Print this page
Saturday, 14 June 2014 12:31

የኢትዮጵያ የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር የሰጠው ማስተባበያ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

       ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው የጋዜጣችሁ ዕትም፣ ጤና ዓምድ ላይ “የጥርስ ህክምና ክሊኒኮች በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ናቸው ተባለ” በሚል ርዕስ ያወጣችሁትን ዘገባ የኢትዮጵያ የጥርስ ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ተመልክቶታል፡፡
በጥርስ ህክምናም ሆነ በየትኛውም የህክምና ዘርፍ ያሉ ጉድለቶችን በማሳየት እርምት እንዲደረግና ህብረተሰቡ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ማሳሰባችሁ አግባብነት ያለው ነው፡፡ ሆኖም የሰራችሁት ዘገባ ማህበረሰቡን ፍርሀት ውስጥ የሚከትና የተሳሳት መረጃ የሚሰጥ  ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
ከሁሉም በላይ በማንኛውም ዜጋ ላይ እንዲደርስ የማንመኘው ችግር የደረሰባት እህታችን፤ የኛም ጉዳይ ነችና ህመሟ ይሰማናል፤ ችግሯም ይመለከተናል፡፡ ነገር ግን ባለሙያ ያልሆኑ ጥቂት ሰዎች በሚሰሩት የተሳሳተ ስራ /በእርግጥ የተባለው ታሪክ ከተከሰተ/ ምክንያት “አብዛኞቹ ክሊኒኮች” ተብሎ መዘገቡ በእጅጉ ያሳምማል፡፡
ለመሆኑ አንድ የጥርስ ህክምና ክሊኒክ ለመክፈት የሚያስፈልገውን መስፈርት አንብባችሁታል? ታዲያ ያን ሁሉ ገንዘብ አፍስሶ፣ የተሳሳተ ስራ በመስራት የሚደሰት ባለሙያ ይኖራል? ለመሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን መቀቀያ ማሽን ዋጋው ስንት ነው? ደግሞስ ሃኪሙ ምን ያህል ሞኝ ቢሆን ነው በአግባቡ ንፅህናው ባልተጠበቀ መሳሪያ እየሰራ ከታካሚውም በላይ እራሱን ለበሽታ የሚያጋልጠው? እውነት እናውራ ከተባለ አይመስልም!!!
ዘገባውን የሰሩት ጋዜጠኛስ መሳሪያዎቹን “አየሁ አላየሁም” የሚሉት፣ ስለህክምና መሳሪያዎቹ እውቀት ኖሯቸው ነው ወይስ የነገሯቸውን ብቻ ይዘው ነው? መቼም ስለሚሰሩት ዘገባ መረጃ ቀድሞ መጠየቅ ግዴታ ይመስለናል፡፡ በእርግጥ ዕውቀቱ፣ ችሎታውና ልምዱ የሌለው በልምድ የሚሰራ ተራ ግለሰብ የህክምና ስህተት ሰራ ቢባል ያስኬዳል፡፡ ባለሙያ ያልሆነ ሰው ምን እንደሰራና ምን እንዳጠፋ ለይቶ አያውቅምና፡፡ እንዲህ ያለው ዘገባ፣ በአሁኑ ሰዓት የህክምና ባለሙያዎች ማህበረሰቡን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እያገለገሉ እንዳሉ ካለመረዳት ወይም ለመረዳት ካለመፈለግ የመነጨ በመሆኑ ማዘናችንን እንገልፃለን፡፡
የእህታችን ታሪክ የተገለፀበት መንገድና የተብራሩት ችግሮችን ለመተቸት እውነተኛውን ታሪክ ማግኘትና መገምገም ይጠበቅብናል፡፡ ሳናነሳ የማናልፈው ግን የጥርስ ህክምና ለመስጠት የሚችሉ የተለያዩ ባለሙያዎች መኖራቸውን እንድታወቁ ሲሆን ዘገባው የሚገልፀው አይነት የጥርስ አካል አለመኖሩንና በተጠቀሰው ሆስፒታል ውስጥ የጥርስ ህክምና ክፍል እንደሌለ እንዲሁም የጥርስ ሀኪም አለመኖራቸውን ነው፡፡ አስተያየት ሰጥተዋል የተባሉት የጥርስ ሀኪምም የማህበሩ አባል አይደሉም፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ጠይቀንም የሚያውቃቸው አንድም ሰው አላገኘንም፡፡ ከአንድ ባለሙያም ይህን አይነት አስተያየት እንደማይሰጥ ስለምናምን፣ የዘገባው አላማ ሌላ ሊሆን እንደሚችል ገምተናል፡፡
ህብረተሰቡ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ማድረግ፤ ባለሙያውም ተገቢውን ስራ በተማረበት መስክ እንዲፈጽም ግዴታዎቹን በአግባቡ ተወጥቶ፣ መብቱም እንዲከበርለት መስራት የተቋቋምንበት ዋና ዓላማችን ነው፡፡ ለዚህም ሚዲያው ያለው ድርሻ ጉልህ መሆኑን ከልባችን እናምናለን፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን አቅምና የባለሙያውን ሁኔታ ባለማጤን “አብዛኞቹ” ክሊኒኮች በሚል የወጣው ዘገባ፤ ለህብረተሰቡ የተሳሳተ መረጃ በማድረስ፣ ሥራችንን ካለውም በላይ ከባድና ውስብስብ ስለሚያደርግብን እባካችሁ በጥንቃቄ ዘግቡ እንላለን፡፡ በተረፈ ማናቸውንም መረጃዎች ለመስጠትና በዘርፉ ለሚከሰቱ ችግሮች አፋጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድና በትብብር ለመስራት ፈቃደኞች መሆናችንን እንገልፃለን፡፡  

Read 2122 times
Administrator

Latest from Administrator