Tuesday, 08 July 2014 08:17

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ዕጩ ፕሬዚዳንትና የከሸፈው የዴቪድ ካሜሮን ቅስቀሳ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከሀያ ስምንቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውስጠ ህብረቱን አምርራ የምትጠላ፣ አባልነቱንም የማትፈልግ አንዲት ሀገር ብትኖር እንግሊዝ ብቻ ናት፡፡
እንግሊዝ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ከአውሮፓ ህብረት አባልነታቸው ለመውጣት ህዝበ ውሳኔ ካካሄዱት ሀገራት አንደኛዋ ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንና በስልጣን ላይ ለው የወግ አጥባቂ ፓርቲ በርካታ ባለስልጣናትና አንጋፋ አባላት እንግሊዝ የአውሮፓ ህብረት አባልነቷን ለቃ እንድትወጣ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሮን፤ በቀጣዩ ምርጫ በድጋሚ መመረጥ ከቻሉ፣ በ2017 ዓ.ም እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ እንድትወጣ ለማድረግ፣ ህዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂዱ ቀደም ብለው ቃል ገብተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ባለፈው ግንቦት ወር በተካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ የእንግሊዙን ዩኬአይፒ ፓርቲን ጨምሮ ፀረ አውሮፓ ህብረት የሆኑ ብሔርተኛና አክራሪ ፓርቲዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው አልተከፉም፡፡
በአንፃሩ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ጠላት የሆኑት የሀገራቸው መራጮች ከሳቸው የወግ አጥባቂ ፓርቲ ይልቅ ዩኬአይፒ ፓርቲን በአንደኛ ደረጃ በከፍተኛ ድምጽ መምረጣቸው፣ በቀጣዩ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሚደረገው ምርጫ በድጋሚ የመመረጣቸውን እድል አጠራጣሪ በማድረግ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል፡ላለፉት ዓመታት የአውሮፓ ህብረት ያጋጠሙትን በርካት ችግሮችና ፈተናዎች እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት በአፍቃሬ አውሮፓ ህብረት አቋማቸው የታወቁት አንጋፋ ፖለቲከኛና የቀድሞው የሉክሰምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር የዦን ክሎድ ዩንከር የአውሮፓ ህብረት ጠንካራ ክንድና የስራ አስፈፃሚ አካል የሆነውን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽንን የወቅቱን ፕሬዚዳንት ፖርቹጋላዊውን ማኑኤል ባሮሶን በመተካት ግንባር ቀደም እጩ ሆነው መቅረባቸው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በቀላሉ የማይቋቋሙት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር፡፡
መጠጥ በመድፈር የታወቁ ጣጤ ከመሆናቸው በስተቀር ለብቃታቸው አንዳችም አቃቂር የማይወጣላቸው ሉክዘንበርጌው አንጋፋ ፖለቲከኛ ዦን ክሎድ ዮንከር፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ የአውሮፓ ህብረት የስራ አስፈፃሚ አካል የሆነውን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የሚታማበትን ችግሮች በተለያዩ የተሀድሶ እርምጃዎች በማስተካከል ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ጠንካራ ኮሚሽን እንደሚያደርጉት በርካቶች እምነታቸውን የጣሉባቸው ሰው ናቸው፡፡ ይህንን ሁኔታና የሚያስከትለውን ፖለቲካዊ ጣጣ በሚገባ የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንም የዥን ክሎድ ዬንከርን ከቻሉ እጩነታቸውን ለማስቀረት፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ በቂ ድምጽ አግኝተው እንዳይመረጡ ለማድረግ ዙሪያ መለስ ቅስቀሳቸውን የጀመሩት ገና በማለዳ ነበር፡፡
ከፊንላንድ እስከ ስፔይን፣ ከፖርቹጋል እስከ ዴንማርክ ድረስ ባደረጉት ፀረ ዦን ክሎድ ዮንከር ቅስቀሳ የአብዛኞችን የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ድጋፍ ማግኘት በመቻላቸው የልባቸውን እንዳደረሱ በመተማመን፣ የተወዳዳሪው ቀንደኛ ደጋፊ በሆኑት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል ላይ የለበጣ ሳቅ ስቀውባቸው ነበር፡፡ ባለፈው አርብ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም ሃያ ስምንቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች አዲሱን የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ስብሰባ እንደተቀመጡም፤ የእንግሊዝ ጠቅላይ ምኒስትር በከፍተኛ የድል አድራጊነትና የእርካታ ስሜት ተሞልተው ከዚህ በፊት አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ አጠገባቸው ተቀምጠው ከነበሩት ከሮማንያና ከስፔይን መሪዎች ጋር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያወሩ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን የብራ መብረቅ የወረደባቸው የምርጫውን ውጤት ሲሰሙ ነው፡፡ በድንጋጤ በተቀመጡበት ክው ያሉት ዴቪድ ካሜሮን ያዩትንም ሆነ የሰሙትን ማመን አልቻሉም። አንጋፋው ፖለቲከኛ ዦን ክሎድ ዩንከር ከሃያ ስምንቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሀያ ስድስቱን ድምጽ በማግኘት፣ አዲሱ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ከሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦባን በስተቀር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ዦን ክሎድ ዩንከርን እንደማይመርጡ ቃላቸውን ሰጥተዋቸው የነበሩት መሪዎች ሁሉ ቃላቸውን በማጠፍ ለሰውየው ድምፃቸውን ሰጡ።
ኢትዮጵያዊያን “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል፡፡” የሚሉት ተረት እነሆ በዴቪድ ካሜሮን ላይ ደረሰና ዦን ክሎድ ዩንከር ተመረጡ። የጠሏቸው እኒሁ ሰውም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽንን በአዲስ ፕሬዚዳንትነት ወረሱባቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አጠገባቸውና ፊት ለፊታቸው የተቀመጡትን መሪዎች በትዝብት አይን እያዩ “የፈፀማችሁብኝ ታላቅ ክህደት ነው!” አሉና በለሆሳስ ተናገሩ፡፡ሁሉም ነገር አልቆ በመውጣት ላይ እንዳሉ ከቻንስለር አንጌላ መርከል ጋር ተገናኙ፡፡
በሰውየው መመረጥ አንጀታቸው ቅቤ የጠጣው አንጌላ መርከል፤ የለበጣ ሳቅ በመሳቅ ብድራቸውን ለመመለስ አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም የዴቪድ ካሜሮንን ጀርባ መታ መታ በማድረግ “አይዞህ! እንግዲህ መቻል ነው እንጂ ምን ይደረጋል!” በሚል አይነት አጽናንተዋቸው አለፉ፡፡   

Read 1770 times