Saturday, 05 July 2014 00:00

የ20ኛው ዓለም ዋንጫ ኮከቦች እነማን ይሆናሉ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

1. ጁሊዮ ሴዛር
2. ካይሎር ናቫስ
3. ማኑዌል ኑዌር
4. ጉሌርሞ ኦቾ
5.ቪንሰንት ኢንየማ
6. ቲም ሀዋርድ

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ስድስት ልዩ  ልዩ ሽልማቶችን በተለያዩ ዘርፎ ለሚመረጡ ተጨዋቾች እና ቡድኖች ያበረክታል፡፡  ለምርጥ በረኛ የወርቅ ጓንት፤ ለኮከብ ግብ አግቢ የወርቅ ጫማና ለኮከብ ተጨዋች የወርቅ ኳስ  የሚሰጡት ሶስትይ ሽልማቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ አብይ ስፖንሰርነት የሚታወቀው አዲዳስ የወርቅ ኳስ እና የወርቅ ጫማ ሽልማቶችን በኩባንያው  ስም ያበረክታል፡፡ በሶስቱም ሽልማቶች በተጨማሪ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ለሚያገኙት ተጨዋቾች የብር እና የነሐስ  ሽልማቶች ይሰጣሉ፡፡ በዓለም ዋንጫ በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ሌሎች ሶስት የክብር ሽልማቶችም አሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ ምርጥ ተጨዋች፤ የዓለም ዋንጫው ምርጥ ስፖርታዊ ጨዋነት እና የዓለም ዋንጫው ምርጥ ቡድን የሚሸለሙባቸው ናቸው፡፡ የዓለም ዋንጫ ምርጥ ወጣት ተጨዋች ምርጫ ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደው በ1958 እኤአ ቢሆንም በደንበኛ ትኩረት መሸለም የተጀመረው በ2006 እኤአ ላይ ጀርመን ባዘጋጀችው 18ኛው የዓለም ዋንጫ ሲሆን የጀርመኑ ሉካስ ፖዶልስኪ ቀዳሚው ተሸላሚ ነበር፡፡ የዚህ ሽልማት ስፖንሰር የመኪና አምራቹ ሃዩንዳይ ኩባንያ ነው፡፡ በ2010 እኤአ በተደረገው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ደግሞ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር ተሸልሞበታል፡፡ የዓለም ዋንጫው የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊን መሸለም የተጀመረው በ1970 እኤአ ላይ ነው፡፡ ከ4 ዓመት በፊት የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማቱን የወሰደው ሻምፒዮኑ የስፔን ብሄራዊ ቡድን ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫው ምርጥ ቡድን ደግሞ ከ1994 እኤአ ወዲህ ሲሸለም ቆይቷል፡፡


በጎል ፌሽታው፤ ማን ብዙ አግብቶ ይጨርሳል?
20ኛው ዓለም ዋንጫ በጎሎች ብዛት የምንግዜም ምርጥ በመሆን ላይ ነው፡፡ ከሩብ ፍፃሜ በፊት በተደረጉ 56 ጨዋታዎች 154 ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡  በየጨዋታው በአማካይ 2.75 ጎል እየገባ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ 64 ጨዋታዎች መደረግ ከጀመረበት ከ1986 እኤአ ወዲህ ዘንድሮ ከፍተኛው የጎል ብዛት እንደሚመዘገብ ተጠብቋል፡፡ በ1994 እ.ኤ.አ 171፤ በ2002 እ.ኤ.አ 161፤ በ2006 እ.ኤ.አ 147 እንዲሁም በ2010 እ.ኤ.አ 145 ጎሎች በ64 ጨዋታዎች ተመዝግበዋል፡፡ ትናንት ከተጀመሩት ሁለት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በፊት የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሲመራ የነበረው በ4 ጨዋታዎች አምስት ጎሎች ከመረብ ያዋሃደው የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ ነው። በ4 ጎሎቻቸው የሚከተሉት ደግሞ የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ፤ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር እና የብራዚሉ ኔይማር ዳሲልቫ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው 3 ጎሎች ያስመዘገቡ 5 ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ቡድኖቻቸው ወደ ሩብ ፍፃሜ በማለፋቸው በፉክክር የሚቆዩት የሆላንዶቹ ቫንፕርሲ እና ሮበን እንዲሁም የፈረንሳዩ ካሬም ቤንዜማ ናቸው፡፡ የኢኳደሩ ኢነር ቫሌንሽያ እና የስዊዘርላንዱ ሻኪሪ 3 ጎሎች ቢኖራቸውም ቡድኖቻቸው ሩብ ፍፃሜ ባለመድረሳቸው ከፉክክር ውጭ ሆነዋል፡፡ 2 ጎሎች በማስመዝገብ ስማቸው የተመዘገበላቸው 16 ተጨዋቾች ሲሆኑ አንድ ጎል ያገቡት ደግሞ 88 ተጨዋቾች ናቸው፡፡
በዓለም ዋንጫው ኮከብ ግብ አግቢነት ለወርቅ ጫማ ሽልማት የሚበቃው ተጨዋች በጎሎቹ ብዛት የሚመረጥ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ የጎል ብዛት የሚጨርሱ ተጨዋቾች ከአንድ በላይ ከሆኑ ደግሞ አሸናፊው የሚለየው ለጎል የበቁ ኳሶችን በብዛት ማን አቀብሏል ተብሎ ነው፡፡ በግብ ብዛትና ለጎል የበቁ ኳሶችን በማቀበል እኩል የሆኑ ተጨዋቾች ከሁለት በላይ ከሆኑ ደግሞ አሸናፊነቱ አነስተኛ ደቂቃዎች ተሰልፎ ብዙ ላገባው ተጨዋች የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የወርቅ ጫማ አሸናፊ ሽልማት በሁሉም ዓለም ዋንጫዎች ሲሸለም የቆየ ነው፡፡ በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ባገባው ጎል አዲስ ታሪክ የሰራው ተጨዋች የ36 ዓመቱ ጀርመናዊ አጥቂ ሚሮስላቭ ክሎሰ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ዋንጫ የውድድሩ የምንግዜም ከፍተኛ ጎል አግቢ ሊሆን የሚችልበት እድል ይዞ መሳተፍ የጀመረው ሚሮስላቭ ክሎሰ ከጀርመን ብሄራዊ ቡድን ጋር በተሳተፈባቸው 3 የዓለም ዋንጫዎች 14 ጎሎች ነበሩት፡፡ ጀርመን ከጋና ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተቀይሮ ከገባ በኋላ 15ኛውን ጎል አስመዘገበ፡፡  በዚህም የዓለም ዋንጫ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ  ከነበረው ብራዚላዊው ሊውስ ናዛርዮ ዴሊማ ጋር ክብረወሰኑን ተጋርቷል፡፡ ከሩብ ፍፃሜው በኋላ ሚሮስላቭ ክሎስ አንድ ተጨማሪ ጎል ካስመዘገበ የዓለም ዋንጫ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ለመሆን ይችላል፡፡



በረኞች ያልተዘመረላቸው የእግር ኳስ ጀግኖች
20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ  በርካታ ጎሎች ሲመዘገቡ መቆየታቸው የበረኞችን ብቃት አጠያያቂ ቢያደርገውም ቢያንስ ስምንት በረኞች በየቡድኖቻቸው አስገራሚ ብቃት አሳይተዋል፡፡  እነዚህ በረኞች በወሳኝ ጨዋታዎች ያለቀላቸውን የግብ እድሎች ሲያመክኑ፤ ቡድኖቻቸውን በአምበልነት በመምራት የሚደነቅ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ፤ የቡድኖችን ውጤት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያሳዩ፤ በጥሎ ማለፍ በተከሰቱ የመለያ ምቶችን በማዳን  ውጤቶችን ሲወስኑ ሰንብተዋል፡፡ በእርግጥ በእግር ኳስ ስፖርት  በኮከብ ተጨዋችነት ብዙውን ጊዜ  ለአጥቂዎች እና ለአማካዮች ትኩረት የሚሰጥ ቢሆንም ፤ በዚህ ዓለም ዋንጫ በረኞች  በምርጥ አቋማቸው ለቡድናቸው የኮከብነት ሚና እንደሚኖራቸው ተረጋግጧል፡፡ በርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች ከበረኞች ስህተት የመጠበቅ ልማድ አለባቸው፡፡ በየጨዋታው በረኞችን አንድ ስህተት ሲያጋጥማቸው ወይም ጎል ሲገባባቸው ለቡድናቸው ሽንፈት ተጠያቂ ያደርጓቸዋል፡፡   አጥቂዎች ብዙ ጎሎችን ሲስቱ የሚደርስባቸው ወቀሳ ግን ያን ያህል ነው። ለበረኞች ሚና አነስተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ በብራዚላዊው ጁሊዮ ሴዛር ላይ የተከሰተውን ሁኔታ እንደ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በብራዚል ለግብ ጠባቂዎች ብዙም አድናቆት የለም፤ እንደውም አንዳንድ ስፖርት አፍቃሪዎች ጁሊዮ ሴዛርን “ዶሮው ሰውዬ” እያሉ ያሾፉበታል፡፡ ብራዚል በጥሎ ማለፍ ከቺሊ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ ግን አዘጋጇን አገር ከውድቀት ያዳነው እሱ ነበር፡፡ ከብራዚልና ቺሊ ጥሎ የሚያልፈው ቡድን በመለያ ምቶች ሲታወቅ ሁለት ኢሊጎሬዎችን በማዳን ጁሊዮ ሴዛር የእለቱ ኮከብ ነበር፡፡ በዚህ ጀግንነቱም ከሌሎች ምርጥ ተጨዋቾች ይልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ተደጋጋሚ ቃለምልልሶች አድርጓል፡፡  “በፊት የሚያናግረኝ አልነበረም፤ አሁን  ሁሉም አስተያየቴን ስለሚጠይቅ በጣም ደስ ብሎኛል” በማለት ጁሊዮ ሴዛር እያነባ ተናግሯል፡፡
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ የታየ ምርጥ በረኛ የብራዚሉ ጁሊዮ ሴዛር ብቻ አይደለም፡፡  ቡድኖቻቸውን ለሩብ ፍፃሜ በማብቃት ጉልህ ሚና ከነበራቸው ምርጥ በረኞች የቤልጅዬሙ ቲቦልት ኮርትዬስ፤ የኮስታሪካው ኬዬሎር ናቫስ፤ የኮሎምቢያው ዴቪድ ኦስፒና፤ የአርጀንቲናው ሰርጂዮ ሮሜሮ፤ የፈረንሳዩ ሁጎ ሎሪስና የጀርመኑ ማንዌል ኑዌር ዋናዎቹ ተጠቃሾች ናቸው።  ከምድብ ጨዋታዎች እስከ ጥሎ ማለፉ  ቡድኖቻቸውን በአስገራሚ ብቃታቸው ያገለገሉ ሌሎችም ምርጥ በረኞች ነበሩ፡፡ የአሜሪካው ቲም ሃዋርድ፤ የናይጄርያው ቪንሰንት ኢኒዬማ እንዲሁም  የቺሊው  ጉሌርሞ ኦቾ  ናቸው፡፡ የዓለም ዋንጫ ኮከብ በረኛ ሆኖ የወርቅ ጓንት ለመሸለም የሚበቃው ከእነዚህ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች አንዱ መሆኑ አይቀርም፡፡ በምድብ ማጣርያው በ3 ጨዋታዎች ግብ ሳይገባበት አንደኛ ደረጃ የተሰጠው የፈረንሳዩ ሁጎ ሎሪስ ነው፡፡ የ22 ዓመቱ የቤልጅዬም በረኛ ቲቦልት ኮርትዬስ  ወደ ጎል ከሚሞከሩ ኳሶች 87 በመቶውን  በማዳን ተደንቋል፡፡ የጀርመኑ ማኑዌል ኑዌር ደግሞ በዓለም ዋንጫው  ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን 29 በመቶ ብቃት አስመዝግቧል፡፡ ማኑዌል ኑዌር ከሌሎቹ ምርጥ በረኞች ልዩ የሚያደርገው  ከግብ ክልል ውጭ እንቅስቃሴ በማድረግ  እንደሊብሮ ተጨዋች ማገልገሉ ነው፡፡ ይህ የማንዌል ኑዌር ብቃት በተለይ ጀርመንና አልጄርያ ባደረጉት ጨዋታ  የታየ ነበር፡፡
የአሜሪካው ግብ ጠባቂ ቲም ሃዋርድ አገሩ ከቤልጅዬም ጋር ባደረገችው ጨዋታ 15 ያለቀላቸው የግብ ሙከራዎችን አድኖ በውድድሩ ታሪክ አዲስ ክበረወሰን ተመዝግቦለታል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው ኛው የዓለም ዋንጫ በረኞች የአዲዳስ ምርት በሆነችው ጃቡላኒ የተባለች ኳስ ምርጥ ብቃታቸውን ለማሳየት አልታደሉም ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን በብራዙካ ኳስ አንድም በረኛ ሲቸገር አልታየም፡፡
የፊፋ ቴክኒክ ቡድን የዓለም ዋንጫውን ኮከብ በረኛ በውድድሩ ላይ ባሳየው አጠቃላይ ብቃት መሰረት መርጦ ለሽልማት ያበቃዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ምርጥ በረኛ ከ1994 እኤአ ወዲህ በታዋቂው ራሽያዊ ግብ ጠባቂ ሌቭ ያሺን መታሰቢያነት የሚሸለም ነበር፡፡ ከ2010 እኤአ በኋላ ግን የወርቅ ጓንት ሽልማት ተብሎ ለአሸናፊው መበርከት ጀምሯል፡፡


በ1ኛው ዓለም ዋንጫ የኡራጋዩ ኢነሪኬ ባሌስትሮ
በ2ኛው የዓለም ዋንጫ የስፔኑ ሪካርዶ ዛሞራ
በ3ኛው የዓለም ዋንጫ የኡራጋዩ ሮክዌ ማስፖሊ
በ4ኛው የዓለም ዋንጫ የቼኮስላቫኪያው ፍራንቲሴክ ፕላኒካ
በ5ኛው የዓለም ዋንጫየሃንጋሪው ጉዮላ ግሮሲክስ
በ6ኛው የዓለም ዋንጫ  የሰሜን አየርላንዱ ሃሪ ግሬግ
በ7ኛው የዓለም ዋንጫ የቼኮስላቫኪያው ቪሊያም ሽኮሪጄፍ
በ8ኛው የዓለም ዋንጫ የእንግሊዙ ጎርደን ባንክስ
በ9ኛው የዓለም ዋንጫ የኡራጋዩ ላዲሳሎ ማዙሪኪኤውሲዝ
በ10ኛው የዓለም ዋንጫ የምዕራብ ጀርመኑ ሴፕ ማዬር
በ11ኛው የዓለም ዋንጫ የአርጀንቲናው ኡባልዶ ፊሎል
በ12ኛው የዓለም ዋንጫ የጣሊያኑ ዲኖ ዞፍ
በ13ኛው የዓለም ዋንጫነየቤልጅዬሙ ጂን ማርዬ ፕፋፍ
በ14ኛው የዓለም ዋንጫ የኮስታሪካው ሊውስ ጋቤሎና የአርጀንቲናው ሰርጂዮ ጎይኮቻ
በ15ኛው የዓለም ዋንጫ የቤልጅዬሙ ሚሸል ፕሩድሜ
በ16ኛው የዓለም ዋንጫ የፈረንሳዩ ፋብያን ባርቴዝ
በ17ኛው የዓለም ዋንጫ የጀርመኑ ኦሊቨር ካን
በ18ኛው የዓለም ዋንጫ የጣሊያኑ ጂያንሉጂ ቡፎን
በ19ኛው የዓለም ዋንጫ የስፔኑ ኤከር ካስያስ
በጎል ፌሽታው፤ ማን ብዙ አግብቶ ይጨርሳል?
20ኛው ዓለም ዋንጫ በጎሎች ብዛት የምንግዜም ምርጥ በመሆን ላይ ነው፡፡ ከሩብ ፍፃሜ በፊት በተደረጉ 56 ጨዋታዎች 154 ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡  በየጨዋታው በአማካይ 2.75 ጎል እየገባ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ 64 ጨዋታዎች መደረግ ከጀመረበት ከ1986 እኤአ ወዲህ ዘንድሮ ከፍተኛው የጎል ብዛት እንደሚመዘገብ ተጠብቋል፡፡ በ1994 እ.ኤ.አ 171፤ በ2002 እ.ኤ.አ 161፤ በ2006 እ.ኤ.አ 147 እንዲሁም በ2010 እ.ኤ.አ 145 ጎሎች በ64 ጨዋታዎች ተመዝግበዋል፡፡ ትናንት ከተጀመሩት ሁለት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በፊት የኮከብ ግብ አግቢነቱን ሲመራ የነበረው በ4 ጨዋታዎች አምስት ጎሎች ከመረብ ያዋሃደው የኮሎምቢያው ጀምስ ሮድሪጌዝ ነው። በ4 ጎሎቻቸው የሚከተሉት ደግሞ የአርጀንቲናው ሊዮኔል
በ1ኛው ዓለም ዋንጫ  በ8 ጎሎች የኡራጋዩ ጉሌርሞ ስታብል
በ2ኛው የዓለም ዋንጫ በ5 ጎሎች የቼኮስሎቫኪያው ኦሊድሪች
በ3ኛው የዓለም ዋንጫ በ7 ጎሎች የብራዚሉ ሊዮኒዴስ
በ4ኛው የዓለም ዋንጫ በ8 ጎሎች የብራዚሉ አዴሚር
በ5ኛው የዓለም ዋንጫ በ11 ጎሎች የሃንጋሪው ሳንዶር ኮሲስ
በ6ኛው የዓለም ዋንጫ በ13 ጎሎች የፈረንሳዩ ጀስት ፎንታይኔ
በ7ኛው የዓለም ዋንጫ በእኩል 4 ጎሎች የብራዚሎቹ ጋሪንቻና ቫቫ፤ የዩጎስላቪያው ድራዛን ጄርኮቪች እና የቺሊ ሊዮኔል ሳንቼዝ
በ8ኛው የዓለም ዋንጫ በ9 ጎሎች የፖርቱጋሉ ዩዞብዮ
በ9ኛው የዓለም ዋንጫ በ10 ጎሎች የጀርመኑ ገርድ ሙለር
በ10ኛው የዓለም ዋንጫ በ7 ጎሎች የፖላንዱ ግሬጎርዝ ላቶ
በ11ኛው የዓለም ዋንጫ በ6 ጎሎች የአርጀንቲናው ማርዮ ኬምፐስ
በ12ኛው የዓለም ዋንጫ በ6 ጎሎች የጣሊያኑ ፓውሎ ሮሲ
በ13ኛው የዓለም ዋንጫ በ6 ጎሎች የእንግሊዙ ጋሪ ሊንከር
በ14ኛው በ6 ጎሎች የጣሊያኑ ሳልቫቶሪ ስኪላቺ
በ15ኛው የዓለም ዋንጫ በ6 ጎሎች የሩስያው ሳሌንኮና የቡልጋሪያው ስቶችኮቭ
በ16ኛው የዓለም ዋንጫ በ6 ጎሎች የክሮሽያው ዳቮር ሱከር
በ17ኛው የዓለም ዋንጫ በ8 ጎሎች የብራዚሉ ሮናልዶ
በ18ኛው የዓለም ዋንጫ በ5 ጎሎች የጀርመኑ ሚሮስላቭ ክሎሰ
በ19ኛው የዓለም ዋንጫ በ5 ጎሎች የጀርመኑ ቶማስ ሙለር

ኮከብ ተጨዋች ከዋንጫው አሸናፊ ይገኛል
የዓለም ዋንጫው ኮከብ ተጨዋች ለማወቅ እስከ ዋንጫው ጨዋታ መጠበቅ ይጠይቃል፡፡ ከሩብ ፍፃሜው በፊት ለዚህ ሽልማት እጩ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የተነገረላቸው በምርጥ ጎሎቻቸው የተደነቁት የሆላንዱ ቫን ፒርሲ እና የኮሎምቢያው ጄምስ ሮድሪጌዝ ናቸው፡፡ የብራዚሉ ኔይማርና የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ቡድኖቻቸውን ለዋንጫ የሚያበቁ ከሆነም ለሽልማቱ ግንባር ቀደም እጩዎች ይሆናሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጨዋች የሚሸለመው የወርቅ ኳስ ሲሆን ምርጫውን የሚያከናውኑት ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች እና ፊፋ ናቸው፡፡

በ1ኛው ዓለም ዋንጫ የኡራጋዩ ጆሴ ናሳዚ
በ2ኛው የዓለም ዋንጫ የጣሊያኑ ጁሴፔ ሜዛ
በ3ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ሊዮኒዴስ
በ4ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ዚዝንሆ
በ5ኛው የዓለም ዋንጫ የሃንጋሪው ፌርኔክ ፑሽካሽ
በ6ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ዲዲ
በ7ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ጋሪንቻ
በ8ኛው የዓለም ዋንጫ የእንግሊዙ ቦቢ ቻርልተን
በ9ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ፔሌ
በ10ኛው የሆላንዱ ዮሃን ክሩፍ
በ11ኛው የአርጀንቲናው ማርዮ ኬምፐስ
በ12ኛው የጣሊያኑ ፓውሎ ሮሲ
በ13ኛው የአርጀንቲናው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና
በ14ኛው የጣሊያኑ ሳልቫቶሬ ስኪላቺ
በ15ኛው የብራዚሉ ሮማርዮ
በ16ኛው የዓለም ዋንጫ የብራዚሉ ሮማርዮ
በ17ኛው የጀርመኑ ኦሊቨር ካን
በ18ኛው የፈረንሳዩ ዚነዲን ዚዳን
በ19ኛው የኡራጋዩ ዲያጎ ፎርላን

Read 3297 times