Print this page
Tuesday, 08 July 2014 08:22

ፕሬዚዳንቱና አፈጉባኤው ኮከባቸው አልገጠመም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“ፕሬዚዳንት ኦባማን
ሳልከሳቸው አልቀርም”

“ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱን ህጎች በታማኝነት እያስፈፀሙ አይደለም፤ ስለዚህ ክስ መስርቼ ፍርድ ቤት ሳልገትራቸው አልቀርም፡፡” ሲሉ የተናገሩት የአሜሪካ ኮንግረስ አፈጉባኤ ቦህነር ናቸው፡፡
በኦባማ የመጀመሪያው አራት አመት የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ዘመን አጋማሽ ላይ በተደረገው የኮንግረስ ምርጫ ሩፐብሊካኖች አሸንፈው አብላጫውን መቀመቻ እንደተቆጣጠሩ የኮንግረንሱ አፈጉባኤ በመሆን የተመረጡት ሪፐብሊካኑ ፖለቲከኛ ቦህነር ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር አንድም ቀን እንኳ ኮከባቸው ገጥሞ አያውቅም፡፡ አንዳቸው ላንዳቸው ያላቸውን ጥላቻም ደብቀውት አያውቁም፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማም የማወጣቸው እቅዶችና ፕሮግራሞች በኮንግረሱ ተቀባይነት አግኝተው ስራ ላይ እንዳይውሉ አላስፈላጊ ችግር እየፈጠረ ስራዬን ይበጠብጣል በማለት አፈጉባኤ ቦህነርን በተደጋጋሚ ይነቅፋሉ፡፡
አፈጉባኤ ቦህነር በበኩላቸው ደግሞ “ፕሬዚዳንት ኦባማ እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነታቸው የሀገሪቱን ህጎች በታማኝነት ሥራ ላይ እያዋሉ አይደለም፤ እንዲያውም ይባስ ብለው በአሜሪካ ህዝብና በኮንግረሱ ላይ ልክ እንደ ንጉስ በግል ስልጣናቸው መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡” ሲሉ በጥላቻ የታሸ ስሞታቸውን በተደጋጋሚ ያቀርባሉ፡፡
ሰሞኑን ግን አፈጉባኤ ቦህነር፤ በፕሬዚዳንት ኦባማ ላይ ስሞታ በማቅረብ ብቻ አልተወሰኑም፡፡ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ በፕሬዚዳንት ኦባማ ድርጊት ቆሽታቸው እንዳረረና ክስ ሊመሰርቱባቸው እየተዘጋጁ እንደሆነ በይፋ አስታውቀዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አፈጉባኤ ቦህነር ፕሬዚዳንት ኦባማን ልን እንደ ንጉስ የግል ስልጣናቸውን በመጠቀም መንቀሳቀስ ጀምረዋል እንዲሉና በንዴት እንዲንጨረጨሩ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ የሚያወጧቸውን አንዳንድ እቅዶችና የሚወስዷቸውን ውሳኔዎች ያለ ኮንግረንሱ ፈቃድና ስምምነት የግል ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን (Executive order) በመጠቀም ስራ ላይ እንዲውሉ በማድረጋቸው ነው፡፡
በእርግጥም ይህ ሁኔታ አፈጉባኤ ቦህነር የፕሬዚዳንት ኦባማን ውሳኔዎች ኮንግረንሱ እንዳያፀድቀው በማድረግ፣ የአፈጉባኤነት ስልጣናቸውን ማሳየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ደግሞ “ከእሱና በሪፐብሊካኖች ከተሞላው ኮንግረንስ ጋር አጽድቁ አታጽድቁ እያልኩ ምን አዳረቀኝ” ባይ ናቸው፡፡
የሆኖ ሆኖ በርካታ የአሜሪካ የዜና አውታሮች የአፈጉባኤ ቦህነርን ውሳኔ በሰፊው አራግበውላቸዋል፡፡ በርካታ የህግ ባለሙያዎች ግን ለቢራ ቤት ወሬ ማዳመቂያ ከመሆን ያለፈ አንዳችም ህጋዊ መሰረትና ፋይዳ የሌለው ነው በማለት አጣጥለውታል፡፡ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የኤርቪን ህግ ትምህርት ቤት ዲን ኤርዊን ቸመሪንስኪ፤ “አፈጉባኤ ቦህነር እንዳለው ፕሬዚዳንታዊ ስልጣኑን ለምን ተጠቀመ በሚል በፕሬዚዳንቱ ላይ ክስ ከመሠረተ የአሜሪካንን ህገ መንግስት ጨርሶ አያውቀውም ወይም አልገባውም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን በአፈጉባኤነት ለሚመራው ለአሜሪካ ኮንግረስ እጅግ ከባድ ሀፍረትና ውርደት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

Read 2161 times
Administrator

Latest from Administrator