Saturday, 05 July 2014 00:00

የሻዳይ በዓል ዘንድሮ በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ይከበራል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

*የአካባቢውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ያስፈልጋልበዋግ ኸመራ ዞንና አካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን የሻዳይ በዓል፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ በድምቀት ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑን የገለፀው የዋግ ልማት ማኅበር ዋልማ)፤የአካባቢውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመቅረፍ እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ አስታወቀ፡፡
የዋልማ ሊቀመንበር አቶ ምትኩ በየነ ከማኅበሩ ሥራ አስፈፃሚ አባላት ጋር በሰጡት መግለጫ፣ ሻዳይ፣ ከጥንት ጀምሮ በአካበቢው ሕዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓል ቢሆንም ተቀዛቅዞ እንደነበር ጠቅሰው፤ ከ7 ዓመት ወዲህ ግን ክልሉና የዞኑ አስተዳደር በዓሉ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለትውልድ እንዲተላለፍና የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ባሳሰቡት  መሰረት፣ ህልውናው ታድሶ እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በየዓመቱ ከነሐሴ 16 እስከ 18 የሚከበረው የሻዳይ በዓል፣ ማኅበሩ ከተቋቋመ ከ2002 ወዲህ ለሦስት ዓመት ከልማት ጋር ተቀናጅቶ እየተከበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማኅበሩ ዘንድሮም ለየት ባለ መልኩ፣ “ኅብረት ለዋግ ልማት” በሚል መሪ ቃል፣ ከፍተኛ አገር አቀፍ ልማታዊ ኅብረት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘንድሮ በርካታ እንግዶች ተሳታፊ ይሆናሉ ያሉት አቶ ምትኩ፤ በዓሉን የሚያከብሩት የዋግ ዞን ልጃገረዶች ብቻ ሳይሆኑ በዓሉን ‹አሸንዳ› በማለት ከሚያከብሩት አጎራባች አካባቢዎች- ትግራይ፣ ላሊበላና ቆቢ የተውጣጡ ልጃገረዶችም እንዲሳተፉ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በአሉን ከልማት ጋር ለማስተሳሰር የተፈለገው አካባቢው በርካታ ዘርፈ ብዙ የልማት፣ የትምህርትና  የጤና ችግሮች ስላሉበት ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ አገሪቷ እነዚህ ችግሮች እያሉባት የምዕተ አመቱን ግቦች ማሳካት ያዳግታታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“አካባቢው በተራራ ስለተሸፈነ ለማልማት አስቸጋሪ ነው፣ እስካሁን በአገሪቷ የተከሰቱ የድርቅ አደጋዎችም አካባቢውን አልፈው ሲያጠቁ ቆይተዋል፣ በአካባቢው ተራራ የሚፈሰው ውሃ ህዳሴው ግድብ ውስጥ የሚገባ ስለሆነ ተራራው ደን ከለበሰ ከተራራው እየታጠበ የሚሄደው ደለል ግድቡን በመሙላት ዕድሜውን ያሳጥረዋል፣ በአስተዳደሩ ውስጥ ካሉ 232 ት/ቤቶች ውስጥ 217ቱ ደረጃ አንድና ሁለት ቢሆኑም ከ106 ት/ቤቶች 514 የመማሪያ ክፍሎች የዳስ ወይም የዛፍ ጥላ መማሪያ ናቸው፡፡ ከ125 ቀበሌዎች ውስጥ 23ቱ ምንም ዓይነት ቁሳቁስ የላቸውም፡፡ በዞኑ የዓይን ህክምና የሚስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም  ህክምናውን  የሚሰጥ ተቋም ባለመኖሩ 6,342 ወገኖች አደጋ ላይ ናቸው” ሲሉ ችግሮቹን በዝርዝር ተናግረዋል፡፡
“ለልማታዊ ኅብረቱ በሚገኝ ገቢ በተመረጡ ቀበሌዎች መዋዕለ ሕፃናት በመክፈት፣የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችንና የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት፣ የጤና ተቋማት በመገንባት እንዲሁም  የዓይን ህክምና ተቋም በመክፈት ዋና ዋና ችግሮች የተባሉትን ለመቅረፍ አስበናል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ሁሉም የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆንና የልማት ዕቅዳቸውን እንዲደግፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡    

Read 1312 times