Saturday, 12 July 2014 12:02

ተቃዋሚዎች የሰሞኑ እስር ምርጫውን ታሳቢ ያደረገ ነው አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

የታሰሩ ፖለቲከኞች ያሉበት ሁኔታ እንዲገለፅ ጠይቀዋል

         የሰሞኑን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች እስር ተከትሎ ፓርቲዎች ባወጡት መግለጫ “እስሩ ኢህአዴግ ቀጣዩን ምርጫ ያለ ተቀናቃኝ ለማለፍ ያደረገው ህገወጥ እንቅስቃሴ አካል ነው” ሲሉ ያማረሩ ሲሆን የታሰሩት ፖለቲከኞች ያሉበት ሁኔታ ለህዝብ እንዲገለፅና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡
አንድነት በበኩሉ፤ በጠበቆቹ አማካይነት የሃቢስ ኮርፖስ ክስ በፌደራል ፖሊስና በፀረ - ሽብር ቡድኑ አዛዥ ላይ መመስረቱን አስታውቋል፡፡
አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ “የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች አቶ ሃብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እንጠይቃለን” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ “ኢህአዴግ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች በማሰር የቀጣዩን ምርጫ ዘመቻ ይፋ አድርጓል” ብሏል፡፡ “እስሩ የተቀነባበረ ድራማ ነው” ያለው አንድነት፤ ቀጣዩን አገር አቀፍ ምርጫ በተለመደው መልኩ በማሸማቀቅና በማወናበድ ጠቅልሎ ለመውሰድ የተጀመረ ዘመቻ ነው” ብሏል፡፡ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፤ ድርጊቱን በመቃወምና ለአለም ህብረተሰብ በማጋለጥ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አንድነት ጠይቋል፡፡ ጠበቆች ታሣሪዎችን መጠየቅ አትችሉም መባላቸውን ተከትሎም አንድነት፣ በፌደራል ፖሊስና በፀረ - ሽብር ቡድኑ አዛዥ ላይ ሃባስ ኮርፖስ ክስ መመስረቱን የፓርቲው ጠበቃ አቶ ተማም አባ ቡልጉ ገልፀዋል፡፡ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአራዳ ምድብ ፍትሃ ብሔር ችሎት ትናንት የቀረበው ክስ፤ ጠበቆች መጠየቅ አትችሉም በመባላቸውና ታሣሪዎች ያሉበት ሁኔታ ሳይገለጽ ከ48 ሰአት በላይ በመሆኑ ነው ብለዋል - አቶ ተማም ለአዲስ አድማስ፡፡
በተመሳሳይ የመኢአድ/አንድነት ውህደት አመቻች ኮሚቴ “የውህደት አመቻች ኮሚቴውን በማሠር ውህደቱን ማደናቀፍ አይቻልም” ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ የአመቻች ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሃብታሙ አያሌው መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ “አቶ ሃብታሙ በኮሚቴው ሰብሳቢነት ስራውን በትጋት እየተወጣ ስለነበር፣ ሆን ተብሎ ውህደቱ ላይ እክል ለመፍጠር ነው መንግስት ያሰረው ብለን እናምናለን” ብሏል፡፡
እስሩ ቀጣዩን ምርጫ በጉልበትና በአፈና ለመንጠቅ እንዲሁም ሰላማዊ ትግሉን ለመድፈቅ ያለመ ነው ያለው አመቻች ኮሚቴው፤ “በዚህ ውህደቱ አይደናቀፍም፣ ሰላማዊ ትግሉም አይሰናከልም” ብሏል፡፡ በትናንትናው እለት ከሰአት በኋላ አንድነት እና መኢአድ በድጋሚ በሰጡት መግለጫ፤ ታሣሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ ይፋ እንዲደረግ አበክረው ጠይቀዋል፡፡  
ሰማያዊ ፓርቲም ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ “መንግስት ሽብርተኝነትን በመከላከል ስም ህገ-ወጥ አዋጅ አውጥቶ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን እንዲሁም የእምነት ነፃነታችን ይከበር ብለው የጠየቁ የሃይማኖት መሪዎችን ጸረ-ሽብር ግብረ ሃይል በሚባል  ቡድን ወደ እስር ቤት እያጋዘ ይገኛል” ሲል ወንጅሏል፡፡
መንግስት፤ የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ የሸዋስ አሰፋን ጨምሮ የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው እንዲሁም የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺና የአረና አመራር አባል የሆኑት አቶ አብረሃ ደስታን ማሰሩ፣ ኢህአዴግ የመጨረሻው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ያረጋግጣል ብሏል - ፓርቲው በመግለጫው፡፡ የፓርቲ አመራሮቹ እስርም ቀጣዩን ምርጫ ኢህአዴግ ያለተቀናቃኝ ለማለፍ የሚያደርገው ህገ ወጥ እንቅስቃሴ አካል ነው ሲል ሰማያዊ ፓርቲ ኮንኗል፡፡
“የየመን መንግስት የግንቦት 7 አመራር የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አሳልፎ መስጠቱ በታሪክ ተጠያቂ ያደርገዋል” ያሉት የፓርቲው አመራሮች፤ “መንግስት የግለሰቡን አያያዝ ግልፅ እንዲያደርግ፣ ሰብአዊ ክብራቸውን እንዲጠብቅ እናሳስባለን” ብለዋል፡፡
የፓርቲ አባላቱን በሽብር ተጠርጥሮ መታሰር ተከትሎ በቀጣይ ስጋት አላችሁ ወይ የሚል ጥያቄ ከአዲስ አድማስ የቀረበላቸው የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች፤ “ስጋት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ እኛ ልንታሰር እንደምንችል እናውቃለን፣ ያ ደግሞ ለነፃነት የሚከፈል ዋጋ ነው ብለን እናምናለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አክለውም መንግስት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እስኪቀየርና ነፃነት እስኪረጋገጥ ድረስ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባላት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ እንከፍላለን ብለዋል፡፡
“እኛም እንደምንታሰር አንጠራጠርም፤ ኢህአዴግም እንደሚያስረን አንጠራጠርም” ብለዋል - የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፡፡
የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ  አቶ ዳንኤል ተፈራ የእስር እርምጃው ሊፈጥር የሚችለውን ስጋት በተመለከተ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “እንዲህ ያሉ እስሮች ዛሬ የተጀመሩ ባይሆንም ይሄ ነገር አልበዛም እንዴ!” የሚሉ ጥያቄዎችን ህዝቡ እንዲያነሳ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ የተቃዋሚ አመራሮቹ መታሰር በተለያየ አደረጃጀት ያሉ ተቃዋሚዎች ይበልጥ ትግላቸውን እንዲያጠናክሩና በጋራ እንዲቆሙ የሚያደርግ ነው ሲሉ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡ “ፓርቲውን በቅርበት የማይከታተሉ ዜጎች ላይ የእስር እርምጃው ፍርሃትን ሊፈጥር ይችል ይሆናል” የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ፖለቲካውን በንቃት በሚከታተሉት ዘንድ ግን “መንግስት ምን እየሰራ ነው?” ብለው እንዲጠይቁ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡
“እስሩ ህገ ወጥ ነው” ሲሉ ያወገዙት አቶ ዳንኤል፤ የፓርቲ አመራሮችን መንገድ ላይ እያነቁ ከማሰርም በላይ የትና በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ህዝብ እንዲያውቅ አለመደረጉ ያሳስበናል ብለዋል፡፡ ታሣሪዎቹ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉና ፍርድ ቤት ስለመቅረብ አለመቅረባቸው ፓርቲው ማወቅ እንዳልቻለ አቶ ዳንኤል ገልፀዋል፡፡
የአረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ፤ ከዚህ ቀደም በህገ ወጥ መንገድ  በርካታ አባሎቻቸው እንደታሰሩባቸው ገልጸው፤ አቶ አብርሃ ደስታ የታሰሩበትን ምክንያት እንዲሁም በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ፓርቲያቸው ማወቅ እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ በንቃት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን የማዳከም እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የሰሞኑ እስር ማሳያ ነው ያሉት አቶ ጎይቶም፤ በዚህ የገዥው ፓርቲ እርምጃ ትግሉ አይቆምም፤ እንደውም የበለጠ እንዲጠናከር ያደርገዋል ብለዋል፡፡ “አሸባሪዎችን እያጠናከርን ያለነው እኛ ሳንሆን ራሱ ኢህአዴግ ነው” ብለዋል ምክትል ሊቀመንበሩ፡፡     
ባለፈው ማክሰኞ ምሽት የፀረ - ሽብር ግብረ ሃይሉ በኢቴቪ ባሰራጨው መግለጫ፤ በሽብርተኛነት የተፈረጀው የግንቦት 7 አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መያዛቸውን ጠቁሞ፤ በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱና ከኢሳት የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ቢገለፅም ማንነታቸውን ግን አልጠቀሰም፡፡

Read 5082 times