Sunday, 06 July 2014 00:00

በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩ አራት የግል ቴአትሮች መታየት አቆሙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“የመግቢያ ዋጋ እንዲስተካከል ብዙ ጊዜ አመልክተን ምላሽ አጥተናል” ፕሮዱዩሰሮች
“የዋጋ ማስተካከያ ጥናቱን ለገንዘብ ሚኒስቴር ልከን ምላሽ እየጠበቅን ነው”  ቴአትር ቤቱ



በብሄራዊ ቴአትር ማክሰኞ፣ ረቡዕ፣ ቅዳሜና እሁድ ለተመልካች ሲቀርቡ የነበሩ የግል ቴአትሮች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ መቋረጣቸውን የቴአትሮቹ ፕሮዱዩሰሮች ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ከስድስት ወር በፊት የቴአትር መግቢያ ዋጋ ከ15 ብር ወደ 30 ብር ከፍ እንደሚል ቃል ቢገባም እስካሁን ባለመስተካከሉና ለኪሳራ በመዳረጋቸው ትያትሮቻቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ በበኩላቸው፤ የመግቢያ ዋጋን በተመለከተ ያጠናነውን ጥናት ለገንዘብ ሚኒስቴር ልከን ምላሽ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ መታየት ያቆሙት አራት ትያትሮች በቶራቶር የቴአትር ኢንተርፕራይዝ ዘወትር ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት የሚቀርበው “አንድዜ”፣ በማይና ፕሮሞሽን ዘወትር ረቡዕ በ11፡30 ሰዓት የሚቀርበው “ዕጣ ፈለግ፣ በኤአይዲ ኢንተርቴይመንት ዘወትር ቅዳሜ በ12 ሰዓት ይቀርብ የነበረው “የብዕር ስም” እና በለታሪክ አድቨርታይዚንግ ዘወትር እሁድ በ12 ሰዓት ይቀርብ የነበረው “ማበዴ ነው” የተሰኙት ትያትሮች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ የብሄራዊ ቴአትር ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ አራቱ ትያትሮች መቋረጣቸውን ጠቁመው፤ ሆኖም የመግቢያ ዋጋውን ጥናት ሰርተን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በመላክ ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል፡፡ የቴአትር መግቢያ ዋጋ እስከ 50 ብር ሲጨምር ይህን የሚያጸድቀው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው” ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ከ50 ብር ላይ ሲሆን ግን በጠቅላላ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ይጨመራል ብለዋል፡፡ የቴአትር መግቢያ ዋጋ ሲጨምር ከመድረክ ጀርባ ያሉ ሰራተኞች፣ ተዋናዮች፣ ደራሲዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ጉዳይ አብሮ መታየት ስላለበት፣ ቴአትር ቤቱ ይሄንን ያካተተ ጥናት መስራቱን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የግል ቴአትር አቅራቢዎቹ ባለፈው አመት የመግቢያ ዋጋ 30 ብር ካልሆነ ለኪሳራ እየተዳረግን ስለሆነ ትያትር አናሳይም በሚል ትያትሮቻቸውን ማቅረብ ማቋረጣቸውን አስታውሰው፤ በቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ በአቶ ተስፋዬ ሽመልስና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ በአቶ ሙሉጌታ ሰይድ ምክክር ከተደረገ በኋላ፣ የመግቢያ ዋጋው እስኪስተካከል ድረስ ከአዳራሹ ኪራይ ሶስት ሺህ ብር ላይ አንድ ሺህ ብር ቅናሽ ተደርጎላቸው ማሳየት መቀጠላቸውን ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ የመግቢያ ዋጋው እንደሚስተካከል ቃል ተገብቶላቸው እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ “የመግቢያ ዋጋው ይስተካከላል በሚል ተስፋ ለኪሳራ እየተዳረግን ማሳየታችንን ቀጠልን” ያሉት ፕሮዱዩሰሮቹ፣ ምንም ለውጥ ባለመምጣቱ ከቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ ጀምሮ ሚኒስትር ዴኤታውና ሚኒስትሩን አቶ አሚን አሚን አብዱልቃድን ማነጋገራቸውን ገልፀዋል፡፡ “ሚኒስትሩ የመግቢያው ዋጋ የተስተካከለ መስሏቸው ነበር” ያሉት ፕሮዱዩሰሮቹ፤ ለአንድ ሰዓት ያህል ጊዜ ሰጥተው ካወያዩዋቸው በኋላ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚስተካከል ቃል ገብተው እንዳሰናበቷቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የቲያትር መግቢያ ዋጋው እንደሚስተካከል ከተነገራቸው አንድ ወር ማለፉን የገለፁት ቴአትር አቅራቢዎች፤ የአዳራሽ ኪራይ፣ የተዋናይ፣ የላይት ማን እና ሌሎች ክፍያዎችን ከፍለው እንዲሁም የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማስታወቂያ አስነግረው፣ በ15 ብር ቴአትር ማሳየት ለኪሳራ እንደዳረጋቸው በመግለፅ ደብዳቤ ፅፈው ለቴአትር ቤቱ በማስገባት ትያትር ማሳየት ማቆማቸውን ተናግረዋል፡፡ “ቴአትሮቹ በመቆማቸው ቴአትር ቤቱ ከአዳራሽ ኪራይና ከቴአትር የሚያገኘውን ገቢ አጥቷል” ያሉት ፕሮዱዩሰሮቹ፤ ህዝቡ ሊዝናና መጥቶ ቴአትር የለም ብሎ መመለስ በኪነ-ጥበቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል፡፡
የቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ሽመልስ፣ ማክሰኞና ረቡዕ የሚታዩት “አንድዜና” እና “ዕጣ ፈለግ” ተመልካቻቸው ከ300 ሰው በታች በመሆኑ በውሉ መሰረት የስምምነት ጊዜያቸው ማለቁን ለባለቤቶቹ በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ገልፀው፤ በፊትም ቢሆን ጥናቱ ተሰርቶና ገንዘብ ሚኒስቴር አይቶት ምላሽ እስኪመጣ በሚል ከ2800 ብር የአዳራሽ ኪራይ ላይ አንድ ሺህ ብር ቅናሽ በማድረግ ወጪ ተጋርተናቸዋል ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስር ያሉት ቴአትር ቤቶች የመግቢያ ዋጋ ሲያስተካክሉ እንዴት ብሄራዊ ቴአትር ዘገየ በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተስፋዬ፤ ብሄራዊ ቴአትር በፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስር መሆኑን አስታውሰው፣ የአዲስ አበባዎቹ ቴአትር ቤቶች ቀደም ብለው ጥናት ጀምረው ስለነበር የመግቢያ ዋጋውን በ30 ብር ማስተካከላቸውን ተናግረዋል፡፡
ቴአትር ቤቱ በቆሙት ትያትሮች ምትክ ምን ለማሳየት እንዳቀደ የተጠየቁት ስራ አስኪያጁ፤ “በአሁኑ ቅዳሜና እሁድ በቴአትር ቤቱ የሚታይ ትያትር ባይኖርም በቅርቡ ወደ እይታ የምናመጣቸው “የቃቄ ወርዲዎት” እና “የቴዎድሮስ ራዕይ” የተባሉ ትያትሮችና የትዕይንት ጥበባት ፕሮግራም ይኖሩናል” ብለዋል፡፡
የመግቢያ ዋጋ ማስተካከያ መቼ እንደሚደረግ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም፤ “በዚህን ቀን ብሎ መናገር ባይቻልም በቅርቡ ግን ይስተካከላል” ሲሉ ተናግረዋል፤ አቶ ተስፋዬ፡፡ ፕሮዱዩሰሮቹ በበኩላቸው፤ ቴአትር ቤቱ የመግቢያ ዋጋውን የሚያስተካክል ከሆነ ትያትሮቻቸውን ለማሳየት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡     

Read 2942 times