Print this page
Saturday, 21 June 2014 14:55

ኢራቅ እያበቃላት ይሆን?

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(8 votes)

        ከዛሬ አስራ አንድ አመት በፊት መጋቢት 20 ቀን 1995 ዓ.ም አሜሪካ የራሷንና የተባባሪዎቿን ሀገራት ጦር አደራጅታ “Shock and awe” (መብረቃዊ አሽመድማጅ ጥቃት) በሚል የሰየመችውን ሁለተኛ ዙር ወታደራዊ የወረራ ዘመቻ በኢራቅ ላይ አካሄደች።
ለዘመቻው መጀመር ያቀረበችው ሰበብ፣ ፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ህዝብ ጨራሽ የጦር መሳሪያዎችን በድብቅ እያመረቱ በድብቅ ያከማቻሉ የሚል ሲሆን አንዳንዶች ግን “አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ” የሚለውን ተረት ተርተውባት ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ዘመቻው በተጀመረ ልክ በአስረኛው ቀን፣ መጋቢት 30፣ ወራሪው አሜሪካ መራሽ ጦር፣ ይህ ነው የሚባል የመከላከል ውጊያ ከኢራቅ ወገን ሳይገጥመው ባግዳድን መቆጣጠር ቻለ። በሁለተኛው ወር ግንቦት ሁለት ቀን፣ አሜሪካ በወረራ የያዘቻትን ኢራቅን የሚያስተዳድር ጊዜያዊ የጥምረት ባለስልጣን ማቋቋሟንና ፖል ብሬመር የተባሉት አሜሪካዊ ይህንን ጊዜያዊ የአሜሪካ አገዛዝ በበላይነት እንዲመሩ መሾሟን አስታወቀች፡፡
ፖል ብሬመርም ስራቸውን በይፋ በጀመሩበት ግንቦት 5 ቀን 1995 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር፤ “አምባገነኑና ጨቋኙ ሳዳም ሁሴንና የባዝ ፓርቲ አገዛዝ ከመላው የኢራቅ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግደዋል፡፡ መጪውም የኢራቅ ጊዜ እጅግ ብሩህና ሰላማዊ እንደሚሆን ቅንጣት ታህል እንኳ አያጠራጥርም፡፡” አሉ፡፡ ንግግራቸውን ጨርሰው ቢሯቸው እንደገቡም ከዋሽንግተን አለቆቻቸው የተላኩላቸው ሁለት ዋነኛ ትዕዛዞች ተግባራዊ እንዲሆኑ በፊርማቸው አፀደቁ፡፡ የመጀመሪያው ትዕዛዝ፣ በፕሬዚዳንት ሳዳም ሁሴን ይመራ የነበረውና በዋናነት አናሳዎቹ ሱኒዎች ይበዙበታል የሚባለው ገዢው የባዝ ፓርቲ አባላት አዲስ በሚቋቋመው የኢራቅ መንግስት ውስጥ እንዳይካፈሉና ቦታም እንዳይኖራቸው የሚያግድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ትዕዛዝ ደግሞ የኢራቅን የመከላከያ ሰራዊት የሚበትን ነበር፡፡ አሜሪካ በዚህ ብቻ አልረካችም፡፡ በሳዳም ጊዜ “እጅግ ተገፍተናል” የሚሉት ብዙሀን ሺአዎች የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንና ሌሎች ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን በመያዝ መንግስቱን እንዲመሩ፣ ኩርዶች ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን እንዲኖራቸውና ምልክት ብቻ የሆነውን የፕሬዚዳንትነት ቦታ እንዲይዙ በማድረግ፣ አናሳዎቹን ሱኒዎች ከመንግስት አስተዳደሩ ጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አደረጓቸው፡፡
ይህንን የአሜሪካ ድርጊት የተመለከቱ ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኞችና የስነ መንግስት ምሁራን፤ ነገርየው ኢራቅን በቀላሉ ወደማትወጣው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በማስገባት ህዝቡን ለከፋ የእርስ በርስ እልቂት ይዳርገዋል በማለት፣ አሜሪካ ደግማ ደጋግማ እንድታስብና ከድርጊቷ እንድትቆጠብ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያቸውን አቀረቡ፡፡ ወራሪዋ አሜሪካ ግን “ጆሮ ዳባ ልበስ” ማለትን መረጠች፡፡ “የጠሉት ይወርሳል፣ የፈሩት ይደርሳል” የሚባለው ተረት እውነት ለመሆን አፍታ አልፈጀበትም። አሜሪካ የበተነችውን የኢራቅ የመከላከያ ሰራዊት ይመሩ የነበሩ ሱኒ ጀነራሎችና መኮንኖች የየራሳቸውን ታጣቂ ቡድን በማቋቋም፣ በአሜሪካ ወታደሮችና በመንግስት ሀይሎች ላይ ያልተቋረጠ ጥቃት በማድረስ፣ በሺአይቶች የሚመራውን አዲሱን የኢራቅ መንግስት ቁም ስቅሉን ማሳየት ጀመሩ፡፡
በኢራቅ የሚንቀሳቀሰው የሱኒ ሙስሊሞች የአልቃኢዳ ክንፍም ሺአ ሙስሊሞችን ነጥሎ የጥቃት ኢላማው በማድረግ፣ በጠራራ ፀሐይ የማይቋረጥ ጥቃቱን አፋፋመው፡፡ ሺአ ሙስሊሞች በወጣቱ የሃይማኖት መሪያቸው ሙቅታዳ ሳድር የሚመራ 60 ሺህ አባላት ያሉትና “የማህዲ ሰራዊት” የተሰኘ ታጣቂ የሚሊሻ ቡድን በማቋቋም፣ ለሚሰነዘርባቸው ጥቃት አፀፋውን ለመመለስ ቢሞክሩም የረባ ውጤት ማግኘትና የሱኒዎችን ጥቃት ማስቆም አልቻሉም፡፡ በዚህ የእርስ በርስ ፍጅት የተነሳም ኢራቅ በአማካይ 30 ዜጐቿን በየቀኑ ለመቅበር ተገደደች፡፡
በሳዳም ሁሴን የባዝ ፓርቲ የአገዛዝ ዘመን የነበራቸውን የበላይነት ያጡትና በሺአዎች ቁጥጥር ስር ባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ኑሪ አልማሊኪ መንግስት ከጨዋታ ውጪ የተገፉት ከኢራቅ ጠቅላላ የህዝብ ብዛት 35 በመቶ የሚሆኑት አናሳዎቹ የሱኒ ሙስሊሞች፤ በተለይ የአሜሪካ ወራሪ ወታደሮች ኢራቅን ለቀው ከወጡበት ከ2003 ዓ.ም በኋላ የኢራቅ መንግስት ላይ የሚወስዱትን የጥቃት እርምጃ አባብሰው ቀጠሉበት፡፡
እነዚህ ሃይሎች ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ግን “Islamic State in Iraq and the Levant” ወይም ISIL በሚል ምህፃረ ቃል (Levant የሚለው ቃል ከኢራቅ በተጨማሪ ሶርያን፣ ሊባኖስን፣ እስራኤልን፣ ዮርዳኖስን፣ ቆጵፕሮስንና ደቡባዊ ቱርክን የሚያጠቃልለውን ክልል ያመለክታል) የሚጠራ በወጉ የተደራጀ፣ የታጠቀና አዲስ ልዩ ሃይል በማቋቋም በመንግስት ሀይሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፍተዋል፡፡
ጥቃቱን መቋቋም ያቃተው የመንግስት ሃይልም የታጠቀውን መሳሪያ እየጣለ እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ከመፈርጠጥ የሚያቆመው አልተገኘም፡፡ 30 ሺ የሚሆኑት የመንግስት ሃይሎች የኢራቅ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ የሆነችውን ሞሱልን ለቀው እግሬ አውጭኝ ያሉት የመንግስት ወታደሮች ስምንት ሺ የሚሆኑትን የአይሲስ ታጣቂ ሃይሎችን ለግማሽ ሰዓት ያህል እንኳን መዋጋት አቅቷቸው ሸሽተዋል ተብሏል፡፡ አይሲስ አሁን ባግዳድን ለመቆጣጠር በሠላሳ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
የቡድኑ እንቅስቃሴ በኢራቅ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ሀገራት ላይም ጥቁር ጥላውን አጥልቷል። ሀይማኖትና ብሔራዊ ጥቅም ኢራንን፣ ሶርያን፣ አሜሪካንንና ተባባሪዎቿን ለጣልቃ ገብነት ጋብዟል፡፡ ሁኔታውን በቅርብ የሚያውቁ ተንታኞችና ምሁራን፤ ኢራቃውያን ከእርስበርስ እልቂት የሚታደጋቸው ሃይል ቢያገኙ እንኳ ሀገራቸው መቼም ቢሆን የበፊቷን ኢራቅ እንደማትሆን ተንብየዋል፡፡ የምር ግን ኢራቅ እያበቃላት ይሆን?

Read 5533 times