Saturday, 21 June 2014 13:47

መኢአድ የአባሎች ግድያና እስራት መባባሱን ገለፀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

      የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ በየቦታው በአባላቶቼ ላይ የሚደርሰው ግድያና እስራት ተባብሶ ቀጥሏል፤ ይህንንም አወግዛለሁ ሲል ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡ በምስራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ ደንጎሊማ ቀበሌ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ምሽት ላይ የፓርቲው የቀበሌ ተጠሪ የነበሩት አርሶ አደር ሞሳ አዳነ በታጣቂ ካድሬዎች ተደብድበው ህይወታቸው ማለፉን መኢአድ ገልጿል፡፡
በወረዳው የፓርቲው ምክትል ሰብሳቢና የዞኑ ወጣቶች ጉዳይ ተጠሪ መቶ አለቃ ደምመላሽ ጌትነት ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፣ ሟቹ አርሶ አደር ከዚህ ቀደም በመኢአድ አባልነታቸው የተነሳ ከእድርና ከቤተክርስቲያን እንዲገለሉ በመደረጋቸው፣ መገለሉ እንዲነሳላቸው ለወረዳው መስተዳደር አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡
የመኢአድ የቀበሌ ተጠሪው ባለፈው ቅዳሜ የወረዳው ታጣቂ ካድሬዎች በሆኑት አቶ አዲሱ ጫኔና አቶ ብርሀኑ ታመነ ተደብድበው ጭንቅላታቸው ላይ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው ለህልፈት እንደተዳረጉ የጠቆሙት መቶ አለቃ ደምመላሽ፤ አንደኛው ካድሬ ወዲያውኑ ሲያዝ ሌላኛው ከስርዓተ ቀብሩ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል፡፡
በዚያው በእነማይ ወረዳ ነዋሪና የመኢአድ አባል የሆኑት አቶ ይበልጣል ወንድሜነህ፤ ቤትህ ውስጥ መሳሪያ ደብቀሃል በሚል ቤታቸው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከተፈተሸ በኋላ ወደ እስር ቤት ትሄዳለህ ተብለው መወሰዳቸውንና እስካሁንም የገቡበት እንደማይታወቅ ፓርቲው አስታውቋል፡፡
“በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ጎንደር፣ ጭልጋ ወረዳ የመኢአድ ሰብሳቢ የሆኑት ሻምበል ንጉሴ ደርሶ፤ በእስርና በእንግልት ላይ ይገኛሉ” ያሉት የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን አለምነህ፤ በየክልሉና በየወረዳው የሚገኙ አባሎቻችም ላይ የሚደርሰው ግድያ፣ እስርና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የአቃቂ አካባቢ ነዋሪና የአዲስ አበባ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ጥጋቡ ደበላ፤ ባልታወቀ ምክንያት ቤታቸው ውስጥ ተገድለው መገኘታቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋሁን፤ አስክሬናቸው የተገኘው ከሞቱ ከሁለት ቀን በኋላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ይፋግ ቀበሌ ውስጥ የማዳበሪያ ብር ክፈል አትክፈል የሚል ውዝግብን ተከትሎ አቶ ሞላ ወረታ በተባሉ የመኢአድ አባል ላይ በተፈፀመባቸው ድብደባ፣ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም ህይወታቸው ማለፉንና በአላማጣ ከተማ የሚገኙ የመኢአድ አባል መምህር ኢያሱ ሁሴን በእስር ላይ እንደሚገኙም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ “በተለያዩ አካባቢዎች በፓርቲው አባላት ላይ አፈናና ግድያ እየተፈጸመ፣ የፓርቲው እንቅስቃሴም እየተገደበ ነው” ያሉት ኃላፊው፤ መንግስት በፓርቲው ላይ ወከባ እየፈጠሩ ያሉትን ካድሬዎች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ያስጠንቅቅልን ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የእነማይ ወረዳን ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ሙከራ ያደረግን ቢሆንም የወረዳው ፖሊስ አዛዥ የኢንስፔክተር መስፍንም ሆነ የወረዳው ወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ስልኮች ዝግ በመሆናቸው ምላሻቸውን ለማካተት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Read 2265 times