Print this page
Saturday, 21 June 2014 14:48

“ካንታ ሎጅ” - የካራት ከተማ ግርማ ሞገስ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

ኮንሶ ወረዳ ከሶስት አመታት ወዲህ በበርካታ ቱሪስቶች አይን ውስጥ እየገባች መጥታለች፡፡
ቱሪስቶቹ ግን የተሟላ ማረፊያና አገልግሎት ቢፈልጉም ካራት ከተማ ገና በእንቅስቃሴ ላይ በመሆኗ የእንግዶቿን ፍላጐት ለማሟላት እየተፍጨረጨረች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከከተማዋ አናት ላይ በሚገኘው ከፍተኛ ቦታ ላይ የተንጣለለው “ካንታ ሎጅ” ከተከፈተ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ ማረፍያ ማግኘት ችለዋል፡፡ ምንም እንኳን በቂ ባይሆንም፡፡ በአካባቢው ስለሎጁ አመሰራረት፣ የስራ እንቅስቃሴና ስለሚሰጠው አገልግሎት ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከሎጁ ስራ አስኪያጅ ከአቶ አሰፋ ቢርቦ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች፡፡


ሎጁ መቼ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው?
ግንባታው ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል፡፡ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ግን ከሶስት ዓመት በፊት ነው፡፡
የሎጁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
የገበያው ሁኔታ እንደወቅቱ ይለያያል፡፡ ሃይ ሲዝን እና ሎው ሲዝን የሚባል አለ፡፡ እንደወቅቱ ይለያያል። በእርግጥ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኑ በርካታ ቱሪስቶች ወደከተማዋ ሲመጡ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት ሎጅ ነው፡፡ እኛም የምንገኘው አማካኝ መንገድ ላይ በመሆኑ እንቅስቃሴው ጥሩ ነው፡፡
ባሩ፣ ሬስቶራንቱም ሆነ የመኝታ ክፍሎቹ የውስጥ አደረጃጀታቸው ዘመናዊ ሆኖ ከውጭ ግን ባህላዊ ነገሮችን ተጠቅማችኋል፡፡ የሎጁ አሰራር የኮንሶን ባህል ይወክላል ብለው ያስባሉ?
በደንብ ይወክላል! መጀመሪያውኑም የኮንሶን ባህላዊ ገጽታዎች በሙሉ እንዲያንፀባርቅ ተደርጐ ነው የተሰራው፡፡ ከ90 በመቶ በላይ የኮንሶን ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸው ወንበሮች፣ መጋረጃዎች፣ ጣሪያውም ግድግዳውም ይመሳሰላል፡፡ ነገር ግን ሌሎች ዘመናዊ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዘመናዊ ነገሮችንም ተጠቅመናል፡፡ ይህን ያደረግነው ለእንግዶቻችን የበለጠ ምቾት ለመጨመር ነው፡፡ ቦታው ቀደም ሲል ሎጁ ከመገንባቱ በፊት በጣም ገደላማ ስለነበር፣ ከኮንሶ ታታሪ ህዝብ የተማርነውን የእርከን አሰራር በመጠቀም፣ ቦታውን ለሎጁ ግንባታ አመቺ እንዲሆን አድርገነዋል፡፡
ከሌላው ለየት ያለ አገልግሎት እንደምትሰጡ ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለምትሰጧቸው አገልግሎቶች ትንሽ ያብራሩልኝ?
እንደማንኛውም ሎጅ የመኝታ፣ የባርና የምግብ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ የተለየን የሚያደርገን የምንሰጠው አገልግሎት ጥራትን ማዕከል ያደረገና ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ነው፡፡ ሎጁ በትልልቅ ከተሞች የሚገኝን ትልቅ ሎጁ ይመጥናል፡፡ በማደግ ላይ ላለችው ካራት ከተማ፣ ትልቅ ግርማ ሞገስ አጎናፅፏታል። በአካባቢው ላይ የመብራት መቆራረጥ፣ የውሃ እና የኢንተርኔት ችግር አለ፡፡ እኛ የራሳችንን ትልቅ ጀነሬተር በመጠቀም የተሟላ አገልግሎት በመስጠት እንታወቃለን።
ሎጁ ምን ያህል ባር፣ ሬስቶራንትና የመኝታ ክፍሎችን ይዟል?
መኝታዎቹ… በጐጆ ደረጃ 29 ክፍሎች አሉን። ሁለት እና አንድ ሰው የሚያስተናግዱና የተለያየ መጠን ያላቸው ጐጆዎች አሉ፡፡ በጣም ንፁህና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ደረጃቸውን እንደጠበቁ በብሎኬት የተሰሩ ፎቅና ምድር ቤት መኝታዎች ናቸው ያሉን፡፡ በአጠቃላይ ግን 56 የመኝታ ክፍሎች አሉን ደረጃውን የጠበቀ አንድ ባርና ሬስቶራንት አለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአካባቢው ተመራጭ ነን፡፡
እንደሚታወቀው የሎጁ ባለቤት የውጭ ዜጋ ናቸው። ኮንሶ ድረስ መጥተው እንዴት ኢንቨስት አደረጉ?
የሎጁ ባለቤት አቶ ፍሬዲ ሄስ ሙሉ በሙሉ የውጭ ዜጋ አይደሉም፡፡ በእናታቸው ኢትዮጵያዊ፣ በአባታቸው የአውስትራሊያ ዜጋ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ነገር ግን ለትምህርት ወደ አባታቸው አገር ሄደው ለተወሰነ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ እዚህ ቦታ ኢንቨስት እንዴት ሊያደርጉ ቻሉ ላልሽው፣ ከዚህ በፊት በማስጐብኘት ስራ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡
አስጐብኚ ድርጅት አላቸው ማለት ነው?
አዎ! “ሔስ ትራቭል” የተሰኘ አስጐብኚ ድርጅት አዲስ አበባ ውስጥ አላቸው፡፡ እናም ቱሪስቶችን ለማስጐብኘት ወደዚህ ስፍራ ይመጡ ስለነበር፣ ለቱሪስቶች ሙሉ አገልግሎት የሚሰጥ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልና ሎጅ አለመኖሩን ከተገነዘቡ በኋላ፣ አካባቢውን ስለወደዱትም ጭምር ይህንን ሎጅ ሊሰሩ ችለዋል፡፡
እርስዎ መቼ ነው ሎጁን በስራ አስኪያጅነት መምራት የጀመሩት?
ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት፣ ሎጁ ስራ የጀመረ ሰሞን ማለት ይቻላል፡፡ ከእኔ በፊት ትንሽ የተንጠባጠቡ አሰራሮች ነበሩ፤ ከመጣሁ በኋላ እየተመካከርን ግቢውንም የበለጠ እያሳመርን ለዚህ አብቅተነዋል፡፡ አሁን ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ በጣም መልካም ነው፡፡
የእርስዎ የትምህርት ዝግጅት ከሆቴል አስተዳደር ጋር የተገናኘ ነው?
በእርግጥ የእኔ የትምህርት ዝግጅት ጀነራል ማኔጅመንት ነው፡፡ ነገር ግን በአጫጭር ስልጠናዎችና ሴሚናሮች እውቀቴን ከሆቴል ማኔጅመንት ጋር በማቆራኘት ውጤታማ እየሆንኩ ነው፡፡
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የኮንሶ የእርከን ስራ፣ ባህላዊ መንደሮቻቸውና “ኒውዮርክ” የተሰኘው ቦታ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ፣ በከተማዋ ያለው የቱሪስት ፍሰት ምን ይመስላል?
እውነቱን ለመናገር ኮንሶ በዩኔስኮ ከተመዘገበችና ዓለም ካወቃት በኋላ፣ የቱሪስቱ ፍሰት በጣም ጨምሯል፡፡ ምናልባት የቱሪስቱ ቁጥር በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ጨምሮ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እኛ ከዚያ በፊት የምናየው እንግዳና በአሁኑ ወቅት የምናየው ይለያያል፡፡ እርግጥ እናንተ የመጣችሁበት ወቅት የግንቦት መጨረሻ “ሎው ሲዝን” የሚባለው ስለሆነ፣ ብዙ ቱሪስት አልተመለከታችሁ ይሆናል። ልክ ከአንድ ወር በኋላ ክረምቱ አካባቢ “ሃይ ሲዝን” ይመጣል፡፡ ያን ጊዜ ለአይን የሚያታክት ቱሪስት ይኖራል፡፡ አጠቃላይ እንቅስቃሴው ይሄን ይመስላል።
ከቱሪስቱ መጨመር ጋር የከተማዋ እድገትና የነዋሪዎቿ ህይወት ላይ የሚታይ ለውጥ አለ?
ወደ እናንተ ሎጅ እየመጡ ለመዝናናት የሚደፍሩስ የከተማዋ ነዋሪዎች አሉ?
ይሄ ጥሩ ጥያቄ ነው! ቀደም ሲል ሎጁ ደረጃውን ጠብቆና አምሮ ስለተሰራ ወደዚህ መጥቶ ለመዝናናት የማይቻል እንደሆነ ነበር ነዋሪዎች የሚገምቱት። በዚህ የተነሳ ሰው ይፈራና ይርቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ባደረግነው አንዳንድ እንቅስቃሴ ማለትም ወደከተማዋ እንግዶች ሲመጡ አብረው የሚመጡ ሰዎችን ስናስተናግድና ስናለማምድ አሁን የሁሉም መዝናኛ ሆኗል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ላይም መጠነኛ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡
ህዝቡ ባለው አገር በቀል እውቀት ነው በዓለም ቅርስነት እርከኖቹንና ባህላዊ መንደሮቹን ያስመዘገበው ስለዚህ አሁን የተለያዩ ለውጦች ይታያሉ፡፡ በእኛ ሎጅ እንኳን ብትመለከቺ፣ በቋሚና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ በርካታ ሰራተኞች ህይወታቸውን እያሻሻሉ ነው፡፡
ለምን ያህል ሰራተኞች የሥራ ዕድል ተከፍቷል?
ግንባታው አሁንም እየተካሄደ ነው፤ ግማሹ ግንባታ ማስፋፊያ እየተካሄደበት ሲሆን፤ ግማሹ ደግሞ የቀድሞው ግንባታ ማጠናቀቂያ ላይ ነው። ሎጁ በ34ሺህ 450 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡ ለ35 ቋሚ ሰራተኞችና ከ50-60 ለሚደርሱ የቀን ሰራተኞች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡ ከሰራተኞቹ 99 በመቶዎቹ የኮንሶ ተወላጆች ናቸው፡፡
አጠቃላይ ግንባታው ምን ያህል ወጪ ፈጀ?
እንዳየሽው ግንባታው ገና አልተጠናቀቀም። ነገር ግን እስካሁን ባለው ሂደት ከ16 እስከ 17 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ለማጠናቀቂያው ምን ያህል ብር ሊፈጅ እንደሚችል መገመት ያዳግታል፡፡
የሎጁን መጠሪያ “ካንታ” ብላችሁታል፡፡ ምን ማለት ነው?
ካንታ ያልነው በአንድ ትልቅ መንደር ውስጥ ያለ ሌላ አነስ ያለ መንደር ለማለት ነው፡፡

Read 2972 times