Saturday, 21 June 2014 14:01

“የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በጋዜጠኞች ደህንነት ዙሪያ ውይይት ያካሂዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

መድረኩ ከውይይቱ በኋላ አቋም ለመያዝ አቅዷል

     አዲሱ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በወቅቱ የሚዲያ ባለሙያዎች ፈተና፣ በፕሬስ ህጉና በፀረ - ሽብር አዋጁ ላይ የሚያጠነጥን የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱንና ነገ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ቀበና አካባቢ በሚገኘው አዲስ ቪው ሆቴል እንደሚካሄድ የመድረኩ ፀሃፊ አቶ ነብዩ ኃይሉ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ “በአሁኑ ሰዓት በጋዜጠኝነታቸው ታስረው ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ባለሙያዎች አሉ፣ እስርና እንግልቱም ቀጥሏል” ያሉት አቶ ነብዩ፤ጋዜጠኛው በሚጋፈጣቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት ከተደረገ በኋላ መድረኩ አቋም በመያዝ መግለጫ እንደሚያወጣ አስታውቀዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማልና አቶ ጌታቸው ረዳ በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ መጋበዛቸውን የገለፁት የመድረኩ ፀሀፊ፣ እስካሁን ግን ኃላፊዎቹ በስብሰባው ላይ መገኘት አለመገኘታቸውን አላሳወቁም ብለዋል፡፡
“የፕሬስ ነፃነት፣ የጋዜጠኞች ደህንነትና ልማት” በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የህግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት ዲን ዶ/ር አብዲሳ ዘርአይም እንደሚገኙና የመወያያ ሀሳብ እንደሚያቀርቡ አቶ ነብዩ ገልፀዋል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት ጋዜጠኞች ሀሳባቸውን በመግለፃቸው መንግስት የፀረ-ሽብር አዋጁን መሳሪያ በማድረግ ለእስር እየዳረጋቸው ነው” ያሉት አቶ ነብዩ፤ በዚህም የተነሳ ጋዜጠኞች በሥራቸው ደህንነት እንደማይሰማቸው ጠቁመው፣ “አፈናው ወደፊት እንዴት መቆም አለበት?” በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ከተካሄደ በኋላ  መድረኩ አቋም ይይዛል ብለዋል፡፡

Read 1850 times