ ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ያልደረሰበት ደረጃ ነው የደረስኩት፡፡ ይኼንን ክብር የሰጠኝ ይሄ መንግስት ነው፡፡ የመቀጠል ያለመቀጠሉ ጉዳይ በእኔ ጉጉት ሊሆን አይገባም፡፡ “ለአገር ትጠቅማለህ ታገለግላለህ፣ አሁን አይተንሃል፣ ለዚህ ትመጥናለህ” ከተባልኩ የእነሱ ውሳኔ ነው የሚሆነው፤ አይ የእኛ አባል የግድ መውሰድ አለበት ከተባለም እኔ ግድ የለኝም፡፡ በየትኛውም መልኩ የሚያጓጓኝ ነገር የለም። የተመረጥኩበት አካባቢ ሄጄ በማነጋግራቸው ወቅት ተጨማሪ ጉልበትና ሀይል ሰጥተውኝ ነው የምመለሰው፡፡
ከተመረጡ በኋላ ለአካባቢው ማህበረሰብ ምን ለውጥ አመጡ?
መንግስት ለሁሉም ክልሎች በጀት ያለ ልዩነት ነው የሚመድበው፡፡ አይደለም ኢህአዴግ ላሸነፈበት አካባቢ ቀርቶ ተቃዋሚ ያሸነፉበት ቦታ ላይም የበጀት ልዩነት የለም፡፡ የአካባቢው ህዝብ ነው ማዕከል የሚደረገው፡፡ ብዙዎች መስዋዕትነት የከፈሉት በአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ነው፡፡ በጀት የሚወጣው ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ያለ ምንም አድልዎና ልዩነት ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ ሃላፊነት የተጓተተ ነገር ሲኖር ሄዶ መጠየቅ፣ ህዝብ የሚያነሳውን ጥያቄ ተቀብሎ ማድረስ፤ የሚታየውን ችግር ለመንግስት ማቅረብ ነው፡፡ በርግጥ በግሌ ሰራሁ የምለው ነገር የለኝም፡፡ የሚሰራው ስልጣን የያዘው መንግስት ነው፡፡ መንገድ፣ ውሃ፣ በጅምር ላይ ያሉ ሥራዎች አሉ፤ ብዙ ለውጦችም ይታያሉ፡፡ እኔ ስወዳደር በበቅሎ ነበር የምርጫ ቅስቀሳ ያደረግሁት፡፡ አሁን መንገድ ተሰርቷል። ይሄን የሰራው ያሸነፈው ፓርቲ፣ መንግስት ነው፡፡ እንደ ፓርላማ አባልነቴ የመንግስት አካል ስለሆንኩ አብረን ነው የምንሰራው፡፡ እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ፓርላማ በተመረጥኩበት ዘመን፤ የዚህ መንግስት የረጅም ጊዜ እቅዶች ተሳክተዋል፤ ህዝቡም ተጠቃሚ ሆኗል፡፡
በተረፈ በግል ለመሥራት ሞክሬ የተበላሹብኝ ነገሮች አሉ፡፡ በአካባቢው ቀድሜ ሆስፒታል ለመስራት የገባሁት እኔ ነበርኩ፡፡ አስተጓጉለውብኝ እስከ አሁን በፍርድ ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡
ሰሞኑን መንግስት የንግድ ማህበረሰቡን ሰብስቦ ሲያወያይ ነበር፡፡ በንግድ ማህበረሰብ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የግሉ ዘርፍ ብድር አያገኝም፤ ጫና አለበት፣ መንግስት በንግድ ዘርፉ ውስጥ ጉልበተኛ ሆኖ እየገባ ነው ብለዋል?
የግሉ ሴክተር በራሱ ጠንክሮ የትኛውንም ስራ ልስራ ካለ፣ መንግስት የማገዝ ፖሊሲ ነው ያለው፡፡ የግሉን ሴክተር ተክቼ ልስራ የሚል ፖሊሲ የለውም፡፡ መንግስት ሸቀጣ ሸቀጥ የማቅረብ ፍላጐት ኖሮት አይደለም የገባበት፡፡ ስንት ትላልቅ ፕሮጀክቶች እኮ አሉ፡፡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ አተኩሮ ግን ሸማቹ ሲሰቃይ መንግስት ቆሞ የማየት ፍላጐት ሊኖረው አይችልም፡፡ ክፍተቶችን ለማጥበብ መንግስት ጣልቃ መግባቱ የግድ ነው፡፡ ልማታዊ መንግስት ስለሆነ ክፍተቶችን ለመድፈን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ወቀሳው አይገባኝም፡፡
ህዝቡን ተጠቃሚ ላድርግ ከተባለ፣ እኔ እየሠራሁ ህዝቡ ተጠቅሟል ወይ ብሎ ማየት ነው፡፡ ብድርን አስመልክቶ እንዲሁ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ብድር ለራስም እዳ ነው፡፡ አሳማኝ የሆነ ፕሮጀክት መቅረብ አለበት፡፡ ባንክ ውስጥ ገንዘብ አለና መንግስት ለማንም አውጥቶ አያድልም፡፡ ጥናት አድርጐ አሳማኝ በሆነ መንገድ የስራ ዕድልን የሚፈጥር ከሆነ፣ በራስ በግል ገንዘብ የተወሰነ ርቀት ሄዶ ባንኩን አበድረኝ የሚል ከሆነ ባንኩ ገንዘብ መያዝ ምን ያደርግለታል?  አሁን እንደውም ተበዳሪ ነው የጠፋው፡፡
በሀገሪቱ ፓርላማ ከጊዜ ጊዜ ወደ የተቃዋሚ ቁጥር እያነሳ እየተመናመነ መጥቷል፡፡ ባለፈው ምርጫ ኢህአዴግ በ99.6 ፐርሰንት አሸንፎ ለአራት አመት ቆይቷል፡፡ በፓርላማ ውስጥ የተነቃቃና የተለያዩ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ በማድረግ በኩል በሚቀጥለው ምርጫ የተቃዋሚ ድርሻ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
በሚቀጥለው ምርጫ የውድድር ሜዳው እኩል መሆን አለበት፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ ይሁኑ፤ ደካማ አላውቃቸውም፡፡ ከእነሱ ጋር ግንኙነት የለኝም፡፡ እስከ 2002 ዓ.ም ምርጫ  የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቀራረብ ደከም ያለ ነው፡፡ ብዙ ዝግጅት አልነበራቸውም፡፡ በእኛ ዞን ምርጫ ተቃርቦ ሳለ፣ እጩዎቻቸውን በአንድ ምርጫ ጣቢያ አንድ ማቅረብ ሲገባ፤ ከአንድ ፓርቲ 4 እና 5 ሰው አቅርበው እርስበርሳቸው ሲጣሉ የምርጫው ጊዜ እንዳለፈ ነው የማስታውሰው፡፡ በቂ ዝግጅት አላደረጉም። ይሄንን አውቃለሁ፡፡ ምንጊዜም ፈራጁ ህዝብ ነው፡፡ አሁንም የቀጣዩ ፓርላማ ዕጣ ፋንታ በህዝቡ እጅ ነው። ምርጫ ቦርድ ሜዳውን የማስተካከል፣ እኩል የማድረግ ሃላፊነት አለበት፡፡ ህዝቡ ለዳኝነት መዘጋጀት፤ ፓርቲዎች ደግሞ ፕሮግራማቸውን ማስተዋወቅ፤ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ፓርላማው ባወጣው የአሸባሪ ህግ ሽብርተኛ ከተባሉት አምስቱ አሸባሪዎች መካከል የግንቦት 7 አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተይዘዋል፤ በቅርቡም ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ታስረዋል፡፡ እንደ ፓርላማ አባልነትዎ የታሰሩበትን ምክንያት ለማወቅ የሚሄዱበት አግባብ አለ ወይ? እንደ ሥራስ ቆጥረውት ያውቃሉ?
በአጠቃላይ ሽብርተኝነትን በተመለከተ በሀገር ደረጃ የወጣ አዋጅ አለ፤ በምክር ቤቱ፡፡ ያን ተከታትሎ ማስፈፀም የህዝቡ፣ የመንግስት፣ የመረጃና ደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እኝህ ሰው በህግ ጥላ ስር ነው ያሉት። እሳቸው ተጠርጣሪ ናቸው፡፡ ተጠርጥረው ተይዘዋል፡፡ የያዛቸው አካል ፍ/ቤት ሲያቀርብ መረጃውን፣ ማስረጃውን አሟልቶ ለፍትህ አካሉ አቅርቦ ፍ/ቤቱ የሚወስነውን ማየት ነው የሚሆነው፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ የፍ/ቤቱን ሂደት መከታተል እንጂ ማንም ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ በምክር ቤቱ የህግና የፍትህ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዎች አሉ፤ ሁሉንም ነገር ያያሉ፡፡ በፍትህ አካባቢ የሚጓደሉ ነገሮች ካሉ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢኖር ይከታተላሉ፡፡ ምክር ቤት የሀገሪቱ የፍትህ ስርዓትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሃላፊነት አለበት፡፡
ፀረ - ሽብር ህጉ የማስፈራሪያ መሳሪያ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እንዴት ይሆናል? ማንም ሰው ፖለቲካኛ፣ ጋዜጠኛ ስለሆነ መታሰር የለበትም፡፡ ነገር ግን ደግሞ በጋዜጠኝነትና በፖለቲከኝነት ስም ሊነገድም አይገባም፡፡ ወንጀል ሰርቶ ሙያተኛ ነኝ ሊል አይገባም፡፡
የሠራው ወንጀል ካለ ማንም ያለመከሰስ መብት ሊኖረው አይገባም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ካለ፤ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለእንባ ጠባቂ ተቋም ማመልከት ነው፡፡ የሃይል የጉልበት ነገር ወይም ከህግ የወጣ ነገር ካለ፣ ለስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በማመልከት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዲሞክራቲክ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚያን ተቋማት በመጠቀም የራስን መብት ማስከበር ያስፈልጋል፡፡  

Read 4899 times