Tuesday, 08 July 2014 08:17

የእፉዬ ገላ አመፃ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(6 votes)

      “በቃ ረስተውናል…እኛ ራሳችን እንሂድ” አለ ሚኪ፤ ሰንሰለቱን የሚጐትቱን ልጆች በጐኑ ሲያልፉ እየተመለከተ፡፡ ሚኪያስ ሰባት አመቱ ነው፤ የሁሉም ታላቅ ነው፡፡ ዴቭ የሱ ታናሽ ስድስት አመቱ ነው፡፡
ዴቭ፤ “እኛ ራሳችን እንሂድ” የምትለዋን ውሳኔ ሲሰማ የሚያንጠባጥበውን ኳስ ያዘ፡፡ የሆነ የሚያስደስት ገድል እየመጣ እንደሆነ አውቋል፡፡
“እነ ራኬብስ…?” አለው ወንድሙን፡፡
“እኔ‘ጃላቸው…ከፈለጉ ይምጡ” አለ ሚኪያስ፡፡
የአመጽ ሐሳብ ሁሌ የሚፈጥረው ዴቭ ነበር…ዛሬ ሚኪያስ ቀደመው፡፡ ሰንሰለቱ ከትምህርት ቤቱ መግቢያ ላይ የሚነሳው የማታ ተማሪዎች ሊገቡ ሲሉ ነው፡፡ የማታ ተማሪዎች ከመግባታቸው በፊት የቀን ተማሪዎች ግቢውን መልቀቅ ይኖርባቸዋል። ዘጠኝ ሰአት ተኩል ላይ የቀን ተማሪዎች ከክፍል ይለቀቃሉ። አብዛኛው ወላጅ ከግቢ ውጭ መኪናውን አቁሞ በእግሩ ወደ ትምህርት ቤቱ እየገባ ልጆቹን ይለቅማል፡፡
እነ ሚኪያስና ራኬብ ጐረቤታሞች ናቸው፡፡ ሚኪያስና ዴቭ…ራኬብና ኪኪ…እንደዚሁም ሙሴ ወላጆቻቸው ኮንትራት ከፍለውላቸው በታክሲ ነው የሚመላለሱት፡፡ ከዚህ በፊት ያመላልሷቸው የነበሩት ጋሽ ጌታቸው ነበሩ፡፡ ስለታመሙ አዲስ ሰው ተተክቷል፡፡ ወጣት ልጅ ነው፡፡ ግን በሰአቱ አይመጣም፤ ሁሌ ያረፍዳል፤ በተለይ ከትምህርት በኋላ ሊወስዳቸው ሲመጣ፡፡
ራኬብ የሚኪያስ እኩያ ናት፡፡ በጣም ጨዋታ ትወዳለች፡፡ አንደኛ ክፍል ናት፡፡ ሚኪያስ ግን ሁለተኛ ክፍል ገብቷል፡፡ በእድሜም ባይሆን በክፍል ስለሚበልጣቸው እንደ አለቃ ያደርገዋል፡፡ ትንሿ ኪኪ ገና ዜሮ ክላስ ናት፡፡ ከእህቷ ጋር አንድ ጥግ ቁጭ ብለዋል፡፡
ራኬብ እፉዬ ገላ አግኝታ አዲስ ትንግርት ሆኖባታል፡፡ ትይዘውና ትለቀዋለች፡፡ ከንፈሯን አሞጥሙጣ እፍ ትለዋለች፤ በአየር ላይ ትንሽ ከተንሳፈፈ በኋላ ንፋስ እንዳይወስደው በስስት መዳፎቿን አጐድጉዳ ትይዘዋለች፡፡ ይዛ በደንብ ታጠናዋለች፡፡ እፉዬ ገላው የራሱ ነብስ እና የጉዞ ምርጫ እንዳለው ማንም አልነገራትም። ሌላ እፉዬ ገላ ተንሳፍፎ ሲመጣ አየች፡፡ ለኪኪ በመዳፉ ውስጥ ያለውን እንድትይዝላት ነግራ ሌላኛውን ለማፈን ሮጠች፡፡ ሲያመልጣት “ዋይ…ይ” ትላለች፤ ትስቃለች። ሙሴ የምታደርገውን ቦርሳው ላይ ተቀምጦ ይከታተላል፡፡ አንደኛ ክፍል ነው። እድሜው ግን ከእነሚኪያስም ከፍ ሳይል አይቀርም። በአንድ ኮንትራት ታክሲ ከእነሱ ጋር ቢሄድም ሁሌ ሚኪያስ ስለሚኮረኩመው ጉዞውን አይወደውም። ምንም ነገር ወዶ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ራኬብን አፍጥጦ ከመመልከት በስተቀር፡፡ ሚኪያስ በኩርኩም እስኪያነቃው ድረስ የሚያየው ራኬብን ነው፡፡ ንፍጡን እየማገ ዝም ብሎ ራኬብን ያያታል፡፡ ሁሌ ነጭ ሽንኩርት የምትመስል ንፍጥ ከአፍንጫው ቀዳዳ መውረድ ትጀምርና ሳትወርድ ምጐ ይመልሳታል፡፡ የዩኒፎርሙ ሱሪ ወገቡ ሁሌ ስለሚሰፋው እንዳይወልቅ በአንድ እጁ ጨብጦ ይይዘዋል፡፡
ግራ እጁን ሱሪው እንዳይወልቅ ከመያዝ ውጭ ለምንም ነገር አይገለገልበትም፡፡ በትምህርት ገበታው፣ በጓደኞቹ እንደዚሁም በአለም ላይ ያለው ስፍራ አይታወቅም፡፡ መሪ ይሁን ተከታይ አያስታውቅም፡፡
“አንተ ሙሴ! ና” ብሎ ኤርሚያስ ጠራው፡፡ ቦርሳውን እየጐተተ መጣ፡፡ ቦርሳው ሁሌ ተወጥሮ የተጠቀጠቀ ነው፡፡ ዘንድሮ የማይማርበትን የአምና መጽሐፍትና ደብተር ይዞ ነው ወደ ት/ቤት የሚመጣው፡፡ ምሳ ዕቃው ትልቅ ነው፡፡ ማንም ሰው ግን ከእሱ ጋር መብላት አይፈልግም፡፡ ከአመት አመት ቢጫ ሽሮ በጥቁር እንጀራ ነው እናቱ የምትቋጥርለት፡፡
“አንቺ ራኬብ… ኪኪ… ኑ አልኳችሁ አይደል” አለ ኤርሚያስ ተቆጥቶ፡፡ ራኬብ አባርራ ያለ ምርጫው ያፈነችውን እፉዬ ገላ በመዳፏ ውስጥ ከድና እያለከለከለች መጣች፡፡ ኪኪ እህቷ በተወቻት ቦታ፣ እናቷ እንዳዘዘቻት፣ ያዥ የተባለችውን በጥንቃቄ ይዛ ቁጭ ብላለች፡፡ ግን እጇ ትንሽ በመሆኑ ምክንያት እፉዬ ገላውን ጨፍልቃዋለች፡፡ እጇን ከፈት አድርጋ ታየውና መልሳ ትከድናለች፡፡ የእፉዬ ገላው ፀጉሮች በመዳፉ ሙቀት መነጫጨት ጀምረዋል፡፡ ወደ እህቷ ሄዳ አደራዋን ለማስረከብ ተነሳች፡፡ በጥንቃቄ ወስዳ አስረከበቻት፡፡
ራኬብ ነጭ የላስቲክ ከረጢት ውስጥ ሁለቱን እፉዬ ገላዎች ከከተተች በኋላ፣ የከረጢቱን አፍ አክብባ እንደ ፊኛ በአየር ሞላችው፡፡ ሁለቱ እፉዬ ገላዎች በላስቲከ ውስጥ እየተሽከረከሩ ይደንሱ ጀመር፡፡ ራኬብ ደስ አላት፡፡ ሳቀች፡፡ እየቦረቀች ወደ እነ ሚኪያስ መጣች፤ እያሳየቻቸው፡፡
“ገና ብዙ ሰብስቤ…ለገና ክሪስመርስ እሰራባቸዋለሁ”
ዴቭ ላስቲኩን መንጭቋት ሮጠ፡፡ ራኬብ አባረረችው፡፡ እየሮጠ የላስቲኩን ከረጢት ከፍቶ ወደ ላይ ወረወረው፡፡ ራኬብ ላስቲኩን አንስታ እንደገና በትንፋሿ ሞላችው፤ ሁለቱም እፉዬ ገላዎች ሞተዋል፡፡ በላስቲኩ ውስጥ አይጫወቱም። ፀጉሮቻቸው በነዋል፡፡ ቢሞቱም በአየሩ ውስጥ እንዲበተኑ ለማድረግ ፊኛውን ደጋግማ እየበጠበጠች ታየዋለች፡፡
በእፉዬ ገላዎቹ ሞት ብዙም አላዘነችም፡፡ አንድ ቦታ ተሰብስበው በር በሩን ማየት ጀመሩ፡፡ ካሁን ካሁን ወጣቱ የኮንትራት ሹፌር ብቅ ይላል በሚል፤ እየተጠባበቁ ማተሩ፡፡ ትልልቅ ሰዎች ግቢውን ቀስ በቀስ እየሞሉት ነው፡፡ ሰዎቹ ቦርሳና ደብተር የያዙ ናቸው፡፡
“የማታ ተማሪዎች እየመጡ ነው…በቃ ረስተውናል…” አለ ሚኪያስ፡፡
“ቢሮ ሄደን ስልክ እናስደውል” አለች ራኬብ፡፡
“የእናንተ እናት ጋ ወይንስ የእኛ?”  ጠየቀ ዴቭ፡፡
“ማሚ መኪና የላትም” አለች ራኬብ፡፡
“የኛም የላትም” አለ ዴቭ፡፡
“የእኔ አጐት ግን አለው” አለ ሙሴ፤ ንፍጡን እየማገ፡፡
“እሱማ የኔም አጐት አለው…ግን ውጭ ሀገር ነው” አለ ዴቭ፡፡
“ብናስደውልም አይመጡልንም፤ ረስተውናል” አለ ሚኪያስ፡፡
“አይረሱንም ይመጣሉ” አለች ራኬብ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ጭንቀት እየተሰማት መጥቷል፡፡ ታናሿን ኪኪን ወደ ራሷ ስባ አቀፈች፡፡
“አይወዱንም ጠልተውናል” አለ ሙሴ…ከራኬብ ጋር ማውራት እንጂ ወደ ቤቱ የመሄዱ ነገር ብዙ አላሳሰበውም፡፡ ቤቱ ሳይሄድ የቀረበት አንድም ቀን የለም፡፡ ቤቴ ሳልደርስ እቀራለሁ የሚል ፍርሐት የለበትም፡፡
“ይወዱናል…አባቢ ሊወስደን ይመጣል” አለች ራኬብ፡፡ ቤተሰቦቿ እንደማይወዷት ማመን አልፈለገችም፡፡ እንደማይረሷት እርግጠኛ ናት፡፡
ሚኪያስ በር በሩን ይመለከታል፡፡ ራኬብ በላስቲኩ ውስጥ ያሉት እፉዬ ገላዎች እንደማይንሳፈፉና እንደሞቱ ስታውቅ፣ ነፃ አውጥታ ለቀቀቻቸው፡፡ እንደተጨፈለቀ ነጭ አባጨጓሬ በመሬቱ ላይ ተንከባለው,ኧ ቦዩ ውስጥ ለመውደቅ የሚገፋቸውን የንፋስ ሽውታ መጠበቅ ጀመሩ፡፡ ፀሐይ ስትጠልቅ በሰማዩ ላይ የተወቻቸው ቀያይ ዳናዎች ሳይጠፉ፣ አይን ያዝ የሚያደርግ ጨለማ ለመምጣት ይዘጋጅ ጀምሯል፡፡
የማታ ተማሪዎች ግቢውን ሞሉት፡፡ ትምህርት ቤቱ የአዋቂዎች እንጂ የህፃናት መሆኑ ተረሳ፡፡ ጨለማ እና አዋቂዎች ተገናኙ፡፡ ብርሐን እና ህፃናቶቹ ተፋቱ፡፡ አዋቂ ሳይሆኑ…በጨለማ ውስጥ ህፃን ሆኖ ለሚቀመጡት ፍርሐት ዋነኛ አጋራቸው ይሆናል፤ ሁሉም ህፃናት አንድ ላይ ፈሩ፡፡
ሚኪያስ ለሁሉም ሀላፊነት ያለበት መሆኑን ማንም ባያሳውቀውም በደመ ነብሱ ያውቃል፡፡ አንድ ውሳኔ ወሰነ፡፡ “ከአንድ እስከ አስር እስክቆጥር የሚወስደን ታክሲ ካልመጣ እኛ ራሳችን እንሄዳለን” አለ፡፡ የሚሄዱት ወደ ቤታቸው መሆኑ ነው። ከዚህ በፊት ብቻቸውን ወደ ሱቅ ሄደው እንኳን አያውቁም፤ ይቅርና ከት/ቤት ወደ ቤት፡፡
“ከአንድ እስከ ሀምሳ” አለች ራኬብ…ተስፋዋ አልተመናመነም፡፡ በመጠበቅ የተሻለ ነገር እንደሚመጣ አምናለች፡፡ ኪኪ የቁጥር ነገር ሲነሳ ቀን ሲያስደግሙዋት የሚውሉትን ቁጥሮች በተርታ መጥራት ጀመረች፡፡ ከአንድ እስከ አስር ስትቆጥር ጣቷ ስላለቀባት….A,B,C,D,E,F,G የሚለውን መዝሙር መዘመር ጀመረች፡፡ ድምጿ ግን አይሰማም፡፡ መዝሙሯን የምትደግመው በደመነፍስ ነው፡፡  ፍርሐቷን ማሰላሰያ ዜማ ነው፡፡
“ከአንድ እስከ ሃያ” በሚለው ተስማሙ፡፡ ፍርሐት ለሰው ልጆች ከፊደልና ቁጥር የሚቀድም እውቀት ነው፡፡ ሙሴ ስምምነቱን የሰማ አይመስልም፡፡ ሰው መሀል ሆኖ የመረሳት እርግማን አለበት፡፡
“ይኼንን ጠጠር እውጣለሁ ወይንስ አልውጥም” አላት፤ ራኬብን አንድ ትንሽ ድቡልቡል ድንጋይ በመዳፉ ላይ አድርጐ እያሳያት፡፡ ጭንቀታቸውን ለቅጽበት ረስተው “አትውጥም” አሉት ወንዶቹ። ሁለቱ ሴቶች ሙሴን ዝም ብለው ያዩታል፡፡ እንደ ቁሻሻ ሳህን፡፡ አይናቸው እንዳይቆሽሽ ተጠንቅቀው ነው የሚያዩት፡፡
ሙሴ ሁሉንም የሚስብ ነገር መናገሩን ሲገነዘብ፣ ድፍረቱን እጥፍ ድርብ አደረገው፡፡ ንፍጡን በደንብ አድርጐ ከማገ በኋላ፣ ጠጠሯን ወደ አፉ ከተታት…አይኑን ጭምቅ አድርጐ ታግሎ ዋጠ፡፡ ቋቅ አለው። አይኑ አለቀሰ፡፡ ጠጠሯን ተፋት፡፡ ሚኪያስ ሆዱን ታቅፎ ሳቀ፡፡ ዴቭ በካልቾ ሙሴን ሳተው፡፡
ራኬብ “አንድ” ብላ መቁጠር ጀመረች፡፡ ወንዶቹ ሙሴ ላይ እየሳቁ ስለነበር አልሰሟትም፡፡ ስድስት ላይ ስትደርስ ባለመስማታቸው ብስጭት ብላ፤“ከአንድ እስከ ሃያ ቆጥሬአለሁ..ነይ ኪኪ እንሂድ” ብላ የታናሽ እህቷን ቦርሳ አነሳች፡፡ የራሷን በጀርባዋ አዘለች፡፡ ዞር ብላ እንኳን ሳታይ ወደ በሩ ገሰገሰች፡፡ ወንዶቹ ሳቃቸውን አቆሙ፡፡
“እንዴ ሳይቆጠር” አለ ሚኪያስ “ሂጂያ…ወደ ቤት መንገዱ ጠፍቶብሽ ክፉ ሰዎች አንቺና ኪኪን አይናችሁን አጥፍተው ለማኝ ቢያደርጉሽ ግን እኔ የለሁበትም” አላት ከጀርባዋ፡፡
“ያድርጉኝ…ታክሲ ተሳፍሬ ቤት ገብቼ እጠብቃችኋለሁ” ብላ ፊቷን ሳታዞር መለሰችላቸው። ሙሴ በአንድ እጁ ሱሪውን ከፍ እያደረገ ራኬብን ለመከተል ሲዳዳ፣ ሚኪያስ ማንቁርቱን ይዞ መለሰው፡፡
“ይኼንን ጠጠር እውጣለሁ ብለህ ተወራርደሀል፤ ካልዋጥክ አስር ኩርኩም ትቀምሳለህ” አለው እያጉረጠረጠ፡፡ ክፋት በልጆች ይብሳል፡፡
“አልተወራረድኩም! መች ተወራረድኩ?” አለ ሙሴ።
“ተወራርደሃል! ደሞ አጐትህ መኪና አለው? ውሸታም እፍርታም!”
ሙሴ ንፍጡን እየማገ “አጐቴ አለው፤ ግን ሞቷል” አለ፡፡
“ምን ሆኖ?”
“ታሞ”
“ምኑን?”
“ሆድ ቁርጠት”
“በሆድ ቁርጠት ሰው ይሞታል?”
“እሺ በብርድ”
ሚኪያስ በኩርኩም እየመታው “አሁን ጠጠር እውጣለሁ ብለህ ተወራርደሃል፤ ዋጥ!”
ከመሬት አንድ ድንጋይ አንስቶ ሰጠው፡፡ ጠጠር የነበረ ድንጋይ ወይንም ድንጋይ በመሆን ላይ ያለ ጠጠር፡፡
“ይኼ ትልቅ ነው…ያንቀኛል…ያስሞተኛል”
“ትንሽማ ማንም ይውጣል”
“ትልቅ ጠጠር መዋጥ ያስሞተኛል”
“ትልቅ ጠጠር ከዋጥክ ጥሩ ምሳ ሳመጣ ሳመጣ… አብረን እንበላለን እሺ… ትውጣለህ?”
“እሺ እውጣለሁ፡፡ ግን ስጋ ወጥ ስታመጣ ታበላኛለህ!”
ድንጋዩን ተቀብሎ ከብዙ መተናነቅ በኋላ ዋጠው። ሲተናነቀውና ቋቅ ሲለው ሚኪያስና ዴቭ ሆዳቸውን ይዘው ይስቃሉ፡፡ ብዙ ከሳቁ በኋላ አንድ አንድ ኩርኩም መረቁለት፡፡ ባይውጥ ኖሮ ኩርኩሙ ወደ ሃያ ከፍ ይል ነበር፡፡
“ስጋ ወጥ ሳመጣ የማበላህ ከመሰለህ ሲያምርህ ይቅር” አለው፤ ሚኪያስ ከምርቃቱ በኋላ፡፡
“ድንጋዩ ጉሮሮዬን ቧጠጠኝ” አለ፤ ንፍጡንና ምራቁን አንድ ላይ ምጎ እየዋጠ፡፡
“ራኬብን ተከትያት ልሂድ…ክፉ ሰዎች ወስደዋት…አይኗን አጥፍተው ለማኝ እንዳያደርጓት…በናትህ ሚኪ ልቀቀኝ…በናትህ”
“አልለቅህም ጠጠር መዋጥ ማነው ያስተማረህ?”
“አባቴ ነው”
“አባቴ ሞቷል አላልክም?”
“አጐቴ ነው የሞተው…እንጀራ አባቴማ አለ”
“አባትህስ?”
“እኔ ሳልወለድ ነው የሞተው”
ሚኪያስ፤ እናቱ አንድ ቀን ከሰራተኛቸው ጋር ስለ ሙሴ አባት ስታወራ በጭምጭምታ የሰማው ትዝ አለው፡፡ እርጉዝ ሚስቱን ለማስተዳደር ስራ ፈልጐ ስላጣ፣ የራሱን አንገት በአናጢ መጋዙ ቆርጦ፣ ሰው እንዳያተርፈው መጋዙን እያወናጨፈ አላስቀርብ ብሎ፣ ሳፋ ሳይደፋበት አንገቱን ተቆርጦ እንደተለቀቀ ዶሮ እየሮጠ እንደሞተ ስትናገር ሰምቷል፡፡  
“አባትህ አንገታቸው ሲቆረጥ እንዴት አሉ…ኮ…ፉ…ፉ…ኮ…ኮ…ፉ….ፉ…አሉ” እየተንገዳገደ እንደ ጭራቅ እያጓራ አሳየው፡፡
“እኔ አላስታውስም፤ አልተወለድኩም ነበር” መለሰ ሙሴ፤ የማያውቀው አባቱ ሳይሆን በማያውቁት መንገድ ወደ ቤት የሄዱት ራኬብና ኪኪ ናቸው ያስጨነቁት፡፡
“አንገታቸው ተቦጭቆ በትከሻቸው ብቻ ነው መንግስተ ሰማይ የሚገቡት”
ሚኪያስ በሚናገረው እያንዳንዱ ነገር ዴቭ ሆዱን ይዞ ይስቃል፡፡
ስለ ኮንትራት ታክሲው፣ ሳይመጣ ስለቀረው ወጣቱ ሾፌር ረስተዋል፡፡ ሚኪያስም እንደ ታናሽ ወንድሙ በቤተሰቦቹ ላይ ይተማመናል። እናቱ ከትምህርት ቤት እንዳልተመለሱ ስታውቅ ተንደርድራ መምጣቷ አይቀርም፡፡ እንደው ለወሬ ያህል፣ ለጉራ ቤተሰቦቻችን ረስተውናል አሉ እንጂ ደፍረው ወደ ቤት ለመሄድ በጭራሽ አይሞክሩም፡፡ አባታቸውም የዋዛ ሰው አይደለም፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ትዕዛዝ ለመውጣት ጭራሽ ድፍረትም ሆነ አላማ የላቸውም፡፡ መወደዳቸውን የሚያረጋግጡት በወላጆቻቸው ጭንቀት መጠን ነው፡፡  
“እና ጠጠር መዋጥ ያስተማረህ ማነው?”
“አባቴ ነው…ማለት እንጀራ አባቴ”
“እንዴት አድርገው አስተማሩህ?”
“ጠጠር ከዋጥክ ሃምሳ ሳንቲም እሰጥሀለሁ ይለኛል፤ እኔ እውጣለሁ”
“እንቢ ብትልስ?”
“ከቤት አባርርሃለሁ ይለኛል”
“ትልቅ ጠጠር ከዋጥክስ?”
“ምንም አያረገኝም…በጣም ትልቅ ጠጠር ከሆነ…ትንሽ ያመኛል ግን ስውጥ ስለሚያስቀው ያዝንልኝና ይወደኛል፡፡ ደብተርና እስክሪፕቶ ይገዛልኛል፡፡ በጣም ካሳቅሁት ጉልበቱ ላይ ያስቀምጠኝና ፀጉሬን ያሻሸኛል”
“እናቴ እንጀራ አባትህ እብድ ነው ብላኛለች…እናትህን የእብድ ውሻ በሽታ ይዞኛል ብሎ ጀርባዋን ነክሷታል አይደል?”
“አሁን ግን የነከሳት ተሽሏታል፡፡ ይቅርታ ብሏታል፡፡ ህመሙ ተሽሎታል፡፡ ወደ ስራው ተመልሷል፡፡”
“ደሞ ለትምህርት ቤት የሚከፍሉልህ ቄሶቹ ናቸው አይደል?”
“አይ እናቴን ለማገዝ ብለው ነው”
“ደግሞ ስታድግ ቄስ መሆን አለብህ ተብለሀል…አይደል?”
“አልተባልኩም”
“ተብለሀል አትዋሽ…እናቴ ነግራኛለች”
“እኔንጃ…”
“ተብለሀል” በኩርኩም አናቱ ላይ ቆፈረው፡፡
“እህ!…እኔን‘ጃ”
“አሁን አጐንብሰህ ሶስት ጊዜ ጫማዬን ሳምና እነ ራኬብን ፈልገህ ኑ…መኪና መጥቷል በላቸው፤ ላይ ጊቢ ናቸው”
“ከሄዱስ?”
“የት ይሄዳሉ…ለብቻቸው መሄድ አይችሉም…”
አጐንብሶ ጫማውን ስሞ ወደ ትምህርት ቤቱ መግቢያ አቅጣጫ ተፈተለከ፡፡ አንዳች ነገር ልቡ ውስጥ እንደ ዘይት የመሰለ የሚዝለገለግ ነገር ፈጥሮበታል፡፡ የተፈጠረበት ነገር ፍርሃት ተብሎ እንደሚጠራ ገና አልገባውም፡፡ ቢገባውም እንዳልተረዳ መሆን አለበት፡፡ የገባንን ነገር እንዳልተረዳን ስንሆን የሚፈጠረው ስሜት “ተስፋ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ሁሌ ጠጠር ሲውጥ የሚከሰት አንድ መጥፎ ነገር እንዳለ ይሰማዋል፡፡ ህይወትን ወደፊት የሚያስቀጥለው የሚሰማንን ባለመስማት ነው፡፡
ራኬብ እና ኪኪ በሩ አካባቢ የሉም፡፡ ቅጽሩን ዞሮ ፈለጋቸው፡፡ በልቡ ውስጥ አንድ መጥፎ ስሜት ይላወስበታል፡፡ ራኬብ እንደ እፉዬ ገላው በና ጠፍታለች። ወይንም እንደ እፉዬ ገላው ወደ ቤቷ አቅጣጫ ስትሄድ በመዳፉ ውስጥ አፍኖ ያስቀራት፣ ሊጫወትባት የሚፈልግ ነገር አለ፡፡
ሙሴ በእነ ራኬብ ፋንታ እናቱን በመግቢያው በኩል ስትመጣ አገኛት፡፡ እቅፍ አድርጋ ሳመችው። የእሱ እናት እንጀራ የመጋገር ስራዋን አቋርጣ፣ ከትምህርት ቤት ወስዳው አታውቅም፡፡
“የታሉ እነ ሚኪ…እነ ራኬብ?”
“ራኬብና ኪኪ ወደ ቤት ሄደዋል
“ምን? ወይ ዛሬ! ጉድ ፈላ… በየት በኩል ሄዱ? ምን እርግማን ነው ዛሬ የወረደብን ሙሱ? ወይ መአት! ሲጨልም አንዴ ነው … አሁን ከመሸ እኮ የመኪና አደጋ ደርሶ እናኑዬና ጋሽ ሚናስ እኔ አፈር ልብላ…. ሆስፒታል ገብተዋል…. ሙሱ ሰማህ?”
የሙሴ እናት ከትምህርት ቤት ልታመጣቸው ከዚህ በፊት መጥታ አታውቅም፡፡ ሚኪያስና ወንድሙ ዳዊት “አባቢ ወይ እማሚ ለምን ሳይመጡ ቀሩ?” ብለው ሲጠይቋት መልስ አልሰጠችም። እንባዋን እንዳያዩ ብትሞክርም መሸሸጉ አልተዋጣላትም፡፡ ሳይደነግጡ ቤታቸው ማስገባት ነው የመጀመሪያ ፍላጐቷ፡፡ የኮንትራት ታክሲ የመክፈያ አቅም እንደሌላት ሳታገናዝብ አንዱን ላዳ ተነጋግራ ልጆቹን አስገባቻቸው፡፡
በመንገዱ ወደ ላይና ወደ ታች እየተመላለሱ ራኬብና ሚጢጢዋ ኪኪን ለማግኘት ለፉ፡፡ እጓለ ማኡታኖቹን ወንድማማቾች ብቻ ይዛ ስትመለስ…በቤቱ ውስጥ ለቅሶው ድብልቅልቅ ብሏል፡፡
ሆስፒታል የገባው የእነ ሚኪ አባትና እናት ሬሳ ሊታከም ሳይሆን ሊሰፋ ነው፡፡ ከተጨፈለቀው መኪና ውስጥ አስከሬናቸው የወጣው በብዙ ብጭቅጫቂ ነው፡፡ በድንጋጤና መከራ በድንገት ወደተረበሸው ቤት ወንዶቹን አድርሳ፣ ለሴቶቹ የእነ ራኬብ ወላጆች ተጨማሪ ረብሻ እንዳይፈጠር በሚል፣እንዳይለቀስ ብላ ነገረቻቸው፡፡
በድንጋጤ ጨርቃቸውን ጥለው ከሚበርሩት ወላጆች ጋር ሴቶቹን ልጆች ለመፈለግ ወደ ትምህርት ቤቱ በድጋሚ ተመለሰች፡፡ ግማሾች ፍለጋው ላይ ሲሰማሩ የተቀሩት ፖሊስ ጣቢያ ለማመልከት ወረዱ፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰአት ገደማ ተስፋ ቆርጠው እየተላቀሱ ወደ ሰፈር ተመለሱ። ከሞቱት ይበልጥ የጠፉት ልጆች ሀዘን የበረታ ነበር። የሙሴ እናት ሙሴን ባዶ ቤት ጥላው ካበደው እንጀራ አባቱ ጋር ሌሊቱን በእነ ሚኪያስ ቤትና በእነ ራኬብ ወላጆች ቤት ተራ በተራ ስትመላለስና ስታጽናና አደረች፡፡ ሊነጋጋ ሲል ተመለሰች፡፡ ሙሴን ከአልጋው ቀስቅሳ ስቅስቅስ ብላ እያለቀሰች አንድ ጥያቄ ጠየቀችው፡፡ አስተያየቷ ፍርሐት የተሞላበት ነው፡፡
“ስንት ጠጠር ዋጥክ?”… ማንም የፈለገውን ያህል ቢበድልህ ጠጠር አትዋጥባቸው ብዬህ እሺ ብለህ ምለህልኝ አልነበር? ለምን ዋጥክባቸው…?!”
“እኔ በእነ ሚኪያስ ላይ ነው መዋጥ የፈለኩት…በሚኪያስ አባትና እናቱ ላይ አይደለም”
“ወላጆቻቸው ከሞቱ እነ ሚኪያስስ ይተርፋሉ?…እንደውም በችጋር ተሰቃይተው አጉል ይሆናሉ አይደል?”
“እኔ ወላጆቻቸውን አልተቀየምኩም” አለ ሙሴ
“እነ ሚኪያስን ብትቀየምስ ጠጠር የሚያስውጥ ደረጃ ትጨክንባቸዋለህ? ታውቃለህ አይደል…አንተ ጠጠር ጨብጠህ መወለድህን፡፡ ጠጠር በሆድህ ከገባ ያስከፋህ ሰው መጥፎ መከራ እንደሚጠብቀው…ግን ለምን እንዲህ ታደርጋለህ… የእኔና ያንተ ተፈጥሮ እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? አንተ እግዜር ነህ እንዴ ቁጣህ እንደዚህ የሚበረታው? እንደው እግዚኦ! ምን አይነት ሲኦል ነው ከማህፀኔ የወጣው?...”
ሙሴም በራሱ ተፈጥሮ አዝኖ አለቀሰ፤ ተንሰቅስቆ፡፡ ምናለ ጠጠር ባልዋጥኩ ኖሮ… ሰዎች እኔን አሳዝነው በድለው ቢገሉኝ ይሻላል…እንጂ እኔ ለምን እበቀላለሁ? እያለ ተነፋርቆ አለቀሰ፡፡ እናቱም እየተንጐራደደች እዬዬ አለች፡፡ የእእምሮ መታወክ ያለበት እንጀራ አባቱ በንጽጽር ጥሩ ስለሆነ ነው ትንሽ ጠጠር ያስውጠው የነበረው፡፡ በንጽጽር አነስ ያለ አደጋ የደረሰበትም ካስዋጠው የጠጠር መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ባይሞትም የማይኖር ዋጋ የለሽ በሽተኛ ሆነ፤ በጠጠሩ ዳፋ፡፡
ለቅሶአቸው ጋብ ሲል፤
“እነ ራኬብስ ምን አድርገውህ ነው እንደ አመድ ቦነው እንዲጠፉ ያደረካቸው?...እሺ ሴቶቹ ምን አደረጉህ?...የት እንደደረሱ ንገረኝ? ሞተዋል?”
“እሱን እኔ አይደለሁም ራሱ እፉዬ ገላው ነው እንደዚያ ያደረጋቸው፡፡ የእፉዬ ገላውን ጉዞ አሰናክላ ራኬብ በላስቲክ ውስጥ ከተተችው፤ ቀጥሎ ኪኪ ደግሞ በላብ በራሰ እጇ የሚበንንበትን ፀጉሩን ነጨችበት፤ ወድቆ ቦይ ውስጥ ገባ፤ መንገዱን ስላሰናከሉት የነሱም መንገድ ይሰናከላል፡፡ ግን አይሞቱም፡፡ ይገኛሉ፡፡
ግን እናቴ የእውነት እልሻለሁ ስለ እፉዬ ገላ የማውቀው ምንም ነገር የለም ነበር፡፡ ራኬብ ስትጠፋ ነው ነገሩን የገመትኩት፡፡ ራኬብና ኪኪ ክፉ አይደሉም። ክፉ ስላልሆኑ አይሞቱም፡፡ ከጠፉበት ወደ ቤታቸው ይመልሳቸዋል፡፡ እነሱ ራሳቸው እፉዬ ገላዎች ናቸው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ጠፍተው አልባሌ ሰው እጅ ውስጥ ቢቆዩም ምንም ሳይሆኑ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ”
ራኬብና ኪኪ በአንድ ሴትዮ መኪና ተጭነው ወደ ቤታቸው መጡ፡፡ ሌሊቱን ግን ያደሩት እንደ እፉዬ ገላዎቹ አንድ የማያውቁት አልባሌ ቦታ ታግተው ነው። መልካም ባልሆኑ እጆችም ተነካክተዋል። ደንግጠዋል። ስነ ልቦናቸው ተሸማቅቋል፤ ግን በህይወት ተርፈዋል፡፡
ሙሴ ወደ ጓሮ ሄዶ ትልቁን ጠጠር አነሳ፡፡ ሊዋጥ የማይችለውን ጠጠር አፉን በስፋት ከፍቶ ታግሎ በጉሮሮው አስገባው፡፡ ሊያወርደው ግን አልቻለም፡፡ ትንፋሹ ተዘጋ፡፡ አይኑ ተገለባበጠ፡፡ ነፍስ ጊቢ ነፍስ ውጪ ላይ ሆኖ ሲንደፋደፍ አእምሮው የታወከው እንጀራ አባቱ፣ ሆዱን ይዞ ሲስቅ ይሰማዋል፡፡ ድሮም ስለሚያስቀው ነው ሳንቲም ልስጥህና ጠጠር ስትውጥ አይቼ ልዝናና የሚለው፡፡ ሙሴ ተንደፋድፎ ሲጨርስ ነፍሱ ወጣች። ከእንግዲህ እሱን ማንም አያስቀይመውም፤ እሱም ከእንግዲህ ቂም አይዝም፡፡ ጠጠርም አይውጥም፡፡  

Read 3112 times