Saturday, 12 July 2014 11:58

ቤተልሄም ጥላሁን ከ10 የአፍሪካ ወጣት ሚሊየነሮች አንዷ ሆነች

Written by 
Rate this item
(14 votes)

የኩባንያዋ ዓመታዊ ገቢ 5ሚ.ዶላር ነው

         ‘ሶል ሪበልስ’ የተባለው የጫማ አምራች ኩባንያ መስራችና ባለቤት የሆነችው ኢትጵያዊቷ የንግድ ስራ ፈጣሪ ቤተልሄም ጥላሁን፣ በታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ለአርአያነት የሚበቁ የአመቱ 10 አፍሪካውያን ወጣት ሚሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ተካተተች፡፡
ፎርብስ ሰሞኑን ባወጣው ዝርዝር ከ39 አመት ዕድሜ በታች ያሉና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ቢዝነሶች ያሏቸው አፍሪካውያን በማለት ከጠቀሳቸው አስር ባለሃብቶች አንዷ የሆነችው ቤተልሄም፤ ከአስር አመታት በፊት ያቋቋመችው ‘ሶል ሪበልስ’ በአሁኑ ወቅት አምስት ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡
የ34 አመቷ ኢትየጵያዊት ቤተልሄም ጥላሁን ያቋቋመችው የጫማ አምራች ኩባንያ፣ ባህላዊውን የጫማ አሰራር ዘመናዊ መልክ በመስጠት በተለያዩ ዲዛይኖች የሚያመርታቸውን ምርቶቹን ወደተለያዩ የአለም አገራት በመላክ ከአመት ወደ አመት ትርፋማነቱን እያሳደገ የመጣ ሲሆን፣ ለ100 ያህል ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በአፍሪካ ውስጥ በሃያዎቹና በሰላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሆኖ በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ሃብት ማፍራት መቻል፣ በእርግጥም አድናቆትና ሙገሳ የሚያስፈልገው ትልቅ ስኬት ነው ያለው የፎርብስ ዘጋቢ ሞፎኖቦንግ ኒስሄ፣ እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ መሰል ስኬት ያስመዘገቡ 10 ተጠቃሽና ለአርአያነት የሚበቁ ሚሊየነሮችን በየአመቱ እየመረጠ ይፋ ማድረጉንም አስታውሷል፡፡
ፎርብስ መጽሄት ለአርአያነት የሚበቁ የአመቱ 10 አፍሪካውያን ወጣት ሚሊየነሮች በማለት ከመረጣቸው ተጠቃሽ ባለሃብቶች መካከል፣ ብቸኛዋ ሴት ቤተልሄም መሆኗን ከመጽሄቱ ድረገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በንግድ ስራ ፈጠራ መስክ ባስመዘገበችው ተጨባጭ ስኬት ፎርብስን ጨምሮ በተለያዩ ታዋቂ መጽሄቶች፣ በአህጉራዊና አለማቀፍ ድርጅቶች፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና መገኛኛ ብዙሃን ስሟ በተደጋጋሚ በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሰው ቤተልሄም፣ በዘርፉ በርካታ ሽልማቶችን ለመቀበል ችላለች፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ በትራንስፖርትና በነዳጅ ምርት፣ በፋሽን ስራ፣ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በኤሌክትሮኒክ ንግድ፣ በቴሌኮም፣ በኮምፒውተርና በሌሎች የቴክኖሎጂ መስኮች ተሰማርተው ትርፋማ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የታንዛኒያ፣ የናይጀሪያ፣ የኬኒያና የደቡብ አፍሪካ ሚሊየነሮች ተካተዋል፡፡

Read 9621 times