Saturday, 21 June 2014 14:38

በአፍሪካ ህፃናት እየቀጨጩ፤ አዋቂዎች እየወፈሩ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሲመረጡ “ልከኛ” የነበሩ የፓርላማ አባላት “ዙጦ” ሆነዋል

      የደቡብ አፍሪካ መንግስት ለበርካታ ዓመታት ኤችአይቪ/ኤድስን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ አሁን ትኩረቱን ከልክ በላይ ውፍረት ላይ ማድረግ አለበት፡፡ መቀመጫውን ለንደን ባደረገው “Lancet” የተሰኘ የህክምና ጆርናል ላይ የታተመ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመለከተው፤ ከደቡብ አፍሪካ አዋቂ ሴቶች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉና 40 በመቶው ወንዶች ከልክ በላይ ወፍራሞች ናቸው፡፡ ልጆቹም ቢሆኑ ከውፍረት አላመለጡም ይለናል ጥናቱ፡፡ ሩብ ያህሉ ልጃገረዶችና 20 በመቶ የሚሆኑ ወንድ ልጆች ሲበዛ ወፍራም ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከስኳር በሽታ እስከ ልብ ህመም ድረስ ላሉ ደዌዎች የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው - ዘ ኢኮኖሚስት እንደዘገበው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በቀሩት የአፍሪካና ሌሎች ድሃ አገራትም በቀጣዮቹ ሁለት አስርት ዓመታት ከልክ በላይ የሆነ ውፍረት በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር የጠቆመው ጥናቱ፤ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ከከተሞች መስፋፋትና ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደሆነ አመልክቷል። ህፃናት በምግብ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በሚቀጭባቸው አካባቢዎች የአዋቂዎች ከልክ በላይ ውፍረት ይበልጥ እየጨመረ መምጣቱ አያዎ (Paradox) ነው ብለዋል-ተመራማሪዎች፡፡
ከልክ በላይ ውፍረት ለተለያዩ በሽታዎች የሚያጋልጥ ቢሆንም አብዛኞቹ ደቡብ አፍሪካውያን ግን በውፍረታቸው ደስተኞች ናቸው፡፡ የኑሮ ዘይቤያቸውንና የአመጋገብ ልማዳቸውንም የመቀየር ፍላጎት የላቸውም፡፡ ቃለ-መጠይቅ ከተደረገላቸው 25ሺ500 ደቡብ አፍሪካውያን መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት አሪፍ ነው ብለው የሚያምኑት የሰውነት አቋም ወፍራምነትን እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
የጤና ሚኒስትሩ አሮን ሞትሶአሌዲ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የህክምና ዶክተር የሆኑት ሚኒስትሩ፤ ጠዋት የእግር ጉዞ በማድረግና ጤናማ የአመጋገብ ልማድን በመተግበር  መሸንቀጥ እንደሚገባ አርአያ በመሆን እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ የሥራ ባልደረቦቻቸው የእሳቸውን ምሳሌነት እንዲከተሉ ያደረጉት ጥረት ግን አልተሳካም፡፡
በያዝነው ወር መጀመርያ ላይ የደቡብ አፍሪካ የፓርላማ አባላት ካፊቴሪያቸው  ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት የሚዳርጉ ምግቦችን ያቀርባል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ አባላት ሲመረጡ “ጥሩና ልከኛ” ነበሩ ያለችው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ የፓርላማ አባል ሼይላ ሲትሆል፤ “አሁን ግን ሁሉም ዙጦ ሆነዋል” ብላለች - ዘ ኢኮኖሚስት እንደዘገበው።
በነገራችሁ ላይ ኢትዮጵያን በተመለከተ የወጣ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ለጊዜውም ቢሆን ከልክ በላይ ውፍረት እኛን አያሰጋንም፡፡ ሌላ የሚያሰጋን ነገር ግን አልጠፋም፡፡ ውፍረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለው አመጋገባችን ላይ የተለየ ጥንቃቄ አድርገን አይደለም፡፡ በከተማ መስፋፋትና በኢኮኖሚ ዕድገት ገና በመሆናችን ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ባወጣው ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ በድህነት ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ይፋ አድርጓል - ከኒጀር ቀጥሎ ማለት ነው፡፡ ጐበዝ ድህነትን ለማጥፋት ብዙ ትጋትና ረዥም ጉዞ ይጠብቀናል፡፡ ግን የማይቻል ነገር የለም!!       


Read 2489 times