Saturday, 14 June 2014 12:42

ኔይማር፤ ሮናልዶና ሜሲ ዓለም ዋንጫን ማሸነፍ የሚፈተኑበት የስኬት ጣሪያ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ብራዚላዊው  ኔይማር ዳሲልቫ ሳንቶስ  ሮናልዶ እና ሜሲ ለዓለም ዋንጫው ድምቀት የሚሆኑ ምርጥ ተጨዋቾች ናቸው ሲል ተናገረ፡፡ በባርሴሎና ክለብ እስከ 2018 ለመጫወት የኮንትራት ውል የፈፀመው ኔይማር ዳሲልቫ ሳንቶስ በሁለት ጎሎች ዓለም ዋንጫውን መጀመሩ ለብራዚል 6ኛ የዓለም ዋንጫ ስኬት ከፍተኛ ተስፋ ያሳደረ ሆኗል፡፡ ሶስቱ ተጨዋቾች ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ለዓለም ዋንጫ ድል ለማብቃት ብቻ ሳይሆን በኮከብነት ለሚሰጡ ልዩ ሽልማቶች በዋና እጩነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የ29 ዓመቱ ክርስትያኖ ሮናልዶ አገሩን በአምበልነት እየመራ በዓለም ዋንጫ ደማቅ ታሪክ የመስራት እድሉ ብራዚል ላይ የመጨረሻ ነው፡፡ ለ26 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲም ከዘንድሮ ዓለም ዋንጫ የተሻለ አጋጣሚ የለም፡፡
ለ22 ዓመቱ ኔይማር ዳሴልሻ ግን ይህን የስኬት ጣሪያ ለማስመዝገብ ሁለት ዓለም ዋንጫዎች ይቀሩታል፡፡
ሮናልዶና ሜሲ በክለብ ደረጃ የሚወዳደሩባቸውን ሊጎች በጎሎች  እያንበሸበሹ፤ ዋንጫዎችን እየሰበሰቡ፤ የቆዩ ሪከርዶችን እየሰባበሩና አዳዲስ እያስመዘገቡ፤ የኮከብ ተጨዋችነት ሽልማቶችን እየተፈራረቁ ሲጎናፀፉ ቆይተዋል። ብቸኛው የቀራቸው የስኬት ጣሪያ ዓለም ዋንጫ ብቻ ነው። ሁለቱም ተጨዋቾች በክለብ ደረጃ የተሳካላቸውን ያህል  በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው የላቀ ውጤት አለማስመዝገባቸው ሁሌም  ለትችት ይዳርጋቸዋል፡፡
በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ሮናልዶ ከፖርቱጋል፤ ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ ከአርጀንቲና ጋር 3ኛውን የዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸውን ያደርጋሉ፡፡ ሁለቱም ተጨዋቾች በዓለም ዋንጫው አገሮቻቸውን ተሸክመው የማራዶና፤ የፔሌን፤ የክሩፍና የዚዳን ስኬት ማምጣታቸው ቢጠበቅም  የሚሳካላቸው ግን አይመስልም፡፡ ከብራዚሉ 20ኛው ዓለም ዋንጫ በፊት በሁለት ዓለም ዋንጫዎች ለአርጀንቲና 571 ደቂቃዎች የተጫወተው ሜሲ ያስመዘገበው አንድ ጎል ብቻ ሲሆን ሮናልዶም ባለፉት ሁለት ዓለም ዋንጫዎች በፖርቱጋል ማልያ 754 ደቂቃዎች ተሰልፎ ያገባው ሁለት ብቻ ነው።  ሶስት የዓለም ዋንጫ ከተሳተፉት የቀድሞ ተጨዋቾች  ጋር ሲነፃፀር ሮናልዶና ሜሲ ምን ያህል ወደኋላ እንደቀሩ ያሳያል።
ዴንማርኩ ዳል ቶማሰን 5፤ የብራዚሎቹ ፔሌ 12 ሮናልዶ 15 እንዲሁም ዘንድሮ የምንግዜም ከፍተኛ ክብረወሰኑን ከሮናልዶ ይነጥቃል የተባለው ሚሮስላቭ ክሎስ 14 የዓለም ዋንጫ ጎሎች በስማቸው አስመዝግበዋል።
ሜሲ በባርሴሎና ክለብ 277 ጨዋታዎች አድርጎ 243 ጎሎች ሲያስመዘግብ ሮናልዶ ደግሞ በ3 ክለቦች ስፖርቲንግ ሊዝበን፤ ማን ዩናይትድና ሪያል ማድሪድ 386 ጨዋታዎች በማድረግ 264  ጎሎች አስቆጥሯል፡፡
በክለብ ደረጃ ሊዮኔል ሜሲ 6 የሊግ፤ 3 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፤ ሌሎች ተጨማሪ 4 ዋንጫዎችን ወስዷል፡፡ ሮናልዶም በ3 ክለቦች 4 የሊግ፤ ሁለት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ሌሎች 4 ዋንጫዎችን አግኝቷል፡፡ 4 ጊዜ በዓለም ኮከብ ተጨዋቾች የወርቅ ኳስ የወሰደው ሜሲ ለአርጀንቲና በ84 ጨዋታዎች 37፤ ሁለቴ የወርቅ ኳስ የተሸለመው ሮናልዶ ለፖርቱጋል በ110 ጨዋታዎች 49 ጎሎች አላቸው፡፡


Read 3449 times