Saturday, 21 June 2014 14:16

ለ178 ቢሊዮን ብር ደንታ ያለን አንመስልም

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     በሥልጣኔ በተራመዱት አገራት፣ ትልቁ የፖለቲካ መከራከሪያ ምን መሰላችሁ? “የመንግስት በጀት” ነው። ታስታውሱ እንደሆነ፤ ከአመት በፊት በርካታ የአሜሪካ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በበጀት ክርክር ሳቢያ ለሳምንታት ያህል ተዘግተው ቆይተዋል፡፡
የተፎካካሪ ፓርቲዎች የበጀት ክርክር መቼም ቢሆን አያባራም፡፡ የእንግሊዝ ፓርላማ አብዛኛውን ጊዜ የሚሟሟቀው በበጀት ሙግት ነው፡፡ የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የግሪክ፣ የስፔን መንግስታት ሲንገዳገዱና ከስልጣን ሲወርዱ የምናየው፤ የአውሮፓ መንግስታት በኢኮኖሚ ቀውስ ሲወዛገቡና ጐዳናዎች በተቃውሞ ሰልፍ ሲጥለቀለቁ የምንመለከተው በሌላ ምክንያት አይደለም፤ በበጀት ጉዳይ እንጂ፡፡ በእርግጥም የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች የአስተሳሰብ ልዩነት፣ በተጨባጭና በግላጭ አፍጥጦና አግጥጦ የሚወጣው፣ የበጀት መጠንና አመዳደብ ላይ ነው።
ወደ ነፃ ገበያ ሥርዓት የሚያዘነብሉ ፓርቲዎች፣ ለምሳሌ በአሜሪካ ሪፐብሊካን ፓርቲ፤ የእንግሊዝ ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ በተቻለ መጠን የመንግስት በጀት በየጊዜው እያበጠ እንዳይሄድ ይከራከራሉ። በአብዛኛው፣ ለፍርድ ቤቶች፣ ለህግ አስከባሪና ለመከላከያ ሃይል የሚመደበው በጀት ግን እንዲቀንስ አይፈልጉም፡፡ በተቃራኒው ለነፃ ገበያ ሥርዓት ያን ያህልም ፍቅር የሌላቸውና  ገናና መንግስት እንዲኖር የሚፈልጉ ፓርቲዎች ደግሞ፤ መንግስት ሁሉም ነገር ውስጥ እንዲገባ እየገፋፉ፣ ለዚህኛውም ለዚያኛውም በጀት እንዲጨመር ይወተውታሉ። በአጭሩ፤ የፓርቲዎች የፖለቲካ አቋም በተግባር የሚገለጠው የበጀት አመዳደብ ላይ ስለሆነ አጥብቀው ይከራከራሉ።
እንደ “አለመታደል” ሆኖ፣ በኛ አገር በበጀት ጉዳይ የሚከራከርና የሚሟገት ፓርቲም ሆነ ፖለቲከኛ ብዙ አይታይም። መንግስት ለ2007 ዓ.ም ያዘጋጀው የበጀት ዝርዝር ለፓርላማ ከቀረበ ሁለት ሳምንት አለፈው። ገንዘቡም ቀላል አይደለም። ከ178 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ከዜጎች ጠቅላላ አመታዊ ገቢ (ምርት) ውስጥ ሩብ ያህሉ ማለት ነው። ግን፣ ስለ በጀቱ መጠንና አመዳደብ እስካሁን ለምልክት ያህል እንኳ ውይይትና ክርክር አልሰማንም።
አንደኛ፤ የበጀቱ መጠን፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ የዜጎችን ኪስና ኑሮን ይነካል። መንግስት፤ በየአመቱ የብዙ ቢሊዮን ብር በጀት የሚመድበው ታክስ በመሰብሰብና የብር ኖት በማሳተም ነው፡፡ ታክስ የሚሰበሰበው ከዜጎች ኪስ ነው። በ2000 ዓ.ም እና በ2003 ዓ.ም እንደተደረገው መንግስት የብር ኖት በገፍ አትማለሁ የሚል ከሆነም፤ በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት የዜጐች ህይወት ይጐሳቆላል፡፡ ሁለተኛ፤ የበጀቱ መጠን ብቻ ሳይሆን የበጀቱ አመዳደብም የዜጐችን ኑሮ ይነካል። ለምሳሌ… ላለፉት 7 አመታት... “በዚህ ዓመት ግንባታቸው ይጠናቀቃል” እየተባለ፣ በየአመቱ ከቢሊዮን ብር በላይ ሲመደብላቸው የነበሩ የተንዳሆ፣ የከሰም፣ ከዚያም የርብ ግድቦች... በመጪው አመትም ከቢሊዮን ብር በላይ ይመደብላቸዋል። ገንዘቡ የት እየገባ ይሆን ግንባታዎቹ ለአመታት የተጓተቱት?
ሃብት በማባከን ዋና ተጠቃሽ ሆነው ለተገኙት ዩኒቨርስቲዎች የሚመደበው በጀትስ? በትምህርት ሚኒስቴር ስር ለሚተዳደሩት ዩኒቨርስቲዎችና ተቋማት፣ ዘንድሮ 25 ቢሊዮን ብር እንደሚመደብላቸው ስንሰማ፣ ይሄ ሁሉ ብር የት ይገባ ይሆን ብለን በደንብ ማሰብ አያስፈልገንም? ይህንን እንደ ዋነኛ ሥራ የሚቆጥሩ ፖለቲከኞች የሚፈጠሩት መቼ ይሆን? ምሁራንስ?

Read 1612 times