Saturday, 21 June 2014 14:03

በግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት የለም - ብሮድካስት ባለስልጣን

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(12 votes)

ጋዜጠኛ መሰለ መንግሥቱና አቶ ሐጐስ ኃይሉ ፈቃድ ተሰጣቸው

         የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዘንድሮ ለ6 የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ በቂ የሬዲዮ ሞገዶችን ቢያቀርብም፣ ፍላጎትና ብቃት ያለው ድርጅት ያለመቅረቡን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ፤ ለአባይ 102.9 እና ለብሥራት 101.1 የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ በሰጡበት ጊዜ እንደገለጹት፣ ለአዲስ አበባ፣ ለባህርዳርና ለሀዋሳ ከተሞችና አካባቢው 6 የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት ሁለት ጊዜ በማስታወቂያ ቢጋብዙም ፍላጎትና ብቃት ያለው ተወዳዳሪ ድርጅት እንዳልቀረበ ገልፀዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ለአዲስ አበባና አካባቢዋ አንድ፣ ለባህርዳር ከተማና አካባቢዋ አንድ የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ፈቃድ ለመስጠት በማስታወቂያ ቢያወዳድሩም፣ ለአዲስ አበባ ሦስት ተወዳዳሪዎች ሲቀርቡ የባህርዳሩን የጠየቀ የለም፡፡ ለአዲስ አበባ ከተወዳደሩት መካከል መስፈርቱን አሟልቶ የተገኘው አባይ ኤፍኤም 102.9 ሬዲዮ ጣቢያ ሲፈቀድለት ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ተሰርዘዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በሁለተኛው ዙር ለአዲስ አበባ ሦስት፣ ለሀዋሳ አንድ የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሞገድ አዘጋጅቶ ቢያወዳድርም፣ ለአዲስ አበባው አንድ ጣቢያና ለሀዋሳው ምንም ተወዳዳሪ አልቀረበም፡፡ ለአዲስ አበባ ከተወዳደሩት ውስጥ አንዱ ያቀረበው ፕሮፖዛል መስፈርቱን ስላላሟላ ሲሰረዝ፣ በመጀመሪያው ዙር ተወዳድሮ ውድቅ የተደረገበት “ኦያያ መልቲ ሚዲያ” (ብሥራት) ስህተቱን አርሞ በመቅረቡ ተመርጦ 101.1 ሜጋ ሄርዝ እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡
ፈቃድ የተሰጣቸው ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ሥራ ሲጀምሩ በብሔራዊ መግባባት፣ በዲሞክራሲ ግንባታና መልካም አስተዳደር እንዲሁም ለልማት ስራዎች ትኩረት እንዲሰጡ፣ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲያቀርቡ አቶ ልዑል አሳስበዋል፡፡
የአባይ 102.9 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት አቶ ሐጎስ ኃይሉ ባደረጉት ንግግርም ሬዲዮ ጣቢያቸው፣ ውጭ አገርና አገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች በአክሲዮን ያቋቋሙት መሆኑን ጠቅሰው፣ ልዩ ድጋፍ በሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
የኦያያ መልቲ ሚዲያ (ብሥራት) 101.1 ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት ጋዜጠኛ መሰለ መንግሥቱ፣ 101.1 ሬዲዮ በአውሮፓና አሜሪካ ተወዳጅ ጣቢያ መሆኑን ጠቅሶ፣ እዚህም ተወዳጅ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በ4 ሰዓት ፕሮግራም እግር ኳስን ብቻ ሲያስተላልፍ መቆየቱን ጠቅሶ፣ አሁን በ18 ሰዓት ስርጭቱ ሁሉንም ስፖርቶችና የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚያቀርብበት ገልጿል፡፡ እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ ፕሮግራም ላይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጽሑፍ መስራታቸው፣ ፕሮግራሙ ምን ያህል ተወዳጅ እንደሆነ ያመለክታል ያለው መሰለ መንግሥቱ፤ የመዝናኛ ፕሮግራሙንም እዚህ አገር ከተለመደው ውጪ በተወዳጅ አቀራረብ በቀጣዩ ሐምሌ ወር እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

Read 4941 times