Saturday, 21 June 2014 14:11

በሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት እየታየ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

በኪሎ 35 ብር የነበረው በርበሬ 55 ብር እየተሸጠ ነው
በ115 ብር እንዲሸጥ የተተመነው ባለ 5 ሊትሩ ዘይት 150 ብር ገብቷል

በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች የስኳር፣ የዘይትና የዳቦ እጥረት ተከስቷል
የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን የፈጠረው ነው ተብሏል

     ሰሞኑን በአንዳንድ መሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ሲሆን ነጋዴዎችና  የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ውጤት ነው ብለዋል፡፡
በተለይ የበርበሬ፣ የስንዴ ዱቄትና የምስር ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን የስኳር፣ ዘይትና ዳቦ እጥረትም መከሰቱን ሪፖርተሮቻችን በአዲስ አበባ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች ተዘዋውረው ባደረጉት ቅኝት አረጋግጠዋል፡፡ ሸማቾች የዋጋ ጭማሪው እንዳማረራቸው ሲገልፁ፣ ነጋዴዎች፤ የሸቀጦች አቅርቦት ከፍላጎት ጋር  አልተጣጣመም ብለዋል፡፡
ከሳምንት በፊት በኪሎ 35 ብር ይሸጥ የነበረው ዛላ በርበሬ፣ እስከ 20 ብር ጭማሪ አሳይቶ ኪሎው በ55 ብር እየተሸጠ ሲሆን በንግድ ሚኒስቴር የመሸጫ ዋጋ ተመን ከወጣላቸው ሸቀጦች አንዱ የሆነው የስንዴ ዱቄት ከ12 ብር ወደ 14 ብር ከፍ ብሏል፡፡ የምስር ዋጋም በኪሎ 21 ብር የነበረው 25 ብር እየተሸጠ መሆኑን ከተለያዩ የገበያ ስፍራዎች የተሰበሰቡ የዋጋ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሌላ በኩል ስኳር፣ ዘይትና ዳቦ የመሳሰሉትን እንደልብ ማግኘት እንደተሳናቸው ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በሳሪስ አካባቢ በአንድ ዳቦ ቤት ዳቦ ለመግዛት ተሰልፈው ያገኘናቸው አቶ ወንድይፍራው ደምሴ፤ ለቤተሰቦቻቸው በየእለቱ ዳቦ እንደሚገዙ ገልፀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደታክሲ ትራንስፖርት ሁሉ ዳቦ ለመግዛትም ሰልፍ መያዝ የግድ ሆኗል ይላሉ፡፡ ከዚህም የባሰው ግን ለረጅም ደቂቃዎች ከተሰለፉ በኋላም ዳቦ አልቋል እየተባሉ በተደጋጋሚ ባዶ እጃቸውን ወደ ቤታቸው መግባታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሳሪስ አብዛኞቹ የችርቻሮ ሱቆች ስኳር የጠፋ ሲሆን ያላቸውም ቢሆኑ ከበፊት ዋጋው  እስከ 4.50 ብር እየጨመሩ እንደሚሸጡ ሸማቾች ተናግረዋል፡፡ መሰረታዊ ሸቀጦችን በማቅረብ የህብረተሰቡን ፍላጎት ያሟላሉ በተባሉ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆችም የአቅርቦት እጥረት እንዳለ የጠቆሙት ሸማቾች፤ ዘይት ባለ 5 ሊትሩ 115 ብር እንዲሸጥ የዋጋ ተመን ቢወጣለትም አሁን እስከ 150 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በጥቂት ቀናት ውስጥ የበርበሬ ዋጋ የ20 ብር ጭማሪ ለምን እንዳሳየ የጠየቅናቸው የበርበሬ አከፋፋይ  አቶ ምሳሌ ወ/አምላክ፣ የበርበሬ ምርት በአብዛኛው የሃገራችን አካባቢዎች በስፋት የሚሰበሰበው ከመስከረም እስከ ህዳር ወር ባለው ጊዜ እንደሆነ ጠቅሰው ወደ ክረምት መግቢያ ላይ ምርት በስፋት ስለማይገኝ ዋጋው እንደሚጨምር አስረድተዋል፡፡ በአሁን ወቅት ከባሌ አካባቢ የሚመጣ በርበሬ ለገበያ እንደሚቀርብ የጠቆሙት ነጋዴው፤ አምራቾች ዋጋው ላይ ጭማሪ በማድረግ ለአከፋፋዮች እየሸጡ እንደሆነ ጠቅሰው የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መኖሩን አብራርተዋል፡፡
ክረምት ላይ የበርበሬ ብቻ ሳይሆን የብዙ መሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ እንደሚጨምርም ነጋዴው ይናገራሉ፡፡ ምርቱ በሚገኝባቸው የገጠር አካባቢዎች መንገዱ ጭቃ ስለሚሆን ነጋዴው ወደ አምራቾች ሄዶ ምርቱን ለማምጣት አይሞክርም ያሉት አቶ ምሳሌ፤ ወቅቱ የእርሻ በመሆኑም ገበሬው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለመግዛት ሲል የምርቱን ዋጋ ያዝ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
“የአብዛኛው ሸማች ገቢ ባላደገበት ሁኔታ የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው መጨመሩ ጤናማ አይደለም” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡን በአለማቀፍ ድርጅት ውስጥ የኢኮኖሚ አማካሪ የሆኑት ባለሙያ፤ ወቅት እየጠበቀ በሸቀጦች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር በማጣጣም ረገድ እያደገ ነው የሚባለው ኢኮኖሚ ክፍተት እንዳለበት ያመለክታል ብለዋል፡፡ መንግስት ገበያውን ለመቆጣጠር መሞከሩም የችግሩ መንስኤ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ገበያው በምርት አቅርቦቱ መጠን እንዲመራ መንግስት መፍቀድ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ የሸቀጦች ዋጋ መጨመርና መቀነስ የአቅርቦቱና ፍላጎቱ መጠን የሚወስነው መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት ገበያ መር ኢኮኖሚ ነው የምከተለው እያለ በሌላ በኩል ዋጋ ትመና ውስጥ መግባቱ ችግር እንደሚያስከትል ይናገራሉ፡፡ መንግስት ዋጋ ከመተመን አልፎ የራሱን ጅምላ ሽያጭ እያቋቋመ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ አሰራሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ይጠቅማል ተብሎ ቢታሰብም ውጤታማ ይሆናል ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡
“በየጊዜው የጤፍ ዋጋ ቀንሷል ቢባልም ሰው መግዛት ስለተወ እንጂ በእርግጥ በሚፈለገው መጠን ዋጋው ስለቀነሰ አይደለም” የሚሉት ባለሙያው፤ የብር የመግዛት አቅሙ እየተዳከመ ከመምጣቱ ጋር ተደማምሮ ከውጭ የሚገቡ ነዳጅ፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳርና የመሳሰሉት ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር ይችላል ብለዋል፡፡
የሸቀጦችን ዋጋ በተመለከተ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ የሚያወጣቸው መረጃዎች ምን ያህል ትክክለኛ ናቸው የሚለው አጠያያቂ ነው የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ 90 ሚሊዮን ህዝብ ባለበት ሰፊ ሀገር አቅርቦትንና ፍላጎትን ማጣጣም ከባድ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ያለው የኑሮ ሁኔታ ከሌላው ለየት ይላል ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ከተማዋ  የዲፕሎማቲክስ መዲና መሆኗ፣ የውጭ ኢንቨስተሮችና አቅም ያላቸው ሰዎች በመዲናይቱ መበራከትና ቀደም ሲል በከተማዋ ዙሪያ የነበረው ገበሬ አሁን ወደ ቀን ሰራተኝነት ተቀይሮ ሸማች መሆኑ ተፅዕኖ አሳርፏል በማለት  ያስረዳሉ፡፡ እስከ 2 ሚሊዮን የሚደርስ ገበሬ ከተማዋን ተቀላቅሎ ሸማች ሆኗል የሚል ግምት እንዳለም  ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
መንግስት በትላልቅ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ብቻ በማተኮር መሰረታዊ ፍላጎቶችን ችላ ማለቱ ጥቂቶች ብቻ በስግብግብነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በር ከፍቷል የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ የተለያዩ የጅምላ ሽያጮች በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡
እንዲህ ያለ የዋጋ ንረት ሲፈጠር መንግስት የተለያዩ የማረጋጊያ ስልቶችን መጠቀም እንዳለበት የጠቆሙት ምሁሩ፤ አንዳንድ መሰረታዊ ሸቀጦች በሃገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ መንግስት አቅሙ ላላቸው ባለሃብቶች ከ500 እስከ 800 ሄክታር መሬት በመስጠት እንዲያለሙ ድጋፍ ማድረግና የምርት አቅርቦቱን መጨመር አለበት ሲሉም ይመክራሉ፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ 6.5 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል የሚል ሪፖርት ማውጣቱን የጠቀሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “ሃገሪቱ የ70 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ባለቤት ሆና ለግብርና አገልግሎት የዋለው 14 በመቶው ብቻ ነው፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የውሃ ማማ ብትባልም ዛሬም ከምግብ እርዳታ ፈላጊነት መላቀቅ አልቻለችም” ይላሉ፡፡  
መንግስት መሬት አልሚዎች ከባንክ ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ እያመቻቸና ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ የምርት መጠኑን በማሳደግ፣ አቅርቦቱን ከፍላጎቱ ጋር ማመጣጠን አለፍ ሲልም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ ማስገኘት አለበት ሲሉ የመፍትሄ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ መንግስት እስካሁን ትኩረት የሰጠው ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ መሆኑን በመግለፅም “የሃገሪቱን ሃብት ተጠቅሞ የዜጎቹን የምግብ ዋስትና ወደ ማረጋገጥ ፊቱን ማዞር አለበት” ብለዋል ምሁሩ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ተወካይ ሆነው በዚምባቡዌ ሲሰሩ፣ሮበርት ሙጋቤ ከእርሻ መሬታቸው ያፈናቀሏቸውን ነጭ ገበሬዎች አግኝተው ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያለሙ በግል ጠይቀው እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ገበሬዎቹ አማራጫቸውን ሞዛምቢክ አድርገው በዘጠኝ ወር ውስጥ የሃገሪቱን ምርት በ3 እጥፍ መጨመራቸውን በመጥቀስ፣መንግስትም እንደነዚህ አይነት ባለሙያዎችን መጋበዝ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የአጭርና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ እቅድ ያስፈልጋል የሚሉት ምሁሩ፤ በተለይ አምራቾችንና ነጋዴዎችን መቆጣጠር የሚችሉ ጠንካራ የሸማቾች ማህበራትን ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የንግድ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አማከለ ይማም “የስንዴ አቅርቦትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በቂ ማብራሪያ ሰጥተናል፣ ደግመን አንሰጥም፤ የዱቄት ዋጋ ጨምሯል የሚባለውም ምናልባት ንግድ ሚኒስቴር ከዘረጋው የገበያ ትስስር ውጪ የሆኑ ነጋዴዎች የሚሸጡበት ዋጋን ተመርኩዞ ሊሆን ይችላል እንጂ በንግድ ትስስሩ ስር ባሉ የንግድ ተቋማት የዱቄት ዋጋ ጭማሪ አልተደረገም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

Read 7183 times