Saturday, 21 June 2014 14:19

የመንግሥት ሠራተኞች ከ2007 ምርጫ ጋር ደሞዝ ይጨመርላቸዋል?

Written by 
Rate this item
(17 votes)

አዲሱ የበጀት ዝርዝር ስለ ሠራተኞች ደሞዝ የሚለው ነገር አለ
ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ይኖራል። የግድ ነው። ለምን? ሶስት ምክንያቶች አሉ።
ለመጪው ዓመት የተመደበው የደሞዝ በጀት(ከነመጠባበቂያው)፣ ከዘንድሮው በ66% ይበልጣል
በጀቱና መጠባበቂያው ከ11.5 ቢ ብር ወደ 19.1 ቢ ብር እንዲጨምር ተደርጓል (የ7.6 ቢ ብር ጭማሪ)
ጊዜው የምርጫ ጊዜ ነው። የመንግሥት ሠራተኞችን በከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ማንበሻበሽ ያዋጣል
ግን ማን ያውቃል! የደሞዝ ጭማሪ ላይኖር ይችላል። ለምን? ሶስት ምክንያቶች አሉ
ባልተለመደ ሁኔታ አብዛኛው የበጀት ጭማሪ “መጠባበቂያ” ተብሎ ነው የተያዘው  (6.5 ቢ. ብር)
ጊዜው የምርጫ ነው። ምርጫ ሲቃረብ ደሞዝ እንደማይጨመር አቶ መለስ ዜናዊ ተናግረው ነበር።
የመንግስት ሠራተኞች ወፍራም ጭማሪ ቢያገኙ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሊፈጠር ይችላል

የመንግስት ሠራተኞችን ደሞዝ በተመለከተ ለ2007 ዓ.ም የተዘጋጀው በጀት፣ ከወትሮው በተለየና ባልተለመደ ሁኔታ፤ የተምታታ ወይም የሚያምታታ ሆኗል። “ደሞዝ ይጨመራል ወይስ አይጨመርም?” ለሚለው ጥያቄ፣ ከበጀት ምደባው ቁርጥ ያለ ምላሽ ማግኘት የለብንም እንዴ? በጀት ማለትኮ እቅድ ነው። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ፣ “ይህን ይህን ያህል ገንዘብ ከዚህና ከዚህ አገኛለሁ”፤ “ያንን ያንን ያህል ገንዘብ ለዚያና ለዚያ እከፍላለሁ” ብሎ እቅጩን መናገር አለበት፡፡ የዘንድሮው በጀት ግን፣ በተለይ የሠራተኞችን ደሞዝ በተመለከተ፣ ቁርጡን ለመናገር የፈለገ አይመስልም።
በእርግጥ በ2007 ዓ.ም ለደሞዝ ክፍያ ይውላል ተብሎ የተመደበው አጠቃላይ በጀት፣ በጣም ብዙ ነው። ከዘንድሮው ጋር ሲነፃፀር በ7.6 ቢሊዮን ብር ይበልጣል። ዘንድሮ ለደሞዝ ክፍያ ከነመጠባበቂያው ተይዞ በነበረው 11.5 ቢሊዮን ብር በጀት ላይ፣ ድንገት በአንድ ጊዜ 7.6 ቢሊዮን ብር እንዲጨመርለት የተወሰነው በምን ምክንያት ይሆን? የሠራተኞች ደሞዝ “በወፍራሙ” ካልተጨመረ በቀር ይሄን ሁሉ ገንዘብ መመደብ አስፈላጊ አይደለም። ሌላ ምክንያት ሊኖረው አይችልም። እንዴት በሉ፡፡
የደሞዝ በጀት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት አመት ቢኖር በ2003 ዓ.ም ነው። ያኔ ታዲያ፤ የደሞዝ በጀት በ40 በመቶ እንዲያድግ የተደረገው፤ በሌላ ምክንያት ሳይሆን ለመንግስት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ስለተሰጠ ነው። የመጪው አመት የደሞዝ በጀት ጭማሪ ግን ከዚህም ይልቃል - ከዘንድሮው በጀት ጋር ሲነፃፀር በ66% ይበልጣል። ይህም ለመንግስት ሠራተኞች ቀላል የማይባል ደሞዝ ለመጨመር መታሰቡን ያረጋግጣል። በዚያ ላይ አስቡት።
የ2007 ምርጫ እየተቃረበ ነው። ገዢው ፓርቲ፣ የደሞዝ ጭማሪውን ለምርጫ ዘመቻ ሊጠቀምበት ከፈለገ፤ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው።
ደግሞስ ብዙዎቹ የመንግስት ሠራተኞች የገዢው ፓርቲ አባላት አይደሉ? “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” በሚለው ፈሊጥ ዳጎስ ያለ የደሞዝ ጭማሪ ቢያሸክማቸው ማንም አይከለክለውም። በእርግጥም ሳያሳንስ የሚቆርሰው ከየራሱ ምጣድና መሶብ እስከሆነ ድረስ፣ “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” የሚለው አባባል ቅንጣት ስህተት አይወጣለትም። ችግሩ ምን መሰላችሁ? ለመንግስት ሠራተኞች ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ለመስጠት፣ ገንዘብ ያስፈልጋል። ገንዘቡ ደግሞ ከሰማይ አይዘንብም። ከሌሎች ዜጎች ኪስ መውሰድ የግድ ሊሆን ነው። ከሌሎች ዜጎች ማዕድ ላይ ቆርሶ መውሰድ... ይሄ ነው ችግሩ።
ሌላኛው አማራጭ የብር ኖት በገፍ ማተም ነው። ምን ዋጋ አለው? ይሄኛው አማራጭም፤ የዋጋ ንረትን በማስከተል የዜጐችን ኪስ ያኮሰምናል፡፡
የሆነ ሆኖ፤ ለደሞዝ የሚመደበው በጀት ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ተደርጓል። ከምርጫው ጋር ግንኙነት ይኑረውም አይኑረው፤ የገንዘቡ ምንጭ ምንም ይሁን ምን፤ በጀቱ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ሊውል የሚችለው፣ ለመንግስት ሠራተኞች ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ከተደረገ ብቻ ነው። አለበለዚያ የወረቀት በጀት ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ የመንግስት ሠራተኞች ያለ ጥርጥር ደሞዝ ይጨመርላቸዋል ብለን በእርግጠኛነት መናገር እንችላለን፡፡
ግን፤ በጀቱ የወረቀት በጀት ሆኖ ቢቀርስ?
እውነት ነው፤ መንግስት ለሠራተኞቹ ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ ለመስጠት ቢወስንም፤ ሙሉ ለሙሉ የቆረጠለት አይመስልም። ለምን በሉ። የበጀት ድልድሉ፣ ከሌላው ጊዜ ይለያል። እንደወትሮው ቢሆን፣ አብዛኛው የደሞዝ በጀት፣ ለእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ምን ያህል እንደሚደርሰው በዝርዝር ተሸንሽኖ ይቀርባል። የተወሰነ ገንዘብ ደግሞ መጠባበቂያ ተብሎ ይቀመጣል። ለእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ከተመደበው የደሞዝ በጀት ባሻገር አንዳች ያልተጠበቀና ያልታሰበ ወጪ ቢያጋጥም ችግር አይፈጠርም። የደሞዝ መጠባበቂያ የሚያስፈልገው ለዚህ ለዚህ ነው። ካቻምናና ከዚያ በፊት በየአመቱ 150 ሚ. ብር  የደሞዝ መጠባበቂያ ይመደብ ነበር። አምና ደግሞ 200 ሚ. ብር። ለዘንድሮ የተቀመጠው የደሞዝ መጠባበቂያ 350 ሚ. ብር ነው።
ለመጪው አመት የተመደበው የደሞዝ መጠባበቂያ ግን፣ ከእስከዛሬው በእጅጉ በእጅጉ ይለያል። 6.5 ቢሊዮን ብር ነው የደሞዝ መጠባበቂያ ተብሎ የተመደበው። ለምን? የገንዘብ ሚኒስትሩም ሆኑ የበጀት ሰነዱ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ትንፍሽ ያሉት ነገር የለም። ለነገሩ፤ ጥያቄ ለመሰንዘር ትንፍሽ ያለ ፓርቲ፣ ፖለቲከኛ ወይም ምሁርም የለም። “ለ12.6 ቢሊዮን ብር መደበኛ ደሞዝ 6.5 ቢሊዮን ብር መጠባበቂያ! ኧረ እንዲህ አይነት መጠባበቂያ በታሪክ ታይቶ አይታወቅም! ምንድነው ነገሩ?” የሚል ጥያቄ እስካሁን አልቀረበም።
እንዲህ ጉዳዩ እንደተድበሰበሰ በጀቱ ቢፀድቅ፤ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት። ምንም አይፈጠርም፡፡ መንግስት ለሠራተኞቹ ደሞዝ የመጨመርና ያለመጨመር አማራጮች ይኖሩታል። ከፈለገ ደሞዝ ይጨምራል። የበጀት እጥረት አይገጥመውም። የደሞዝ መጠባበቂያ ተብሎ የተመደበ ብዙ ገንዘብ አለለት። ካልፈለገ ደግሞ ደሞዝ አለመጨመር ይችላል። መጠባበቂያውን ትቶ፤ ለየመሥሪያ ቤቱ ተከፋፍሎ የተመደበውን የደሞዝ በጀት ብቻ ይጠቀማል። በሌላ አነጋገር፣ “መንግስት ደሞዝ ለመጨመርና ላለመጨመር እያመነታ ይሆን ነገሩን በእንጥልጥል ለማቆየት ፈልጐ ይሆን?” ብለን እንድናስብ ይገፋፋናል - ያልተለመደው የበጀት አመዳደብ፡፡
ነገር ግን በደፈናው “የደሞዝ መጠባበቂያ” ተብሎ 6.5 ቢ.ብር የተመደበው በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የበጀት ዝግጅት ሲጀመር፣ ደሞዝ የመጨመር ሃሳብ መነሳቱ አይቀርም። ከተወሰነ ክርክር በኋላ፣ ሃሳቡ ውድቅ ይሆንና፣ ዝርዝር በጀት ይዘጋጃል። የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚገልፀው፤ የየመሥሪያ ቤቱ ዝርዝር የበጀት ድልድል የተዘጋጀው የደሞዝ ጭማሪ አይኖርም በሚል መመሪያ ነው፡፡ የበጀት ዝግጅቱ ከተጋመሰ በኋላ ወይም ሊጠናቀቅ ከተቃረበ በኋላ፤ መንግስት ሃሳቡን ቢቀይርስ? ማለትም፤ ደሞዝ የመጨመር ሃሳብ እንደገና ይነሳል። ለምን?
የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለሚዋዥቅ፤ ከዚሁ ጋር አብሮ የመንግስት ሃሳብም ቢዋዥቅ አይገርምም። ደሞዝ የመጨመር ሃሳብ ከወራት በፊት ውድቅ ቢደረግ፣ ከጊዜ በኋላ ፖለቲካው ሲንገራገጭ እንደገና ደሞዝ የመጨመር ሃሳብ ይነሳል፤ ባለቀ ሰዓትም ተቀባይነት ያገኛል። ነገር ግን፣ በዝርዝር የተዘጋጀውን በጀት እንደገና ለመከለስ ቀላሉ ዘዴ ምንድነው? ለደሞዝ ጭማሪ የሚያስፈልገውን በጀት፣ በደፈናው “መጠባበቂያ” ተብሎ እንዲገባ ማድረግ ነው ቀላሉ ዘዴ።
ግን ከምር የሠራተኞች ደሞዝ ይጨመራል? አንዱ ችግር፤ 2007 ዓ.ም የምርጫ አመት መሆኑ ነው፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ በ2002 ዓ.ም ለሠራተኞች ደሞዝ እንዲጨመርላቸው ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡
የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄውን አልተቀበሉትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄውን ውድቅ ያደረጉት “ለመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ ሊጨመርላቸው አይገባም” በሚል አይደለም፡፡ ምርጫ በሚቃረብበት ወቅት ለመንግስት ሠራተኞች ደሞዝ መጨመር የአገሪቱን ፖለቲካ እንደሚያበላሽ የተናገሩት አቶ መለስ፤ ኢህአዴግ በምርጫ አመት የደሞዝ ጭማሪ እንደማያደርግ ተናግረው ነበር - በ2002 ዓ.ም፡፡ በ2007ስ?

Read 15863 times