Saturday, 21 June 2014 14:53

በኬንያ- ያላባራው የሽብር ጥቃት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ያልተቋረጠ የሽብር ጥቃት ከራሳቸው ላይ አልወርድ ብሎ እጅግ ግራ የተጋቡ ሁለት የአፍሪካ ሀገራት አሉ ከተባለ ከኬንያና ናይጀሪያ ውጭ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ያላባራ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆነችው ኬንያ፤ ባለፈው እሁድና ሰኞ በተከታታይ የወረደባት የሽብር መአት የጦርነት ቀጠና አስመስሏታል፡፡
የአልሸባብ አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀረ በሰፊው የተጠረጠሩ ሽብርተኛ ታጣቂዎች ባለፈው እሁድ የሱማሊያ አዋሳኝ የኬንያ ግዛት ከሆነችው የላሙ ደሴት አቅራቢያ በምትገኘው የምፒኪቶኒ ከተማ ላይ ድንገት አደጋ ጥለው አርባ ስምንት ኬንያውያንን ገድለዋል፡፡ እሁድ እለት ማታ ላይ ከተፈፀመው ከዚህ ጥቃት ያመለጡ የአይን እማኞች፤ ሽብርተኛ ታጣቂዎቹ ቤት ለቤት እየዞሩ የቤቱ አባወራ ሙስሊም መሆኑንና የሶማሊያ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን አለመሆኑን ያጣሩ እንደነበረ ጠቁመው በተለይ ሆቴል ውስጥ ካገኟቸው ወንዶች ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑትን ብቻ ለይተው በማውጣት፣ሚስቶቻቸው ፊት በጥይት ደብድበው እንደገደሏቸው አስረድተዋል፡፡
የምፒኪቶኒ ከተማ ነዋሪም ሆነ መላ ኬንያውያን የዚህ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ድንጋጤ ገና በወጉ እንኳ ሳይለቃቸው ሰኞ እለት ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የማጂምቤኒ ከተማ እነዚሁ ሽብርተኛ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የአስር ኬንያውያንን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡
ድፍን አለሙም ሆነ መላ ኬንያውያን እንደጠረጠሩት፣ የሶማልያው ሽብርተኛ ቡድን አልሸባብ ኬንያ በሶማልያ ላይ ለፈፀመችው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና በሙስሊሞች ላይ ላደረሰችው በደል ሁለቱንም ጥቃቶች በማድረስ የእጇን እንደሰጣት በመግለፅ ሃላፊነቱን ወስዷል፡፡
የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ግን አልሸባብ የሰጠው መግለጫ ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ በሽብር ጥቃቱ ከተገደሉት አብዛኞቹ የእሳቸው ብሔር አባላት የሆኑ ኪኩዩዎች መሆናቸውን መሰረት በማድረግ ሃላፊነቱን ከወሰደው አልሸባብ ይልቅ በዘረኝነት የታወሩ ባሏቸው ኬንያውያን ፖለቲከኞች ላይ ጣታቸውን በመቀሰር ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ውንጀላ ተከትሎም የኬንያ ፖሊስ በሽብር ጥቃቱ እጃቸውን አስገብተዋል ያላቸውን በርካታ ኬንያውያንን ከያሉበት ለቃቅሞ ወህኒ ከርችሟቸዋል፡፡

Read 1894 times