Saturday, 28 June 2014 13:03

ሮበርት ሙጋቤ ዚምባብዌን መግዛት ሰለቻቸው?

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(3 votes)

የዚምባቡዌ ህዝብ ከሙጋቤ በቀር ሌላ መሪ አይተው አያውቁም

የሆነ ሆኖ በድፍን ዚምባብዌ አሁን አየሩን የሞላው ትኩስ የመጋገሪያ ወሬ፣ የሽማግሌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በሽታ ካንሰር ነው አይደለም የሚለው ሳይሆን እርሳቸውን የሚተካው መሪ ማን ይሆን የሚለው ብቻ ነው፡፡

ከአመታት በአንዱ አፍሪካ ሙአመር ጋዳፊና ሆስኒ ሙባረክ የተባሉ መሪዎች ነበሯት፡፡ እነዚህ መሪዎች ሀገራቸውን ለረጅም ጊዜ በፕሬዚዳንትነት በመምራት የአፍሪካን ሬከርድ የያዙ ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ሊቢያን ለአርባ አራት አመት፤ ሆስኒ ሙባረክ ደግሞ ግብጽን ለሰላሳ ሁለት አመት በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት በሊቢያና በግብጽ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አብዮት፣ ፕሬዚዳንት ጋዳፊን ስልጣናቸውን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውንም ሲያሳጣቸው፤ ፕሬዚዳንት ሙባረክን ደግሞ ከስልጣናቸው ተፈንግለው ወህኒ ለመጣል አብቅቷቸዋል፡፡
አሁን ሬከርዱ የተያዘው በሮበርት ሙጋቤ ነው፡፡ እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1980 ዓ.ም ነፃነታቸውን የተቀዳጁት ዚምባቡዌአውያን ከሮበርት ሙጋቤ በቀር ሌላ መሪ አይተው አያውቁም፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሰባት አመታት (1980-1987) በጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በፕሬዚዳንትነት የሚመሯቸው ሮበርት ሙጋቤ ናቸው፡፡
በደቡባዊ ዚምባብዌ በምትገኘው የኩታማ ከተማ፣ ጥቅምት 21 ቀን 1924 ዓ.ም ከአናፂ ቤተሰብ የተወለዱት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ፤ የከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በደቡብ አፍሪካና በጋና ነው፡፡ በ1963 ዓ.ም ከቄስ ንዳባንጊ ሲቶሌ ጋር በመሆን ጆሽዋ ንኮሞ ይመሩት ከነበረው የዚምባብዌ የአፍሪካ ህዝቦች ህብረት (ዛፑ) ተገንጥለው፣ የዚምባብዌ የአፍሪካ ብሔራዊ ህብረት (ዛኑ) በማቋቋም፣ ለነፃነት ትግል ነፍጥ አንስተው፣ ውጊያ እስከጀመሩበት ጊዜ ድረስ በሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት መምህር ነበሩ፡፡
ሮበርት ሙጋቤ፤ ዛኑን አቋቁመው ጫካ እንደገቡ መላ ዚምባብዌአውያን ነፃነታቸውን ለመጎናፀፍ በቁርጠኝነት እንዲታገሉና ከድርጅታቸው ከዛኑ ጎን እንዲሰለፉ ዛሬም ድረስ እጅግ ቀስቃሽ ነው የሚባልላትን ንግግር አደረጉ፡፡ ይህን ንግግር ባደረጉ ልክ በሰባተኛው ወር 1964 ዓ.ም በአያን ስሚዝ በሚመራው የነጮች መንግስት የደህንነት ሀይሎች እጅ ወደቁ፡፡ አፍታም ሳይቆይ የእኛ ሀገር መንግስት “ህገ መንግስታዊውን ስርአት ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በኃይል ለመናድ” እንደሚለው አይነት ክስ ተመስርቶባቸው፣ ወንጀለኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ የአስር አመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ፡፡
ሮበርት ሙጋቤ የእስር ጊዜአቸውን እንዲሁ አላሳለፉትም፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በተልዕኮ በመከታተል በህግ ትምህርት ሁለት ዲግሪያቸውን ለማግኘት ችለዋል፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴአቸውም ቢሆን እስር ቤት የታሰበውን ያህል ከጨዋታ ውጪ ሊያደርጋቸው አልቻለም፡፡ እዚያው ወህኒ ቤት ውስጥ እያሉ በ1974 ዓ.ም የዛኑ መስራችና መሪ የነበሩትን ቄስ ንዳባኒንጊ ሲቶሌን በመፈንቅለ ስልጣን በማስወገድ ቀጥተኛ አመራር ይሰጡ ነበር፡፡  
በ1974 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ከእስር ቤት የተለቀቁት ሮበርት ሙጋቤ፤ እስከ 1979 ዓ.ም ድረስ ለነፃነት የተካሄደውን የትጥቅ ትግል በዋናነት መርተዋል፡፡ በየካቲት ወር 1980 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው ድህረ ነፃነት ምርጫ፣ ከጆሽዋ ንኮሞ ጋር በጥምር ይመሩት የነበረው የዚምባብዌ አፍሪካ ብሔራዊ ህብረት አርበኞች ግንባር (ዛኑ ፒኤፍ) በከፍተኛ ድምጽ በማሸነፉ፣ ሮበርት ሙጋቤ የነፃይቱ ዚምባብዌ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሃምሳ ስድስት አመት የጐልማሳነት እድሜአቸው የመሪነት ስልጣኑን ተቆናጠጡ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ከመሪነት መንበሩ አልወረዱም፡፡
አምና ለ89 አመቱ አዛውንት ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ እድሜና ስልጣን አመጣሽ በሽታዎች እየተፈራረቁ የጤናቸውን ሁኔታ በከባዱ ወሰድ መለስ እያደረጉት በጣም ተቸግረው ነበር፡፡ በወቅቱ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይወዳደሩ ይችላሉ ተብሎ በሠፊው ተገምቶም ነበር፡፡
ላለፉት 33 አመታት የተቀመጠቡትን የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ወንበር መልቀቅ ሞት መስሎ ይታያቸው የነበሩት ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ  “ዚምባብዌ እኮ የእኔ ናት፤ ለሌላ ሰው እንዴት አድርጌ አሳልፌ እሠጣታለሁ?” በማለት በምርጫው እንደሚሳተፉ አሳወቁ፡፡ የተካሄደውን ምርጫም ዋነኛ ተቀናቃኛቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር መርጋን ቻንጋራይን በከፍተኛ ድምጽ በማሸነፍ አዳሜን ሁሉ ኩም አደረጉት፡፡
ከሰሞኑ ግን ብዙዎች ከፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ አፍ ይወጣል ብለው በቀላሉ የማይገምቱት ንግግር ተሰምቷል፡፡ የ90 አመቱ አዛውንት ላለፉት 34 አመታት በብቸኝነት የተቀመጡበት የፕሬዚዳንትነት ወንበር እንደሰለቻቸውና በዚህ አመት መጨረሻ ላይ ከስልጣን ወርደው ጡረታ መውጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ አብዛኛውን ያለፉትን ስድስት ወራት ያሳለፉት ካንሰር ነው እየተባለ የሚወራባቸውን በሽታቸውን ለመታከም ወደ ሲንጋፖር በመመላለስ ነው፡፡ መንግስታቸውም ስለ ጤንነታቸው ግልጽ መረጃ ከማቅረብ ይልቅ ስለጉዳዩ የሚያወራና የሚጽፍን ሰው ሁሉ እንደሚቀጣ ማስፈራራትን መርጧል፡፡
የሆነ ሆኖ በድፍን ዚምባብዌ አሁን አየሩን የሞላው ትኩስ የመጋገሪያ ወሬ፣ የሽማግሌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በሽታ ካንሰር ነው አይደለም የሚለው ሳይሆን እርሳቸውን የሚተካው መሪ ማን ይሆን የሚለው ብቻ ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ፣ የሳቸው ተተኪ ከምክትል ፕሬዚዳንቷ ጆይብ ሙጁሩ፤ ወይም “አዞው” በሚል ቅጽል ስም ከሚታወቁትና የፍትህ ሚኒስትር ከሆኑት ኤመርሰን ምናንጋዋ አሊያም የዚምባብዌ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ ከነበሩት ጌዲዮን ጐኖ አያልፍም፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን እኔ ልቀጣ፡፡

Read 5933 times