Saturday, 21 June 2014 14:28

“ባለ እንጨት ስትጥል አይታ፣ ባለ እንስራዋም ጣለች…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…አንድ በጣም የቸገረን ነገር አለ…ለምንድነው ሁልጊዜ ወጥተንም፣ ወርደንም ሌላው ሰው ያደረገውን እኛም ማድረግ የምንፈልገው! አይገርማችሁም! ፉክክር አይሉት፣ መንፈሳዊ ቅናት አይሉት፣ ጤናማ ውድድር አይሉት…ያኛው ስላደረገው ብቻ ሌሎቻችን ‘ኮፒ ፔስት’ ለማድረግ ስንሽቀዳደም የምር ቀሺም ነገር ነው፡፡
አንድ ወዳጄ የነገረኝን አባባል ስሙኝማ…“ባለ እንጨት ስትጥል አይታ፣ ባለ እንስራዋም ጣለች…” እንስራው ሲከሰከስ አስቡትማ! አሀ…ያቺኛዋ ጥላለቻ! “ጓደኛዋ ጥላ እሷ አንከርፍፋ መጣች…” የምትባል ይመስላታላ! ኮሚክ ነገር እኮ ነው…“ማን ጥሎ ማን ይቀራል!” አይነት ነገር ነው የሚመስለው!
እኔ የምለው… አንዳንድ የሬድዮ ፕሮግራሞችን ነገሬ ብላችሁልኛል! ምን አለፋችሁ… እንጨት ሲጥሉ አይቶ እንስራ… ነገር በሽ በሽ ነው፡፡ አንዱ ፕሮግራም ሞክሮት ጥሩ አድማጭ ያገኘ የሚመስለውን አቀራራብ ሌሎች ‘ኮፒ ፔስት’ ለማድረግ ሲሞክሩ ትሰማላችሁ፣ ታያላችሁ፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ ምን መሰላችሁ… አንዳንዴ ‘ኮፒ ፔስት’ ሲደረግ የድምጽ ቅላጼው እንኳን አይቀርም!  
ስሙኝማ..እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ማስታወቂያዎች ላይ በተለይ እንዲሀ አይነት ነገር ደጋግማችሁ ታያላችሁ (‘ቤት አመታት’ ሳይቀር..ቂ..ቂ..ቂ…)፡፡  
“ባለ እንጨት ስትጥል አይታ፣ ባለ እንስራዋም ጣለች…” አሉ፡፡
ስሙኝማ…የአባባል ነገር ካነሳን አይቀር…አንድ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ምን የምትል አባባል አለች መሰላችሁ…“ክፉ ቀንና ጥይትን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ነው፡፡” ሚኒባሶች “እንደ ቤትሽ አትንጣጪ” “ዝቅተኝነት ከተሰማህ፣ ዛፍ ላይ ውጣ…” አይነት እየለጠፉ እንደሚያበሽቁን ሁሉ፣ እንደዚችኛዋ አይነት አሪፍ አባባሎች አልፎ አልፎ ታገኘላችሁ፡፡
ነገርዬውማ… ክፉ ቀንን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ አሪፍ ነው፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ… እዚች እኛይቱ አገር አንድን እንቅልፍ ያሳጣችሁን ችግር “ዝቅ ብዬ አሳለፍኩት…” ስትሉ ነገርዬው በየትም፣ በየትም ዞሮ ይመጣና ከምድር ውስጥ ፈልፍሎ ይወጣላችኋል፡፡ እናም ማምለጫ መንገዱም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡
እናላችሁ…“ባለ እንጨት ስትጥል አይታ፣ ባለ እንስራዋም ጣለች…” አሪፍ፣ ለእኛ በልክ የተሰፋች አባባል ትመስላላች፡፡
ልክ ነዋ…አገር እንኳን ‘እንጨት ሲጥሉ አይታ እንስራ የምትጥል…’ ትመስላለች፡፡ “እነእንትና እንዳደረጉት…” “እንትን አገር ተሞክሮ ስኬታማ የሆነ…” ተብሎ ይጫንላችኋል፡፡ ታዲያላችሁ… እንኳን እኛ ዘንድ ስኬታማ ሊሆን ቀርቶ… አለ አይደል… ነገርዬው ሁሉ ‘እንጨት ሲጥሉ ታይቶ እንስራ መጣል’ ይሆናል፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ማህጸንም ለ‘ማከራየት’ ደረስን አይደል! እናላችሁ… ስለ ማህጸን ኪራይ ስታነቡ “ምነው ይሄ ‘ማከራየት’ የሚሉት ነገር ለሌላ ሁሉ ቢሠራ…” ያስብላችኋል!
ልክ ነዋ…ለምሳሌ ‘ቦተሊከኞቻችን’ ህዝብን ፊት የመናገር ጥበብን ከሰለጠኑት ‘ይከራዩልን’፡፡ አሀ… “ሁልህም አናውቅህምና ነው… ሱሪህን ሁሉ በቀበቶ መታጠቅ የጀመርከው ዕድሜ ለእኛ በል!” “ውስጥ ለውስጥ የምትጎነጉኑትን የማናውቅ መሰላችሁ…” አይነት የፊት ለፊትና ‘የሾርኒ’ ንግግር ሰለቸና!  የምር እኮ ብዙ “ፖለቲካ ከእኛ በላይ ላሳር!”፣ “አገር መውደድ ከእኛ በላይ ላሳር!” “አዋቂ ከእኛ በላይ ላሳር!”፣ የሚሉ በሁሉም ወገን ያሉ የዘመናችን ሰዎች የኪራይ አእምሮ ቢያገኙ አሪፍ ነበር፡፡ የምር እኮ…. ፊት ለፊታቸው ማይክ በቀረበ ቁጥር አርጩሜ የያዙ ‘ክፉ የኔታ’ መሆን የሚቃጣቸው መአት አለሉላችሁ፡፡
‘የአእምሮ ኪራይ’ የሚባል ነገር ይጀመርልንማ። አሀ… አንዱ ችግራችን እዛ ላይ ነዋ!… ከፍ ብለን የጠቀስነውን አይነት… “ከእነእንትና የቀዳነው ህግ…”፣  “ከእነእንትና ባገኘነው ተሞክሮ…” ምናምን ከማለት አንደኛውን አእምሯቸውን ‘ያከራዩን’ና እኛው ‘እንፍጠራ’!
ፈራንካ ባይኖረንም በምግብ ለሥራም ቢሆን እንከፍላለና! ያው ብድር ስናበዛ “የሰጠናችሁን ብድር ቁጭ አድርጓት…” ማለታቸው ባይቀርም… የሆነ ነገር፣ ወይ የውሀ ጉድጓድ፣ ወይ ተቆፍሮ የሚወጣ ነገርዬ ያለበት ቦታ ሰጥተን አፋቸውን እናሲዛለና! እንኳንም ለወዳጅ የሚሆን ጉድጓድ አላሳጣንማ!
“አእምሮ ለመከራየት የወጣ ዓለም አቀፍ ጨረታ፡፡ መስፈርቶቹ የሚመረጠው አእምሮ ከኔኦሊበራሊስቶች፣ ናፋቂዎች፣ አተራማሾች፣ ምንምን ንክኪ እንደሌለው የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ከቤይጂንግ ወይም ከሻንጋይ ክሊኒክ ማምጣት ይኖርበታል፡፡” አሪፍ አይደል! ሀርቫርድ፣ ኦክስፎርድ ጅኒ ጅቡቲ ብሎ ነገር የለም፡፡ ቤይጂንግና ሻንጋይ ብቻ! (ስሙኝማ…መቼ ነው ወዳጆቻችን ቤይጂንግ ህንጻ ስር መኪና ተደግፈው “መኪናዬን ተደግፌ በምኖርበት አፓርተመንት ስር…” ምናምን የሚል የተጻፈበት ፎቶ መላክ የሚጀምሩት! እዛ ፓርኪንግ ሥራ የለም እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
ምን አለ በሉኝ፣ ነገራችን ሁሉ “ባለ እንጨት ስትጥል አይታ፣ ባለ እንስራዋም ጣለች…” አይነት ስለሆነ ሁለት ሰው እንደዛ አይነት ፎቶ በላከ ማግስት ሁለት ሺህ ሰው ይልካል፡፡ (እግረ መንገዴን…ጓዳኞቻቸው “አወጣኋት…” የሚሏትን እንትናዬ ሁሉ የሚያሳድዱ ሰዎች ገጥመዋችሁ አያውቁም! እንደ ጀግንነት ይቆጥሩታል መሰለኝ፡፡)
“የሚጠቅሱ ሴቶች በዝተዋል…” ያልከኝ ወዳጄ በግራ ነው በቀኝ ዓይናቸው የሚጠቅሱት? አሀ… በቀኝ ከሆነ ቀኝ አክራሪ ሊሆኑ ስለሚችሉ እንጠነቀቃለና! ልጄ… አውሮፓ ሁሉ ቀኝ፣ ቀኝ እያለ ስለሆነ ‘መጥኔ ለመጤ’ እያልን ነው፡፡
ሴቶችን ለጥቅሻ ያበቃህ አንድዬ በቀን አምስቴ እንቆቆ የሚጠጡ የሚመስሉ ቦሳቻችንን ፈታ አድርጋቸውማ! ቢደብሩንም እንኳን ትንሽ እኛን መስለው ቢደብሩን ይሻላል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንድ ካፌ ውስጥ “ከ30 ደቂቃ በላይ ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ማንበብ ክልክል ነው፣” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፏል፡፡ እንዴት ቢቸግራቸው እንደሆነ አይታያችሁም! ኮሚክ እኮ ነው፣ አንዳንዶቻችን በአንድ ማኪያቶ አምስት ጋዜጣ ካላነበብንና ሌሎች ስምንት ዘጠኝ መጽሔቶች ካላገላበጥን በስተቀር ‘ወንበር አንለቅም’፡፡ አይደለም የንግድ ቤት የዘመድ ቤት እንኳን ምሳ ሰዓት አልፈን እስከ መክሰስ ከቆየን እኮ ፊታቸውን ትንሽ ጠቆር ማድረጋቸው አይቀርም። ሲበዛም አሪፍ አይደለማ! እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ሬስቱራንቶቹ አንደኛውን “ጋዜጣ ማንበብ አይፈቀድም” ብለው ቢለጥፉ ሊደርስባቸው የሚችለውን እያሰቡ የሚተዉት ይመስለኛል፡፡ እኛም “ስሙኝማ…” ማለታችን አይቀርማ!
አሁን፣ አሁን አንዳንድ ቤቶች “ላፕቶፕ መጠቀም ክልክል ነው…” እያሉ መለጠፍ ጀምረዋል። ምን ይደረግ! አንዳንዱ ላፕቶፑን ሶኬት ላይ ይሰካና ለአንድ ሻይና ለአንድ ቦምቦሊኖ ሬስቱራንቱን ቢሮው ያደርገዋል፡፡ ሦስት ሰዓት ገብቶ ሰባት ሰዓት ይወጣላችኋል፡፡ እስከዛ ድረስ እኮ የጥበቃ ሠራተኞች ሺፍት እንኳም ተለውጦ ሊሆን ይችላል፡፡
አንድ ሬስቱራንት ደግሞ… “ከተገለገሉ በኋላ ለሌላ ተገልጋይ ቦታውን ይልቀቁ፣” የምትል ማስታወቂያ አለች፡፡ የምር ግን እኮ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ብዙዎቻችን ይቺን ታክል ይሉኝታ እያጣን እኮ ነው! የአራት ብር ሻይ አዘን አራት ሰዓት ሙሉ ተደላድለን እንቀመጣለን፡፡ ለንግድ የተቋቋመም ሬስቱራንትን ብሔረ ጽጌ መናፈሻ አይነት ማድረግ ልክ አይደለም!
እኔ የምለው…‘እዛ ቦታ’… አለ አይደል…በር ተንኳኩቶ “ሰዓት ሞልቷል…” ስንባል ወይ እንወጣለን ወይ ጮክ ብለን “እጨምራለሁ!” እንላለን፡፡ ያውም ‘መጮህ’ ከተቻለ!  አሀ… ልጄ ‘አንዳንድ ነገሮች’ እኮ ድምፃችንን ያጠፉና በ‘ትንፋሽ ብቻ’ ይተኩታል! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“ባለ እንጨት ስትጥል አይታ፣ ባለ እንስራዋም ጣለች…” አይነት አስተሳሰብ ራሳችንን እንዳንሆን እያደረገን ነው፡፡
እንጨቱም፣ እንስራውም አይውደቁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4102 times