Tuesday, 08 July 2014 08:07

ቢዝነስ የሚመራበት ዋነኛ ነጥቦች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(45 votes)

እስካሁን የነበረው የቢዝነስ አሰራር ባህላዊ በልምድና በግምት የሚመራ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ከእጅ ወደ አፍ እንጂ ለእድገት እንዳላበቃን የሚታወቅ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ግን በቀድሞው መንገድ መቀጠል አይቻልም። ምክንያቱ ደግሞ ለውጥና እድገት ስለሚያስፈልገን ነው፡፡
አሁን ለውጥ (ፓራዳይምሺፍት) ያስፈልገናል። ከቀድሞው ባህላዊና ልማዳዊ የቢዝነስ አሰራር ወጥተን፣ በእቅድና በዘመናዊ የቢዝነስ አሰራር መመራት ያስፈልጋል፡፡ ያኔ ነው በአጭር ጊዜ ሀብት ማፍራት፣ መክበርና አገር ማሳደግ… የምንችለው፡፡
አንዳንድ የቢዝነስ ሰዎችና ወጣቱ ኃይል፣ ለአገሪቷ አዲስ የሆነው የቢዝነስ አሰራር የገባቸው ይመስላል። ምክንቱም የቢዝነስ ዕቅድ፣ የቢዝነስ ግብ፣ … ማለት ጀምረዋላ! የእኔም አነሳስ ይህንኑ ዘመናዊ የቢዝነስ አሰራር ማጠናከር ነው፡፡ ምክንያቱም 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ቢዝነስም ሆነ ሕይወት ያለ ዕቅድና ግብ መምራት ኋላ ቀርነት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ወጣቶች፣ በግልም ሆነ ተደራጅተው በዝንባሌና በችሎታቸው የራሳቸውን ቢዝነስ እየጀመሩ ነው፡፡ ይኼ ጥሩ የዕድገት መሰረት ነው፡፡ ታዲያ ድካማቸው ፍሬ እንዲያፈራ ግልጽና የጠራ ዓላማና ግብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ማንኛውም ዕቅድና ግብ ደግሞ በሳይንስ በተረጋገጠ “ስማርት” በተባለ ዘዴ መፈተን አለበት፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች የተቃኘ ቢዝነስ ስኬታማ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
ቢዝነስ የጀመራችሁ፣ ዕቅድና ግባችሁን በ”ስማርት” እንድትፈትሹና እንድታቃኑ፣ ዝግጅት ላይ የሆናችሁ ደግሞ እቅድና ግባችሁን በ”ስማርት” እንድትቀርፁ አራቱን ዘዴዎች አቅርበናል፡፡ “ስማርት” የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ቢኖረውም SMART ስፔሲፊክ፣ ሜዠረብል፣ አቴንኤብል፣ ሪያሊስቲክ ታይምቴብል ከሚሉት ቃላት የመጀመሪያ ፊደላት የተወሰደ ምህፃረ ቃል ነው፡፡
ስፔስፊክ (Specific):- የሚለው የቢዝነስ ግባችሁ፣ ከሌላው የቢዝነስ ፕላንና ግብ ጋር የማይመሳሰል፣ በራሱ የጥራት ደረጃና ነባራዊ ሁኔታ የሚተገበር፣ ግልፅና ጥርት ያለ፣ በወረቀት ላይ የሰፈረ መሆነ አለበት፡፡
በደፈናው ግባችን ሀብት ማፍራት፣ ዕድገት ማስመዝገብ፣ ኤክስፖርት ማድረግ፣… የሚል ከሆነ ልክ አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ ማምረቻ መሳሪያዎች በመትከል፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል (ባለሙያ) በመጠቀም በአንድ፣ ሁለት፣ አምስት፣ አስር፣… ዓመት እዚህ ደረጃ ላይ (አንድ፣ ሁለት፣ አምስት፣ ሀምሳ፣… ሚሊዮን ብር ገቢ ላይ እንደርሳለን… በማለት አሰራሩንና የሚደረስበትን ደረጃ ጥርት ባለ መንገድ በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፡፡
ግቡ የሚለካ (Measurable) መሆን አለበት። አንድ ድርጅት በየጊዜው የደረሰበትን ውጤት (ደረጃ) መመዝገብ አለበት፡፡ ውጤት ማወቅ እደርስበታለሁ ለተባለ ግብ፣ ትክክለኛ መስመር ላይ መሆን ወይም ወደኋላ መቅረትን ያመለክታል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ አንድ ሚሊዮን ብር ገቢ ይኖረናል ካላችሁ፣ በዓመቱ አጋማሽ ግማሽ ሚሊዮን ብር ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ካልሆነ አተገባበራችሁ ወይም ሌላ ስህተት ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ግባችሁን ለማሟላት ቆም ብላችሁ ራሳችሁን መፈተሽና ስህተትን አርሞ፣ ግብን ለማሳካት መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች መቀየስ ያስፈልጋል፡፡
የበጀት መዝጊያው የሚያሳየው ግባችሁ መሳካቱን ወይም ችግር እንደገጠመው ነው፡፡ ግባችን ያልተሳካው በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ማነስ፣ በገበያ መጥፋት፣ በመብራት መቆራረጥ፣… ምክንያት መደርደር አይገባም፡፡ ለምን መሰላችሁ? መጀመሪያውኑ ዕቅዱ ሲወጣ፣ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ገምቶ ጥሬ ዕቃ ቢያጥረን፣ ገበያ ቢጠፋ መብራት ቢቆራረጥ … ብሎ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
ግቡ የሚሳካ (Attainable) መሆን አለበት። ግብ ለይስሙላ ሳይሆን፣ በእርግጠኝነት ማሳካት የሚቻል፣ ወይም አስቸጋሪ ሁኔታ እንኳ ቢያጋጥም መስዋዕት በመክፈል የሚሳካ እንጂ በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ፣ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ከመጠን በላይ የተለጠጠና (Ambitious) ስሜታዊ መሆን የለበትም፡፡
ዓመታዊ ግባችሁ አንድ ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ነው እንበል፡፡ ነገር ግን በዓመቱ መጨረሻ የደረሳችሁበት ገቢ 100ሺ ብር ቢሆን መጀመሪያውኑ ስታቅዱ ምናልባት ገቢያችን በፍፁም ያልጠበቅነው ቢሆን በምን ዓይነት መስዋዕትነት እናሳካዋለን? በማለት ካላሰባችሁ በጣም ከባድ ችግር ነው፡፡
ቀደም ሲል የነበረው ዓመታዊ ገቢ የሽያጫችሁን 20 በመቶ ቢሆን ያልተጠበቁ ድንገተኛ ሁኔታዎች ተከስተው ችግር ቢፈጠር፣ ግባችሁን ለማሳካት በሳምንት ከ90 እስከ 100 ሰዓት መስራት እንዳለባችሁ ካልወሰናችሁ፣ ከፍተኛ ውድቀት ያጋጥማችኋል፡፡
ተጨባጭና ትክክለኛ የጊዜ ገደብ (Realistic Timetable) አንድ ፕሮጀክት ወይም ግብ የጊዜ ገደብ ከሌለው፣ የውሸት ይሆናል፡፡ ምን ማለት ነው? በዓመቱ መጨረሻ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ እናገኛለን፣ ፕሮጀክቱን በ18 ወር ጨርሰን እናስረክባለን፣… ተብሎ መታቀድና ግብ መቆረጥ አለበት፡፡ ያለበለዚያ ዋጋ የለውም፡፡
ብዙ ጊዜ የጊዜ ገደብ ሲቃረብ መጣደፍ የሰው ልጅ ባህርይ ነው፡፡ የጊዜ ገደብ ሳይቃረብ የሚሰሩት ቅድሚያ የሚሰጣቸው አጣዳፊ ነገሮች ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ሕልምና ግብዎን ወደ ኋላ ይገፋል፤ ዕቅድ ያሰናክላል፡፡ አንድ ፕሮጀክት ጊዜ በወሰደ ቁጥር የብዙ ነገር ወጪ ይጨምራል፤ ትርፍ ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ነው ብዙ የውጭ ተቋራጮች በተዋዋሉበት ወይም ከዚያ በታች በሆነ ጊዜ ጨርሰው ለማስረከብ የሚጣደፉት፡፡


Read 15311 times