Saturday, 21 June 2014 14:49

“ኢትዮጵያ ጥሩ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ቢኖራትም ቢሮክራሲው ከባድ ማነቆ ነው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ሊሲና አፈጻጸም ካልተጣጣመ ከባድ አደጋ ይፈጥራል - የእስራኤል የቢዝነስ ልዑካን ቡድን አባል
ቢሮክራሲ የሰለቸው ኢንቨስተር አማራጩ ጥሎ መሄድ ነው
            በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሚ/ር አቪጋዶር ሊበርማን የተመራ 50 አባላት ያሉት  የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ሰሞኑን ከኢትዮጵያ የንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ የልዑካን ቡድኑ፤ ከእርሻና ውሃ ቴክኖሎጂ፣ ከኢነርጂና ማዕድን፣ ከሕይወታዊ ሳይንስ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከማዕድን ቁፋሮና ከመሰረተ ልማት ኢንዱስትሪ፣ ከባንክ፣ ከአገር ደህንነት (ሆምላንድ ሴኩሪቲ)፣ ከአማካሪና ከአቪዬሽን፣ … ዘርፎች የተውጣጣ ነው፡፡
ቡድኑ ጉብኝት ያደረገው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአራት የአፍሪካ አገራት:- በሩዋንዳ፣ በኮትዲቯር፣ በኬንያና በጋና ጭምር ነው፡፡ የእስራኤላውያን የቢዝነስ ሰዎች የአፍሪካ ጉብኝት፣ ትልቅ ዓላማ እንዳለው ከልዑካን ቡድኑ ጋር የመጡት ትወልደ ኢትዮጵያዊው ቤተ እስራኤላዊ ኢንቨስተር አቶ ለማ ልጅኢሻል ይናገራሉ፡፡
አቶ ለማ እስራኤል የገቡት ከ24 ዓመት በፊት ነው፤ በ1982 ዓ.ም፡፡ በመንግሥትና በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ለማ፤ ቀደም ሲል የሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች አማካሪ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀዳሚ በሆነውና አሽግድ በተባለው የእስራኤል ወደብ እየሰሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበሩት ጊዜ፣ ወላጆቻቸው በሁመራ የሰሊጥ እርሻ ነበራቸው፡፡ እሳቸውም ከዘጠኝ አመት በፊት (ከ2009 ጀምሮ) ኢትዮጵያ መጥተው በሁመራ ሰሊጥ እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰሊጥ አምራች ብቻ ሳይሆኑ ኤክስፖርትም ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱ ከ100 እስከ 150 ኮንቴይነር ሰሊጥ፣ ሽምብራ፣ ጤፍ፣ የቅባት እህሎች ኤክስፖርት ያደርጋሉ፡፡ በሁለትና ሦስት ወር ስለሚመጡና ወኪሎችም ስላላቸው፣ ቢዝነሳቸው ጥሩ እየሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቶ ለማ፣ የእስራኤል የቢዝነስ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የቢዝነስ አማራጭ ባደረጉላቸው ገለጻ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት የአንድ ለአንድ የልምድ ልውውጥና የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገላቸው አቀባበል ከልብ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት፣ ከ5 እና 6 ዓመት ወዲህ የሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊስ፣ ለልማት አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል፤ እኛም የምንመላለሰውና የውጭ ኩባንያዎችን እያሳመንን የምናመጣው መንግሥት ለውጭ ዜጎችና ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ያዘጋጀው የኢንቨስትመንት ሕግ አመቺና አደፋፋሪ ስለሆነ ነው፡፡ አገራችን ደግሞ ለልማት ምቹ ናት፡፡ መንግሥት፤ ለሚሊኒየሙ የመጣን ጊዜ፣ ከዚያም ወዲህ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ እየተዘዋወረ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ የቢዝነስ አመቺነትና አማራጮች፣ … ለውጭ ዜጎችና ለዲያስፖራው የሚያደርገው ገለጻ በጣም ጥሩ ከመሆኑም በላይ ለኢንቨስትመንት ቆርጦ መነሳቱን ያመለክታል ብለዋል፡፡
የእስራኤል ትላልቅ የቢዝነስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ይላሉ - አቶ ለማ፡፡
ከ6 ዓመት በፊት በውጭ ጉዳይ የተመራ ቡድን መጥቶ ነበር፡፡ ከሦስት ወር በፊትም እኔም ያለሁበት 50 የቢዝነስ ልዑካን መጥተን ነበር፡፡ የአሁኑ ቡድን ጉብኝት በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም - በአፍሪካም ነው። ከሩዋንዳ፣ ከኮትዲቯርና ከጋና ጉብኝት በኋላ ነው ኢትዮጵያ የመጣነው፡፡ በኬንያ በምናደርገው ጉብኝት ነው የምናበቃው፡፡
እስራኤል ቴክኖሎጂና እውቀት እንጂ ለኢንቨስትመንት የሚሆን የተፈጥሮ ሀብት የሉትም። የነበራትንም ስለጨረሰች እውቀትና ቴክኖሎጂዋን ኢንቨስት የምታደርግበት ትፈልጋለች፡፡ ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ተመራጭ ነች፡፡ “በአፍሪካ ኢንቨስት ማድረግ ተረስቶ የቆየ ጉዳይ ነው” ብላ ስላመነች ነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን ይዛ የቢዝነስ አማራጭ አገር የምታስሰው፡፡ ስለዚህ ቡድኑ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል፡፡  
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ያለውን ችግርም አልደበቁም፡፡ አንድ ችግር አለ፡፡ ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከዓለም ባንክና ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር በተወያየንበት ወቅት ተናግሬዋለሁ፡፡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲውና መንግስት ለቢዝነስ ያለው አመለካከት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ቢሮክራሲው ከባድ ማነቆ ነው። ከላይ የሚነገረውና እታች የሚፈጸመው አይገናኙም። ታች በዞንና በወረዳ ያሉት አመራሮች ኢንቨስተሩን አልተረዱትም፡፡ ሊያለማ ሳይሆን የሚበላው አጥቶ እርቦትና ቸግሮት የመጣ ነው የሚመስላቸው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ያለው ፖሊሲ ሌላ፣ አፈጻጸም ሌላ። የፌዴራል ፖሊሲና የክልል አፈጻጸም ካልተቀናጀ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ የፖሊሲ ማማር ብቻውን ምንም አይሰራም፡፡ እታች ብዙ ችግር አይቻለሁ፡፡ አመራሮቹ አብረሃቸው እንድትበላ እንድትጠጣ፤… ይፈልጋሉ፡፡ ኢንቨስተሩ ደግሞ ጠቅሞ ለመጠቀም እንጂ ለዚህ ዓይነት አሰራር ቦታ የለውም - ጥሎ ነው የሚሄደው፡፡
ብዙ ጥሬና አሳምኜ ያመጣሁት አንድ ኢንቨስተር፣ ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡ 10 ዓመት ከሥራ በኋላ የታች አመራሮች “የሊዝ ክፈል” አሉት፡፡ “ለ40 ዓመት ነው’ኮ የተዋዋልነው” ቢልም ሰሚ አላገኘም፡፡ ለክልል ጽ/ቤት አመለከተ፡፡ ውላቸው እንደዚያ ባይሆንም ክልልም፣ የበታች አመራሮችን ሐሳብ ደግፎ “ከ10 ዓመት በኋላ የሊዝ መክፈል አለብህ” በማለት ወሰነ፡፡ ኢንቨስተሩ፣ እምነት በሌለበት በዚህ አይነት መንገድ መቀጠል ስላልፈለገ ጥሎ ወደ ሌላ ክልል ሄደ፡፡
ቢሮክራሲው በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ መልኩን ለውጦ ይመጣል፡፡ የዚህ ዓይነት ቢሮክራሲ የሰለቸው ኢንቨስተር የሚወስደው እርምጃ ተመሳሳይ ነው - ጥሎ መሄድ፡፡ የበለጠ የሚጎዳው ክልሉ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአሰራር እውቀት፣ …. ያመጣ፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል የፈጠረ ኢንቨስተር ጥሎ ሲሄድ፣ ጉዳቱ የሚያመዝነው ማን ላይ እንደሚሆን መገመት አያቅትም፡፡ እዚህ ላይ ነው መንግሥት ጠንክሮ መሥራት ያለበት፡፡ ፖሊሲውና አፈጻጸም ካልተቀናጀ አገሪቷ ከባድ አደጋ ውስጥ ናት ማለት ነው፡፡
ሌላ የምለው ነገር መንግስት ለኤክስፖርት ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ ምርታቸው እንዲጨምር ማድረግ አለበት። ምርት ባነሰ ቁጥር ዋጋ መጨመሩ ከሌላው አገር ጋር ለመወዳደር ከባድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ጥራቱ ጥሩ ቢሆንም ምርቱ አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ምርቱ ዝቅተኛ በሆነ መሬት ላይ ማዳበሪያ በመጠቀም፣ ምርቱን ማሳደግ ያስፈልጋል በማለት አቶ ለማ ልጅኢሻል ለአገሪቷ ይበጃል ያሉትን ምክር ሰጥተዋል፡፡
አቶ ደረጀ ዳርጌ በኮንስትራክሽንና በማማከር ዘርፍ የተሰማራ ኢንቨስተር ነው፡፡ ከእስራኤል ከመጡ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ሊሰሩ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡ የተያዘለት ፕሮግራም ከ3 ድርጅቶች ጋር የልምድ መለዋወጥ ቢሆንም አንዱ አልመጣም፡፡ ከሁለቱ ጋር ግን ተወያይቶ ጥሩ መግባባትና የልምድ ልውውጥ እንዳደረገና ወደፊት የበለጠ ለመቀራረብ አድራሻ መለዋወጡን ገልጿል፡፡
ከእኔ ጋር ውይይት ያደረጉት ድርጅቶች ሥራ የጀመሩና ለመጀመር በዝግጅት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ጥሩ የልምድ ልውውጥ አድርገናል፡፡ ሁለታችንም የምንፈልገው ነገር አለ፡፡ እኛ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማኔጅመንት እውቀት እንፈልጋለን፡፡ እነሱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ቢዝነስ መስራት እንደሚቻል ስለማያውቁ፣ ልምድ ተለዋውጠን በጋራ መጠቀም የምንችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ተግባብተናል ብሏል፡፡
አቶ ተፈሪ አስፋው በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ልዩ አማካሪ ናቸው፡፡ ስብሰባው ውስጥ አገኘኋቸውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከብዙ አገራት የቢዝነስ ሰዎች በቡድን እየመጡ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ለመሆኑ ፍላጎት ብቻ ነው? ወይስ ኢንቨስትም ያደርጋሉ? አልኳቸው፡፡
አሁን ቁጥሩን በትክክል ልነግርህ አልችልም እንጂ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ብዙ ኢንቨስት ያደረጉ ኩባንያዎች አሉ፡፡ የንግድ ም/ቤቱ ዓላማ የአገር ውስጥና የውጪዎቹን የንግድ ማኅበረሰብ በማቀራረብ፣ የውጪዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማግባባት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ዓመታት ከኔዘርላንድስ፣ ከሕንድ፣ ከቱርክ፣… በም/ቤቱ አስተባባሪነት የመጡ ባለሀብቶች በአገራችን ኢንቨስት በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። መንግሥትም የኢንቨስትመንቱን አዋጅ በማሻሻሉ በዚያ እየተሳቡ የመጡ ኢንቨስተሮችም አሉ፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ከአሜሪካ ከእንግሊዝ፣ … የመጡም አሉ፡፡ በ
ቅርቡ የኦባማ የኢነርጂ ኢኒሸቲቭ ኮንፈረንስ በአገራችን ተካሂዶ ነበር። በዚያ ጉባኤ ለመሳተፍ የመጡ የአሜሪካና የሌሎች አገራት ባለሀብቶች፣ በግላቸው ወይም ከኢትዮጵያውያን ጋር በሽርክና ኢንቨስት ለማድረግ ተስማምተዋል በማለት ገልጸዋል፡፡  

Read 2623 times