Saturday, 12 July 2014 11:57

የመን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ልትመልስ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

                 የመን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ታዚ በተባለ አካባቢ በቁጥጥር ስር የዋሉትንና የስደተኝነትን መስፈርት አያሟሉም፣ ጥገኝነት ጠያቂም አይደሉም ያለቻቸውን 44 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ልትመልስ እንደሆነ የመን ታይምስ ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ከሰንዓ ዘገበ፡፡
የኮስት ጋርድ ቃል አቀባይ የሆኑትን ሁሴን አል ሃራዚን ጠቅሶ ጋዜጣው ከሰንኣ እንደዘገበው፣ በኢትዮጵያዊ ካፒቴን በምትንቀሳቀስ ጀልባ ተሳፍረው ሲጓዙ ሞካ ተብሎ ከሚጠራው የየመን ወደብ አቅራቢያ የተያዙት እነዚሁ ስደተኞች፣ በአካባቢው ወደሚገኝ የደህንነት ማዕከል እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡
በኢትዮጵያና በየመን መካከል ይህ ነው የሚባል የጎላ ግጭት እንደሌለ የገለጹት የኮስት ጋርድ አካባቢ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ኮሎኔል ሳልህ አልፋኒ በበኩላቸው፤ አገሪቱ ኢትዮጵያውያንን በአግባቡ እንደምትይዝና እንደማንኛውም ስደተኛ እንደማታያቸው ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያኑ ከአገራቸው ወጥተው ወደ የመን ለመግባት ጥረት ያደረጉት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው በየመን የስራ ዕድል ለማግኘት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በየመን በኩል አድርገው ወደሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለመግባት ነው” ብለዋል ኮሎኔል አልፋኒ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የመገናኛ ብዙሃን ረዳት የሆኑት ዚያድ አል አልአያ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያኑ ስደተኞች ወደ አገሪቱ ለመግባት የሞከሩት የኢኮኖሚ ችግራቸውን ለመፍታት እንጂ ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ አለመሆኑንና በስደተኞች መጠለያ ለመቆየት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ወደ አገሪቱ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደ ሶማሊያዊያን ስደተኞች በአፋጣኝ በስደተኛ ጣቢያዎች መኖር የሚያስችላቸውን ፍቃድ እንደማያገኙና በአጠቃላይም በስደተኝነት ለመቀበል ብቁ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡
በሰንዓ የፓስፖርትና የኢሚግሬሽን ባለስልጣን የስደተኞች መላሽ ክፍል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አብዱላ አል ዙርቃ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያኑ በስደተኛነት እስካልተመዘገቡ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ እስካልሆኑ ድረስ በአገሪቱ መቆየት ስለማይችሉ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ እ.ኤ.አ በ2013 ብቻ 53 ሺህ 941 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመን ገብተዋል፡፡

Read 2174 times