Saturday, 05 July 2014 00:00

የባሌ ብሔራዊ ፓርክን በሰፊው የማስተዋወቅ ዘመቻ ተጀመረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ለእይታ ቀርቧል
ሁለት የቱሪስት መምሪያ መጻህፍት ታትመዋል
 የደጋ አጋዘን ሲያረጅ ታድኖ ከ3 መቶ ሺ ብር በላይ ይሸጣል

በአፍሪካ ብርቅዬ የአዕዋፍ ዝርያዎችን በመያዝ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጠውን የባሌ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪስቶች ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያግዛሉ የተባሉ ሁለት መጻህፍትን ጨምሮ ዌብሳይት የተመረቁ ሲሆን የፓርኩን ገጽታ የሚያስተዋውቁ ፎቶግራፎችም ባለፈው ማክሰኞ  ለእይታ ቀርበዋል። ፍራንከፈርት ዞሎጂካል ሶሳይቲ የተባለ የውጭ ድርጅት ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ፓርኩን በተሻለ ለማስተዋወቅ ይረዳል ብሎ በቀረፀው ፕሮጀክት መሠረት፣ ባለ 77 ገጽ የቱሪስት መመሪያ መጻህፍት እና በቱሪስቶች ተመራጭ የሆኑትን የፓርኩን የአዕዋፋት ፀጋ የሚያንፀባርቅ በፎቶግራፍ የተደገፈ ባለ 51 ገጽ መጽሐፍትን አሳትሞ ለአስጐብኚ ድርጅቶችና ለሚመለከታቸው አካላት እያሰራጨ መሆኑን ሰሞኑን በካፒታል ሆቴል የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በተዘጋጀው የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገልጿል፡፡
ባለ 77 ገፁ የቱሪስት መመሪያ መጽሐፍ፣ በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳትን፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህል እንዲሁም ወደ ፓርኩ የሚወስድ የጉዞ አቅጣጫ ማመላከቻ ያካተተ ሲሆን ሌላው መጽሐፍ ደግሞ በፓርኩ በሚገኙ 282 የወፍ ዝርያዎች ዙሪያ ሠፋ ያለ መረጃ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
በቱሪስት መመሪያ መጻሐፍቱ ምረቃና በፎቶግራፍ ኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ስነ ስርአት ላይ ተገኝተው ስለ ፓርኩ አጠቃላይ ገለፃ ያደረጉት የፓርኩ ዋና ሃላፊ (ዋርደን) አቶ አስቻለሁ ጋሻው፣ በፓርኩ 78 የተለያዩ አጥቢ እንስሳት እንዳሉ ገልፀው ከነዚህ ውስጥ 20 ያህሉ ብርቅዬ ናቸው ብለዋል፡፡
ከብርቅዬ እንስሳቱ አንዱ የባሌ ብሄራዊ ፓርክ መለያ የሆነው የደጋ አጋዘን፣ በወጣትነት ዘመኑ ቱሪስቶች ሲጎበኙት ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር፣ በእርጅና ዘመኑ ታድኖ ሲሸጥ 15 ሺህ ዶላር ወይም 3 መቶ ሺ ብር ያወጣል ብለዋል አቶ አስቻለው፡፡
ከአዲስ አበባ በ4 መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በዚህ ፓርክ፣ 1600 የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች ሲኖሩ 32 የሚሆኑት በሌላው አለም የሌሉ ብርቅዬ ናቸው ተብሏል፡፡ ከእፅዋቱ 40 በመቶዎቹ ለመድኃኒት ቅመማ ይውላሉ፡፡    


Read 2504 times