Saturday, 28 June 2014 11:57

ቁጡ ነብር! ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ

Written by  አጭር ልብወለድ ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
Rate this item
(8 votes)

     ሾጎሎማንጎጭ በምድር በመካከለኛው ክፍል የሚገኝ በባህር የተከበበ ለም ሀገር ነው፡፡ እዚህ ሀገር ውስጥ ሰው ሁሉ ሀገሩን የሚወድድ፣ ወገኑን የሚያፈቅርና መልካም ባህል ያለው ህዝብ ይኖርበታል፡፡ ሾጎሎማንጎጫውያን ሁለት ዓበይት የጎሣ ክፍሎች አሏቸው፡፡ አንደኛው አዝሮድ ሲባል ሌላው ምርሻድ ይባላል፡፡ ጥቂት አዝሮዶች በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል በእርሻ ሥራ ሲተዳደሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ በምሥራቁ ክፍል የባህር ዳርቻ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ የተቀሩት በመላው የሀገሪቱ ክፍል እየኖሩ በግል ሥራ ላይ ሆነው የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ምርሻዶች ደግሞ በሁሉም ቦታ እየተዘዋወሩ ከፊሉ በንግድ ሥራ፣ የተቀሩት ደግሞ በእጅ ሥራ ሙያ ላይና በሌላውም ጥበባዊ ዕውቀት ላይ ሁሉ ተሰማርተዋል፡፡
ምርሻዶችና አዝሮዶች ሥርወ የዘር ግንዳቸው ከሁለት ወገን ቢሆንም፣ ይህንን የሚያስብ በመካከላቸው አንድም ሰው አይገኝም፡፡ የሀገሩ ሰው ሁሉ የሚያምነው በቃ ሾጎሎማንጎጫዊ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ተፋቅረው ሲጋቡ፣ ተጋብተው ሲዋለዱ፣ በአገራቸው ላይ የሚመጣውን ጥቃት ሁሉ ባንድነት ሆነው ሲመክቱ፣ በሀዘንም በደስታም ጊዜ በህብረትና በስምምነት ሆነው ይኖራሉ፡፡ የሾጎሎማንጎጫውያን ብቻ የሆነውን የተቆጣ ነብር ምልክት ደረቱ ላይ ያልተነቀሰ ሰው በሾጎሎማንጎጭ ምድር አይገኝም፡፡ ይህ ከአንገቱ በላይ የሚታየው የቁጡ ነብር ምስል ለሀገራቸው ቀናዒ አንድ ህዝብ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ምልክታቸው ነው፡፡ ይህን ምስል ከፈጣሪያቸው በታች ከልባቸው ያፈቅሩታል። ማንም ፍቆ ሊያጠፋው የማይችል የልብ ውስጥ ማህተማቸው ነው። አገራቸው ሾጎሎማንጎጭ፣ እነሱም ሾጎሎማንጎጫውያን ናቸው፤ በቃ ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚያስቡት ነገር የለም - ቁጡ ነብር!
ሾጎሎማንጎጫውያን ሎማዲን የምትባል ንግሥት አለቻቸው፡፡ ይህች ሴት በአስተዋይነቷና በብልህነቷ ወደር የማይገኝላት ነች፡፡ መልካም የሆነው ቅን ሥራዋ በህዝቧ ዘንድ የተከበረችና የተወደደች እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ለህዝቧና ለሀገሯ እጅግ ቀናዒ በመሆኗ በግዛቷና በመንግሥቷ ብዙ ዘመን ቆይታለች፡፡
በሾጎሎማንጎጫውያን የዘመን አቆጣጠር በአንደኛው ቀን እንዲህ ሆነ፡፡ የሀገሪቱ ህዝብ በመላ ባንድ ላይ ተሰበሰቡና ከመካከላቸውም ቅን የነበሩትን ሁሉ ጥቂት ሰዎች መረጡ፡፡ የተቀሩትን በተኑ፡፡ እኒያ የተመረጡትም ለብቻቸው ሆነው ምክር ያዙ፡፡ እጅግ በጣም የሚወዷትና የሚያከብሯት ንግሥታቸው ድንገት በጠና ስለታመመች፣ ሁላቸውም በማዘናቸው ልባቸው ተሰብሯል፡፡ በምክራቸውም ዘልቀው ንግሥታቸው ድንገት በጠና ስለታመመች ሁላቸውም በማዘናቸው ልባቸው ተሰብሯል፡፡ በምክራቸውም ዘልቀው ንግሥታቸውን በፍቱን መድኃኒት የሚያድንላቸውን ሰው ማፈላለግ ያዙ፡፡ በመጨረሻም ካዚሪዚ የተባለ የገነነ ስም ያለው የታወቀ መድኃኒት አዋቂ ሰውን አገኙ፡፡ ካዚሪዚን ንግሥቲቷን በመድኃኒቱ ይፈውሳት ዘንድ ወደ ቤተ መንግሥት አመጡት፡፡
ይህ ካዚሪዚ የተባለው መድኃኒት አዋቂ ሰው ከሀገር ውጪ እየተዘዋወረ በልዩ ልዩ ሀገራት መድኃኒት ይሰጥ ነበርና፣ በሀገሩ የሌሉ ብዙ ሁኔታዎችን በየጊዜው ሊመለከት ችሏል፡፡ በሥራው ምክንያት የተነሳ የየሀገሩን አንዳንድ ባለስልጣናትን መተዋወቅ ችሎ ስለነበረ ስለ ሀገሩ ልበ ጎዶሎ ሰው ሆኗል፡፡ ዛሬ ግን ንግሥቲትን ሊፈውስ ታዝዞ ቤተ መንግሥት ገብቷል፡፡ የህመሟን ዓይነት እየጠያየቃት ካጠገቧ ባለው ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡
“ንግሥት ሆይ!... ህመሙ እንዴት ነው የሚሰማሽ?” ብሎ ካዚሪዚ ሎማዲንን ጠየቃት፡፡
“ራሴን ይነድለኛል፡፡ ሰውነቴን ብዙ ቦታ ላይ ይቆረጣጥመኛል፡፡ ትኩሳቱ እንቅልፍ ነስቶኛል፣ ህመሙም ምግብ ከልክሎኛል…” አለችው፡፡
“ይኸው ነው?...ሌላስ የሚሰማሽ ነገር አለ?”
“ልቤን ይወጋኛል፡፡ ህመሙ ከፍቶ ነው መሰል የሠራ አካሌ ዝሏል”
“ጥሩ ነው፡፡ ህመምሽን ደርሼበታለሁ፡፡ ኒማክዶራቫ የሚባል ክፉ ደዌ አድሮብሻል፡፡ ፈዋሽ መድኃኒቱን በጥንቃቄ ቀምሜ ለማዘጋጀት አንድ ሳምንት ስለሚፈጅብኝ ትጠብቂኛለሽ፡፡ አይዞሽ አትፍሪ.. ትድኚያለሽ” በማለት ካፅናናት በኋላ፣ ከክፍሏ ወጥቶ ሄደ።
በሩ ላይ የንግሥቲቷ እልፍኝ አስከልካይ ይጠብቀው ኖሮ ህመሟ ምን እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ካዚሪዚም ህመሟ ትንሽ ከበድ ያለ እንደሆነና ሊያድናት እንደሚሞክር ገለፀለት፡፡ አክሎም ከአንድ ሳምንት በኋላ መድኃኒቱን ይዞ እንደሚመለስ ነገረው፡፡
ከሾጎሎማንጎጭ ደሴት ከባህሩ ማዶ በቅርብ ርቀት የሚታይ አርኪሞጥ የሚባል ሀገር አለ፡፡ ይህ ሃገር ከሾጎሎማንጎጫውያን ምድር በብዙ ነገር ስለሚለይ የሚመሳሰሉበት የጋራ የሆነ ምንም ነገር አይታይባቸውም። አርኪሞጣውያን እኛ ከሌሎች ልቀን እጅግ ሰልጥነናል ብለው ራሳቸውን ስለሚገምቱ፣ የሌላው ሀገር ህዝብ ከእነሱ በታች ዝቅ ያለ እንደሆነ አድርገው ይገምታሉ፡፡ በዚህም ትዕቢት ከልባቸው ነው፡፡ ሀሰትና ተንኮል የተፈጠሩበት ድርና ማጋቸው ነው፡፡ ስስትና ፍቅረ ንዋይ ከደምና ሥጋቸው ተዋህዷል፡፡ አንዱ ሰው ከሌላው እንዲመስልና ተዋህዶ እንዲኖር አይወዱምና የረጋውን ማማሰል፣ ጅላጅሉን መደለል… የተጣበቀውን መላጥ፣ ውሃ ቅቤ እንዲያወጣ መናጥ… የዘወትር ሥራቸው ነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ በህዝብ መካከል ከብዙ ዓመታት በፊት የተደረገን የስህተት አጋጣሚ፣ ዛሬ ላይ አምጥተው አዲስ ትኩስ ቁስል እንዲፈጠር ቀንና ሌት ይደክማሉ፡፡ ዓይናቸውም ከጥቅማቸው ውጪ ሊመለከት አይችልምና፣ የሌላውን ጉስቅልና እይ ቢባል ወዲያው ይታወርባቸዋል፡፡ አርኪሞጣውያን እንዲህና ከዚህም የባሱ ናቸው፡፡
መድኃኒተኛው ካዚሪዚ ስለ ሀገሩ ልበ ጎዶሎ የሆነበት ምክንያትም ከእነዚህ አርኪሞጣውያን ጋር የልብ ወዳጅነት ይዞ ስለነበር ነው፡፡ በገንዘብ ይደልሉታል፣ በቆነጃጅት ያማልሉታል፡፡ በህመም ፈዋሽነቱ ምክንያት ባገኘው ህዝባዊ ክብር ተጠቅሞ ተንኮላቸውን በራሱ ሀገር ህዝብ ውስጥ እንዲዘራ ይመክሩታል፡፡ ካዚሪዚም ቢሆን ልቡን ሰጥቶ ከገበረላቸው እነሆ ጊዜው ቆየ፡፡ ይኸው ዛሬ ደግሞ የራሱ ንግሥት የሆነችው ሎማዲን በመታመሟ ሊፈውሳት መድኃኒት ፍለጋ ብሎ አርኮሞጥ መጥቷል፡፡
የንግሥት ሎማዲን ህመም እያደር እየጠና መጣ። ህመሟን እንዲህ ነው የሚል በሾጎሎማንጎጭ ምድረ ማንም አዋቂ ነኝ ባይ ሰው አልተገኘም፡፡ በየዕለቱ እየደከመች መጣች፡፡ በዚህ መካከል መድኃኒተኛው ካዚሪዚ ከሄደበት ሀገር መድኃኒቱን ይዞ በድንገት ከተፍ አለ፡፡ የእሱን መምጣት የሰማው ሰው ሁሉ እጅጉን ተደሰተ፡፡ ወሬውም ባገሩ ሁሉ ናኘ፡፡
ህዝቡ ስለ ንግሥቲቷ በቶሎ መዳን ከመጓጓቱ ተነሳ ጆሮውን አቁሞ ለንፋሱ ሰጠ፡፡ ህዝቡ እንዲህ መሆኑ ሲያንሰው ነው፡፡ ህዝብን በአንድ ዓይን ተመልክቶ አድልዖ የማያደርግ መሪ እንደ ንግሥት ሎማዲን ዓይነት የት ማግኘት ይቻላል? ከራሱ ቤተሰብ ውላጆችና በዙሪያው ሸብ ረብ ከሚሉት አሽቃባጮቹ ባሻገር፣ ወደ ታች ወርዶ የህዝብን ረሃብና ጥማት ተረድቶ በቶሎ የሚያስወግድ ከሎማዲን በስተቀር ሀገር በጫጩት ቢታሰስ የት ይገኛል? ለሀገሩ ባህልና ታሪክ ክብር ያለው፣ ለሰንደቁና ለዳር ድንበሩ ሁሌም ዘብ የቆመ፣ በጥቅም ታውሮ ለባዕዳን የማይንበረከክ መሪ ሎማዲን ብቻ እንጂ፣ በዚያ አካባቢ ሌላ ወየት አለ? ዕቡያን ብቻ እንጂ ሎማዲንን በሴትነቷ ዝቅ አድርጎ የሚያያት ሰውስ ማነውሳ? እንጥስ! ሲል፣ ‘ይቀንጥስህ!’ በሚባሉ ብዙ የሀገር መሪዎች መካከል፣ ሾጎሎማንጎጫውያን ሎማዲንን የመሰለ ጥሩ መሪ በማግኘታቸው በእርግጥም ዕድለኞች ናቸው፡፡ ታዲያ ክፉዋን ማን ይመኛል? እንዲህ ያለውን ነገር ሾጎሎማንጎጫውያን መካከል ሆኖ ማሰብ ይቻላል ወይ? ለዚህም ነው ህዝቡ በመላ እንደ አንድ ሰው ሆኖ በህመሟ ሲጨነቅ የከረመ፡፡ የመልካም ሥራ ውጤቱ ደግሞ ይህ ነው፡፡
ንግሥት ሎማዲን በቀናው ሥራዋ ከፍ ከፍ አለች። በቅንነቷና በመልካምነቷ የህዝቧን ልብ ማረከች፡፡ እንደ ጧት ጤዛ ፈጥኖ በሚያልፈው ህይወቷ ለማያልፍ ስምና ክብር በቃች፡፡ አቤቱ ፈጣሪ!.. ሾጎሎማንጎጫውያን እንዴት ታድለዋል!? በአልኮል ብዥታና በምርቃና ሞቅታ ምናምኑን እየጫረ አስደንግጎ ከሚገዛ መሪ አምላካቸው ለወደፊቱ ይሰውራቸው እንጂ፣ ዛሬስ እንደ ሎማዲን ያለ ደግ መሪ አላቸው፡፡
*   *   *
ካዚሪዚ ቀምሞ ያመጣውን መድኃኒት ንግሥት ሎማዲንን አጠጣት፡፡ እንደምትድን ተስፋ ሞልቶባት በበነጋው ወደ አርኮሞጥ ምድር ተሻገረ፡፡ የአርኪሞጥ ንጉሥ የሆነው ሳንቶርቢ፣ ካዚሪዚን ከቤተ መንግሥቱ ተቀብሎ አስተናገደው፡፡ በምስጢር ሁለቱ ብቻ የዶለቱት ክፉ ነገር በመካከላቸው ስላለ በልቦቻቸው ተግባቡ፡፡ የአርኮሞጡ ንጉሥ ካዚሪዚን እንዲህ አለው፡፡
“ወዳጄ ሆይ!... የወሰድከውን መድኃኒት ንግሥት ሎማዲንን ይፈውሳት ዘንድ አጠጣሃትን?”
“አዎ!... በትክክል እንዲያ ነው ያደረግሁ” ብሎ፤ ለንጉሡ መልስ ሰጠ፡፡ ንጉሡም መልሶ፤
“ከዛሬ ጀምሮ የእኔና የአርኪሞጣውያን ወዳጅ ሆነሃል፡፡ በል ንሣና የታዘዘልህን ስጦታ ከግምጃ ቤቱ ዘንድ ሄደህ ውሰድ!” አለው፡፡
ካዚሪዚም እንደተባለው አደረገ፡፡ የሾጎሎማንጎጯ ንግሥት ሎማዲንም በማግሥቱ አረፈች፡፡
በሾጎላማንጎጭ ምድር ከባድ ሀዘን ደረሰ፡፡ ዋይታ ሆነ፡፡ ህዝቡ በመላ ማቅ ለበሰ፡፡ እሪታና ጩኸት ምድሪቱን ሞላት፡፡ እያንዳንዱ ሰው በማስመሰል ካንገቱ በላይ ሳይሆን ፍቅሯን አስቦና ልቡ ፈንቅሎት ተንሰቅስቆ እንባዎቹን አፈሰሰላት፡፡ የደጓ ንግሥት ሎማዲን ሞት መሪር ሀዘን ሆነ፡፡ ዜና እረፍቷ እንደተሰማም የየሀገሩ ሰው ሁሉ ወደ ሾማሎማንጎጭ ምድር ጎረፈ፡፡ ከቦታው ለመምጣት ንጉሥ ሳንቶርቢን የቀደመው አልነበረም። በጣም ብዙ ተከታዮቹን አስከትሎ ከሎማዲን ቤተ መንግሥት ገብቶ ሀዘን ተቀምጧል፡፡ ካዚሪዚም በድንጋጤ ክው ያለ በመምሰል ኩርምት ብሎ አንገቱን ደፍቷል፡፡
ካዚሪዚ ከተቀመጠበት ድንገት ብድግ አለና ልቅሶ ለተቀመጠው ሰው ሁሉ እንዲህ አለ፡-
“ያገሬ ሰዎች ሆይ! ዛሬ በደረሰብን ከፍተኛ ሀዘን በጣሙን አዝኛለሁ፡፡ ንግሥትን ለማዳን ሁነኛ መድኃኒት እስካገኝ ድረስ በየሀገሩ እየዋተትሁ ቆየሁ፡፡ በመካከሉ የንግሥት ደዌ ክፉ ነበርና፣ እኔ እስክመለስ ድረስ ደክማ ጠበቀችኝ፡፡ እየሰጋሁ ቢሆንም ሌላ ምርጫ ባለመኖሩ መድኃኒቱን ሰጠኋት፡፡ ተጎድታ ቆየችኝና ያመጣሁት መድኃኒት ሊሠራላት አልተቻለውም፡፡ እናም…” ብሎ፣ የሚናገረውን ሳይገታ ይነፈርቅ ገባ፡፡
ሎማዲንን በመርዝ እንደገደላት ሆዱ እያወቀ የአዞ እንባውን አፈሰሰ፡፡ ኃጢአቱን በሆዱ ቋጥሮ ይዞ ከህዝቡ ሊመሳሰል ቀበጣጠረ፡፡ “የመገበሪያ ስንዴ የበላ ያስፈልገዋል”… እንዲሉ ሆነበት፡፡
በዚያ ግርግርና የህዝቡ ልብ በሀዘን በተሰበረበት ወቅት፣ እነዚያ ንጉሥ ሳንቶርቢን ተከትለው የመጡት ሰዎች ማንም ሰው ልብ ባላለው መንገድ በሀገሪቱ ሁሉ ተበተኑ፡፡ ቀደም ብለው በሃገራቸው ሳሉ የሾጎሎማንጎጫውያን ምልክት የሆነውን     ቁጡ የነብር ምስል ሁላቸውም ከደረታቸው ላይ ተነቅሰው ኖሮ፣ ከሌላው የሀገሪቱ ዜጋ በጭራሽ መለየት አይቻልም ነበር፡፡ በፍጥነት ተመሳስለዋል፡፡ ውለው ሳያድሩ ንጉሣቸው ሳንቶርቢ ያዘዛቸውን ተግባር ሁሉ መከወን ተያያዙ፡፡
በጥንቃቄና በዘዴ መርዛቸውን መርጨት ጀመሩ። በየሰዉ ልብ ከጠፋ የቆየውን አዝሮድና ምርሻድ ይባል የነበረውን የሾላማንጎጫውያን ሥርወ የዘር ግንድ እያነሱ ልዩነታቸውን ማራገብ ጀመሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ያለ እረፍት ለሚያላዝኑ ቡችሎቻቸው ውስጥ ለውስጥ ብዙ ገንዘብ ይረጫሉ፡፡ “አንገተ ረጅም ማሽላ አንድም ለወፍ፣ አንድም ለወንጭፍ” እንዲሉ፣ ለምን? እንዴት? በማለት የሚሞግታቸውን ሰው በስውር ያጠፉታል፡፡ የእነሱን አስተሳሰብ የማይደግፍ ሰው ጠላታቸው ነው፡፡ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ሀገራቸው አርኪሞጥ ታላቅነት ይሰብካሉ፡፡ የሸቀጥ ዕቃዎቻቸውን በጀልባ እያጓጓዙ ሸጎሎማንጎጭ ምድር ያራግፋሉ፡፡ ዝሙት እንዲሰራጭ፣ ተንኮል እንዲስፋፋ፣ ባህልና ወግ እንዲጠፋ በብዙ ደከሙ፡፡ በዚህ ተግባራቸውም ሆድ አደሩን ሁላ አማልለው ብዙ ሰው ወደ እነሱ አመጡ፡፡ እንዲህ እየሆነ አያሌ ወራትና ዓመታት አለፉ፡፡ ህዝቡም እያደር ቀስ በቀስ በሃሳቡ እንዲለያይ ሆነ፡፡ ሾጎሎማንጎጭ የበፊቱ ዝናዋ እየወረደ ደበዘዘች፡፡ አርኪሞጣውያንም በውስጧ ሥር እየሰደዱ ሄዱ፡፡
እንዲህና ሌላም እየሆነ ጊዜው ሲደርስ፣ የአርኪሞጡ ንጉሥ ሳንቶርቢ ወታደሮቹን አዝዞ በብዙ ጀልባ ሆነው በመንፈስ ደክሞ ጫንቃው የጎበጠውን የሾጎሎማንጎጭን ህዝብ ወረሩ፡፡ ከህዝቡ መካከል አሻፈረኝ ያለው ባለ ወኔው ወራሪዎቹን ወጋ፡፡ ብዙ ነፍስም ጠፋ፡፡ በመጨረሻ ግን ንጉሥ ሳንቶርቢ ሀገሪቱን በሙሉ ያዘ፡፡ መድኃኒተኛው ካዚሪዚንም ኃላፊ አድርጎ በቤተ መንግሥቱ ላይ ሾመው።
በምዝበራው፣ በጭቆናውና በመከፋፈሉ ተንኮል ሁሉ የንጉሡ ሰዎች እጅግ አድርገው ሰለጠኑ። የሾጎሎማንጎጭ የሆነውን ውድ ዕቃዎች ሁሉ እየዘረፉ ወደ እናት ምድራቸው ወደ አርኪሞጥ አሻገሩ፡፡ አርኪሞጣውያን ስለ ሾጎሎማንጎጫውያን ከአባቶቻቸው የወረሱትን ጥላቻና ክፉ ነገር ሁሉ በምድሪቱ ላይ ዘሩ፡፡
የሾጎሎማንጎጭ ብዙ ወንዶች ያለ ባህላቸው የጉትቻ ጌጥ በጆሯቸው ላይ ማንጠልጠል ጀመሩ። ሴቶቹ ጨርቃቸውን አሳጥረው አካሎቻቸውን ገላለጡ፡፡ ወጣት ሾጎሎማንጎጫውያን የሀገር ፍቅር አድሮባቸው ወራሪዎቹ ላይ እንዳይነሱ በጥቅማ ጥቅምና በርካሽ ብልጭልጭ ነገሮች ማርከው መንፈሰ አልባ አደረጓቸው፡፡ ዕፀ ፋርስ በየሰዉ አፍና አፍንጫ ይጉተለተል ገባ፡፡ ህዝቡ ያለ ልማዱ የጎሪጥ መተያየት ጀመረ፡፡ ለምለሚቷ ምድር ጠወለገች። የምላስ አርበኛ እንጂ የተግባር ሰው ጠፋ። ሾጎሎማንጎጭ አንዳች ጉድ ወረደባት፡፡ ህዝቧም በባህር ላይ እየሆነ ወደ ሌላ ምድር ተሰደደ፡፡
በመንግሥታቸው ሞት ሾጎሎማንጎጫውያን በብዙ ተጎዱ፡፡ ይህን ሁሉ ጉድ ያመጣባቸው ከሃዲው ካዚሪዚ በምቾት ቢሆንም፣ የወገኖቹ ጉዳት እያደር ልቡን እያቆሰለው መጥቷል፡፡ ሰላምና እንቅልፍ አጣ፡፡ ወትሮስ ቢሆን ነፍስን ያስገዙለት ምቾትና የህዝብ ገንዘብ እያደር እንደ እሳት ለብልቦ በስተመጨረሻ አይሆኑ ነገር ያደርግ የለ!? አዎ!...
ካዚሪዚ የሆነው ከዚህብ በላይ ነው፡፡ የህዝቡ ጩኸት ጆሮውን ነደለው፡፡ እናም ከዚህ በላይ ከቶም መሸከም አልተቻለውም፡፡ ኑዛዜውን ጻፈና ከደረት ኪሱ ቆልፎበት ወደ አንድ ትልቅ ገደል ሄዶ ራሱን ወደታች ወረወረ፡፡
የኃጢአት ምንዳው ክፉ አሟሟት ነውና፣ ካዚሪዚ በዚህ መንገድ ከሲዖል የማያድነውን ንስሃውን ከፈለ፡፡ አንዲት ክፉ ነፍስ ብዙ ደጋግ ሰዎችን ይዛ ትጠፋለች፡፡ የሾጎሎማንጎጭ ምድርም በዙሪያዋ ወደ ከበባት የባህር ጠለል ዝቅ ዝቅ እያለች ነው፡፡ የምትመካበት የፈጣሪዋ ኃያል ክንድ ቶሎ ይታደጋት ዘንድ ግን እምነቷ ፅኑ ነው። ይህ ሊሆን ደግሞ ሾጎሎማንጎጫውያን ብርቱ ተስፋ አላቸው፡፡


Read 3804 times