Tuesday, 08 July 2014 07:37

የአዲስ አበባ ጐዳና ተዳዳሪዎች ኑሮ ከፍቶብናል ይላሉ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከ60ሺ በላይ የሚሆኑት ራሳቸውን እንዲችሉ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል
5ሺ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ከነገ ወዲያ  ለሥልጠና ወደ አፋር ይጓዛሉ
በኮብልስቶን ከሰለጠኑት ውስጥ ብዙዎቹ ወደ ጐዳና ተመልሰዋል
“ፖሊሶች ጥፉ ይሉናል፤ ወዴት እንጥፋ? የትስ እንኑር?”

የ27 ዓመት ወጣት ነው፡፡ ለጎዳና ህይወት የተዳረገው ወላጆቹን በኤችአይቪ በማጣቱ ነበር። በጎዳና ላይ ከጓደኞቹ ጋር ለ7 ዓመታት የኖረው ታዴ፤ አንድ ቀን ከጐዳና ወጥቼ እንደማንኛውም ሰው የተሻለ ህይወት ይኖረኛል ብሎ ያስብ እንደነበር ይናገራል፡፡
እንዳለውም ሰው ሆኖ መኖር የሚችልበት አጋጣሚ ባልጠበቀው ጊዜ ተፈጠረ፡፡ መንግስት የጎዳና ተዳዳሪዎችን አሰባስቦ በማሰልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ ድጋፍ መጀመሩን የሰማው በ2003 ዓ.ም ነው፡፡ ወዲያው መስቀል አደባባይ አካባቢ ከሚኖርባት የፕላስቲክ ጎጆው በመውጣት፣ ከሁለት የጎዳና ጓደኞቹ ጋር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሄዶ፣ የጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን በማስመስከር ተመዘገበ፡፡ ከዚያም ከ2500 በላይ ከሚሆኑ ሌሎች የጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ጨፌ ወደሚገኘው የማሰልጠኛ ካምፕ ገባ - በሁለተኛ ዙር ምልምልነት፡፡
ስልጠናው ለአንድ ወር ብቻ የዘለቀ እንደነበር የሚናገረው ታዴ፤ በዚህ ወቅትም  የኮብልስቶን አመራረትን ጨምሮ በመጠኑም ቢሆን ከስነልቦና ጋር የተገናኘ ትምህርት እንደተሰጣቸው ያስታውሳል፡፡ በስልጠናው ወቅት በየቀኑ በሬ እየታረደ በቀን ሶስት ጊዜ የስጋ ተዋፅኦ የሆኑ ምግቦችን  ይመገቡ እንደነበር ይናገራል፡፡ የአንድ ወሩ ስልጠና እንደተጠናቀቀም እዚያው ጨፌ በሚገኘው የኮብልስቶን ማምረቻ  ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆኑ ትናንሽ ክፍል ቤቶች ተሰጥቷቸው መኖር እንደጀመሩ ታዴ ይናገራል፡፡ ገቢ ማግኘት ከጀመሩ በኋላ  ቁርስ፣ ምሳ እና እራት በ15 ብር ኩፖን ይቀርብላቸው ነበር፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የምግቡ ዋጋ 20 ብር ገባ፡፡
“መንግስት በሚገባ ተንከባክቦናል፤ ምቾታችን እንዳይጓደልም ብዙ ጥሯል” የሚለው ታዱ፤ አንድ ነጠላ የኮብል ድንጋይ በ2.10 ብር እንድንሸጥ ገበያ አመቻችቶልናል፤ የበረታ በቀን እስከ 200 እና 300 ብር የሚያወጣ ጥርብ ድንጋይ ማምረት ይችላል” ብሏል፡፡ በወቅቱ አንድ አምራች በወር 4ሺህ እና 5ሺህ ብር ያገኝ ነበር የሚለው ታዴ፤ እያንዳንዳቸው የባንክ ቁጠባ ደብተር ተከፍቶላቸው ሙሉ ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ ይደረግ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በባንክ የገባውን ቁጠባም እንደፈለጉ ማውጣት አይቻልም ነበር ብሏል፡፡
የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች በዚህ መልኩ እየሰሩ እየቆጠቡ፣ ከመንግስት በቅናሽ ዋጋ ምግብ እየቀረበላቸው እየተመገቡ፣ በነፃ መኖርያ ቤት ተሰጥቷቸው እየኖሩ ሳለ፣ ኤልሻዳይ የሚባል ድርጅት “ራሳችሁን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ አለባችሁ፤ እኔ በብረታ ብረትና በማሽን ኦፕሬተርነት፣ በእንጀራ መጋገርና በተለያዩ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የምትሰለጥኑበትን መንገድ አመቻችላችኋለሁ” እንዳላቸው ታዴ ያስታውሳል፡፡
ይሄኔ ነው ቀድሞ የማይፈቀድላቸውን የቁጠባ ገንዘብ እንዳሻቸው እንዲያወጡ የተፈቀደላቸው። አብዛኞቹም ገንዘቡ የሚያልቅ አልመሰላቸውም ነበር፡፡ በባንክ ለሁለት አመት ገደማ ያጠራቀሙትን ገንዘብ በማውጣት፣ መንግስት በነፃ ከሰጣቸው ቤት ወጥተው እዚያው መድኃኒዓለም ጨፌ አካባቢ የግለሰብ ቤት እየተከራዩ መኖር ይጀምራሉ - የኤልሻዳይን ስልጠና ተስፋ በማድረግ፡፡ ብዙዎቹ የቀድሞ የገቢ ምንጫቸው የነበረውን ኮብልስቶን የማምረት ስራ እርግፍ አድርገው በመተው፣ የቆጠቡትን ያለስስት እያወጡ መብላት ጀመሩ፡፡
“ከኛ መሃል እዚያው ተጋብተው ልጆች የወለዱም ነበሩ” ይላል ታዴ፡፡ ተስፋ የጣሉበት ኤልሻዳይ ግን የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች ያለ ስራ ተቀምጠው ገንዘባቸውን ሙልጭ አድርገው ጨረሱት ይላል፡፡ “የሚያሳዝነው ታዲያ ዛሬ እነዚያ ወጣቶች ተመልሰው ጎዳና ላይ ወድቀዋል” ሲል ታዴ በሃዘን ተሞልቶ ይናገራል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በካምፑ ከነበሩት አንደኛና ሁለተኛ ዙር ምልምሎች መካከል እሱን ጨምሮ ከ10 የማይበልጡ ብቻ መቅረታቸውን የሚገልፀው ወጣቱ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት ተመልሰው ጐዳናን ሲቀላቀሉ፤ ነቃ ያሉት ጥቂቶች ደግሞ ጥሩ ደረጃ በሚያደርሳቸው  የስራ መስክ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ ብሏል፡፡
ሪፖርተሮቻችን ቦታው ድረስ በመገኘት እንደታዘቡትም፤ በማምረቻ ማዕከሉ ከ1ኛና ሁለተኛ ዙር ሠልጣኞች ውስጥ ከ10 የማይበልጡ ወጣቶችን የተመለከቱ ሲሆን በካምፑ ያሉ የቆርቆሮ ቤቶችም ኦናቸውን መቅረታቸውን አስተውለዋል፡፡ በካምፑ በአጠቃላይ በ3 ዙሮች ከገቡት መካከል ደግሞ 170 ያህል ሰልጣኞች ብቻ እንደሚገኙ በካምፑ ውስጥ ለሁለት አመታት የቆየው ታዴ ገልፆልናል፡፡
“ህዳሴ” የሚል ስያሜ በተሰጠው የጨፌ የኮብልስቶን ማምረቻ ማዕከል ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ወጣቶች አንዱ የሆነው ዘሪሁን (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ)፣ ከሱ ጋር በየክፍለ ከተማው ከሚገኙ ጎዳናዎች ተለቃቅመው በ3ኛ ዙር ወደ ማዕከሉ ከገቡት ከ2ሺ በላይ ምልምሎች መካከል እሱን ጨምሮ 160 ብቻ መቅረታቸውን ይናገራል፡፡ አብዛኞቹም ወደ መጡበት ጎዳና ተመልሰዋል የሚለው ወጣቱ፤ “መገናኛና ካዛንቺስ፣ አራት ኪሎ፣ ሜክሲኮ፣ መስቀል አደባባይና ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎች ስዘዋወር ብዙ የህዳሴ ፍሬዎችን ጐዳና ላይ  እያገኘኋቸው በኪሴ የያዝኳትን ሳንቲም አካፍላቸዋለሁ” ብሏል፡፡
መንግስት ስልጠናውን ሲያዘጋጅ መጀመሪያ የልጆቹን አመለካከትና አስተሳሰብ የሚለውጥ የስነ ልቦና ምክር መሰጠት ነበረበት የሚለው ዘሪሁን፤ ይህ ባለመደረጉ ብዙዎቹ ትንሽ ጊዜ ሰርተው በዝግ ሂሳብ  የተቆጠበላቸውን ገንዘብ እንኳ ሳይቀበሉ “ጎዳና ናፈቀን” እያሉ ወደ ቀድሞው ህይወት ተመልሰዋል  ብሏል፡፡ እስከ 10ኛ ክፍል መማሩን የነገረን ዘሪሁን፤ በአሁን ሰዓት ከኮብልስቶን ሥራ በሚያገኘው ገቢ ከፍተኛ ክፍያ እንደሚያስገኙ ከሚነገርላቸው የሙያ መስኮች አንዱ በሆነው የዶዘር ኦፕሬተርነት እየሰለጠነ መሆኑን ገልፆልናል፡፡ “በእርግጠኝነት ነገ ራሴን የተሻለ ቦታ አገኘዋለሁ” የሚለው ወጣቱ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ጓደኞቼ ተመልሰው ጐዳና መውጣታቸውን ባሰብኩ ቁጥር ግን ሃዘን ይሰማኛል ብሏል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን በሄደበት አጋጣሚ የቅርብ ጓደኛው የነበረ የማዕከሉን ሰልጣኝ፣ በልመና እየተዳደረ እንዳገኘውም ወጣቱ ተናግሯል፡፡ መገናኛ አካባቢም አብረውት ሲሰልጥኑና ሲሰሩ የነበሩ ወጣቶች ጎዳና ላይ ወድቀው፤ ለእለታዊ ሱሳቸው ማስታገሻ፣ የሲጋራ ቁሩና የጫት ገረባ ሲያስሱ በተደጋጋሚ እንደገጠመው  ጠቁሟል፡፡
ከዛንቺስ አካባቢ ጎዳና ላይ የላስቲክ ጎጆ ቀልሶ የሚኖረው ሌላው ወጣት በበኩሉ፤ ከሁለተኛው ዙር ሰልጣኞች አንዱ እንደነበር ጠቁሞ፤ “ኤልሻዳይ” የሚባለው ድርጅት በተለያዩ ሙያዎች እንድትሰለጥኑ አድርጌ፣ተደራጅታችሁ የራሳችሁን ቢዝነስ ትሰራላችሁ” በማለቱ ከጓደኞቹ ጋር በመመካከር፣ ያጠራቀሙትን 20 ሺ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከባንክ አውጥተው መገናኛ አካባቢ በ600 ብር የግለሰብ ቤት ለሶስት ሆነው በመከራየት መኖር እንደጀመሩ ይናገራል፡፡
“ያጠራቀምነው ብር ብዙ ስለመሰለን ከመንግስት ጥገኝነት በፍጥነት ለመውጣት ጉጉት ነበረን” የሚለው ወጣቱ፤ “በእንጨት ስራ፣ በዳቦ ቤት፣ በእንጀራ መጋገር፣ በብሎኬት፣ በፕሪካስት ስራና በመሳሰሉት ተደራጅታችሁ እንድትሰሩ ይደረጋል የሚለው ተስፋ፣ በቃ ከእንግዲህ ራሳችንን ችለናል፤ ወደ ኋላ አንመለስም ብለን እንድናስብ አድርጎናል” ይላል፡፡ ኤልሻዳይ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በዚህን ቀን ወደ ስልጠና ትሄዳላችሁ እያለ በተስፋ ስንጠብቅ፣ ጊዜው እየነጎደ ገንዘባችንም እያለቀ መጥቶ፣ የማታ ማታ ለጎዳና ህይወት ተመልሰን ተዳረግን ይላል ወጣቱ፡፡
የጎዳና ልጆች የራሳቸው ፓርላም አላቸው። ስብሰባም ይቀመጣሉ፡፡ ውሳኔዎችም ይወስናሉ፣ ለማንኛውም ውሳኔ የጎዳና ልጆች መገዛት ግድ ይላቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ህይወታቸውን  የሚመሩት የጎዳና ልጆች፤ ዛሬ  እጣ ፈንታቸው ካጋፈጣቸው ፈተና በተጨማሪ “መንግስት እየጨከነብን ነው” ሲል ይናገራል - ሌላው ተስፉ የተባለ የጎዳና ተዳዳሪ፡፡ በኮብልስቶን ሥልጠና አለመሳተፉን የጠቆመው ወጣቱ፤በርካታ ለኮብልስቶን ስልጠና ተለይተውት የነበሩ ወዳጆቹን ተመልሰው ጎዳና ላይ ወድቀው እያገኛቸው እንደሆነ ተናግሯል፡፡  “እናንተ በኮብልስቶን ሰልጥነው የተመለሱትን ትላላችሁ፤ዛሬ ከዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ተመርቀው የጎዳና ወዳጆቻችን ሆነው የቀሩ ብዙ ወጣቶች አሉ” ብሏል - ተስፉ፡፡
በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አጋዥነት በስካቫተር፣ በዶዘርና ሎደር ኦፕሬተርነት፣ በኤሌክትሪሻንነት፣  በብረታ ብረት ሥራና በመሳሰሉት ሙያዎች ከ8 ወራት በላይ ሰልጥነው የነበሩ ወዳጆቹም ስራ በማጣት ተመልሰው ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸውን ይኸው ወጣት ይገልፃል፡፡
በጎዳና ተዳዳሪዎች ዘንድ በተግባቢነቱ ከፍተኛ ዝና እንዳለው የሚነገርለትና በ97 ዓ.ም የጐዳና ልጆችን ፊርማ አሰባስቦ ለፓርላማ  ሊወዳደር አቅዶ ያልተሳካላት ተስፉ፤ በዘንድሮው አመት ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር ጨምሯል፤ በየእለቱም ቁጥራቸው እየጨመረ ነው ባይ ነው፡፡ ቀደም ሲል መንግስት ለስልጠና የሰበሰባቸው ወጣቶች ተመልሰው ወደ ጎዳና መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን የጨረቃ ቤቶች በዘመቻ እንዲፈርሱ መደረጋቸውም በርካቶችን ለጎዳና ዳርጓቸዋል፤ ከጎዳና ህይወት ከወጡ በኋላ ተመልሰው ለጎዳና የተዳረጉ በርካታ ወዳጆችም አሉኝ ይላል፡፡
ለአንድ ቀን ማደርያ 4 ብር እና 3 ብር ይከፈልባቸው የነበሩ አልጋ ቤቶች ወደ 20 እና 30 ብር ማሻቀባቸው የጎዳና ተዳዳሪውን ቁጥር እንዳበራከተው ተስፉ ይናገራል፡፡ ከደቡብ፣ ከአማራና ከትግራይ ክልሎች የሚመጡ ስራ ፈላጊዎችም ያሰቡት ሳይሳካላቸው ለጎዳና ህይወት መዳረጋቸው ለቁጥሩ መጨመር አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚለው ወጣቱ፤ ህፃናት በብዛት ከሸዋሮቢትና ከሻሸመኔ አካባቢ እንደሚመጡ ይገልፃል፡፡
“ኑሮ በጎዳና ከፍቷል”
የጎዳና ልጆች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከመንግስት አካላት ጥቃት እየደረሰባቸው ነው የሚለው ተስፋ “ፖሊሶች ምሽት ላይ ባገኙን ቁጥር ‘ከዚህ አካባቢ ጥፉ’ ይሉናል፣ የላስቲክ ቤታችንን ያፈርሱብናል፤ ወዴት እንጥፋ? የትስ እንኑር?” ሲል ተስፉ  ይጠይቃል፡፡
“ሴቶች የጎዳና ተዳዳሪዎች ከሰው ተራ ወጥተው ገላቸውን በአነስተኛ ዋጋ በየአጥሩ ስር ይቸረችራሉ፣ ስጋዋን ሸጣ የምታድረውም ለፖሊሶች ራት መግዛትና ካርድ መሙላት ይጠበቅባታል” የሚለው ወጣቱ፤ ከሆቴሎች ለምነን የምናገኛትን ፍርፋሪ እንኳ ሆቴሎቹን እንዳትሰጧቸው እያሉ ስለሚያስፈራሯቸው የምንቀምሰው እያጣን ነው ሲል ያማርራል፡፡
ምን እንሁን ብለን ስንጠይቅ ሃገሪቱ እየተለወጠች ነው፤ እናንተም ተለወጡ ይሉናል፤ ያለው ወጣቱ፤ ‘እንዴት እንለወጥ?’ ስንል ግን እነሱም መልስ የላቸውም ብሏል፡፡ “ስራ ለማግኘት፣ እንደሰው ለመቆጠርና ለመታመን ተያዥ ያስፈልጋል” የሚለው ወጣቱ፤ በርካታ ወጣት እውቀት እያለውና መስራት እየቻለ በእነዚህ ምክንያቶች በየጎዳናው መናኛ ሆኖ ቀርቷል” ሲል ምሬቱን ይገልፃል፡፡
“አብዛኞቹ የጎዳና ልጆች እለታዊ ችግራቸውንና ረሃባቸውን ለማስታገስ አደገኛ ሱሶች ውስጥ ከመደበቃቸው ባሻገር፤ ኑሮ ይበልጥ ሲመራቸው ለአጭር ጊዜ የምታሳስር ቀላል ወንጀል ሰርተው ማረሚያ ቤት ለመግባት ይተጋሉ፤ ይህ መሰሉ ድርጊት በተለይ በክረምት ወራት የተለመደ ነው” ብሏል - ወጣቱ የጐዳና ተዳዳሪ፡፡
ከአረብ ሃገር የስደት ተመላሾች መካከል ለጐዳና የተዳረጉት “መቀሌ ኤምባሲ” በሚል በሰየሙት የጎዳና ነዋሪዎች አካባቢ እንደሚገኙ የጠቆመው ተስፉ፤ አብዛኞቹ ቀኛማችነትን የእለት ጉርስ ማግኛ እንዳደረጉት ገልጿል፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ  እንደሚሉት፤ መንግስት “ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኮሌክሽን” ከሚባል ሃገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመሆን ባለፉት 8 ዓመታት ወደ 60ሺ 759 ወገኖች ከጎዳና ላይ ተነስተው ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ የተለያዩ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ወደ 19 ሺ 50 ያህሉ ህፃናት ናቸው፡፡ ህፃናቱ መስራት ስለማይችሉ ትምህርት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
እነዚህን የጎዳና ተዳዳሪዎች “ለመጪው ትውልድ ልማትን እንጂ ልመናን አናወርስም፤ ልመና የሌለባት ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን” በሚል መርህ መንግስት በነፃ ማሰልጠኑንና እያሰለጠነ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ ፤ ከስልጠናው በኋላ ያለውን ሂደት የሚከታተለው ኤልሻዳይ የተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፈው አመት 2400 የሚሆኑ የጎዳና ልጆች በአፋር ክልል ኢሚባራ ወረዳ በሚገኘው የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አዲስ ራዕይ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተው በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጥነው እንደተመረቁ የጠቆሙት  አቶ ግርማ፤ ከነገ በስቲያ ሰኞ 5 ሺህ ዪደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች በሁለተኛ ዙር እንዲሰለጥኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት አሸኛኘት ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡ “ሰልጣኞቹ ወደ ጎዳና እንዳይመለሱ ኤልሻዳይ ይከታተላል፤መንግስትም ድጋፍ ያደርጋል፤ ወደ ጎዳና ተመልሰዋል ስለሚባለው ግን መረጃው የለንም” ያሉት ኃላፊው፤ የሰልጣኞቹን ቁጥርና የት ደረሱ የሚለውን ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ ያለው ኤልሻዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር በኮብልስቶን ሲሰለጥኑ የነበሩት የጎዳና ተዳዳሪዎች የኤልሻዳይን ስልጠና በመጠባበቅ ገንዘባቸውን ጨርሰው ወደ ጎዳና ተዳርገዋል የሚለውን በተመለከተ የጠየቅናቸው የኤልሻዳይ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነህ፤ ሥልጠናው መዘግየቱን አልካዱም፡፡ “ሁኔታዎች ናቸው ያዘገዩት፤ ላቅ ያለ ነገር ለመስራት ስለታቀደ ለመቆየት ተገደናል፡፡ ወጣቶቹ በሚያገኙት ስልጠና እስካሁን የተጉላሉትንና ያጋጠማቸውን ችግር እንደሚረሱት ተስፋ እናደርጋለን›› ያሉት የኤልሻዳይ መሥራች፤ ቀደም ሲል ወደ አፋር ሄደው ከሰለጠኑት ውስጥ 95 በመቶ ያህሉ ስኬታማ መሆናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

Read 4999 times