Saturday, 21 June 2014 14:56

የመስቀሉ ቋሚ እና አግዳሚ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

        በአጠቃላይ ጥበበኞች ናቸው - የዚያ ሰፈር ልጆች፡፡ ጥበበኞች እና ድሆች:: ድሮም ጥበበኞች ነበሩ ለማለት ግን አይቻልም፡፡ ለአንድ ሰሞን ነው ንሸጣው የሚጠናወታቸው፡፡ ያ ሰሞን ሲያልፍ ወደ ሌላ ተቀይረው ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም ነገር መሆን ይችላሉ፤ ንሸጣው ሲጠናወታቸው፡፡ ከዚህ በፊት የፎርጅድ ሰራተኛ ሆነው ነበር፡፡ በተቆረጠ ድንች ማህተም ሲመቱ ይውሉ ነበር፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፎርጅድ የሀኪም ወረቀት ሲሰሩ ከርመው… የዩኒቨርሲቲ መመረቂያ ወረቀት ለራሳቸው መስራት ሲያቅታቸው ፊልዳቸውን ቀየሩ፡፡ የታክሲ ተራ አስከባሪ እንዳይሆኑ አቅም ያንሳቸዋል፡፡ ሱስና ምናምንቴ አጥቅቷቸዋል፡፡
ከፎርጅዱ በኋላ ተደራጅተው ኮብል ስቶን ለማንጠፍ ሞክረው ነበር፡፡ ከገጠር እንደመጡት ልጆች አቅምም ሆነ አላማ ሲያጥራቸው ወደ ፊልም ፅሁፍ ተሸጋገሩ፡፡ አንድ ላይ ተደራጅተው አንድ ስክሪፕት ፃፉ፡፡ አንድ እስክሪብቶ እየተዋዋሱ፡፡ መሸጡ እንደ መፃፍ ቀላል አልሆነላቸውም፡፡ ስክሪፕቱን ወደ ቴአትር በመቀየር ላይ እንዳሉ አዲስ ሀሳብ ብልጭ አለላቸው። “ለምን የህልም ጥበበኛ አንሆንም?” ተባባሉ፡፡ ስክሪፕቱንና ትያትሩን ወዲያ ወርውረው የሙሉ ሰአት ህልመኛ ሆኑ፡፡
ገጣሚና ሴተኛ አዳሪ የሚበዛበት የተጨቆነ ሰፈር ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ በከተማው ዙሪያ የተዘረጉት አዳዲሶቹ “ልማታዊ” መንገዶች ወደ እነሱ ሰፈር አቅራቢያ ደርሰው አያውቁም፡፡ በእነሱ ሰፈር ውስጥ ከመኪና የበለጠ የጋማ ከብት ሲዘዋወር ይታያል። የጋማ ከብትና የጋማ ሰው ተስማምቶ ይኖራል፡፡ ከባለሱቆቹ በስተቀር ማንም ቋሚ ገቢ ያለው የለም፡፡
ስለዚህ ህልመኛ መሆን በጣም የሚያዋጣ የስራ ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ህልመኛና እብድ በየስርቻው ሲያልጎመጉም ይታያል፡፡ በዚህ ሰፈር ውስጥ ብዙ የፉክክር ፍላጎት የለም፡፡ ፉክክራቸው በተጨባጭ ነገሮች ላይ ሳይሆን በህልም ላይ ብቻ ያጠነጥናል፡፡ ህልም በመፍጠር እና በማባዛት ጊዜያቸውን ይገፋሉ፡፡
አንዱ የጀመረውን ህልም ሌላው ተቀብሎ፣ ቀጥሎበት ያቀብላል፡፡ ህልምን ተውሶ አብሮ ሲተኛት አድሮ ለአበደረው ሰው ይመልሳል፡፡ የኪራይ ክፍያ የለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ከሚል ወንጀል ሁሉም ነፃ ናቸው፡፡ በህልሙ የፈጠራትን ሴት ሌላው ጠልፎ ሲያገባ… የተዘረፈው በሰርጉ ላይ ተገኝቶ ያጨበጭባል። አንድ ህልም አግብቶ አብሮ ማርጀት ሞኝነት ነው፡፡ አግባብቷት ይሰነብትና ይፈታታል፡፡ ከህልም ልጅ ማፍራት አይቻልም፡፡
በግጥም ላይ ግጥም ይፈጥራሉ፡፡ በአፋቸው ያወሩታል፡፡ የፈጠሩትን ግጥም ለመፃፍ የሚያበቃ አቅምም ሆነ ምክኒያት የላቸውም፡፡ ህልምን ግጥም ማድረግ ራሱ መግደል እንደሆነ ማመን ጀምረዋል። መፃፍ ግን የማይበሰብስ አፅም መፍጠር ነው፡፡ ማሳተም አፅምን ወደ ሐውልት ቀይሮ እንደ ማምለክ ነው፡፡ ሀጢአት ነው! ህልም ማየት እንዲችሉ ብዙ ነገሮችን ያጨሳሉ፡፡ የሚያጨሱትን ነገር የሚለኩሱት በክብሪት ሳይሆን ከነብሳቸው በተቀጣጠለ እሳት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ይጠጣሉ፡፡ የሚጠጡትን ነገር የሚበርዙት በአምቦ ውሃ ሳይሆን በደማቸው ነው፡፡ የህልም ጥበበኞች ናቸው፡፡
ገፅ እና ባህሪያቸውን መለየት አይቻልም፡፡ ከህልም ሱሰኝነት የተነሳ ገፅታቸው ሁሉ ወደ ቅዠት ተቀይሯል፡፡ ባልተከፈተ በር ወጥተው ይሄዳሉ፡፡ እንደ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ይሾልካሉ፡፡ መናፍስት መሆን እና አለመሆናቸውን እራሳቸውም ለማወቅ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሰይጣን ሆነው ሳለ የሰይጣን ስም ሲጠራ በርግገው ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ህልም ማየት እስከቻሉ ድረስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖራቸው አይገዳቸውም፡፡
ህልም ጎታታ ነው፡፡ ጎታታ ነው ብለው አንቀላፍተው ሲጠብቁት ግን ህልመኛውን ቀድሞት ይጓዛል፡፡ ህልመኛውን ቀድሞ ያደገ የህልም ዝርያ መፈጠሩ በዚያን ሰሞን ሲወራ ነበር አሉ፡፡ ወሬውን ማን እንዳወራው፣ ማን ለወሬው ምክንያት የሆነውን ገድል እንደፈፀመው ግን አይታወቅም፡፡ በህልም የተከናወነ ድርጊትን በእውነተኛው አለም ላይ እንደተከናወነ አድርጎ መተረክም ለዚያ ሰፈር ልጆች ከሀጢያተኝነት ያስፈርጃል፡፡
እናም ይህ ማንነቱ ያልተጠቀሰ ህልመኛ ከፍተኛ ደሀ በነበረበት ጊዜ ያየውን ህልም ነው ጉድ ተብሎ የተወራለት፡፡ አሁን ላይ ይኸ ህልመኛ ከድህነቱም ወጥቷል፡፡ ህልም ማየትንም እርግፍ አድርጎ ትቷል፡፡ ታሪኩ እንደሚከተለው ነው፡-
የእንቅልፍ ቀጠሮ ቢደርስበትም ወደ ፍላጎቱ መድረሻውን መኝታ በማፈላለግ እኩለ ሌሊት ደረሰ። መኝታ ማፈላለግ ብቻም ወደ ግቡ አያደርሰውም። መኝታው ላይ ይዞት የሚያድረው ህልምም ግዴታ ማግኘት አለበት፡፡ ለህልም ስቃይ ማስታገሻ የሚሆን ቁራሽ እንጀራ ለማግኘት በመንደሩ ጉራንጉር እንደ መጥፎ ወሬ ተሽከረከረ፡፡ ቢንከራተትም ህልም የሚያጎርሰው ግን አጣ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ተቀምጦ ለመነ፡፡ ህልምና መኝታ አጥቶ እንዳፈጠጠ አደረ ዋለ፡፡ በዚህ አኳኋን ሳምንታት ዘለቀ፡፡
ከሰው ላይ የተሰረቀ ህልም ይዞ ለመሸጥ ሲሞክር የዋለ የሰፈራቸው ላቦሮ… የሱ ስቃይ በሆነ ተአምር ገብቶት… ወይንም የማይሸጥ ህልም፣ ሸክም ስለሆነበት… ከዚያው ላይ ቀንሶ ሰጠው፡፡ ህልም የተራበው ደሀም ተቀበለው፡፡ ተቀብሎ ጎረሰው፡፡ ጎረሰውና በተቀመጠበት ፍንግል ብሎ ተኛ፡፡
ህልሙ ማስጠንቀቂያ ቢጤ አለው “ያለ ፍቃድ አባዘቶ መሸጥ.. አይቻልም፡፡ እድሜያቸው ከአስራ ስምንት በታች የሆነ ህልመኞች አይመልከቱት…” ወዘተ… ወደ ህልሙ ለመግባት በመቸኮሉ ማስፈራሪያውን ችላ ብሎ አለፈው፡፡ ከማስጠንቀቂያው በኋላ እንደ ማብሪያ እና ማጥፊያ የመሰለ ጉጥ እንደ ሰመመን በተዘጋው አይኑ ውስጥ ተደቀነበት፡፡ ሳይጫነው ቢጠብቅም በደንብ እንቅልፍ አልወስድ ስላለው ፈራ ተባ እያለ ተጫነው፡፡
ህልሙ ጀመረ፡፡ የተዋንያኖቹ ስም ዝርዝር ይወጣል ብሎ አስቦ ነበር፡፡ አልወጣም፡፡ መጀመሪያ የታየው የራሱ ምስል ነው፡፡ “እኔ ተኝቼ እያለምኩ እንዴት ቆሜ ስተውን ታየኝ” ብሎ ግር ሊሰኝ ሲል ነገሩ ተገለፀለት። ተኝቶ በህልሙ ውስጥ እየታየው ያለው ማንነቱ ወደፊት እሱ በምኞቱ ሊሆን የሚፈልገውን ሰው ነው። ደሀው እሱነቱ ተኝቶ፣ ሀብታሙ ምኞቱ ነቅቷል ማለት ነው፡፡
እናም ደሀው ህልመኛ የሀብታሙን ህይወት መመልከት ጀመረ፡፡ ይኼኛው ሜዳ ላይ ተኝቶ እየታዘበ፣ ያኛው ከንጉሳዊ አልጋው ላይ ተነስቶ እያፋሸከ በመንጠራራት ላይ ነው፡፡ አብራው የተኛችው ልጃገረድ ፀጉሯ እንጂ ፊቷ ተከልሏል፡፡ ሃብታምየው ለጥቂት ሰከንዶች ልጃገረዲቷን  በጥሞና ተመለከታት፡፡ አስተያየቱ ላይ ሃዘኔታ፣ መቆርቆርና የአለኝታነት ስሜት ይነበባል፡፡ ደሀው ህልመኛ ሚስቱ መሆን አለባት አለ፡፡ በጨለማ ውስጥ ተቀምጦ ፊልም እንደሚያይ ሰው ነው ትዕይንቱን የሚከታተለው። ተቀምጦ ሳይሆን ተጋድሞ የሚያድርበት ጨለማ ግን ህይወቱ እንደሆነ ይታወቀዋል፡፡ በጨለማው ላይ ፊልሙ ሲያልቅም መብራቱ እንደማይበራ በእንቅልፍ ልቡም ቢሆን አልተጋረደበትም፡፡
ሀብታሙ እሱነቱ ሚስቱን ሲታዘባት ቆይቶ.. እንዳይቀሰቅሳት ተጠንቅቆ ወደ ባኞ ቤት ገባ፡፡ እንደዚህ አይነት ስፋት ያለው ባኞ ቤት እንዳለ ህልም ተመልካቹ አያውቅም ነበር፡፡ የብዙ ሰዎችን የመኖሪያ ሰፈር ያክላል፡፡  ልክ እንደ አልጋው ንጉሳዊ ስፋት አለው፡፡ በሀብታሙ ሰው ህይወት ደሀው ህልመኛ ለምን የክብሪት ሳጥን የሚያክል ጥበት እንደተሰማው አልገባውም፡፡ የዚያኛው ህይወት ከደሀው ህልመኛ ጋር የሚገናኘው በእንቅልፍና ቅዠት ብቻ አለመሆኑ ታወቀው፡፡
ሀብታሙ ፒጃማውን በመስቀያው ላይ ሲያደርግ፣ ደሀው በተኛበት ሆኖ ብርድ አሸማቀቀው። በተጋደመበት መስቀል ላይ የተቸነከረ መሰለው፡፡ ያኛው ሙቅ ሻወሩ ውስጥ ገብቶ በሚሰማው ሙቀት፣ ደሀው እንደ በረዶ ዝናብ እያንዘፈዘፈ ፈጀው፡፡
እንዴት አይቶት የማያውቀውን ነገር ለማለም እንደደፈረ ሊገባው አይችልም፡፡ ከሻወሩ ውሃ የሚወጣውን ሙቀት የሚያጣጥመው ሃብታሙ ነው፤ ደሀው ህልመኛ ከውሃው የሚመነጨውን ደስታ መጋራት አይችልም፡፡ ሀዘኑ ግን ይሰማዋል፡፡ ውሃው ሲፋጅ የሚሰማው ህልመኛውን ነው፡፡ ከዚያኛው ገላ ላይ እየታጠበ የሚነሳው እድፍና ቆሻሻ በተኛው ህልመኛ ላይ ተላከከበት፡፡ ሀብታሙ ከሻወሩ ነቅቶ ሲወጣ ይኼኛው በተኛበት ድካም ይጫጫነዋል፡፡
ሃብታሙ ከሻወሩ ወጥቶ ቲሸርት እና ቁምጣ አድርጐ ከመኝታ ክፍሉ ወጣ፡፡ ኮሪደሩ ላይ ያለውን አንዱን ክፍል ከፍቶ ገባ፡፡ ጂምናዚየሙ የሚገኝበት ክፍል ነው፡፡ ክብደቶቹን ማንሳት ጀመረ። የሚያነሳቸው ክብደቶች እንደ እፉዬ ገላ ቀልለው የሚበንኑ ይመስላሉ፡፡ ፊኛ እንጂ ብረት የሚያንከበክብ አይመስልም፡፡ ተኝቶ ለሚመለከተው ህልመኛ ግን ብረቱ ብረት ሆኖ ሲደፈጥጠው ይሰማዋል፡፡ የሀብታሙ ጡንቻ በእስፖርቱ የሚዳብረውን ያህል የደሀው ህልመኛ ጡንቻ ሲሟሽሽ ይሰማዋል፡፡
ከእስፖርቱ በኋላ ሻወር ለመውሰድ በድጋሚ ባኞ ቤት ገባ፡፡ ታጥቦ ሲወጣ ወደ ተራራ መሳዩ ቁምሳጥን ሄዶ በጥንቃቄ ልብሶቹን መረጠ፡፡ ንፁህ ሱፍ ሰማያዊ ቀለም ያለው፡፡ ከነጮች የነጣ ሸሚዝ፡፡ ክራባቱን አጥብቆ ሲያስር…የተኛው ህልመኛ የመታነቅ ስሜት ተሰማው፡፡ ባለ ክራባቱ በጭካኔ ክራባቱን የበለጠ አጠበቀ፡፡ በጠበቀ ቁጥር የላላ የተፍታታ ንቃት ይሰማዋል፡፡ ደሃውን እያፈነው እንደሆነ የሚያውቅ ይመስላል፡፡ ፈገግታው የጭካኔ ነው፡፡
ደረጃውን ሲወርድ እርምጃው እና ክብደቱ የሚያርፈው በእንቅልፋሙ ደሃ አናት ላይ እንደሆነ የሚያውቅ ይመስላል፡፡ ባለሁለት ፎቅ የሆነውን ደረጃ ወርዶ የተንጣለለው ሳሎን ግርጌ ወደሚገኘው ማዕድ ቤት ገባ፡፡ ሰራተኛው ያሰናዳችው ገበታ ላይ ተሰይሞ ቁርስ ማድረግ ጀመረ፡፡ አጐራረሱ ጤና የተላበሰ ነው፡፡ ህልመኛው በእያንዳንዱ የሀብታሙ ጉርሻ እድሜውን ከሆዱ ውስጥ እየቀነሰበት መሆኑ ተሰማው፡፡ ስቃዩን አልቻለውም፡፡ መንቃት ቢፈልግም ህልምን እንደ ፊልም ጥሎ መውጣት አይቻልም፡፡ በልቶ ሲጨርስ ትልቁን ቦርሳውን በእጁ አንጠልጥሎ ወደ ውሎው ወጣ፡፡ መኪናዋ፤ በማቆሚያ ስፍራ ጭራዋን እንደ ውሻ እየቆላች ጠበቀችው፡፡ ተሳፈራት፡፡ ረገጣት፡፡ ተፈተለከች፡፡
…ቀኑን ሙሉ ከሃብታሙ ጋር በህልሙ ሲንከራተት የዋለው ደሀ …እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት ድረስ ነፃ ለመውጣት መቆየት እንዳለበት አልገመተም ነበር። ያኛው ከበላው ክትፎ ያተረፈው የኮሶ ትሉን ነው፡፡ ያኛው ከጠጣው ውስኪ ያተረፈው የጉበት መጠበሱን ነው፡፡ ያኛው ከሚስቱ ጋር ካሳለፋቸው የፍቅር አመታት ደሃው ህልመኛ ያተረፈው በሁለቱም ልብ ውስጥ ያለውን የውሸት ሸክም ነው፡፡ ሁለቱ ከፈፀሙት ወሲብ ያተረፈው ድካሙን ነው፤ ወይንም ጥንቃቄ ከሌለው ወሲባቸው የበሽታ ስጋቱን፡፡
ከአልጋው ትግል በኋላ ሃብታሙ ለመተኛት ብዙ ቢያመነታም እንቅልፍ ጣለው፡፡ እንቅልፍ ሊጥለው ሲል ፈገግ ብሎ በአይኑ ላይ የተደቀነችውን ጉጥ ተጫናት፡፡ እንቅልፍ ወሰደው፡፡ ወፍራም እንቅልፍ፡፡ ጉጧ በሁለት አቅጣጫ የምትሰራ ናት፡፡ ከደሃ ህልመኛ ወደ ሃብታም እርግጠኛ እንደምትወስደው ሁሉ…በተቃራኒው ትሰራለች፡፡ ሀብታሙ ያበራው ተቃራኒውን ነው፡፡ በዛኛው ወፍራም እንቅልፍ ደሃው ነቃ፡፡ ከእነ ድካሙ፤ ከእነ ረሃቡ፣ ከእነ ቁንጫው፣ ከእነ ተስፋ እጦቱ…
የት መሄድ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ርቦታል፡፡ በባዶ ሆዱ ሲመለከት ያደረውን ህልም የሰጠውን የተሰረቀ ህልም የሚሸጥ ሰው ለመፈለግ መንከራተት ጀመረ፡፡ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ አዲስ ህልም የሚለውጠው ሰው ካጣ፣ ከዚህ ሃብታም ሰው ጋር በድጋሚ ማታ መፋጠጡ አይቀርም፡፡
የራሱ የህይወት ስቃይ ሳያንሰው የሃብታሙን ደስታ በራሱ ስቃይ እየቀለበ መሆኑ የባሰ አንገበገበው፡፡ ያኛው እንዲኖር ሲባል እሱ እንዲሞት ከህይወት በታች እና ከሞት በላይ ሆኖ እያለመ መቀጠል ይጠበቅበታል።
እሱ የያዘውን ህልም ማንም ስለማይፈልገው የሚለውጠው አጣ፡፡ ቀኑን ሙሉ ህልም ወይንም ራዕይ ሲፈልግ ዋለ፡፡ የባሰ እንጂ የተሻለ አላገኘም፡፡ ሀብታሙ ሲጠጣ እሱ እንደሚሰክረው፣ ደሃው ሲጠጣ ግን ሃብታሙ እንዲያውም ንቁ ሆኖ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ አውቋል፡፡ የሀብታሙን ሸክም ከራሱ ህይወት ላይ ማራገፍ ካልቻለ ቢሞት ይመርጣል፡፡
የሚገጨውን መኪና ቢፈልግም በእነሱ ሰፈር የጋማ ከብት እና ሰው እንጂ መኪና ጠፋ፡፡ ሲመሽ መተኛትን ፈርቶ በእግሩ ሲጓዝ አደረ፡፡ እንቅልፍ አዳፋው፡፡ እንደ ማብሪያና ማጥፊያ የመሰለችው ጉጥ ከፊቱ ተደቀነች፡፡ በእንቅልፍ ልቡ እየተንሰቀሰቀ ተጫናት፡፡
ሃብታሙ ከእንቅልፉ ተነሳ፡፡ ተንጠራራ፡፡ ግን እንዳለፈው ቀን ንቃት አይታይበትም፡፡ ፈዟል፡፡ የተኛችውን ሚስቱንም ዞሮ አላያትም፡፡ ተነስቶ ወደ መስታወቱ አመራ፡፡ የራሱን መልክ አተኩሮ አስተዋለ፡፡ በሆነ ምክንያት ግን እያስተዋለ ያለው የተኛውን እና እሱን በህልሙ በማስተዋል ላይ ያለውን ደሃ ሰው መሆኑ ህልመኛውን ታወቀው፡፡ ለራሱ ጐንበስ ብሎ በመስታወቱ ነፀብራቅ ሰላምታ ሰጠ፡፡ ሰላምታው የአክብሮት ይመስላል፡፡ ተኝቶ የሚያልመው ደሃ …ሀብታሙ የእሱን የደሃ ህይወት ሲታዘብ እንደዋለ ትዝ አለው፡፡ ለምን የእሱን ድህነት እንዳከበረ ሊገባው ግን አልቻለም፡፡ ምናልባት ደሀው ቢሞት ሃብታሙ እያቀለጠ የሚያበራው እና ህይወቱን የሚያስጌጥበት መብራት አይኖረውም፡፡ የመስቀሉ ቋሚ እና አግዳሚ ናቸው፡፡ እጣ ፈንታቸው ከአንድ ጭራ ሁለት መስሎ የተገመደ ነው፡፡ የሃብታምነት ዝቃጮች እና መከራዎች እንደተሸከመው፣ ያኛውም የእሱን የድህነት መስቀሎች በተኛበት ተሸክሞ በማደሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል ያከበረው፡፡
በመስታወቱ ውስጥ ዝቅ ብሎ እጅ ነሳው፡፡ ከእንግዲህ ተሸካክመው መኖራቸው ስለገባው መሆን አለበት፡፡ የአንደኛው ህይወት ከሌላኛው ሞት ጋር መጣመሩ የተቀየረ መሰለ፡፡ ሃብታምየው ገላውን በመታጠብ ፋንታ ዝም ብሎ ልብሱን ለበሰ፡፡ ክራባቱን በማጥበቅ ፋንታ ላላ አደረገለት፡፡ መተሳሰብ አለባቸው፤ ካልሆነ ይጠፋፋሉ፡፡ ደሀ ቀን ቢራብ፣ ሃብታም ማታ… የማታ ማታ መራቡ አይቀርም፡፡
ሃብታሙ በቀን ወደ ደሃው በቀረበ ቁጥር ደሃው በማታ… የማታ ማታ ወደ ሃብታሙ ይቀርባል፡፡ ሃብታሙም ወደ ደሃ ህልም፣ ደሃውም ወደ ተጨባጩ አለም ቀርበው በመሃከለኛ ርቀት መኖር ጀመሩ፡፡ 

Read 1714 times