Saturday, 12 July 2014 11:59

ዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎች ያስመርቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ለአራት ሰዎች የክብር ዶክተሬት ይሰጣል
የማስተርስ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ ውጤት ሳይታወቅ አትመረቁም ተባሉ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በ10 ኮሌጆችና በሰባት የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን ከስምንት ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ያስመርቃል፡፡
ዘንድሮ 146 ተማሪዎች ዶክተሬት፣ 2832 ተማሪዎች በሁለተኛ ዲግሪ (ማስትሬት) 5222 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ (ቢኤ) የሚመረቁ ሲሆን እነዚህ ተመራቂዎች፣ ባለፈው መስከረምና የካቲት ወር የተመረቁትንና ትምህርታቸውን ጨርሰው በዚህ ወር የሚመረቁትን ጨምሮ በአጠቃላይ 8055 እንደሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር ዶ/ር በቀለ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር በቀለ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት፣ ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ አራት ሰዎች እንዲሸለሙ በወሰነው መሰረት፣ ለእነዚህ ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ማዕረግ እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ ከየኮሌጁና የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 11 ተማሪዎች እንዲሁም ከአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሦስት ተማሪዎች የወርቅ ሜዳሊያ እንደሚሸለሙ አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በከል በርካታ የሁለተኛ ዲግሪ (ማስትሬት) ተማሪዎች በዘንድሮው ምረቃ ያለመካተታቸው፣ “ድንገተኛ መርዶ” ሆነብን ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ለበርካታ ዓመታት በቆየው አሰራር የማስተርስ ተማሪዎች ኮርሳቸውን ጨርሰው የመመረቂያ ጽሑፋቸውን (ቴሲስ) ሳያብራሩና የሚነሱ ጥያቄዎችን ሳይመልሱ (ዲፌንድ ሳያደርጉ) ጋዋን ለብሰው የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ተሳታፊ ይሆኑ እንደነበረ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያስታውሳሉ፡፡
“እኛም ኮርሳችንን ጨርሰን የመመረቂያ ጽሁፋችንን በተለያዩ ምክንያቶች (በተማሪውና በመምህሩ) “ዲፌንድ” የምናደርገው በመጪው መስከረምና ጥቅምት ወር ቢሆንም፣ በነባሩ አሰራር መሰረት ጋዋን ለብሰን በምረቃ ሥነ-ሥርአቱ ላይ እንደምንገኝ ገምተን ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት ለቤተሰቦቻችን አሳው    ቀን ብዙ ገንዘብ አውጥተው፣ ጉልበትና ጊዜያቸውን አባክነው የደገሱና ከክፍለ ሀገርም የመጡ በርካቶች ናቸው፡፡ አሁን በመጨረሻው 11ኛ ሰዓት መጥፎውን መርዶ ነገሩን፡፡ የእኛም ተስፋ ሆነ የቤተሰቦቻችን ዝግጅትና ድግስ ከንቱ ሆነ፡፡ ይኼ ሁሉ ጥፋት ከመድረሱ በፊት ለምን አያሳውቁንም ነበር?” በማለት ክፉኛ አዝነዋል፡፡  በዚሁ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ሬጅስትራሩ ዶ/ር በቀለ፤ አሠራሩ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዩኒቨርስቲው የወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ጉዳት ማስከተሉን የተገነዘቡት አሁን ጉዳዩ ሲነገራቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“እኔ ወደዚህ ክፍል ከመጣሁ ሁለት ዓመቴ ነው፡፡ ይኼ አሠራር መች እንደተጀመረ አላውቅም እንጂ የቆየ ነው፡፡ ይህን ትክክል ያልሆነ አሠራር ለማስቆም ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አካል (ሴኔቱ) አሠራሩ መቆም አለበት ያለው ዘንድሮ አይደለም፡፡ ተግባራዊ አልሆነም እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ሲነገር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ስህተቱ እንዲታረም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ እኛም እያደረግን ያለነው ይህንኑ ነው፡፡” ሲሉ ሬጅስትራሩ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡  
ትምህርቱን የልጨረሰ ተማሪ ከጨረሰው እኩል ጋዋን ለብሶ “ይመረቅ” ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ያ ተማሪ ጋዋን ለብሶ “ከተመረቀ” በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ቴሲሱን በሚገባ ላይከላከል (ዲፌንድ ላያደርግ) ይችላል፡፡ ይህ ችግር እኔ ራሴ አጋጥሞኛል፡፡ ይህ ተማሪ ትምህርቱን አላለፈም፣ ወደቀ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሲፈተን ሊወድቅ የሚችል ተማሪ አስፈላጊውን ነጥብና የመመረቂያ መመዘኛዎችን በሚገባ ካሟላው ጋር እኩል ጋዋን ይልበስ ማለት ትክክል እንዳልሆነ አምናለሁ በማለት ተናግረዋል፡፡
ለምን ለተማሪዎቹ ቀደም ብሎ እንዳልተነገረ ሲገልጹም፤ “ኮሌጆች፣ ለተማሪዎቻቸው አልነገሩ ይሆናል እንጂ የቀድሞው ዓይነት አሠራር መቅረቱን ሁሉም ያውቃሉ፡፡ ስህተት የሆነ ነገር ለማረምና ለማስቀረት የጊዜ ገደብ ሊኖረው አይገባም የሚል አቋም አለኝ፤ በማንኛውም ጊዜ ሊታረም ይችላል” ብለዋል፤ ዶ/ር በቀለ፡፡
የዚህ ዓመት ምረቃ፣ ከዕለቱ ሥነ - ሥርዓት በኋላ ባሉት 6 ሳምንታት ውስጥ እንደሚቀጥል ም/ሬጅስትራሩ አቶ መሰለ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ የዕለቱ ተመራቂዎች ከ8ሺህ በላይ ናቸው የተባለው፣ የመመረቂያ መስፈርቶችን ሁሉ ስላሟሉ፣ ኮሌጆችና ተቋማት ለመመረቅ ብቁ መሆናቸውን አምነው፣ ስማቸውን ለሬጅስትራር ያስተላለፏቸው ናቸው፡፡ ዘንድሮ ትምህርታቸውን የሚጨርሱት የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን “ዲፌንድ” ያላደረጉ ተማሪዎች በቀጣይ 6 ሳምንታት ውስጥ ሲያጠናቅቁ፣ ከ500-600 ያህል ተማሪዎች “መመረቅ ይችላሉ” ብለው ኮሌጆቹ ስማቸውን ስለሚልኩልን፣ ያኔ የዘንድሮ ተመራቂዎች ቁጥር ከዛሬው በጣም ከፍ ይላል በማለት አብራርተዋል፡፡   

Read 3230 times