Saturday, 14 June 2014 12:40

ከጥሎ ማለፍ እስከ ዋንጫው የደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ ቡድኖች ይተናነቃሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   በ20ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ተሳታፊ በሚሆኑ 32 ብሄራዊ ቡድኖች 5 የፊፋ ኮንፌደሬሽኖችን ይወክላሉ፡፡ ከጥሎ ማለፍ እስከ ዋንጫው ትንቅንቅ የሚደረገው ግን በሁለት አህጉራት ደቡብ አሜሪካና አውሮፓ ተወካዮች እንደሚወሰን ይገልፃል፡፡ ለሻምፒዮናነት በከፍተኛ ደረጃ ከተጠበቁት 4 ቡድኖች ሁለቱ ከደቡብ አሜሪካ ሁለቱ ከአውሮፓ  ናቸው፡፡ ብራዚል፤ አርጀንቲና፤ ስፔንና ጀርመን ናቸው፡፡  
ብራዚል በአዘጋጅነት ዓለም ዋንጫን ለማሸነፍ የበቃች 7ኛዋ አገር ሆና ለመመዝገብ ታቅዳለች፡፡ ባለፉት 19 ዓለም ዋንጫዎች የውድድሩ አስተናጋጅ ከነበሩ አገራት መካከል 6 ብሔራዊ ቡድኖች ዋንጫውን በሜዳቸው አንስተዋል፡፡ በ1930 እ.ኤ.አ እንግሊዝ፣ በ1974 እ.ኤ.አ ጀርመን፣ በ1978 እ.ኤ.አ አርጀንቲና እንዲሁም በ1998 እ.ኤ.አ ፈረንሳይ ናቸው፡፡ በ1950 እ.ኤ.አ ላይ ብራዚል እንዲሁም በ1958 እ.ኤ.አ ስዊድን ባስተናገዱት ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ደረጃ ሲወስዱ፤ በ1962 እ.ኤ.አ ቺሊ፣ በ1990 እ.ኤ.አ ጣሊያን እንዲሁም በ2006 እ.ኤ.አ ጀርመን ውድድሩን አዘጋጅተው 3ኛ ደረጃን አግኝተዋል፡፡  
የዓለም ዋንጫው በደቡብ አሜሪካ  አህጉር ዘንድሮ የሚካሄደው ለ8ኛ ጊዜ ነው፡፡ ከ20ኛው የዓለም ዋንጫ በፊት ለ7 ጊዜያት ውድድሩ በደቡብ አሜሪካ ሲስተናገድ ሁሉንም የዚሁ አህጉር ተወካዮች አሸንፈውታል፡፡ በ1930 እ.ኤ.አ ኡራጋይ አዘጋጅታ ኡራጋይ፣ በ1950 እ.ኤ.አ ብራዚል አዘጋጅታ  ኡራጋይ፣ በ1968 እ.ኤ.አ  ቺሊ አዘጋጅታ ብራዚል፣ በ1972 ብራዚል፣ በ1976 አርጀንቲና፣ በ1986  እ.ኤ.አ ብራዚልና በ1994 እ.ኤ.አ ብራዚል ናቸው፡፡  የአውሮፓ ቡድኖች በደቡብ አሜሪካ በተዘጋጁት 7 የዓለም ዋንጫዎች በ4 ለፍፃሜ ደርሰው ዋንጫውን ማግኘት አልተሳካላቸውም፡፡
ከ19 ዓለም ዋንጫዎች አስሩን ያሸነፉት የአውሮፓ ቡድኖች ሲሆኑ ዘጠኙን ደግሞ የደቡብ አሜሪካ ቡድኖች አሸንፈዋል፡፡ ለአውሮፓ አህጉር 10 የዓለም ዋንጫዎችን ያገኙት አምስት አገራት ሲሆኑ፤ 4 ጊዜ ጣሊያን፤ 3 ጊዜ ጀርመን እንዲሁም እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ያሸነፉት እንግሊዝ ፈረንሳይ እና ስፔን ናቸው፡፡ ለደቡብ አሜሪካ አህጉር 9 የዓለም ዋንጫዎችን ያሸነፉት  ደግሞ ሶስት አገራት ሲሆኑ፤ 5 ጊዜ ብራዚል፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ ደግሞ ኡራጋይ እና አርጀንቲና ናቸው፡፡ ባለፉት 19 ዓለም ዋንጫዎች ለፍፃሜ ጨዋታ መድረስ የቻሉት የደቡብ አሜሪካ እና የአውሮፓ ተወካዮች ብቻ ናቸው፡፡ ከሁለቱ አህጉራት ውጭ ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻሉት አገራት ከሌሎች ኮንፌደሬሽኖች የተገኙት ሁለቴ ብቻ ሲሆን በ1930 በመጀመርያው ዓለም ዋንጫ ሰሜንና መካከለኛው አሜሪካን የወከለችው አሜሪካ እና በ2002 እኤአ ኤስያን የወከለችው ደቡብ ኮርያ ያስመዘገቡት ናቸው፡፡ ከአፍሪካ ቡድኖች ደግሞ ሶስት አገራት ለሩብ ፍፃሜ መድረሳቸው ትልቁ ውጤት ነው፡፡


Read 2023 times