Print this page
Saturday, 21 June 2014 14:06

46 ሚ. ብር የወጣበት የጋምቤላ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ብልሽት ገጠመው

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(2 votes)

ነዋሪዎች በውሃ እጦት እየተሰቃየን ነው ሲሉ አማረሩ

በጋምቤላ ከተማ ለሃያ ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ በውሃ ሃብት ሚኒስቴር በ46 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጋምቤላ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በመበላሸቱ፣ ነዋሪዎች በውሃ እጦት እየተሰቃየን ነው ሲሉ ምሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ሆቴል ባለቤት እንደተናገሩት፤ አገልግሎት ከጀመረ የሰባት ዓመት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረው  የጋምቤላ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ   ለሁለት ሳምንትና ከዚያም በላይ ለሆነ ጊዜ ከተማዋ የውሃ እጥረት ያጋጥማታል፡፡
የውሃ ችግሩ  በማየሉ የተነሳም የጋምቤላ ከተማን ለሁለት ከፍሎ ከሚያልፈው የባሮ ወንዝ ውሃ እየቀዱ ለመጠጣት መገደዳቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ልጆቻቸው በውሃ ወለድ በሽታ እየተጠቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በ1996 ዓ.ም. ለ20 ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ  የተገነባው የጋምቤላ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሁለት መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉበት ያመለከቱት ምንጮች፤ የውሃ መሳቢያ ፓምፑ የዲዛይን ችግር ስላለበት በደለል እንደሚሞላና የተገጠሙት ፓምፖችም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በመጠጥ ውሃ እጦት ክፉኛ እንደተቸገሩ የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፤ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ለችግራቸው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል፡፡  የጋምቤላ ክልል የውሃና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዶራር ኮሞን በስልክ አግኝተን ስለጉዳዩ ልንጠይቃቸው ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ “ስብሰባ ላይ ነኝ” በማለታቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡
የጋምቤላ ክልል የውሃና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዶራር ኮሞን በበኩላቸው፤ የውሃ እጥረቱ መከሰቱን አምነው አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ቢሆንም ውሃ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለውሃው መቋረጥ ምክንያት የሆነውን ችግር ለመቅረፍም በ2ሚ. ብር ፓምፕ መገዛቱን የጠቆሙት ሃላፊው፤ እስከ 2007 ምርጫ ብልሽቱ ተስተካክሎ ነዋሪው የተሟላ የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ያገኛል ብለዋል፡፡

Read 2227 times