Tuesday, 08 July 2014 07:19

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 8ኛውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ተረከበ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

በአምስት ወራት ውስጥ ተጨማሪ 2 አውሮፕላኖች ያስገባል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደተለያዩ አለማቀፍ መዳረሻዎች የሚያደርገውን በረራ የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችለውን 8ኛውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን መረከቡን ገለጸ፡፡
የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በመጠቀም ከጃፓን ቀጥሎ በአለማችን ሁለተኛው መሆኑን የገለጸው አየር መንገዱ፣ 8ኛውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት መረከቡንና እስከ መጪው ታህሳስ ወር መጨረሻም ሌሎች ሁለት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እንደሚያስገባ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡የመጀመሪያውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን በነሃሴ ወር 2012 ማስገባቱን ያስታወሱት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ መድህን፣ አውሮፕላኑ ለተሳፋሪዎች ምቾት በመስጠትና በአጠቃላይ ይዞታው በዘርፉ አቻ የማይገኝለት መሆኑን ጠቁመው፣ አየር መንገዱ ለወደፊትም የደንበኞቹን ፍላጎት ለማሟላት የአዳዲስ  ቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በማስመጣት አገልግሎቱን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ይህን ዘመናዊ አውሮፕላን በመጠቀምና አገልግሎት በመስጠት ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በዚህ አውሮፕላን ወደተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ ሃገራት፣ ብራዚል፣ አሜሪካ፣ ካናዳና ቻይና በረራ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
አየር መንገዱ ቦይንግ 777፣ ቦይንግ 787ና ቦይንግ 737ን ጨምሮ 68 ያህል እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም፣ በአምስት አህጉሮች ወደሚገኙ 82 አለማቀፍ መዳረሻዎች በረራ እያደረገ የሚገኝ አለማቀፍ ዝናን ያተረፈ ተቋም መሆኑንም አስታውቋል፡፡  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት ቪዥን 2025 የተባለውንና ስምንት የንግድ ማዕከላት ያሉት የአፍሪካ መሪ የአቪየሽን ግሩፕ ለመሆን የሚያስችለውን የ15 አመታት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርጾ በመተግበር ላይ እንደሚገኝና ባለፉት ሰባት አመታት በአማካይ 25 በመቶ አመታዊ ዕድገት ማስመዝገቡንም አክሎ ገልጿል፡፡

Read 3417 times