Saturday, 28 June 2014 11:20

የሞተር ቅባትና ዘይት የሚያመርት ፋብሪካ በገላን ሥራ ጀመረ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በእርግጥ በአብዛኛው የተሰማሩት በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ነው። እነሱን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለማምጣት ቀላል ባይሆንም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ትልቅ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና የማኔጅመንት ብቃት ይጠይቃል፡፡


ሱዳናዊ ናቸው - የናጠጡ ባለሀብት፡፡ ዋና መ/ቤታቸውን ዱባይ አድርገው ናዝቴክ ፔትሮሊየም ኢንቨስትመንት ግሩፕ የተባለ ኢንዱስትሪ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች፡- ሱዳን፣ ኮንጎ፣ ቻድ… ከፍተው እየሰሩ ናቸው፡፡
እኚህ ሰው ኢ/ር ናዛር ኢብራሂም ኦማር ይባላሉ። በነዳጅ ሥራ ኢንዱስትሪ 15 ዓመት እንደቆዩ የተናገሩት ኢ/ር ኦማር፤ አሁን ደግሞ ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ መልሰዋል፡፡ ኢንቨስተሩ፣ መቀመጫው ዱባይ ከሆነ ሌላ በነዳጅ ንግድ ከተሰማራ ሚሊዮን ኢንተርናሽናል ከተባለ የጀርመን ኩባንያ ጋር በመተባበር በ10 ሚሊዮን ዶላር (200 ሚሊዮን ብር) ካፒታል፣ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ፣ ሉብታም በመባል የሚጠራና ለተለያዩ ተሽከርካሪዎችና ሞተሮች ዘይትና ቅባት ማቀነባበሪያ (ሉብሪካንት ብሌንዲንግ) ፋብሪካ ከፍተዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ያመጣን በአገሪቱ ያለው ሰላም፣ ምቹ ፖሊሲና አመቺ የኢንቨስትመንት አማራጭ ነው ያሉት ባለሀብቱ፤ ከመንግሥትና በየዘርፉ ካሉት የኢንቨስትመንት ቢሮዎች መልካም ድጋፍና ትብብር ስለተደረላቸው አመስግነዋል፡፡ ሉብታም፣ በአሜሪካ ፔትሮሊየም ኢንዱስትሪ የተረጋገጠና ጥራቱ ከፍተኛ የሆነ ልዩ የተሽከርካሪ፣ የኢንዱስትሪና የባህር ሞተር ማመላለሻ ቅባቶችና ዘይቶች የምናመርት መሆኑን መንግሥት ማረጋገጥ ይችላል ብለዋል፡፡
የሉብታም ሉብሪካንት በኢትዮጵያ መቋቋም፣ ዓላማው እዚህ ብቻ ሳይሆን ምሥራቅ አፍሪካንም ያጠቃልላል፡፡ ሉብታም በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት 50 ሺ ቶን ዘይትና ቅባት ሉብሪካንት ያመርታል። የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሉብሪካንት ፍጆታ 35ሺ ቶን መሆኑን የክብር እንግዳው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ዕቅዳቸው የምርታቸውን 40 በመቶ ለኢትዮጵያ ፍጆታ፤ ቀሪውን 60 በመቶ ለምሥራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች፡- ለኬንያ፣ ለጂቡቲና ለደቡብ ሱዳን እንደሚሸጡ ኢ/ር ናዛር ኦማር ገልጸዋል፡፡ ኢ/ር ናዛር እነዚህ የተሽከርካሪና የሞተር ቅባቶችና ዘይቶች አገር ውስጥ በመመረታቸው በአንድ ወገን ኢትዮጵያ የሞተር ማለስለሻዎቹን (ሉብሪካንቶች) ከውጭ ለመግዛት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ሲያስቀርላት፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሉብሪካንቶቹ ለውጭ አገራት ኤክስፖርት ሲደረጉ የሚሸጡት በዶላር ስለሆነ የውጭ ምንዛሪ ያስገኝለታል ብለዋል፡፡ ሌላው ጥቅም ደግሞ የምንጠቀመው ቴክኖሎጂ እጅግ የረቀቀና ዘመናዊ በመሆኑ የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የማኔጅመንት ብቃት ሽግግር ይፈጠራል፡፡ በዩኒቨርሲቲ የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች እውቀት ይቀስሙበታል፤ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚጫወተው ከፍተኛ ሚና ሳይዘነጋ በማለት የፋብሪካው መቋቋን ያለውን ጥቅም ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ያልነበረ የአውቶሞቢልና የኢንዱስትሪ ሞተሮች ማለስለሻ ቅባትና ዘይቶች ፋብሪካ መቋቋሙ፣ ሌሎች የውጭ ኢንቨስተሮች በዘርፉ እንዲሳተፉ በር መክፈቱ፣ የጥራት ደረጃው ከፍተኛነት፣ በአገሪቱ ያሉ ዘይትና ቅባቶች ደረጃ መለየት የሚችል እጅግ የረቀቀ ላቦራቶሪ መያዙ፣ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለተማሪዎች መስጠቱ፣… የፋብሪካው መቋቋም ከሚሰጣቸው ጥቅሞች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚሳተፉት አብዛኞቹ የውጭ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን ቁጥር ያነሰው ለምንድነው? ተብለው የተጠየቁት የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር መብራህቱ፤ በዚህ ዘርፍ ከተሰማሩት ባለሀብቶች አብዛኞቹ የውጭ ኢንቨስተሮች መሆናቸው መልካም ነው፡፡ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የማኔጅመንት ሽግግር ያመጣሉ፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ሊያሟሉ የማይችሉትን ነገር ይዘው ይመጣሉ፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በእርግጥ በአብዛኛው የተሰማሩት በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ነው። እነሱን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለማምጣት ቀላል ባይሆንም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ትልቅ ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ፣ እውቀትና የማኔጅመንት ብቃት ይጠይቃል። የንግድና አገልግሎት ዘርፍ ከዚህኛው ጋር ሲነፃፀሩ ቀላል ስለሆኑ ባለሀብቶቹ እዚያው መቆየት ይፈልጋሉ፡፡
መንግሥት ይህ ዘርፍ እንዲስፋፋ ይፈልጋል። ስለዚህ በዘርፉ ለውጭና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚያስፈልገው ድጋፍ ቀላል አይደለም፡፡ ካፒታል፣ እውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣… ማቅረብ ይከብዳል፡፡ ለውጪዎቹ ኢንቨስተሮች የሚደረገው ድጋፍ ከዚህ ጋር ሲተያይ ቀላል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግልጽ ፖሊሲ፣ የመሬት አቅርቦት፣ ምቹ የሥራ አማራጭ፣ ተስማሚ የሥራ ሁኔታ፣… መፍጠር ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የማቀርበው ጥሪ፣ አለ፡፡ በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ቢመጡ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ትርፍ የሚገኝበት ጊዜ ትንሽ ረዘም ያለ ቢሆንም፣ ትርፍ መስጠት ሲጀምር ግን የሚያስገኘው ጥቅም፣ ከንግድና አገልግሎት ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጅ የላቀ ነው፡፡
ሌሎች ጥቅሞችም አሉት፤ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፤ አገርና ሕዝብ ይጠቀማል። ስለዚህ ሚ/ር መ/ቤቱ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሸጋገሩ እየሰራ ነው፡፡ ከውጭ አገር ምግብ በማስመጣት የተሰማሩት እዚሁ ምግብ እንዲያቀነባብሩ፣ በኬሚካል ማስመጣት የተሰማሩት ወደ ኬሚካል ኢንጂነሩንግ እንዲገቡ፣… ጥረቶች ተጀምረዋል፤ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አለ፡፡ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ ሁለቱም ለአገሪቷ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ሁለቱ ተቀናጅተው በሽርክና ቢሰሩ አንደኛው የሌለውን ሌላኛው ይኖረዋል፡፡ ይህ እንደ አንድ አማራጭ ሊታይ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። በአሁኑ ወቅት ሉብታም ለ30 ባለሙያዎችና ለለሌሎች 45 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ወደፊት በመላ አገሪቱ ሱቆችና ማከፋፈያዎች ሲከፈቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ኢ/ር ናዛር ተናግረዋል፡፡  

Read 2179 times