Tuesday, 08 July 2014 08:02

መድኃኒቶች በታዘዘላቸው ሰዓት ካልተወሰዱ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

መድኃኒት ቤት (ፋርማሲ) ሄደው ሐኪም ያዘዘልዎትን የመድኃኒት መግዣ ወረቀት ሲሰጡ ፋርማሲስቱ፣ አወሳሰዱን በብልቃጡ ኮሮጆ ወይም ክኒኑን በጠቀለለበት ወረቀት ላይ ‹በቀን አንድ ጊዜ› ብለው ይሰጣሉ፡፡ ስህተቱ መድኃኒቱን ያዘዘው ሐኪም ይሁን ወይም የፋርማሲስቱ አይታወቅም እንጂ ልክ አይደለም፡፡ መድኃኒቱስ ‹በቀን አንድ ጊዜ› ይወሰድ። ግን መቼ? ጧት፣ ቀን፣ ማታ ወይስ ሌሊት? ግልጽ አይደለም፡፡
መድኃኒቶቹ የሚወሰዱበት ሰዓት ካልታወቀ ችግር አለው፡፡ ምክንያቱም ውጤታማ የሚሆኑባቸው ሰዓት አላቸው፡፡ ያለበለዚያ፣ ማሻላቸውንና ማዳናቸው ቀርቶ ጉዳት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ እንዴት? ቢባል እንስሳትም ሆኑ ተክሎች እንቅልፍ የሚተኙበት፣ ሆርሞን የሚያመርቱበት፣ ሌሎች ሂደቶችን የሚቆጣጠሩበት ተፈጥሯዊ የሰዓት ዑደት አላቸው፡፡
ብዙ መድኃኒቶች መወሰድ ባለባቸው ሰዓት ካልተወሰዱ ጥቅም ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ “በተሳሳተ ሰዓት ከተወሰዱ፣ ድርጊቱን ዝም ብለው በቸልታ አይመለከቱትም፡፡ መልሳቸው መጥፎ ሊሆን ይችላል” ይላሉ በቴክሳስ አውስተን ዩኒቨርሲቲ የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ሚሼል ሰለንስኪ፡፡ “መድኃኒቶቹ በጭራሽ ዋጋ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ውጤታቸው በጣም ዝቅተኛ ይሆናል ወይም ድርጊቱን በቸልታ ላይመለከቱ ይችላሉ፡፡ ‹ባዕድ አካል መጣብን› ብለው መድኃኒቱን የሚያከሽፍ ነገር ሊያዘጋጁ ይችላሉ” ብለዋል ምሁሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚወሰዱት መድኃኒቶች ከፍተኛ ጥቅም እንዲሰጡ ወይም የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳት ዝቅተኛ እንዲሆን drug chronotherapy advocats cyncing የተባለ የመድኃኒት አወሳሰድ ዘዴ መጥቷል፣ በዚህና በሌሎች ዘዴዎች ላይ ተመስርቶ ለተለያዩ ሕመሞች የሚታዘዙ መድኃኒቶች መወሰድ ያለባቸውን ሰዓት (ጊዜ) እንዲህ አቅርበናል። (ማሳሰቢያ፡- በፍፁም ሐኪምዎን ሳያማክሩ ወይም መድኃኒት የሚሸጥልዎትን ባለሙያ ሳያነጋግሩ መድኃኒት የሚወስዱበትን ጊዜ እንዳይለውጡ!!)
በጧት መወሰድ ያለባቸው መድኃኒቶች
የድብርት መድኃኒት፡- የተወሰኑ ሰሮቶኒን (Cerotonin) የተባሉ ነርቭ አነቃቂ ኬሚካሎች፣ የድብርት (ድባቴ) ሕመም ያለባቸው ሰዎች ጥሩ እንቅልፍ እንዳይተኙ (እንዳያገኙ) ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ሕሙማኑ ጧት ሲነሱ ድብር ይላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ባለሙያዎች ብዙ ጊዜ ሕሙማኑ ከእንቅልፍ ሲነሱ መድኃኒታቸውን እንዲወስዱ የሚያዙት፡፡
የአጥንት መሳሳት መድኃኒቶች፡- ይህ የአጥንት በሽታ አብዛኛውን ጊዜ ያረጡ ሴቶችን አጥንት በጣም በመቦርቦር፣ በቀላሉ እንዲሰበርና በዝግታ እንዲያብጥ የሚያደርግ ነው፡፡ ሰውነታችን ታዲያ ለዚህ በሽታ የሚታዘዙትን እንደ ቦኒቫ እና ፎሳማክስ (Boniva and Fosamax) ያሉ መድኃኒቶችን በቀላሉ አይቀበልም፡፡
ስለዚህ ሐኪሞች ሕሙማኑ፣ ጧት በማለዳ ምንም ሳይቀምሱ ባዶ ሆዳቸውን መድኃኒታቸውን በአንድ ብርጭቆ ከዋጡ በኋላ፣ ምንም ሳይበሉ፣ ሳይጠጡ ወይም ሌላ መድኃኒትም ሆነ በተጨማሪነት የሚወሰዱ ሳፕሊመንቶችን ሳይወስዱ ለአንድ ሰዓት እንዲቆዩ ይመክራሉ፡፡
በእራት ሰዓት አካባቢ
ለቃር የሚወሰዱ መድኃኒቶች፡- ሆድ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ከማንኛውም የዕለቱ ጊዜ (24 ሰዓት) ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ የበለጠ አሲድ ያመነጫል፡፡ እንደ ፔፕሲድ (Pepcid) ወይም ዛንታክ (Zantac) ያሉ አሲድ የሚቀንሱ መድኃኒቶች የሚወስዱ ከሆነ እራት ከመብላትዎ 30 ደቂቃ በፊት ይውሰዱ፡፡
ሆድ ከፍተኛውን የአሲድ መጠን የሚያመነጨው በሌሊት ስለሆነ መድኃኒቶቹ በዚህ ሰዓት ሲወሰዱ ለመቆጣጠር ይረዳቸዋል፡፡
የአለርጂ መድኃኒቶች፡- አብዛኛውን ጊዜ የመተንፈሻ አካላት ይብስ የሚታፈኑትና የበለጠ አጣዳፊ ሆነው የበሽታ መከላከያ ሴሎች የሚያመነጩት የሽታው ቀስቃሽ የሆነው ሄስታሚን (Histamine) የተባለ አፋኝ ምልክት መጠን ከፍተኛ የሚሆነው በጧት ማለዳ ነው፡፡
እንደ ክለሪቲን (Claritin) ያሉ የአለርጂ መድኃኒቶች በቀን ውስጥ አንዴ ከተወሰዱ የመከላከል ኃይላቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሰው ከስምንት እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ነው፡፡ መድኃኒቱን በእራት ጊዜ መውሰድ፣ በማለዳ የሚከሰተውን ማፈን (የአለርጂ ምልክቶች) የበለጠ ለመከላከል ይረዳል፡፡ ስለዚህ የአለርጂ መከላከያ የሆነውን ፀረ ሄስታሚን በቀን ሁለት ጊዜ ጧትና ማታ ይውሰዱ፡፡
III.  በመኝታ ሰዓት የሚወሰዱ
የኮሌስትሮል መድኃኒት - በጉበት ውስጥ የሚፈጠረው የኮሌስትሮል (ስብ) ምርት መጠን ከፍተኛ የሚሆነው እኩለ ሌሊት ላይ ነው፡፡ ዝቅተኛ ምርት የሚኖረው ደግሞ ጧትና ከእኩለ ቀን ብዙም ሳይረፍድ ነው፡፡ ስለዚህ እንደስታቲን (Statin) ያሉ ደም ውስጥ ያለ የስብ መጠን የሚቀንሱ መድኃኒቶች መወሰድ ያለባቸው ከመኝታ ሰዓት በፊት ነው፡፡
የደም ግፊት መድኃኒቶች - አብዛኛውን ጊዜ የደም ግፊት መጠን ከፍ የሚለው ቀን ላይ ነው፡፡ ዝቅ የሚለው ደግሞ ሌሊት በመኝታ ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ብዙ ሰዎች በተለይ ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ይህን የሌሊት ደም ግፊት ዝቅ ማለት በትክክል አያረጋግጡም፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት ደግሞ ለስትሮክ፣ ለልብ ሕመም (ኧርት አታክ) ለኩላሊት በሽታ መፈጠር መንስኤ ይሆናል፡፡
እንዴት መሰላችሁ? ሌሊት፣ የደም ግፊት አነስተኛ ነው ብለው ስለሚያስቡ፣ ሲተኙ፣ ምንም ዓይነት የደም ግፊት መቀነሻ መድኃኒት አይወስዱም፡፡ የደም ግፊቱ መጠን ከቀን ይቀንሳል ተባለ እንጂ አለ፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ ሰዎች የደም ግፊታቸው በዝቶ እንዳሸለቡ በዚያው የሚቀሩት፡፡
ስለዚህ ሐኪሞች የሌሊት የደም ግፊት መጠን ከቀኑ ጋር ተመሳሳይ እንዲሆንና የተጠቀሱት የበሽታ ስጋቶች እንዳይፈጠሩ፣ በመኝታ ሰዓት፣ የደም ግፊት መቀነሻ መድኃኒት መወሰድ እንዳለበት እያሳሰቡ ነው።
 IV. የሕመም ምልክት ሲሰማ የሚወሰዱ -
የመጋጠሚያ ሕመም - እንደ የፈረንሳይ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ከሆነ ብዙ ጊዜ ለመጋጠሚያ ሕመም ማስታገሻ በስፋት የሚወሰዱት እንደ ናፕሮክሲን (Naproxen)፣ ኢቡፕሮፊን (ibuprofen) ያሉ መድኃኒቶች፣ ሕመሙ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ 6 ሰዓት በፊት ቢወሰዱ፣ በትክክለኛው ሰዓት ሕመሙን ያስቆማሉ፡፡
ከሰዓት በኋላ ሕመሙ የሚያጠቃዎት ከሆነ በ5 ሰዓት ገደማ፣ ለምሽት ሕመም መከላከያ 10 ሰዓት አካባቢ፣ ለሌሊት ሕመም፣ ከእራት ጋር ማስታገሻዎቹን ቢወስዱ ጥሩ እፎይታ ያገኛሉ፡፡
ምንጭ - (“Readers digest – July 2014
USA” የተወሰደ)

Read 4801 times