Saturday, 28 June 2014 11:01

‘ሰፊ ደረት’ና የሜዳሊያ ድርድር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንዴት ያለው ሩቅ ጭንቅ ያለው መንገድ
አሻቅቦ ወጥቶ ወደ ታች መውረድ
የሚሏት የጥንት አባባል አለች፡፡
ሰሞኑን አንዱ ሰውዬ ወጥቶ፣ ወጥቶ ‘ወረደ’ አሉ! ምን ግርም ይልሀል አትሉኝም… ለዚህ ሰውዬ እንደዛ በአገሪቱ ሚዲያዎች ሁሉ እንዳልተጨበጨበለት፣ ‘መወድስ ቅኔ’ አይነት ነገር እንዳልተዥጎደጎደለት…አሁን ሲወድቅ “ጉዱን’ኮ ድሮም አውቅ ነበር…” ባዮች መብዛታችን!
ስሙኝማ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ አገር አንድ ጊዜ ተንሸራታችሁ አትውደቁ እንጂ…አለ አይደል…‘ዘጭ’ ከተባለ በኋላ፣ “እኛ እኮ ድሮም እናውቅ ነበር…” ባይ መአት ነው፡፡ ስለራሳችሁ እናንተ እንኳን ሰምታችሁ የማታውቋቸው ነገሮች ሁሉ ይዘከዝኩላችኋል፡፡ እኔ የምለው ማህበረሰባችን ራሱ እንዲህ ራሳችንን በሌለ መሰላል ላይ ለምናንጠላጥል ሰዎች ምቹ ሆነ ልበል! አንድ ሰው የሆነ ነገር አደረገ ተብሎ አንድ ላይ ብልጭ ካለ አሥራ አምስት ቀን ውስጥ ጽሁፉ የማይነበብበት፣ ድምጹ የማይሰማበት፣ ምስሉ የማይታይበት መድረክ ቢኖር በጣም ጥቂት ነው፡፡
እኔ የምለው…የእውነት እናውራ ከተባለ ቦምብ ተራ በአሮጌ ቆርቆሮ የተሠራ ሜዳልያ ደረቱ ላይ ደርድሮ “አርበኛ ነበርኩ…” እያለ በየዓመቱ አራት ኪሎና ምንሊክ አደባባይ ጦሩን እንደ ሽመል የሚወዘውዙ አሉ ይባላል አይደል እንዴ! የስድሳ ምናምኑ ዓመት ሰው ከሰባ ዓመት በፊት በተደረገ ጦርነት ላይ “አርበኛ ነበርኩ…” ማለት ያው እንደ በቀደሙ ሰውዬ መሆን ማለት አይደል!
ስሙኝማ…የሜዳሊያ ነገር ከተነሳ አይቀር የሆነች ቀልድ ትዝ አለችኝማ! ሌኒን ሆስፒታል ይገባል አሉ። እናላችሁ… ሰዎች ዋናውን ዶክተር “ጓድ ሌኒን ምኑን ነው ያመመው?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ዶክተሩም “ኸረ ምንም አላመመውም!” ይላል፡፡
“ታዲያ ካላመመው ሆስፒታል የገባው ለምንድነው?” ብለው ይጠይቁታል፡፡ ዶክተሩም፣ “ሆስፒታል የገባው የደረት ቀዶ ጥገና ሊካሄድበት ነው፣” ይላቸዋል፡፡ ግራ ይገባቸዋል (ዘንድሮ እኛም ግራ እንደገባን…)
“ካልታመመ ለምንድነው የደረት ቀዶ ጥገና የሚደረግበት? ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ ዶክተሩ ምን ብሎ ቢመልስላቸው ጥሩ ነው…“ደረቱ በሜዳሊያ ስለተሞላ ለተጨማሪ ሜዳሊያዎች ቦታ ለማግኘት ደረቱን ሰፋ ለማድረግ ነው…” ብሏቸው አረፈ፡፡ አሪፍ አይደል!
እናላችሁ…እዚህ አገር እንደ ሰሞኑ ሰውዬ የሚያደርገን መአት ነን፡፡ የቦተሊካ ቦሶቻችን ሲለወጡ “ውስጥ ሆኜ እታገላቸው ነበር፣” የምንል መአት አልነበርን እንዴ! ይሄም ያው እንትን ዩኒቨርሲቲ ወርቅ ሜዳሊያ አጠለቀልኝ፣ እንትን ዩኒቨርሲቲ ፈራንካ ሸለመኝ ማለት አይደል!
እናላችሁ…“ዓለም ያጨበጨበልኝ ነኝ…” “አገር እጥፍ ዘርጋ የሚልልኝ ነኝ…” ምናምን የምንል መአት ነን፡፡ ልጄ ቀን አይጣል እንጂ…
ስሙኝማ…ለምሳሌ አንዱ ተርጉሞ በሌላ ‘ተርጓሚ’ ስም የሚወጡ መፅሐፍት አሉ የሚባል አሉባልታ አለ አይደል እንዴ! (ደግሞ ለአሉባልታ!) ግጥም ተገጥሞላቸው በስማቸው መድረክ ላይ የሚያቀርቡ አሉ ይባል የለም እንዴ!
ይህን ካነሳን አይቀር…የእነሱ ባልሆነ ሥራ የተጨበጨበላቸው ‘ትላልቅ ሰዎች’ ሌሎች አገሮችም አሉላችሁ፡፡
ማሞሩ ሳሙራጎቺ የተባለ የታወቀ ጃፓናዊ ሙዚቃ ቀማሪ ነው፡፡ እንደውም ‘ጃፓናዊው ቢትሆቨን’ ተብሎ ነበር የሚታወቀው፡፡ በተለይ ደግሞ መስማት የተሳነው መሆኑ ዝናውን በጣም ከፍ አድርጎታል፡፡ በአሥር ዓመቱ ቤትሆቨንና ባክን መጫወት የቻለው የ50 ዓመቱ አቀናባሪ ላለፉት ሀያ ዓመታተ በስሙ የወጡት ቅንብሮች በሙሉ የእሱ ሳይሆኑ ሌላ ሰው ቀጥሮ ያሠራቸው መሆኑን በቅርቡ ተናግሯል፡፡
ደግሞላችሁ…ከማይክል ቦልተን ምርጥ ዘፈኖች አንዱና ብዙዎቻችን የምናውቀው በ1991 ያወጣው ‘ላቭ ኢዝ ኤ ወንድርፉል ቲንግ’ የሚለው ቅንብር ነው፡፡ ታዲያላችሁ… ለካስ ይህ ዘፈን የተወሰደው ኤስሊ ብራዘርስ የሚባለው የሙዚቃ ቡድን በ1966 ካወጡት ዘፈን ላይ ነበር፡፡ እናማ…ማይክል ቦልተንን ከሰውት 5.4 ሚሊዮን ዶላር አስፈርደውበታል፡፡
እወቁ የሲ.ኤን.ኤንና የታይም መጽሔት ጸሀፊ ፋሪድ ዘካሪያ እንኳን በቅርቡ ከሌላ ሰው ሥራ ላይ የወሰደውን ጽሁፍ የራሱ አስመስሎ ጽፎ በመገኘቱ ሁለቱም የሚዲያ ተቋማት አግደውት ነበር፡፡ በኋላ ‘በጨዋ ደንብ’ ይቅርታ ጠይቆ አሁን እንደ ቀድሞው ተጽእኖ ፈጣሪ ከሚባሉ የሚዲያ ሰዎች አንዱ ሆኗል።
ስሙኝማ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…በቃ ‘ታሪካዊ ጠላቶቻችን’ የሚመጡበት መንገድ ላይታወቅ ነው! እኛ “ዓለም እየተደነቀብን ነው…” “ቱጃሩ ሁሉ ዓይኖቹ እኛ ላይ ነው…” እያልን ደረታችንን ስንነፋ ጭራሹኑ  ‘የዓለም ጭራ ለመሆን አንድ ፈሪ ናችሁ’ ይሉናል! (እና…ኒጀር የሚሏት አገር ባትኖር ኖሮ ውራ ልንሆን ነበር! እንኳንም ኖረች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ… እነ አምኔስቲ፣ እነ ሲፒጄ፣ እነ ሂዩመን ራይትስ ዋች… ቅብጥርስዮ ‘የሚያበጠለጥሉን’… አለ አይደል… “እድገታችን ስለማይዋጥላቸው” ነው። ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሰዎች ወይ አስተማሪ ይላኩልን፣ ወይ ስኮላርሺፕ ምናምን ይስጡን እንጂ… ምን አደረግናቸውና ነው ዓለም ፊት የሚያሳጡን! (ብቻ፣ ብቻ ቀላል ባቡሩ ይለቅና ያኔ እንዴት ‘ኩም እንደሚሉ’ ይታየኛል! ምን እናድርግ…ቀላል ባቡሩ የመዘመን አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ ይሰማን ጀምሯላ!) የምር ያሳዝናል…ኤርትራ እንኳን የሌለችበት ዝርዝር ውስጥ እንግባ! አሀ…ነገርዬው ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት ሚስቴን አለ አይደል የሚባለው! (‘ሚስት’ የሚባለው በጥሬ ትርጉሙ ሳይሆን በተምሳሌነቱ እንደገባ ግንዛቤ ይያዝልንማ፡፡ ልጄ…ዘንድሮ ከአፍ የወጣ አፋፍ ነዋ!)
የምር ግን…እሺ እነሱስ ‘ቺስታ’ ናቸው ይበሉን…ስንት ዓመት ሙሉ ስትጠራቀም የቆየችው ተከታታይ ‘ሁለት ዲጂቷ’ የት ደረሰች! አሀ…ኬኩ ቢቀር ከፉርኖው ይድረሰና! ይቅርታ፣ ማስተካካያ… ለካስ ፉርኖውም እየጠፋ ነው! ከሁለት ዲጂቷ ድርሻችን ካልተሰጠን ኑሮ ከበደና! ‘ዳያስፖራ’ ወዳጆቻችንን ዶላር መጠየቁም እንደ ድሮ አልመች አለ፡፡
ስመኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ከኢትዮዽያ  አሜሪካ ወዳለ ዘመዱ ይደውላል፡፡ እናላችሁ…
“ውድ የሆነ ስኒከር ላክልኝ” ይለዋል፡፡ የአሜሪካው ወዳጁም… “ምን አልከኝ?” ይላል፡፡ ይኸኛው ድምጹን ከፍ አድርጎ “ውድ የሆነ አሪፍ ስኒከር ላክልኝ” ይለዋል፡፡ አሜሪካ ያለው ሰው አሁንም፣  “ምንድነው ይሄ ስልክ! የምትለው ምንም አይሰማኝም” ይላል፡፡
ይሄን ጊዜ ኦፕሬተሯ ጣልቃ ትገባና “ውድ የሆነ ስኒከር ጫማ ላክልኝ ነው የሚልህ” ትለዋለች። አሜሪካ ያለው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው…“ታዲያ ከሰማሽው አንቺ አትገዥለትም!” ብሎ ስልኩን ጠረቀመላችሁ፡፡
እሷስ የምን ጥልቅ ብዬ ናት! የስልክ ኦፕሬተር ነች እንጂ ማን ‘ቱርጁማን’ አደረጋት! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እንደ ሰሞኑ ሰውዬ በተለያየ መንገድ የሌለ ወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ መአት ነው፡፡ አሜሪካ ፓርኪንግ የሚሠራበት ቦታ መኪና ተደግፎ የተነሳው ፎቶ ላይ “ሰከንድ ሀንድ መኪና መሸጫ ድርጅቴ ነው” እያለ ሲያሞኘን የኖረ መአት አይደል እንዴ!
ስሙኝማ… ይሄ የባለስልጣን (ባለስልጣን ሁሉ እኩል ስላልተፈጠረ “የባለጊዜ” ማለቱ ይሻል ይሆን!) ስም እየጠሩ መሸወድ የተለያየ ቦታ የሚገጥማችሁ ነው፡፡ “ከእንትን ሀላፊ ጋር በእናቴ በኩል እንዛመዳለን…” ይላችኋል፡፡ እናተም “እናትህ አገራቸው እንትን፣ ሰውየው ደግሞ አገሩ እንትን… እንዴት ነው የምታዘመዱት?” ሲባል… “አንተ ነህ እኔ የምናውቀው!” ሊላችሁ ይችላል፡፡ ለነገሩ እኛም’ኮ የሆነ ነገር ሲቸግረን፣ ማለፊያ ማግደሚያው ሲጠፋን… “እባክህ፣ የምታወቅው ባለስልጣን ነገር ይኖራል?” ለምዶብናል፡፡ ግራ ገባና! ዋናው ጥያቄ “ምን ታውቃለህ?” ሳይሆን “ማንን ታውቃለህ?” በሆነበት ዘመን ምን እናድርግ!
ደግሞላችሁ…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ባለስልጣን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ በቀጥታ አይመጡም፡፡ የሆኑ ‘ሎቢዪስት’ ነገሮች አሏቸው፡፡ እናማ… “ለምን እንትናን አታናግረውም፣ ከሥራ አስኪያጁ ጋር አብረው አይደል እንዴ የሚጠጡት!” ይባላል፡፡
ታዲያላችሁ…የዘንድሮ ነገራችን ሁሉ “ቀይ ምንጣፍ አንጥፉልኝ…” “ኒሻን ደርድሩልኝ…” ምናምን ለሚሉ የተመቸ ሆኗል፡፡ ጉዳችንን “ቤቱ ይቁጠረው…” ማለት ይሄኔ ነው፡፡
እናማ…እንደ ሌኒን ቀልድ ለተጨማሪ ሜዳሊያዎች ደረትን ማስፋት አይነት ልምድን ካላጠፋን በስተቀር እንዲሁ ሁሉም የሚጫወትብን ዶሚኖ ምናምን ሆነን መቅረታችን ነው፡፡
ዶሚኖ ከመሆን አንድዬ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3614 times