Saturday, 28 June 2014 10:41

ኢትዮጵያና ግብጽ በ7 ነጥቦች ላይ ተስማሙ

Written by 
Rate this item
(25 votes)

      ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ከትናንት በስቲያ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ከተማ ተገናኝተው አዲስ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የተዘገበ ሲሆን፤ የጋራ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ለመስራትና ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅቶችን በመጀመር በሶስት ወራት ውስጥ የጋራ ስብሰባ ለማድረግ መስማማታቸውን የግብጽ መንግስት ገለፀ፡፡
የሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት ስኬታማ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ የአባይ ወንዝን በሚመለከት የግብጽ ህልውናና የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል፡፡ በአባይ ወንዝ እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መሪዎቹ ተወያይተው በ7 ነጥቦች እንደተስማሙ ሚኒስትሮቹ ገልፀው፤ ለሁለቱ አገራት ጥቅም የሚበጀውን የውይይትና የትብብር መርህ እናከብራለን የሚል ነጥብ በቀዳሚነት ጠቅሰዋል፡፡
እያደገ የመጣውን የውሃ ፍላጎት ለማሟላትና የውሃ እጥረትን ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ አቅም የሚያስገኙ ክፍለ አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን ለመዘርጋት ቅድሚያ እንሰጣለን ብለው እንደተስማሙም ሚኒስትሮቹ ተናግረዋል፡፡
ሶስተኛው የስምምነት ነጥብ፣ የአለም አቀፍ ህግ መርሆዎችን እናስከብራለን የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ሁለቱ አገራት “የአለም አቀፍ ህግ መርህ” በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያየ ትርጓሜ በመስጠት እንደሚወዛገቡ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ እልባት የሚሰጥ አዲስ ሃሳብ አልመጣም፡፡ በግብጽ በኩል፤ ከ90 አመት በፊት ግብጽና እንግሊዝ እንዲሁም ከ50 ዓመታት በፊት ሱዳንና ግብጽ የተፈራረሟቸው ስምምነቶች መከበር አለባቸው የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ የአባይ ተፋሰስ አገራትን ያላሳተፉ የድሮ ስምምነቶች ተቀባይነት የላቸውም፤ የአባይ ተፋሰስ አገራት የፈረሙበት አዲስ ውል ሊከበር ይገባል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡
ጠ/ሚ ሃይለማርያም እና ፕ/ት አልሲሲ የተስማሙበት አራተኛው ነጥብ፤ ሱዳንን ጨምሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተቋቋሙት የሶስትዮሽ ኮሚቴን የሚመለከት ነው፡፡ በግብጽ ተቃውሞ ሳቢያ ኮሚቴው ስራ እንደቆመ የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን የኮሚቴውን ስራ በአፋጣኝ መልሶ ለማስጀመር ተስማምተናል ሲሉ ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተናግረዋል፡፡  አለማቀፍ የባለሙያዎች ኮሚቴ ያቀረባቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ለማስተግበር እንዲሁም በቀጣይ የግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ በሚካሄድ ጥናት የሚገኙ ውጤቶችን በጸጋ ለመቀበል መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
አምስተኛው ነጥብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ሃላፊነትን የሚጥል ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ በግብጽ የውሃ አጠቃቀም ላይ ማናቸውም  ችግር እንዳይፈጠር  በፅናት እጥራለሁ ይላል፡፡ የግብጽ መንግስት ላይ ሃላፊነትን የሚጥለው 6ኛ ነጥብ ደግሞ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት ከግምት ውስጥ ከሚያስገባ ገንቢ ውይይት ላለማፈንገጥ ቃል እገባለሁ የሚል ነው፡፡
ሱዳንን በሚጨምረው የሦስትዮሽ ኮሚቴ ስር በቅንነት ለመስራትም ሁለቱ መሪዎች ተስማምተዋል፤ በ7ኛው ነጥብ፡፡
የሁለቱ መሪዎች ውይይት ግልጽነት የተመላበት ነበር ያሉት የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሾክሪ፤ ውይይቱና ስምምነቱ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት ትልቅ ስፍራ አለው፤ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ከፍተናል ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ በግብጽ የውሃ አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳይፈጥር ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ትችላለች ተብለው የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የግድቡ ዲዛይን የተሰራው ምንም አይነት ችግር ሊያስከትል በማይችል መልኩ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ አገራቱ በተስማሙት መሰረት በጉዳዮቹ ዙሪያ በጋራ መወያየትና መፍትሄ ማበጀት ይችላሉ ብለዋል፡፡

Read 5829 times