Saturday, 28 June 2014 11:06

መፈንቅለ - እ’ግዜር

Written by  አበባ የሺጥላ
Rate this item
(3 votes)

የአጭር አጭር ልብ ወለድ በግጥም
ከዕለታት  ባንዱ ቀን እንዲህ ሆነ . . .
እባብ ድንገት መነኮሰ
 ቆዳ ቀዶ ማቅ ለበሰ
እንዲህ ሲሰብክ ተደመጠ . . .
  «በመጀመሪያ ፈጣሪ ወደገነት ደጅ ወረደ፤
   ፀሐይን ከነሙቀቷ፣
   ጨረቃን ከነድምቀቷ፣
   ሔዋንንም ከነሳቋ ፈጠረና፤
   ሰማይን በብርሃን አጣፈጠው
   ሌላውን ሁሉ ለ’ርሱ ወስዶ
     ሔዋንን ግን ለአዳም ሰጠው፡፡
ሲሰነብት ይህን ታዘበ
   ጨረቃስ ቀንን ትፈራለች
   ፀሐይም ምሽት ታፍራለ‹
   ሔዋን ግና ወቅት አትመርጥም
     ዕድሜ ልኳን ትስቃለች፡፡»
 ስለዚህ እግዜር ተቆጣ
 ተቆጣና ህግ አወጣ፤
«ከጥጋብ ፍሬ እ‘ንዳትቀምስ ሔዋን በረሀብ ትቀጣ!»
ይሄው ሄዋን ጠግባ አታቅም ያ ‘ርጉም ቀን ከመጣ
አባ እ‘ባብ ይህን አሉ፡፡
   አዳምን ደሞ ይህ አስከፋው
     ነፍሱ ባምላኩ ሻከረ፤
   ንጉሱን ታግሎ ሊጥለው
     ከሄዋን ጋር ተማከረ፤
-‘ምን ተሻለ ሔዋንዋ? ’
-‘ምኑ ሆዴ? ’
-‘ባክሽ  ውዴ ሆዴ አትበይኝ
 ራብሽ  መንፈሴን ናጣት ሆድሽ ሆኜ እየታየኝ’
-‘ዋ! አዱ ታድያ ምን ተሻለን
 እንቢኝ አንል አቅም የለን?’
-‘ባንችማ ዝም አልለውም
 ፊለፊት ለምን አልገጥመውም !!’
-‘አይ! ይቅርብን አዱዬ የሱን ልኬት አናቀውም
ባይሆን ይህችንም እንዳናጣ
ካባ እባብ መክሬ ልምጣ!’
   ቀንም ሆነ፡፡
ሄዋን በህቡ ተማከረች
የመደብ ትግል እናርግ አሏት
የመደብን አተጋገል ካባ እባብ ሰለጠነች
   ማታም ሆነ፡፡
ደረቱ ላይ ነች . . .
ላዳም ሁሉን ነገረችው
አዳም የገባው መሰለ
ግን ምንነቱን ያልፈታችው አንዳች ስጋት ውስጧ አለ ‘
-’አዳምዬ . . .’
-’ወዬ የኔ ዓለም’
-ሞክረኸው ታውቅ ነበር
እኔ ሳልኖር ከዚህ ቀደም?’
‘ምኑን?’
‘የመደብ ትግሉን’
‘ኧረ እኔ ካንቺ ውጪ ከማንም ታግዬ አላውቅ’
‘ከኔ ጋር ደግሞ የት ታገልክ?’
‘  መደባችን ላይ፡፡’
አዲዮስ አዳም ምን ነክቶታል
መጋደምን ከመጋደል መለየት እንኳ ተስኖታል!
       ቀንም ሆነ . . .
አዳምስ ምኑን ተዋደቀ
የሄዋንን ከግዜር ትግል  ለይቶ እንኳ አላወቀ
ሔዋን ለእባብ ሹክ አለችው፤ እባብም መፍትሔ አፈለቀ፡፡
       ማታም ሆነ . . .
ዛሬም ደረቱ ላይ ነች
ግን በስጋት ታየዋለች
‹አዳምዬእ›
‹ወዬ›
-’ማታ ያልኩህን በቃ ተውኩት፤
የመደብ ትግል ሳይሆን የትጥቅ ትግል ነው የፈለግኩት፡፡’
-’ምን ልንታጠቅ ነው ፍቅሬ?’
-’ከከለከለን የዛፍ ፍሬ፡፡’
-’ዝናር የለን በምናችን’
-’እባብ እንዳለው በሆዳችን . . .
ሌት ተነስተን ፀሐይ ከምስራቅ ሳትርቅ
ጫካ ገብተን በሆዳችን እንታጠቅ፡፡’
       ቀንም ሆነ . . .
አዳም ባምላኩ ሸፈተ
ይሄው ታግሎ እንዲጥለው
ቅጠል መሃል ተከተተ፡፡
       ማታም ሆነ . . .
ጦር ከፈታው፤ ድምጽ የፈታው፤
አዳምን መጠራት ረታው፡:
ሽንፈትና  ሞት እርቃን ያስቀራሉ
  አዳም ዕርቃኑን ወረደ
የሽፍታነት ወግ ነውና፤
  ግዛት ለቆ ተሰደደ፡፡
የሰማይ ወፎች ይህን አዩ፤
የሰማይ ወፎች ይህን ሰሙ፤
ውዳሴ አዳማቸውን ትተው
እንዲህ የሚል ሙሾ ቀመሙ . . .
  አዲዮስ አዳም ምን ነካው
  ነጻነትን በሆድ ለካው
  ሆድስ ከእዳሪ በቀር
    ምን ያሳድራል እስቲ አስብ
 ዘር እንኳ እእስኪዘራ
    የሚቋጠር ባባት ወገብ፡፡
  እባብስ በሆዱ ቢታጠቅ፤
  ሆድን ከወገብ ለይቶ አያውቅ፡፡
  አዳም ቅሉ ወገብ ሳለው፤
  ትጥቅን በምግብ መሰለው
  በልቶ መተለቅ ስላየ፤
  በልቶ መታጠቅ አማረው፡፡
ሆድን ከዝናር አተለቀ
ይኸው በሆዱ ታጠቀ
እኛንም ጥሎን ወደቀ፡፡
ያመንናቸው ለሆዳቸው ይተውናል
የተውናቸው ለሆዳቸው እንድናምን ያገዱናል!!!
 ቀንም ሆነ . . . ማታም ሆነ . . .
           (ለ1997 ዓ.ም መታሰቢያ)

Read 3084 times