Print this page
Tuesday, 08 July 2014 08:09

ZTE የ300ሺ ብር መፃሕፍት ለት/ቤቶች ለገሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በሞባይል ኔትወርክ ዝርጋታ የሚታወቀው ZTE የተባለው አለምአቀፍ የቻይና ኩባንያ ለሶስት የኦሮሚያ ት/ቤቶች የ300ሺህ ብር መፃሕፍትን ለገሰ፡፡
በፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሙሎ ወረዳ ሰኞ ገበያ ለተባለው የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ኢሉ ወረዳ ለሚገኘው አስጐሪ አንደኛ ደረጃ ት/ቤትና በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀሬ ወረዳ ለሚገኘው ኤፌብሪ ለተሰኘው አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ለእያንዳንዳቸው 1559 የማጣቀሻ መፃሕፍትንና የተለያየ መጠን ያላቸው አራት አራት ሉሎችን (Globes) አበርክቷል፡፡
የእንግሊዝኛ፣ የሂሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ኦክስፎርድ፣ እሌሌ፣ ሜሪትና ሌሎች መዝገበ ቃላት ለትምህርት ቤቱ ቤተ-መፅሐፍት የተሰጡ ሲሆን መጽሐፍቱ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በኦሮምኛ የተዘጋጁ ናቸው፡፡
እነዚህ መጽሐፍት ሰኞ ገበያ ት/ቤት ለሚማሩ 645 ተማሪዎች፣ አስጐሪ ት/ቤት ለሚማሩ 1702 ተማሪዎችና ኤፌብሪ ለሚማሩ 1865 ተማሪዎች ጥቅም ላይ ይውላሉም ተብሏል፡፡  የሰኞ ገበያ ት/ቤት ዳይሬክተር አቶ ደምሴ በቀለ ባደረጉት ንግግር፤ የት/ቤቱ ቤተ - መጽሐፍት ባዶ እንደነበር አስታውሰው፤  ZTE ባደረገው የመጽሐፍት ልገሳ ተጠቅመው መምህራንም ሆነ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
የ ZTE የሰው ሃይል ዳይሬክተር ሚስተር ሀን ዩን ጂ በበኩላቸው፤ ለየትኛውም አገር እድገት መሰረቱ እውቀት በመሆኑ ተማሪዎቹ በእውቀት ታንፀው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ መጽሐፍቱ ወሳኝ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ባለሙያው አቶ ይርጉ ለሽ ይበሉም በበኩላቸው በኦሮሚያ ከሚገኙ ወደ 13 ሺህ የሚጠጉ ት/ቤቶች ለአዲስ አበባ ቅርብ የሆኑ ት/ቤቶችን መርጠው እንዲሰጡ ከትምህርት ሚኒስቴር በደረሳቸው ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሱትን ትምህርት ቤቶች ለእርዳታ መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

Read 2196 times