Saturday, 21 June 2014 14:00

ኢዴፓ በአምስት ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ሊጠራ ነው

Written by  አበባየሁ ገበያው
Rate this item
(9 votes)

“በመጪው ምርጫ ከ80 በመቶ በላይ ድምፅ ለማሸነፍ እየተጋን ነው”

ኢዴፓ በመጪው ዓመት ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ለማድረግ በቀጣዩ ሐምሌ ወር  በአምስት ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚጠራ አስታወቀ፡፡ ከምርጫ 97 በፊት ወደነበርንበት አቋማችን  ተመልሰናል ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ በቀጣዩ ምርጫ ከሰማንያ በመቶ በላይ ድምፅ በማግኘት ፓርላማ ለመግባት ከወዲሁ ዝግጅት መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡
አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ከተመረጠ ወዲህ ከህዝብ ጋር የመገናኛ መድረክ አለመፈጠሩን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም ምክንያቱ የፋይናንስ እጥረት እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን ችግሩ ተቀርፎ በአምስት ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲውን ጽ/ቤቶች በየክልሉ ለማደራጀትና ለመክፈት በስፋት እየሰሩ እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ጫኔ፤ በአፋር ክልል አምስት ዞኖች እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ስምንት ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ ደጋፊዎችና አባላትን እንደመለመሉ አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው ከምርጫ 97 በፊት ወደነበረበት አቋሙ መመለሱን በመግለፅም በመጪው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ከ80 በመቶ በላይ ድምጽ በማሸነፍ፣ ፓርላማ ለመግባት ከወዲሁ በትጋት እየሰሩ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡  
ፓርቲው በመጪው ሐምሌ 12 በአዲስ አበባ መብራት ሃይል የመሰብሰቢያ አዳራሽ የመጀመሪያውን ህዝባዊ ስብሰባ የሚያካሂድ ሲሆን በመቀጠልም በመቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ሃዋሳና ናዝሬት ተመሳሳይ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያደርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2126 times