Saturday, 28 June 2014 10:33

አይዟችሁ፤ “ስንዴው ከሳምንት በኋላ ጂቡቲ ይደርሳል”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

መንግስት፣ በየጊዜው “የምስራች” እያለ የሚነግረንን ወሬ ማመን ቢቀርብን ይሻላል። ግን፣ መስማትና ማመን ለምዶብናል፡፡ መልካም ነገር ስለምንመኝ ይሆን፤ “ለማመን” የምንቸኩለው? መንግስት አዲስ ወሬ ሲያበስረን እንሰማዋለን፤ “የዛሬውስ እውነት ሊሆን ይችላል” ብለን እናምነዋለን፡፡ ሌላው ይቅርና፤ “ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ሲለን እንኳ አምነነዋል። በየጎዳናው የምናየው ድህነትና በየጓዳው የሚያጋጥመን የኑሮ ችግር በጣም ከባድና አሳዛኝ እንደሆነ ብናውቅም፤ የምስራች ሲበሰር ቶሎ ለማመን ዝግጁ ነን።
ምን ዋጋ አለው? ዳቦ ቤቶች በስንዴ እጥረት እንደ ዘንድሮ ተቸግረው አያውቁም፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ገደማ ነው ነገሩ የተጀመረው። “አዝመራው ጥሩ ምርት ይዟል” ተባለ በደፈናው፡፡ ግን በዚሁ ተደፋፍኖ አልቀረም፡፡ በእህል አይነት እየተዘረዘረ፤ ከነመጠኑ በኩንታል እየተጠቀሰ  “ከፍተኛ የእህል ምርት ይሰበሰባል” የሚል የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርት ወጣ። ይህን ሪፖርት ተከትሎ፤ የእህል ንግድ ድርጅት መግለጫ ለመስጠት ቀናት አልፈጀበትም። ስንዴ ከውጭ ለመግዛት ነው ወራት የሚፈጅበት፡፡
የእህል ገበያ ድርጅት ሃላፊዎች፤ የእህል ምርት በብዛት እንደሚሰበሰብ በመጥቀስ ታህሳስ ወር ላይ በሰጡት መግለጫ፤ የእህል ዋጋ አሽቆልቁሎ ገበሬዎች ተጎጂ እንዳይሆኑ እንሰጋለን በማለት ጭንቀታቸውን አስረድተዋል።
እንዲያውም፣ የእህል ዋጋ ገና ካሁኑ የመቀነስ አዝማሚያ ጀማምሮታል በማለት የተናገሩት የድርጅቱ ሃላፊዎች፣ ለምሳሌ የጤፍ ዋጋ በኩንታል 20 ብር ቀንሷል በማለት ማስረጃ አቅርበዋል፡፡ የአንድ ኪሎ የጤፍ ዋጋ ላይ የሃያ ሳንቲም ቅናሽ መታየቱ እንደ ትልቅ ነገር መወራቱ አያስገርምም? ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ በየአመቱ ከታህሳስና ከጥር ወር በኋላ የእህል ዋጋ እንደሚጨምር እንዴት ይዘነጉታል? ለዚያውም “የእህል ንግድ” ላይ የተሰማሩ ሃላፊዎች ናቸው!
ለማንኛውም የእነሱ ጭንቀት፣ የእህል ምርት “ተትረፍርፎ” ገበያ ላይ ዋጋው እንዳይወድቅ ነው። ደግነቱ፤ ችግር የለም፡፡ ችግር አይፈጠርም። የእህል ንግድ ድርጅት አለልን፡፡  ሃላፊዎቹ፤ እህል በመግዛትና በመሰብሰብ በገበያ ላይ ዋጋው እንዳያሽቆለቁል ለማድረግ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል - በታህሳስ ወር።
በእርግጥ እንደዚህ ቢያስቡ አይገርምም። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች ሲታዩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ስንዴ በተለይ ባለፉት ስድስት አመታት በእጅጉ ጨምሯል። በ2001 ዓ.ም የስንዴ ምርት 25 ሚሊዮን ኩንታል፤ በ2004 ዓ.ም ደግሞ 29 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር ይገልፃል የባለስልጣኑ መረጃ። አምና በከፍተኛ የምርት እድገት 34 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደተሰበሰበ አመታዊው የባለስልጣኑ ሪፖርት ያመለክታል። ዘንድሮ ደግሞ አርባ ሚሊዮን ኩንታል።
ሪፖርቶቹ እውነተኛ ከሆኑ፣ የስንዴ ምርት በሁለት አመታት ውስጥ በ11 ሚሊዮን ኩንታል ጨምሯል ማለት ነው። የ45% እድገት ቀላል አይደለም፡፡ አስደናቂ ነው፡፡ “ምርት ተትረፈረፈ” ያስብላል፡፡
ግንቦት 20 በሚከበርበት እለት ደግሞ ተጨማሪ ትልቅ ስኬት ተበሰረ፡፡ ለተከታታይ አመታት በተመዘገበው የግብርና እድገት ዘንድሮ ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች በማለት ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡ ድንቅ ነው፡፡
የእህል ምርት እየጨመረ መምጣቱ አይካድም፡፡ ጥሩ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ብሎ መናገር ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ያለ መንግስት ድጐማ ኑሯቸውን መቀጠል የማይችሉ 6.5 ሚሊዮን ችግረኛ የገጠር ነዋሪዎች አሉ፡፡ ያለ ውጭ እርዳታ በህይወት መቆየት የማይችሉ 6.5 ሚሊዮን ረሃብተኞች መኖራቸውን ደግሞ ዩኤን ገልጿል፡፡ በድምሩ 13 ሚሊዮን
ተረጂዎች ያሉባት አገር “በእህል ምርት ራሷን ችላለች” ሲባል ምን ትርጉም አለው?
የመንግስት ብስራት ግን በዚህ አላቆመም፡፡ የስንዴ ምርት በእጅጉ እያደገ መሆኑን በመጥቀስ፤ “ኤክስፖርት ይደረጋል” በማለት የመንግስት ባለስልጣናት ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ የሆይ ሆይታው ተከፋይ የሆኑት የእህል ንግድ ድርጅት የስራ ሃላፊዎች፤ ከዚህ “ብስራት እና “ስኬት” የተለየ ነገር አልተናገሩም፡፡ እንዲያውም የተወሰነ ያህል ቁጥብነት አሳይተዋል፡፡ ባለፈው አመት ምን እንደሰሩና ለዘንድሮ ምን እንዳቀዱ የድርጅቱ የስራ ሃላፊዎች ሲዘረዝሩ እንመልከት፡፡
በ2005 ዓ.ም ወደ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ገደማ ስንዴ በ4.5 ቢሊዮን ብር ከውጭ ሀገር በመግዛት ገበያውን ለማረጋጋት እንደተቻለ ለዋልታ የገለፁት ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ብርሃኑ ሃይሉ፤ ዘንድሮ በቂ ስንዴ ስለተመረተ ከውጭ አገር ገዝተን አናስመጣም አላሉም፡፡ ግን እንደሌላው ጊዜ በፍጥነት ስንዴ ለመግዛትም ውሳኔ አላስተላለፉም።    
ከ2005 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ2006 ዓ.ም የሚሰበሰበው የስንዴ ምርት በ4 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚበልጥ የተናገሩት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ፤ የስንዴ እጥረትንና የዋጋ ንረትን ለማቃለል ታስቦ ከውጭ እየተገዛ የሚመጣው ስንዴ ዘንድሮ በግማሽ እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡ አምና ከውጭ ተገዝቶ የመጣው ስንዴ ከ5 ኩንታል በላይ ስለሆነ ዘንድሮ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡
 “ዘንድሮ ከውጭ ገበያ የሚገዛው ስንዴ በግማሽ እንደሚቀነስ ነው ዋና ስራ አስኪያጁ ያመላከቱት” ብሏል ፋናቢሲ በታህሳስ 28 ቀን ዘገባው።
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ሆይሆይታ እና የእህል ንግድ ድርጅት ሃላፊዎች ውሳኔ ውሎ አድሮ መጨረሻው አላማረም፡፡
ገና የካቲት ወር ላይ ነው በስንዴ እጥረት የአገሪቱ ዳቦ ቤቶች መቸገር የጀመሩት፡፡ እንደታሰበው በ2.5 ሚሊዮን ኩንታል ግዢ ብቻ የስንዴ እጥረትን ማቃለል እንደማይቻል በግልጽ እየታየ የመጣው፤ ስራ ፈትተው በራቸውን የሚዘጉ ዳቦ ቦቶቹ ሲበራከቱ ነው፡፡
ለዚህም ነው የኋላ ኋላ አራት ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት የተወሰነው፡፡ ለነገሩ ቀደም ሲል የታሰበው 2.5 ሚ ኩንታል ስንዴ፤ ቶሎ ተገዝቶ አልመጣም። ለጊዜው በቂ ስንዴ ተመርቷል ስለተባለ ከውጭ አገር ገዝቶ ማስመጣት የሚያስቸኩል ጉዳይ አልሆነባቸውም፡፡
አሁን እንደምታዩት፤ የስንዴ እጥረት አፍጥጦ ወጥቷል፡፡ የመንግስት እና የእህል ንግድ ድርጅት ሆይሆይታ በመጨረሻ “ዳቦ አልቋል” ወደሚል ችግር አደረሰን፡፡  ነገር ግን የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ የድርጅቱ ሃላፊዎች በተሳሳተ ግምት የስንዴ እጥረት እንደፈጠሩና ጥፋት እንደሰሩ አምነው አይቀበሉም፡፡
“የስንዴ እጥረት ተፈጠረ፤ ዱቄት ጠፋ፣ ዳቦ አለቀ” የሚል ቅሬታ ሲቀርብባቸው፤ “የአቅርቦት እጥረት የለም፤ ችግሩ የስርጭት ነው” የምትል የተለመደች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡
የስርጭት ችግርምኮ የነሱ ጥፋት ነው፡፡ ግን ይሄንን ለማሰብ ጊዜ የላቸውም። በወሬ ብቻ የስንዴ እጥረትን የሚያስወግዱ ስለሚመስላቸው፤ ሌላ ነገር አይታያቸውም፡፡ “የአቅርቦት እጥረት የለም” የሚል ወሬ አላዋጣ ሲል ነው፤ የተስፋ ቃል መናገር የሚጀምሩት፡፡ “አይዟችሁ፡፡ ከሳምንት በኋላ ስንዴው ጅቡቲ ይደርሳል” በማለት በተስፋ እንድንጠብቅ ሰሞኑን ነግረውናል፡፡

Read 3306 times