Saturday, 14 June 2014 12:36

ባለታክሲዎች በአሜሪካና በአውሮፓ አመፁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በስፔን ርዕሰ ከተማ በማድሪድ ወደ 15ሺ ታክሲዎች ቢኖሩም፣ ረቡዕ እለት ለምልክት ያህል አንድም ታክሲ አልነበረም። የለንደን ታክሲዎችም ድምፃቸውን አጥፍተው ውለዋል፡፡ በመኪኖቹ ፋንታ ሾፌሮች ናቸው ሲጮሁ የነበሩት፡፡ 4ሺ የለንደን ባለታክሲዎች ቅሬታቸውን ለማሰማት በከተማዋ ዋና ዋና ጐዳናዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። በጀርመንም፣ በሺ የሚቆጠሩ የታክሲ ሹፌሮች በርሊን ከተማ በሚገኘው ኦሊምፒክ ስቴዲየም ዙሪያ ተሰብስበው ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።
የፓሪሶቹ ባለታክሲዎች የባሰባቸው ናቸው። ወደ አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደውን መንገድ ዘግተው ነው የቆሙት። በሌሎች ጎዳናዎች ደግሞ ታክሲያቸውን በዝግታ እያንቀራፈፉ የትራፊክ ጭንቅንቅ ሲፈጥሩ ውለዋል። ማርሴ፣ ሚላን፣ ሮም፣ ኔፕልስ... ትልልቆቹ የጣሊያን ከተሞችም ከባለታክሲዎች አድማ አላመለጡም። ባለታክሲዎች ሰው ሲያመላልሱ ሳይሆን፣ የቅስቀሳ ወረቀት ሲበትኑ ቀኑን አሳልፈውታል፡፡
ለንደን፣ ፓሪስ፣ ሮም፣ በርሊን፣ ማድሪድ... በአውሮፓ ዋና ዋና ከተሞች፣ ባለታክሲዎች በአድማ ስራ ያቆሙት ለምን ይሆን? ተፎካካሪ ስለመጣባቸው ነው። ባለ መኪና ሁሉ ተፎካካሪያቸው ሆኗል - ኡበር በተሰኘ ኩባንያ ምክንያት።
“ኡበር” አስገራሚ ኩባንያ ነው፡፡ በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ከተሞች፣ የታክሲ አገልግሎት ረዥም እድሜ አስቆጥሯል - ከ80 ዓመት በላይ። ኡበር ግን፤ ገና የ5 ዓመት ጨቅላ ነው። እንዲያም ሆኖ፤ በአለም ካሉት የታክሲ አገልግሎት ድርጅቶች ሁሉ ይበልጣል። ከታላቁ የእንግሊዝ አየርመንገድም ይልቃል። አይገርምም? የድርጅቱ ቢሮ የሚገኘው አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ነው። ግን በአለም ዙሪያ በመቶ ከተሞች አገልግሎት ይሰጣል። ይሄስ ይገርማል? የታክሲ አገልግሎት የሚያቀርብ ኩባንያ ነው ቢባልም፤ ታክሲዎች የሉትም። አጃኢብ ነው፡፡ እና  የኩባንያው ስራ ምንድነው?
የኩባንያው ዋና ስራ፤ ባለመኪኖችንና ተሳፋሪዎችን፣  በኢንተርኔት አገናኝቶ “ማዳበል” ነው። አሁንማ ኡበር በከፈተው ቀዳዳ ሉሎች ኩባንያዎች እየገቡ፣ ነባሩ የታክስ አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ መልኩ ተቀይሯል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ 11 ሰዓት ላይ፣ ሳሪስ አካባቢ ካለው ቢሮ ወጥተው፣ የአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎችን... ጎተራን፣ መስቀል አደባባይን፣ መገናኛን አቆራርጠው ኮተቤ አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤትዎ እንደሚያመሩ ያውቃሉ እንበል። ቶዮታም ይሁን ቢኤምደብሊው…የግልዎ አስተማማኝ መኪና ይዘዋል። ግን የነዳጅ ወጪው አልቻሉትም። በየጊዜው ይወደዳል። ሰሞኑን የነዳጅ ዋጋ እንደገና ጨምሮ የለ! ወጪውን የሚጋራ ሰው ቢያገኙ ትልቅ ግልግል ይሆን ነበር። 11 ሰዓት ላይ እርስዎ በሚሄዱበት አቅጣጫ ታክሲ ለመሳፈር የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸው አያጠራጥርም። የትንንሾቹ ታክሲዎች ዋጋ ቀላል አይደለም። “አነስ ባለ ዋጋ የሚያሳፍረው ባለመኪና ባገኝ” እያለ ይመኛል መኪና ያልያዘ እግረኛ፡፡
ግን ምን ዋጋ አለው? ፈላጊና ተፈላጊ፣ ባለ መኪናና ተሳፋሪ እንዴት ይገናኙ? አስቸጋሪ ነው። ማለቴ... ድሮ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ግን ችግር የለም። ከርስዎ የሚጠበቀው ነገር ቢኖር፤ መቼ  ወዴት እንሚጓዙ የሞባይል ስልክዎ ላይ መመዝገብ ብቻ ነው - ለምሳሌ “11 ሰዓት ላይ ወደ ኮተቤ” ብለው ይመዘግባሉ፡፡ መኪና የሌለውና ተዳብሎ መሄድ የሚፈልግ ሰው በበኩሉ፤ ሞባይሉን ከኪሱ አውጥቶ ... ኮተቤ መሄድ እፈልጋለሁ ብሎ ይመዘግባል። የስማርት ፎን አሪፍነት... ነካ ነካ በማድረግ መረጃ መለዋወጥና ትዕዛዝ ማስተላለፍ ይቻላል። ባለመኪናና ተሳፋሪ ፈላጊና ተፈላጊ መገናኘት የሚችሉበት ዘዴ ተፈጠረ ማለት ነው።
 ባለመኪናው የነዳጅ ዋጋን የሚጋራለት ተሳፋሪ ያገኛል። እግረኛው ደግሞ አነስ ባለ ክፍያ የሚያሳፍር ባለመኪና ያገኛል። የድሮውን ችግር የሚያስወግድ አዲስ ዘዴ የተፈጠረው ኡበር በተሰኘው ኩባንያ ነው። ቢዝነስ ማለት፣ ችግርን የሚያስወግድ ወይም የሚያቃልል መፍትሄ ማቅረብ ነዋ። እናም ከክፍያው 20% ይወስዳል። ተሳፋሪው ሃምሳ ብር ቢከፍል፣ አርባ ብር ለባለመኪናው፣ አስር ብር ደግሞ ለኡበር ይሆናል። ተመሰጋግነው መለያየት ነው። እናም ሁሉም ተደሰተ ይባላል።
“እኛ ደስተኛ አይደለንም” ባይ ናቸው - ባለታክሲዎች።
ከአምስት አመት በፊት የተመሰረተው ኡበር፣ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደንበኞችን የሚያስተናግድ የ17 ቢሊዮን ዶላር ኩባንያ ሆኗል። በእርግጥ አንዳንድ የታክሲ ሾፌሮች ራሳቸው፣ የኡበር ደንበኛ ሆነዋል። ቆመው ተሳፋሪ ሲጠብቁ ከመዋል፣ በኡበር አማካኝነት ከተሳፋሪ ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት መገናኘት ይሻላቸዋል። ብዙ የታክሲ ሾፌሮች ግን፣ ነባሩን አሰራር መተው አልፈለጉም።    “በከተማ የትራስፖርት ቢሮ ተመዝግበው ፈቃድ ያላገኙ መኪኖች የታክሲ አገልግሎት እንዳይሰጡ የከተሞቹ ህግ ይከለክላል። ኡበር ይህንን ህግ ይጥሳል” የሚሉት ባለታክሲዎች፣ አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ጠይቀዋል - በተቃውሞ ሰልፍና በአድማ። ግን፤ እንዲህ አይነት አገልግሎቶችን ማስቆም አይቻልም በማለት የዘገበው ቢቢሲ፤ ከሁለት መቶ አመታት በፊት፣ የእንግሊዝ ሸማኔዎች የልብስ ፋብሪካዎችን ካላወደምን ብለው ያካሄዱ የተቃውሞ ሰልፍና አመፅ ብዙም አላዛለቀም ብሏል።

Read 2077 times