Tuesday, 08 July 2014 07:56

ጮቄ - የውሀ ማማ

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(1 Vote)

በመንግስት ሹመኛ የተበደለና የመረረው፣ በእጁ የሰው ህይወት የጠፋበትና መደበቂያ ያጣ ገበሬ ወደ ጮቄ ያማትራል፡፡ “ዱር ቤቴ!” ብለው የሚመሽጉበት ጥንታዊ ደን ነው፡፡ ብርቅየነቱና ግርማ ሞገሱ ይማርካል፤ ብርዱ ግን አይጣል ነው፡፡ ቅዝቃዜው ከበጋ እስከ ክረምት አንድ በመሆኑ ደጋ መባል ያንሰዋል፡፡ ውርጭ ነው - የ24 ሚሊዮን ዓመት ባለጸጋው የጮቄ ተራራ፡፡
የነዋሪው የአመጋገብና የአለበበስ ባህል ብርድን እና ውርጭን ያገናዘበ ነው፡፡ በጥጥ የተሰራ ኮፍያ፣ ሙቀት ሰጪ ካፖርት፣ ጓንት፣ ከክር የተሰራ ኮፍያ፣ ስካርፕ፤ ጎጃም አዘነ የተሰኘው ፎጣ መልበስ ያዘወትሩሉ - ‹‹ደገኞቹ›› የጮቄ ነዋሪዎች በመባል ይጠራሉ፡፡  
በምስራቅ ጎጃም ከደብረማርቆስ ከተማ የ70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ ከአራት ሺህ ሜትር በላይ በሆነ ከፍታ የተነሳ ሃይለኛ ቅዝቃዜው ለደገኛ ነዋሪዎቹ ፈታኝ ቢሆንም፤ ለሌሎቻችን ከአጠገባችን የማይደርስ የሩቅ ወሬ ሊመስለን ይችላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ የጮቄ ተራራ ከሁላችንም ሕይወት ጋር የተሳሰረ እንደሆነ በጮቄ ላይ ምርምር ያካሄዱት ዶ/ር መለሰ ተመስገን ይናገራሉ፡፡ “እንዴት?” በሉ የጮቄ ተራራና አካባቢው የ273 ምንጮችና የ59 ወንዞች መፍለቂያ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ 23ቱ የአባይ ገባር ወንዞች እንደሆኑ የገለፁት ዶ/ር መለሰ፤  ከጠቅላላው የአባይ ውሃ 9.5% ያህል ከጮቄ እንደሚመነጭ ይናገራሉ፡፡ ይህንን መረጃ በማየት ብቻ ከሕይወታቸው ጋር ምንኛ የተሳሰረ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከኛ ህይወት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሱዳንና ከግብጽ ጭምርም እንጂ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ክረምት ከበጋ፤ ሲያሰኘው በዶፍ ዝናብ፣ ሲያሻው እንደ ጥጥ ብናኝ ሰማይ ምድሩን በሚሸፍን የበረዶ መና ከአመት አመት ከእርጥበት የማይላቀቀው የጮቄ ተራራ አህጉርና ባሕርን የሚያሻግር ግንኙነት አለው፡፡
የጮቄ ዝናብና እርጥበት፣ ከአትላንቲክ ውቅያኖስና ከምዕራብ አፍሪካ የአየር ንብረት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር መለሰ፤ ነገሬ ብለን መመርመርና ማጥናት፤ ተፈጥሯዊውን ፀጋ መጠበቅና መንከባከብ አለብን ይላሉ፡፡ እስከ ዛሬ ግን አላደረግነውም፡፡  
ዛሬ ዛሬ ግን የዚህ ተራራ ዕድሜ ጠገብ ተፈጥሮዊ ማንነት እየከሰመ፣በአፈር መሸርሸርና በደን መራቆት የብዝሀ ህይወት ፀጋዎቹ እየጠፉ፣ ምንጮቹና ወንዞቹም እየደረቁ ነው፡፡ የጮቄ ተራራ መዘዙም ለአካባቢው ብቻ አይደለም፡፡ በሰፊው ለአገራችን አሳዛኝ ጥፋት ነው ሌላው ቢቀር ታላቁ የአባይ ወንዝን ይነካላ፡፡ ግን በአህጉር ደረጃና ለአለም የአየር ንብረት ለውጥም አንድ ተጨማሪ ስጋት እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የአካባቢው መራቆት  የህዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ የእርሻ መሬት ያለው  ነዋሪዎች፤ ወደ ተራራው እየወጡ ደንና ጢሻውን በመመንጠር ከመሬቱ ተዳፋታማነት ጋር ተዳምሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጐርፍ እየበረታ ወጥቷል፡፡ በአንድ በኩል ለም አፈር በፍጥነት እየተሸረሸረ የአካባቢው ልምላሜ ይራቆታል፡፡ በሌላ በኩልም ቁልቁል የሚንደረደረው ውሃ ወደ መሬት መሰረግ ጊዜ ስለማያገኝ ምንጮች ይደርቃሉ፡፡ የጮቄ ተራራ ተፈጥሯዊ ገጽታ መራቆት አደገኛ መሆኑን የተገነዘቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ጮቄን ወደ ቀድሞው ይዞታው በመመለስ ወደ ፓርክነት ደረጃ ለማሳደግ የምርምር ፕሮጀክት ቀርፀው መስራት ጀምረዋል፡፡
ከካርቱም ዩኒቨርስቲ እና ኔዘርላድ ከሚገኝ ተቋም ጋር በመተባበር በጮቄ ዙሪያ ጥናት የሚያካሂዱት ዶ/ር መለሰ ተመስገን፤ ስለ ጮቄ ሲናገሩ፤
ከ24 ሚሊዮን ዓመት በፊት የመጨረሻው እሳተ ጎመራ በሚፈነዳበት ጊዜ ገንፍሎ የወጣው የቀለጠ አለት በአንድ አቅጣጫ በመፍሰሱ የተፈጠረ ተራራ ነው ይላሉ፡፡ መሆኑ እርጥበት አዘል ቀዝቃዛ አየር ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ተነስቶ ዛየር እና ኮንጎ ላይ ካረፈ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ዶ/ር መለሰ ጠቅሰው፤ እርጥበት አዘሉን አየር ገጭቶ የሚያስቀረው ጮቄ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በምንጮችና በወንዞች መፍለቂያነቱም ነው፤ የውሃ ጋን(የውሃ ማማ) የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይላሉ ተመራማሪው፡፡
ጮቄን ለመታደግ መታተሩ የአካባቢውን ስርዓተ ምህዳር ለመመለስ እና ለመጠበቅ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ የሚሰሩ ስራዎች በተፋጠነ መልኩ ወደ ተግባር ቢገባበት እየተመናመነና እየተሸረሸረ ያለውን አካባቢ፤ ከንክኪ ከማጽዳት በተጨማሪ የደን፣ የብዝሃ ህይወት፣ የአፈር መሸርሸርን የጮቄን ተፈጥራዊ ይዞታ በመጠበቅ የዓለም የአየር ንብረት መዛባትን ከመቀነስ አንፃር ተፅዕኖ ይኖረዋል ይላሉ አጥኝው፡፡
በደቂቃዎች ልይነት አንዳንዴ ደመናማ ቆየት ብሎም ብራ እየመሰለ የተፈጥሮ መቅበጥበጥ  በሚታይበት የጮቄ ተራራ አናት ላይ ተወጥቶ፤ አካባቢውን ለመጎብኘት የቅዝቃዜውና ውርጩ ያስቸግራል፡፡ ግን ደግሞ አስደናቂ ነው፡፡ የጮቄ በረዶ ብዙዎቻችን ከምናውቀው ጠጣር በረዶ ይለያል፡፡ ጉም ይመስላል፡፡ የበረዶ ካፊያ እንደተነደፈ ጥጥ በጸጉርና በሰውነት ላይ ብትን ብሎ ሲታይ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የበረዶው ካፊያ ግን አያረጥብም፣ ምክንያቱም ቶሎ አይሟሟም፤ አይቀልጥም፡፡
ጭጋግ በወረሰው ተራራማ ስፍራ ተቁሞ ዙሪያ ገቡን ለተመለከተው ድንቅ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው ባይሆንም፤ በተራራው ዙሪያ ዛሬም መንፈስን የሚያረካ የደን ልምላሜ ይታያል፡፡ ነገር ግን  ችም ችም ጥቅ ጥቅ ብለው ከሚታዩት ደኖች መሃል በየቦታው የሚታዩ ጎጆ ቤቶች ተቀልሰዋል፡፡ ከጐጆ ቤቶቹ ውስጥ እለት ተእለት የማይጠፋ ነገር ቢኖር እሳት ነው፡፡ ከጐጆዎቹ አናት የሚወጣውን ጪስ ከሩቅ ለተመለከተ ሰው፤ የተራራው ደን ውስጥ በየቦታው እሳት የተለቀቀበት ይመስለዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ከደን ማገዶ እየቆረጠ ከማንደድ ውጭ ምን አማራጭ አለው? ክረምት ከበጋ ውርጭ ነው፡፡ የማገዶ እሳት ባህላዊ “ኤር ኮንድሸነር” ነው፡፡ የአካባቢውን ደን ቀስ በቀስ እሳት እየተበላ መሆኑ ግን አያከራከርም፡፡ በተራራው አናት ላይ ከተተከሉት የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የቴሌ የመቀባበያ አንቴናዎች አጠገብ ሆኖ ዙሪያ ገባው ከየጐጆው የሚወጣውን ጭስ ማየት ልብን ይሰብራል፡፡
በተቃራኒው በተራራው አናት ላይ ለተወሰነ ደቂቃ ከጮቄ ብርቅ ተፈጥሮ ጋር እየተነጋገሩ መቆየት መንፈስን ይማርካል፡፡ ልዩ ነው፡፡ ታዲያ ብርዱ ፋታ አይሰጥም፡፡ ለአንቴና ጥበቃ ኑሯቸውን ከተራራው አናት ላይ የቀለሱት ባለትዳሮቹ በላቸውና የሰውዘር ብርዱን እንዴት እንደሚችሉት እንጃ? ለማንኛውም የእነሱን ብርታት በማየት “የዛሬን የመጣው ይምጣ” ብሎ ውርጩን ማሸነፍ አያቅትም፡፡
“ብርዱ እንዴት ነው ብዬ ጠየኩት” በላቸውን
“እራ.. እሱስ ይከረስሳል” አለኝ በጭንቅላቱ ላይ የሹራብ ቆቡን እያስተካከለ፡፡ ጨዋታ ለመቀጠል አቅም አልነበረኝም፡፡ ብርዱ ያንዘፈዝፈኝ ጀምሯል፡፡
“ቤታችሁ ገብቼ ትንሽ እሳት መሞቅ እችላለሁ?” አልኩት ቅዝቃዜው አንጀቴ ውስጥ ሲገባ፡፡
“እህ ግቢ እንጂ” አለኝ …እንግዳ ማስተናገድ ባህላችን አይደለም በሚል ስሜት፡፡
ባህላቸው እንደሆነ ለማወቅ ግን ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ ባለቤቱ የሰው ዘር አፍታ ሳትዘገይ፤
እየተቀቀለ የነበረውን ትኩስ ድንች የአካባቢው መለያ ከሆነው ማባያ ተልባ ጋር አቀረበችልኝ “ቤት ያፈራውን” ብላ፡፡
አስከትላም፤ ከተለያዩ እህሎች የተሰራ አረቄ ቀድታ ጋበዘችኝ - “ይጠቅምሻል ለብርዱ፤ ባትውጅም ቅመሽው” በማለት፡፡ ተቀበልኳት፡፡ ገና ሳልቀምሰው፣ መዓዛውን ፈራሁት፡፡ ግን ከብርድ አይብስም፡፡ ቀመስኩት..እሳት የሆነ አረቄ፡፡
“ይጠቅምሻል” ያለችኝ በከንቱ አይደለም፡፡ እውነትም አሁን በተራራው አናት ላይ እንደ ጅብራ መገተር እችላለሁ፤ ሰውነቴን ሙቀት ተሰማኝ፡፡ ዝምታዬ በኖ ጠፋ፡፡
“ታርሳላችሁ?”
“አዎ” አለኝ ባሏ ቀበል አድርጎ፤ “ግን መሬቱ ተደፋት ሆኖ ተጠራርጎ ይሄዳል”
“እናስ ምን ዘየዳችሁ”
“እረ መላም የለው” አለኝ
“እንዴት?”
“ውርጩ ይይዘዋል፤ መሬቱም አንድኛውን ተዳፋት ሆኖ እህሉንም በደንብ አይዝ..”
“አመሉ ነው ወይስ ዛሬ ነው እንደዚህ የሆነ” አልኩት
“እራ!! መሬት ሲጠበን ወደ ላይ መጣን እንጂ..ፊትማ ወደ ታች መስኩ ላይ ነበርን” አለ፡፡
ባለቤቱ የሰው ዘር ቀበል አድርጋ “ተዳፋት ላይ ተንጠልጥለን ተራራ መቧጠጥ፤ ከውርጪ በቀር ምንም አላተረፈልን” አለች እሳቱ ላይ ማገዶ እየጨመረች፡፡
“ማገዶ ከየት ነው የምታገኙ?”
“ያው ከጫካ..” አለች
በአካባቢው እየተመናመነ ወደ አለው ደን አቅጣጫ እያመለከተች፡፡
አረቄውን ብዙ ባልደፍረውም፤ አዲስ እንደተገጠመ ሞተር ሴሎቼ መሟሟቅ ስለጀመሩ ከውርጩ ጋር ለመጋፈጥ በድጋሚ ወደ ተራራው አናት ተመለስኩ፡፡
በተራራው አናት ዙሪያም በየቦታው ፍልቅ ፍልቅ ብለው የሚታዩ ምንጮች ‹‹ጠጡኝ፣ ጠጡኝ›› የሚል፣ ከፍሪጅ የወጣ ጥም የሚቆርጥ ውሃ ይመስላል፡፡ አሁን ‹‹ጮቄ የማዕድን ውሃስ የማይወጣ ሆኖ ነው?” ይህንን ለተማራማሪዎች እንተወው፡፡
የጮቄ ተራራ ልዩ መለያ ነባር እፅዋቶች ጅብራ፣ አስታ እና የተለየ ሳር ዓይነቶች ናቸው፡፡ ቀደም ሲልም የዱር አራዊቶች ይገኙበት እንደነበረ ይነገራል፡፡ የደን ጭፍጨፋውን ማስቆም እና የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ተጠናክሮ፣ አርሶ አደሩ በመስኖ ዘመናዊ እርሻ በመጠቀም ምርታማነቱን በመጨመር የጮቄ ተራራን ፓርክ በመከለል በኢኮቱሪዝም መስክ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ አመቺ ሆነ የመኪና መንገድ የመዝናኛ ስፍራዎች በአካባቢው ቢሰሩና በሰፊው የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራ የቱሪስት መስህብነቱ ከአገር አልፎ በአለማቀፍ ጎብኝዎች ትኩረት የሚስብ ተፈጥሮዊ ቦታ ነው ብለዋል - ዶ/ር መለሰ፡፡
ከጮቄ ተራራ ላይ የሚነሱ ሀምሳ ዘጠኝ ወንዞች፣ ሃያ ሶስቱ የአባይ ገባር በመሆናቸው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጐላ መሆኑ ስጠቀስም አካባቢው ተጠበቀ ማለት ከአባቢው የሚመነጩ ወንዞች አመቱን ሙሉ እንዲፈሱ እና የአባይን፣ ውሃ መጠን ከፍ  በማድረግ የወንዞች ሙሉ አቅም ወደ አባይ በማስገባት የአፈር መሸርሸሩን በመቆጣጠር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በደለል እንዳይሞላ መከላከል እንደሚቻል የምርምር ውጤቱ ይጠቁማል፡፡

Read 4045 times