Saturday, 14 June 2014 12:22

ለማሸነፍ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ጋሻው በጠባቧ ስቱዲዮ ውስጥ በዘረጋት አነስተኛ አልጋ ላይ በጀርባው ተንጋሎ ይቃትታል፡፡ በእልህ ይቃጠላል ፣ በብሽቀት ይወራጫል፣ በምኞት ይንጠራራል . . .
እንደተንጋለለ ዓይኑን ፊት ለፊቱ በሰቀለው ፎቶ ግራፍ ላይ ወረወረ፡፡ እይታው እዚህ ትልቅ ባለቀለም ፎቶ ግራፍ ላይ ካረፈ በቀላሉ አይነሳም፡፡ ቀይ ዳማ ሴት፣  አንገቷን ቀለስ አድርጋ በዓይኖቿ ጠርዝ ታስተውለዋለች፡፡ ዛሬስ «አይ አሸናፊው» እያለች የምታሾፍበት መሰለው፡፡
ትልቁን የሀናን ፎቶ ግራፍ ዘወትር በዓይኑ እንዲዳብሰው ከሚጋብዙት ነገሮች ዋንኛው ዳሌዋ ነው ፡፡
ዳሌዋ ፣ልክ እንደ ዋንጫ ከላይ ሰፋ ብሎ ወደታች እየጠበበ መውረዱ ያስደንቀዋል፡፡
«ወይ የሰው ልጅ !»አለ ባግራሞት «ለካስ የዋንጫን ዲዛይን የኮረጀው ከውብ ሴቶች ዳሌ ነው።
አቤት ተንኮል ! ለካስ ለዋንጫ የመንሰፍሰፋችን ምስጢር ይህ ሆኗል? ሴቶቹም ቢሆኑ ለራሳቸው የአካል ቅርፅ ያላቸው ፍቅር ሳያውቁት ለዋንጫ እንዲሳቡ ያደርጋቸዋል፡፡ እኛም እንዲሁ ሳይገባን የወንድነታችን ስሜት በረቀቀ ሁኔታ ይማልላል. . . » እያለ ይፈላሰፋል፡፡
* * *
. . .  ሃና በፎጣ ተጠቅልላ ከባኞ ቤት እንደወጣች ወደ መኝታ ክፍሏ አመራች፣ ከውስጥ ሆና በሩን ዘጋች፡፡ ያገለደመችውን ፎጣ ከላይዋ ላይ ገፋ በመጠቅለል  ወረወረችው፡፡ ዕርቃኗን ሆነች ፡፡ እየተዟዟረች  ቁመናዋን  ገመገመች  ፣  በተፈጥሮዋ  ተደሰተች፡፡ «የሚሊኒየሙ አሸናፊ ሴት!»  አለችና ፈገግ ፣ ወዲያው ኮስተር፣ እንደመጸየፍ ደግሞ ፈገግ፣ አይኗን ቦዘዝ፣ ሰለምለም . . .   ይህን ጊዜ ጋሻው ወደ አዕምሮው ገባ ፡፡
አፈረች፡፡ እሮጣ  የወረወረችውን ፎጣ አነሳች፣ ተሸፋፍና ቆመች፡፡ ልቧ ደነገጠ፣ ሌሊት በህልሟ አይታዋለች፡፡ ጭልጥ ባለ የሳር ሜዳ ላይ ያገኛታል . . .
በህልሟ፡-
ይቀርባታል «ዛሬ ራቁትሽን ፎቶ ላነሳሽ ፈልጌ ነበር፡፡»
«ምንም ሳልለብስ?»
«አዎ! ዕርቃንሽን ትሆኚና እኔ በማሳይሽ ስታይል
አነሳሻለሁ፡፡ በዚህ ፎቶ የአለም «ሚስ ሞዴሊንግ»  አሸናፊዎች እንሆናለን!»
ትጓጓለች፣  ታቅማማለች፣  ይህን  ጊዜ  ጋሻው  ስውር ይልባታል «እሺ» ትላለች ዛሬ በእውኗ፡፡ ለሕልሙ አለም ጥያቄ በገሃዱ ዓለም መልስ ሰጠች። የሰማት ግን የለም፡፡ ብቻዋን ናት መኝታ ቤቷ ውስጥ፡፡
«እንዴ! ጋሻውንም ልወደው ነው?» ራስዋን በፍርሃት ጠየቀች፡፡ እሷን እንደመውደድ የሚያስፈራት ነገር የለም፡፡
ሰዓቷን ተመለከተች፡፡ ከቶማስ ጋር የመገናኛቸው ሰዓት! «የራሱ ጉዳይ!» አለች ብስጭት ብላ... ሦስት ጊዜ በተከታታይ ቀጥሯት መቅረቷን አልረሳችም፡፡ አሁን ደሞ አራተኛ መሆኑ ነው፡፡
«አሁንስ ያመራል»
«ያምርራ! ምን ያመጣል!» ከራስዋ ጋር ሙግት ገጠመች፡፡ በግቧ መሰረት ማንነቷን ማግኘት፣ የዓለም ምርጥ ሞዴሊስት በመሆን ራሷን፣ ቤተሰቧን፣ ሀገሯን ማኩራት ይጠበቅባታል፡፡ የዚህንም ጊዜያዊ የምስክር ወረቀት ከጋሻው እቅፍ ውስጥ መውሰድ ይኖርባታል፡፡
«የእኔ እጣፈንታ አለማቀፋዊ ዝና ነው! ከጋሻው በቀር የሚቀርቡኝ ወንዶች ሁሉ፣ ሚስት እንድሆናቸው፣ ምግብ እንዳበስልላቸው፣ ልጅ እንድወልድላቸው፣ ምናምን ነው የሚፈልጉኝ። ድንጋዮች! ከእንግዲህ እኔን ለእንዲህ  ዓይነቱ አነስተኛ ዓላማ ማጨቱ አበቃ፡፡
ዛሬ ሄጄ ከምንም በላይ ውድ የሆነ ዓላማዬን መስመር ማስያዝ አለብኝ፣ ሰማይ ጥግ ወደሚገኘው ዙፋኔ አስፈንጥሮ ለሚያደርሰኝ ለጋሻው በመውጣት፣ ፍቅርን በልቡ ማቀጣጠል፣ እሱን የሙጥኝ ይዤ አብሬው መተኮስ. . . »
እቅዷን በሃሳቧ እያውጠነጠነች ከመስታወቱ ዞር ብላ ልብስ መራረጠች፡፡ ከጉልበቷ በላይ የምትንጠለጠል ጉርድ ቀሚስ፣ እንበርቷን የምታሳየው ካኔተራ፣ ክፍት ጫማ፣ ከመስታወቱ ፊት ቆመች ቅልል ያለች ፍልቅልቅ ሴት «እምጵዋ!» የራሷን ምስል ሳመች ፡፡
ብር ብላ ከግቢያቸው ወጣች፡፡ ሚኒባስ ታክሲ መጣ፡፡ የጋቢናውን በር ከፍታ ገባች፡፡ ሹፌሩ ተነቃቃ፣ የሙዚቃውን ድምጽ ጨምሮ ተፈተለከ፡፡
የሞባይል ስልኳ በንዝረት መጥራት ጀመረች፣ ቁጥሩን ተመለከተችው፣ ቶማስ ነው! አላነሳችውም። ደጋግሞ ነዘራት፣ ዝም አለችው «ግፋ ቢል ያቺ ሳንቲሙ ነች የምትቀርብኝ ፣ ዘላለም በሱ ድጎማ እኖራለሁ እንዴ ? ገደል ይግባ !» እያጉረመረመች ወንበሯ ላይ ተመቻቸች፡፡
* * *
ጋሻው ከአስር ለሚበልጡ ዓመታት ፍላጎቱን ገድቦ፣ትዳር ሳይመሰርት፣ ንብረት ሳያካብት ፣ ትኩረቱን በሙሉ ሥራው ላይ በማድረግ ዓለማቀፋዊ አሸናፊነትን ለመቀናጀት ወጣ፣ ወረደ፣ አሸናፊነት እንደከበረ እንቁ ውድ ሆነችበት፡፡ ለበርካታ ጊዜያት፣ ተሳካልኝ ሲል ተንደባሏል፡፡
«አረ የድል ያለህ !» ውስጡ ጮኸ፡፡ እጁን ወደ ራስጌው አካባቢ ሰዶ አንድ ኤንቨሎፕ አወጣ፣ ሲውዲን ፣ እስቶኮልም ሚገኘው ዓለም አቀፍ የፎቶ ግራፍ ውድድር አዘጋጅ ማዕከል የተላከ ነው፡፡ በውስጡ መጽሔት ይዟል፡፡
አሱም የዚህ ውድድር ተካፋይ ነበር፡፡ በመጽሔቱ የላይኛው ሽፋን ላይ አሸናፊ የሆነው የዓመቱ ምርጥ ፎቶ ታትሟል፡፡ ምስሉ አክሊል የደፋች ንግስት በዙፋኗ ላይ እንደተቀመጠች ያሳያል፣ ድባቡ በጣም ደስ አለው፡፡ ፀጥታን ሳይቀር የመዘገበ ድንቅ የእንግሊዝ ሀገር ፎቶ ነው፡፡ ክብር፣ ውበትና ሰላም ይነበብበታል፡፡
መጽሄቱን ገለጠው፣ የሕንድ ቆንጆ! አሁንም
ገለጠው፣ እርጅና በአስፈሪ ክንዱ የደቆሳት የጀርመን አዛውንት! አረጋዊነትን ውብ አድርጎ አቅርቧል፡፡
አሁንም ገለጠው፣ የሩቅ ምስራቅ ልጃገረድ ዓይኗን ጭፍን አድርጋ ተንከተከተችበት! ቶሎ ገለጠው፡፡ አሁንም ገላለጠው! የሱ ሃና የለችም፡፡
እርር አለ! ወደ ፎቶ ግራፍ ሙያ የተሰማራበትን ቀን አስታውሶ ተፀፀተ፡፡ በመስራት ያሳለፋቸውን ከአስር የማያንሱ ዓመታትን ረገመ፡፡ አልቅሶ ቢወጣለት ተመኘ፣ ይህንንም አልቻለም!
በሩ ተንኳኳ. . . ከነ እልሁ፣ ከነብግነቱ ተነስቶ ከፈተው፡፡
ሃና ነች፡፡
ዓይኖቹ የጋለ ብረት መስለዋል፣ በመጀመሪያ ያረፋት በጡቶቿ ክፍላት ላይ ነው፣ ደነገጠ ፡፡
«አንድ» አለች በልቧ፡፡
ከዚያም  እይታው  ቁልቁል  ተንሸራቶ  ጭኖቿ  መሀል ተሰነቀረ፡፡
«ሁለት»
ወዲያው ሽቅብ አነጣጥሮ ከናፍሮቿን ቃኘ
«ሦስት» ፈገግ አለች፡፡
ከመቅጽበት ዓይኖቹን በዓይኖቿ ውስጥ ሰደዳቸው፣ ፍትወተ ሥጋ ቦግ ብሎ ታየው፡፡ አሁን እሱም ሳቀ፡፡ «ታድያስ ሃኒ» እጁን ዘረጋላት፡፡
የቀኝ ጉንጯን አስጠጋችለት፡፡
ሳመው፡፡
የግራ ጉንጯን ሰጠችው፡፡ ደገመው፡፡
ጉንጮቿ የተቀደሱላት መሰላት፡፡ እፎይታ ተሰማት፡፡
ወደ ውስጥ እንድትዘልቅ ጋበዛት፡፡ ሰተት ብላ ገባች . . .
ከሴቶች ጋር የሚኖርህ ቀረቤታ ላይ ጥንቃቄ ማድረግህን አታላላ፡፡ ሴቶቹን ሳይሆን እነሱን ተከትሎ የሚመጣው ትኩረትህን የሚሰርቅህን ስሜት ፍራው፣ ጥላው ሽሸው! ይህ ስሜት ባንተ ላይ ሲበረታ፣ስራ አስፈትቶ በሐሳብ ሲያናውዝ አይተኸዋልና የገዛ ህሊናው አንሾካሾከለት፡፡
ሃና ከስቱዲዮና   መኝታ ቤቱ ጋር በተያያዘችው ጠባብ ሳሎን ውስጥ ነግሳለች፡፡
«ዋው. . . ደረትህ እንዲህ ፀጉር በፀጉር አይመስለኝም
ነበር»
አሁን ይሄ ምን ያስደንቃል? በውስጡ ተቃወመ።
«ወደ ዓርባ ምንጭ እሄዳለሁ ያልከው መቼ ነበር?»
«ነገ ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ ከዚህ እወጣለሁ»
ዓይኖቹን ማስቀመጫ እንዳጣለት ዕቃ እያንከራተተ መለሰላት፡፡
«ለምን እኔም አብሬህ አልሄድም? ወደ ደቡብ  እኮ ምንም ሀገር አላውቅም» በዓይኖቿ ቀስፋ ይዛው ትማፀነዋለች፡፡
«በእውነት?»
«ጋሻዬ ሙት ስልህ» ገላዋ ሁሉ በራ፡፡
«እነ ላንጋኖ፣ ሻላ፣ አዋሳ ሐይቆችን አታውቂያቸውማ?»
«የት አባቴ ሄጄ? »
«አዞ፣ ጉማሬ፣ ሰጎን  አይተሸ አታውቂማ?»
«ጋሻዬ ስሞትልህ?» ቅላፄዋ ሊያስፈነጥዘው ደረሰ፡፡ ሁለንተናው ሞቀ «በይ እንግዲህ ለለሊት 12 ሰዓት ተዘጋጂ ፣ እወስድሻለሁ»
«በጣም አመሰግናለሁ ጋሻዬ!»  ተወርውራ ተጠመጠመችበት፤ ዓይኖቹ ከስቱዲዮ ጋር ከተያያዘችው የመኝታ ቤቱ በር ላይ ተጣበቁ፡፡ የተገዛለት አላማ ተፈተነ፡፡
* * *
እሁድ፡፡
ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት፡፡
2000 ዓ.ም
በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል፣ ከጂንካ ወጣ ብላ የምትገኝ፣ ቃቆ የምትባል ቦታ ላይ ፡-
«ከምድር እኩል የተፈጠረው ንፁህ አየር ይኸውልሽ» አለ ጋሻው እንደ ጥላ የምትከተለው ሃናን እያየ፡፡
«እንዴት ደስ ይላል ! የተራራው አቀማመጥ፣ የዛፎቹ አቋቋም፣ የወንዞቹ አወራረድ» ዙሪያ ገባውን አደነቀች፡፡
«በዚህች ቃቆ በምትባል አካባቢ በና የሚባል የጎሳ መጠሪያ ያላቸው ኢትዮጵያን ይኖራሉ፡፡ ወዲያ ማዶ ደግሞ ማሊ የሚባሉ አሉ ! የሁለቱም ጎሳ አባላት ልብስ የሚባል ነገር አያውቁም፣ እንዲያው ሀፍረታቸውን ለመሸፈን ያህል ብቻ ትንሽዬ ቆዳ ያንጠለጥላሉ. . .»
«አ . .  ሃ . . . ከቡስካ በስተጀርባ የተባለው መጽሀፍ
ውስጥ እንዳሉት ሀመሮች?»
«አዎ፡፡ አንብበሽዋል?»
«እንዴ? ለዛውም ደጋግሜ ነዋ»
«ብራቮ ሃኒ »
ዛሬ በመካከላቸው ከፍተኛ የመሳሳብ ስሜት አለ፣ በየደቂቃው ትደገፈዋለች፣ በየምክንያቱ ያቆላምጣታል፣ ብዙ ያወራሉ፣ በጋራ መምጣታቸውን ወደዱት፡፡
ረጅሙን የዙም ሌንስ በዘመናዊ ካሜራ ላይ እየገጠመ «አሁን እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት   ማንሳት እችላለሁ!» አላት፡፡
በጣም ተደነቀች፡፡
ካሜራውን ለመግዛት ያየውን ፍዳ እየተረከላት፣ ወንዙ ዳር ያለችው ዛፍ ላይ ወጣና ወዲያ ማዶ ደን ላይ አነጣጠረ፡፡ ምንም የለም፡፡ ወዲህ አነጣጠረ እንደዚያው ነው፡፡ ዱብ ብሎ ወረደ፡፡
በዛፍና ቅጠላ ቅጠሉ መሃል እየተሽሎኮለኩ፣ በሳቅ እየተፍነከነኩ ገላጣ ቦታ ላይ ብቅ አሉ፡፡
አፍረቷ አካባቢ ብቻ ሦስት ማዕዘን ቁርበት ጣል ካደረገች የበና ልጃገረድ ጋር ተፋጠጡ፡፡ ደንግጣ እንደሐውልት ድርቅ አለች የበናዋ ቆንጆ። ጡቶቿ ለመተኮስ የተወደሩ ሮኬቶች ይመስላሉ፡፡ በቀይ አፈር የታሸው ፀጉሯ ቁልቁል ይጥመዘመዛል። ከቀላጭ ብረት የተሰሩ ሦስት ቀለበቶች በአንገቷ ዙሪያ ተጠምጥመዋል፡፡
ሃና አፏን ከፈተች፡፡ የበናዋ ቆንጆ ተክለሰውነት ትንግርት ሆኖባታል፣ ጠይምነቷ ወከክ ያደርጋል፡፡
ጋሻው ቀስ ብሎ ጣቶቹን ከካሜራው ጋር አገናኘ። ልጃገረዲቱ ሃናን በዓይኖቿ ወጋቻት፡፡ ጆሮዎቿም ትልልቅ ሎቲዎችን አንጠልጥለዋል፡፡ ክንዶቿ ከላይ እስከታች በመዳብና ቀላጭ ብረቶች አጊጠዋል፡፡
የጋሻው፣ የሃና፣ የበናዋ ጉብል የልብ ትርታ ቆሟል። የዓይን እርግብግቢት ሳይቀር ተቋርጧል። ፀጥታውን የሚያደፈርስ ጠፋ፣ የበና አሞሮች ክንፋቸውን ሳይቀዝፉ በርቀት ቁልቁል ያስተውላሉ...
የበናዋ ቆንጆ ፊት ላይ ታሪክ ይነበብ ጀመር፡፡ ቁጣ፣ ድፍረት፣ ግርምት!
ጋሻው  ካሜራውን  ዓይኑ  ላይ  ሳያደርግ  በግምት  በማንሳት ተክኗል፡፡ የበናዋ ጉብል አፈገፈገች። የሃና ዓይኖች ልጃገረዲቱ ባዶ እግሮች ላይ አረፉ። አልቦዎቿ አንፀባረቁባት፡፡ ጉብሊቱ አፈገፈገች፡፡ ጋሻው የካሜራውን መምቻ ተጫነ፡፡ ቀጭ!
ቱር አለች እንደሚዳቋ፡፡
«ወይኔ ጋሻዬ አመለጠችህ?» ሃና ጮኸች፡፡
የበና አሞሮች ክንፋቸውን አማቱ፡፡ እነሱም አንቋረሩ ለቆንጇቸው!
ጋሻው ዘሎ ከፍታ ላይ ወጣ፡፡ ካሜራውን ዓይኑ ላይ ነው፡፡ በሌንሱ ውስጥ የጉብሊቱ ምስል ይርመሰመሳል፡፡
«ከሞን!» ይላል ጋሻው ሌንሱን ዞር፣ ቀጭ! ዞር ቀጭ! በተከታታይ የካሜራውን መምቻ ተጫነው፡፡ ፊልሙ ሲያልቅ ቆመ፡፡ በፍጥነት ቀይሮ አነጣጠረ፡፡
የበናዋ ቆንጆ የለችም፡፡
ካሜራውን ለቀቀው፣ አንገቱ ላይ ተንጠለጠለ። ሁለት እጁን ወደ ቃቆ ደመና ወጠረ፣ አምላኩን ማመስገን ሲፈልግ ሁለት እጁን ወደላይ ይወጥራል፡፡
ከከፍታው ላይ ዱብ እንዳለ ካሜራውን ወደ ጀርባው አዞረና ሀናን አቀፋት፡፡
የበና አሞሮች ሌላ ትእይንት ያዩ ጀመር፣ መቅዘፋቸውን ትተው ቁልቁል አሰገጉ. . .
በመጪው ዓመት ካናዳ ቶሮንቶ ውስጥ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፎቶ ግራፍ ውድድር አሸናፊነቱን ደመነፍሱ ከወዲሁ ሹክ
አለችው፡፡ ስለዚህ ሀናን እንዳቀፋት አንገቷ ሥር ይስማት ጀመር፡፡ የበናዋ ጉብል በስቱዲዮ የታጨቁ ፎቶ ግራፎቹን ነፃ ስታወጣለት ታየው፡፡
ሀና ከናፍርቷን ወደ ከናፍርቱ በመስደድ ላይ ነች፣ ጡቶቿ እስኪፈርጡ ተለጥፋበታለች፡፡
«ሄይ . . . ሄይ . . . ሄይ . . . ጃላ . . .  ጃላ . . .!» ይላል አንድ ሸካራ ድምጽ እንደብራቅ ጮሆ፡፡
ጋሻው ሀናን ለቆ ዞር አለ፡፡
የበናው ወጣት ቁራጭ ቁርበቱን እንዳገለደመ በግራ እጁ ቅቤ የጠጣ በርኮታ፣ በቀኝ ክንዱ የእባብ መርዝ የተለወሰ ቀስቱን እንዳነገበ በኩራት ቆሟል፡፡
ሀና የዓለሟ ፍፃሜ የሆነ መሠላት፡፡
የጋሻው ፊት እንደ በና ፀሐይ አበራ፣ ቅንድቦቹ ሽቅብ ተነሥተው ፀጉሩ ውስጥ ተወሸቁ፡፡ ዓይኖቹ ከመበልጠጣቸው የተነሣ ወልቀው የሚወድቁ እንክብሎች መሰሉ፡፡ ልክ እንደበና አሞሮች ክንፉን ዘረጋ «ሃይ ሃይ ጃል» ብሎ አጸፋውን መለሰ ድምጹ በበና ግዛት ውስጥ አስተጋባ፡
አሞሮቹ ግራ ገባቸው፡፡
ሮጦ አቀፈው የበናውን ወጣት፡፡
እሱም ቀስትና በርኮታውን ቁልቁል ለቀቃቸው፣ ሳሩ ውስጥ ሰጠሙ፡፡
የበናው ወጣት ፈነደቀ ፣ጋሻው ቀልቡን ሳተ «የክፍለ ዘመኑን ፎቶ አገኘህ» እያለች ደመነፍሱ ደስታውን አበዛችለት፡፡
ሀና ራሷን ጠዘጠዛት፣ እያዞራት ነው፡፡
የበናው ወጣት እግሩ ሥር ያስቀመጠውን ቅል ከሳሩ ውስጥ አወጣና ለጋሻው ሰጠው፡፡
ጋሻው አላቅማማም ግጥም አድርጎት ጠጣ፣ ዞሮ ሀናን ያናግራታል «ሀኒ ነይ ወዲህ፣ ይህ ጃላዬ ነው። ተዋወቂው፡፡ በበናዎች ቋንቋ ጃላ ማለት ጓደኛዬ ማለት ነው፡፡ እንዴት ያለ ወዳጄ መሰለሽ . . . » እያለ ቅሉን ይሰጣል «ቅመሺው!»
ጎንጨት ታደርገዋለች፡፡ ቆመጠጣት ቀና ብላ አየችው፡፡
«ዋጭው  ምንም  አይልሽም፣  የማሽላ  ቦርዴ  ነው፣  ጨቃ ይባላል»
ነጭ ነገር ተፋች፡፡
የበናው ወጣት ሳቀ . . .
ጋሻው የበነዋ ጉብል ባሳደረችበት ብሩህ ተስፋ ተነቃቅቷል፡፡ ያለውን ገንዘብ አሟጦ፣ ከሚያውቃቸው ሁሉ ተበድሮ፣ ካነሰውም ንብረቱን በሙሉ ሽጦ፣ ተጨማሪ ፎቶ ግራፎችን ከወሎ፣ ትግራይና ሐረር ማንሣት አለበት፡፡ ከነዚህ መካከል መርጦ በሚልከው በአንዱ ማሸነፉ አይቀርም! ካሸነፈ ሽልማቱ የሃናን ዳሌ የመሰለ ዋንጫ አይደለም፡፡
በአወዳዳሪው  ድርጅት  ስፖንሰር  አድራጊነት  ዓለም  አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ኢግዚቢሽን እንዲያዘጋጅ እድል ይሰጠዋል፡፡ የዕድሜውን አጋማሽ ለሚክል ጊዜ የሰበሰባቸው ፎቶ ግራፎች ቀን  ወጣላቸው  ማለት  ነው፡፡  ተወዳጅ  የሆኑት በጨረታ ይቸበቸባሉ። ያልተሸጡትም ቢያንስ የሀገሪቱን ወርቃማ ባህል፣  ጀግንነት፣ ውበትና ማንነት ለዓለም ሕዝብ በጣፋጭ ለዛቸው ይሰብካሉ።
በኢግዚቢሽኑ የሚያገኘውን ክብር፣ ቱጃር የሚያደርገው ረብጣ ዶላር፣ በቀጣይ ዘመኑ የሚኖረውን የሙያ መሣሪያዎች፣ ያሠራር ደረጃና፣ የአሸናፊነት ሌሎች ፀጋዎች ሁሉ ታዩት፡፡ የጨበጣቸው ያህል እየቋመጠ፣ በቁሙ እያለመ ሳለ ጀምበር በስተ ምሥራቅ እርቃኗን ብቅ አለችለት፡፡ የመጨረሻው ፎቶ ሆና  በካሜራው ጠቀሳት፡፡
ወዲያው   የተከራያት   መኪናን   በመጣችበት   ፍጥነት እያስወነጨፈ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ጀመሩ...
ለሊቱን ሙሉ በበናዎች የእሳት ዳር ጨዋታ ሲዝናና ያደረው ጋሻው፣ እጎኑ እንቅልፍ እየጣለ የሚያነሳት ሃናን እረሳ፡፡ ሃሳቡን ከመሪው ጋር እየጠመዘዘ፣ ምኞቱን ከነዳጅ መስጫው ጋር እየተጫነ ያልማል፡፡
እሷ  የሁለት  ዓመት  ምኞትዋ  መና  እንደማይቀር  እርግጠኛ ሆናለች፡፡ አልፎ አልፎ የሽርደዳ ሚመስው ፈገግታዋን ብልጭ አያረገች ትመለከተዋለች፡፡
እሱ እዚህ የለም፡፡ በሃሳብ ጠፍቷል፡፡
ሁለቱን የአሸናፊነት ጥማት ያቃጠላቸውን ተጓዦች የያዘችው መኪና የሶዶ፣ የሻሸመኔ፣ የዝዋይ አየርን ሰንጥቃ ሞጆ ደረሰች፡፡
ተፋላሚዎቹ  የደብረዘይት  ከተማን  ከሩቅ  ሲመለከቱ  ከሃሳብ ጎሬያቸው በመውጣት ተያዩ። አንዳቸው በሌላኛው ዓይን ውስጥ እንግዳ ነገርን አስተዋሉና ተሳሳቁ፡፡
ሁለቱም ድክም ብሏቸዋል፡፡ ማረፍ ይፈልጋሉ፣ ደብረዘይት ምቹ ናት፡፡ ከመኪናው ወርደው ቡና ጠጡ፡፡
«ሳሎኑ ተደፍሯል፡፡ የጉዞ  እቅዶቹ ተካፋይ ሆኛለሁ፣ የስቱዲዮ በር ቀላል ነው ፡፡
የመኝታ ቤቱ ቁልፍ ከተከፈተ አልጋ አለ፣ እዛ ላይ ከወደቅን አለቀ! ይወደኛል፡፡ ይህ ደግሞ ከባድ አይደለም ጊዜ ብቻ ያስፈልገዋል አንጂ. . . » የጣቷን  ጥፍር  በጥርሷ እየከረከመች እራሷን አረጋጋች፡፡
አዲስ አበባ ሲገቡ መሽቷል፡፡ ቤቷ በር ላይ አደረሳት። ጉንጩን ስማው ወረደች፡፡ እንደ እርጥብ ስጋ ቀዘቀዘው፡፡
* * *
ወራት እንዳአቃጠላቸው ፊልሞች ላይመለሱ ጋዩ። በቁርጠኝነት የዘመተበት ውድድር ካሰበው በላይ መስዋት አስከፍሎታል፡፡ የነበረውን ገንዘብ አሟጧል፡፡ ያችኑ ጥቂት ቁሳቁስ ሸጧል፣ የተበደራቸውንም ብሮች በተባለው ጊዜ ባለመመለሱ ቅሬታን አትርፎ መንገድ አጥቷል፡፡
አሁን ጠባቧ ስቱዲዮ ውስጥ፣ ብረት እንደታጠረበት አቦሽማኔ ይንቆራጠጣል፡፡ ከካናዳ ቶሮንቶ የተላከው የተወዳዳሪዎች ውጤት ማስታወቂያ መጽሔት እንደታሸገ ደርሶታል። ኢንቨሎፑን የሚከፍትበት አቅም አጥቶ ይሽከረከራል፡፡
በርግጥ  ኢትዮጵያን  ከዳር  እስከ  ዳር  አካልሎ  ብርቅዬ አእዋፍቷን፣ ድንቅ የመልካ ምድር አቀማመጧን፣ አስገራሚ ቅርሶቿን፣ ታሪካዊ መስህቦቿን ሁሉ ደረጃውን በጠበቀ ብቃት አንስቷል፡፡
አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ቢያደርግም፣ የማሸነፍ ሚስጥሩ የሚፈታው አቅም የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ሳይሆን ጉዳዩ ሊያስከፍል የሚገባውን ዋጋ መክፈል በመቻል ብቻ መሆኑን ማወቁ አስጨንቆታል፡፡
የታሸገው የውጤት ማሳወቂያ ኢንቨሎፕ ውስጥ ያ መፅሔት አለ፡፡ የመፅሄቱ ፊተኛ ሽፋን ላይ ያሸናፊው ፎቶ ይኖራል፡፡ እዚህ አሸናፊ ቦታ ላይ የበናዋ ጉብል ከሌለች ጋሻው ያከትምለታል! በቀጣዩ ጊዜ ስራውን በአግባቡ የሚያከናውንበት የመንቀሳቀሻ አቅም ያጣል፣ ይሰደዳል! አበዳሪዎቹ የቀረውን ካሜራና አንዳንድ ቁሳቁስም ይነጥቁት ይሆናል . . .
በዚህም አለ በዚያ በቀላሉ ለማያንሰራራበት የሞራል ውድቀት፣ የስሜት ስብራት፣ ብሎም መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት የማይችልበት የድህነት ማጥ ውስጥ ይዘፈቃል፡፡
ጭንቀቱን የሚጋራው አጣ፡፡ ላቡ ችፍ አለ በፊቱ ላይ፡፡ በህይወት ዘመኑ የዛሬውን ያህል ጠንካራ ውጥረት ገጥሞት አያውቅም፡፡ አድርጎ የማያውቀወን ቤተአምልኮ ጎራ ማለት አማረው፡፡ እዛ ሄዶ ኢንቨሎፑን ሊከፍት አሰበ፡፡ የበናዋ ጉብል በሚፈልገው ቦታ ከሌለችስ ? እግዚኦ በሉልኝ ! ልል ነው? በራሱ ላይ ዘበተ፡፡
«ቀድሞውንም በዚህች ደሃ ሀገር ውስጥ እየኖርኩ፣ የፎቶ ግራፍ ጥበቡ የመጠቀበት ዓለም ላይ ካሉ ባለሙያዎች ጋር  መወዳደር አልፎ፣ ተርፎም ለማሸነፍ መጎምጀቴ እንዴት
አልፎ፣ ተርፎም ለማሸነፍ መጎምጀቴ እንዴት ያለ ቅዠት ነበር ?» አለ ለራሱ፡፡
ሀይሌ ገብረ ስላሴ በአዕምሮው ተከሰተ፣ የምፀት ፈገግታውን እንደ ካሜራው ፍላሽ ብልጭ አደረገበት፡፡ ዞሮ ፈለገው፣ ድንቅ ፎቶውን በስቱዲዮ ሰቅሏል፡፡ እግሩ  ስር ወድቆ ጭንቀቱን ሊያካፍለው ዳዳውና ፎቶው ፊት ቆመ፡-
«ባላሸንፍስ?»  ጠየቀው፡፡
«ትሸነፋለሃ! »
«መሸነፍ ምንድን ነው?»
«መታገልና ተረትቶ መውደቅ!»
«ማሸነፍስ?»
«ከውድቀት መነሳት!»
«በቃ?»
«አልበቃም»
«ሌላ ማሸነፍ አለ ?»
«አዎ?»
«እባክህ ንገረኝ »
«በውድቀትህ ውስጥ ባለህበት ጊዜ ፣ይህን ውድቀትክን በማሸነፍ እንደምትተካው በፍፁም እምነት ማመን»
«ማመን ብቻ?»
«አሂሂ . . .  ውጤቱ አስኪመጣ ደጋግሞ መሞከር ያስፈልጋል . . .  ይኸውልህ ምን መሠለህ . . . »
እንዳያብድ ሰጋ! ቀልቡን ሰብሰብ  አድርጎ ወደ ኢንቨሎፑ አመራ፡፡
ግድግዳውን ያጣበቡት ፎቶ ግራፎች፣ መደርደሪያው ላይ የተሰቀሉት ካሜራና ሌንሶች ሸምቅቅ እንዳሉ ኢንቨሎፑ ያመጣውን መልዕክት የሚጠባበቁ መስለው።
መንቆራጠጡን ቆም አደረገና አፈፍ አደረገው ኢንቨሎፑን፡፡ ይከብዳል፡፡ በፍጥነት ሊሸረክተው ቆነጠጠ፡፡ አይ! አይ!» ካሜራና ሌንሶቹ ሲንጫጩ ተሰማው፡፡
ፎቶ ሲያድን «ሰላይ!» ተብሎ የታሰረና የተንገላታበት ወቅት፣ በሌሊት ሲማስን በማጅራት መቺ የተዘረፈበትን፣ ጫካ ለጫካ ሲያስስ ከአውሬ መንጋጋ ለጥቂት ያመለጠበትን፣ ገንዘብ እያጠረው የተራበበትን፣ አዕምሮው ጥበቡ ላይ ተጣብቆ ገላው ያደፈበት ልብሱ የመነቸከበትን፣ ጊዜያት አስታወሰ፡፡
የአሸናፊት ጎዳናን የማይሽር የመንፈስ ደዌ  አድርጎ ቆጠረው! ለአመታት የታተረለት አሸናፊነትን ደጋግሞ ረገመው፡፡
የማይቀርለትን ጽዋ ለመጎንጨት ኢንቨሎፑን አነሳ፣ ጠበቅ አድርጎ ከያዘው በኋላ ጥርሱን ነክሶ አይኑን እንደጨፈነ ስቦ አወጣው፡፡ እንደበረደው ህንፃ አገጩ ተርገበገበ፣ ችፍ ያሉት ላቦቹ ተድበልብለው ወደቁ . . .
እንደጨፈነ መጽሔቱን ወደ ኢንቨሎፑ ሊመልሰው አሰበ፡፡ አላደረገውም! ዓይኑን ገለጠው። ከበናዋ ጉብል ጋር ተፋጠጡ! ፊቷ ላይ ታሪክ ይነበባል፡፡ ቁጣ፣ ድፍረት፣ ግርምት! ጋሻው አፈገፈገ የስቱዲዮ ግድግዳ አገደው፡፡ ህልም እንዳይሆን ሰጋ፡፡
መጽሔቱን ወደ ዓይኑ አስጠጋ፣ ሮኬቶቿ አነጣጡሩበት፣ በቀይ አፈር የታሸው ጥምዝ ፀጉሯ፣ የአንገት ቀለበቷ፣ ሁሉም
አሉ፡፡  በእጁ  ዳበሳት  አልደነበረችም፡፡  እቅፍ  አደረጋት፡፡  ሰላም ሰጠችው፡፡
«አላልኩህም»  እያለች ጮኸች ደመነፍሱ «በል ሳማት»
አዘዘችው፡፡
መጽሔቱን ሳመው፡፡ የስቱዲዮ በር ተበረገደ፡፡ አቅሉን ስቶ ወጣ፣ አስፋልት አቋረጠ፣ ታክሲ ያዘ፣ ርቆ ወረደ በተለያዩ ቅያሶች እያሰባበረ ገስግሶ እነ ሃና ሳሎን፣ በሃና ፊት ተገኘ፡፡
ሃና ጆሮ የሚበጥስ ጩኸት አሰማች፡፡ እናቷ ተንደርድረው ገቡ፡፡
መጽሔቱን እያሳየች የሆነው ሁሉ አነበነበችላቸው፡፡
ከቁብ ሳይቆጥሯት ገርምመዋት ወጡ፡፡
መጽሔቱን ገለጠችው፡፡ የግሪክ እመቤት!
ጋሻው ከጥይት ያመለጠ መሰለው፡፡
አሁንም ገለጠችው፣ የአርመን ኮረዳ ፡፡
ሃና ደነዘዘች፡፡ ገለጠችው የሩስኪ ውብ፡፡ ገለጠችው የህንድ…
የበናዋ ጉብል ናፈቀችው፡፡ መጽሔቱን ከሃና ቀማትና ወደ ሽፋኑ መለሰው፣ ሮኬቶቿን ወደረችበት። መጽሔቱን ሳመው፣ ፆታዊ ፍቅር ተፀነሰበት፡፡
«አገባታለሁ! » ሲል ተናገረ፡፡
«ምን»
«ሚስቴ አደርጋታለሁ!»
«ም . . .  ምን አልክ ጋሻዬ? » “እቺ ናት ሚሰቴ፣ አ ገ ባ ታ ለ ሁ”
«እውነት የምትለውን ታደርገዋለህ? አንተእኮ… እኔ…» የምትናገረው ጠፋት፡፡ «ይሆናል የኔ ጌታ? በመካከላችሁ ያለውን ሰፊ የባሕል ፣ የአኗኗር፣ የስልጣኔ፣ ልዩነት አላስተዋልከውም? ይህን ያህል የተራራቀ ልዩነት ያላቸው ሰዎች በትዳር ሊጣመሩ ይችላሉ? ጋሻዬ? ይቻላል ጋሻዬ?. . . »
ሀይሌ ገብረስላሴ ፈገግ አለ፡፡ ያ ህያው ምስል በጋሻው ሕሊና ደግሞ ተከሰተ፡፡ ጋሻውም እሩቅ እያለመ፣ እሩቅ እያሰበ አብሮት ፈገግ አለ፡፡
ሃና ይህን የመሰለው በረከት ተቋዳሽ ባለመሆኗ ከልቡ አዘነላት፡፡ በጓደኝነት ስሜት ጠልቆ መረመራት፣ ጉድለቷን አስተዋለ፡፡ ከሕይወት ፍልስፍናው ይበልጥ ሊያካፍላት፣ እምነቱን ሊተክልባት ወሰነ። «ይሄውልሽ ሃንዬ. . . ጉዳዮችኮ ቀላል ወይም ከባድ ስለሆኑ አይደለም የሚሳኩልን፣ ልናሳካቸው በቆራጥነት ስንወስንና ያላማቋረጥ ስንጥር ብቻ ነው የሚሳካልን፡፡» የግል እምነቱን አሰረፀባት፡፡
ምንም እንኳን ጋሻውንና ያልጨበጠችውን ዓለማቀፋዊ ዝናን፣ ተስፋ አድርጋ የቶማስን ንፁህ ወዳጅነት ብትረግጥም፣ መልሳ ልታገኘውና እስከ መጨረሻውም በፍቅሩ ውስጥ ልትሆን እንደምትችል አመነች፡፡ ልታደርገውም ወሰነች፡፡
ወዲያው በአይነ ህሊናዋ እንዲህ ይታያት ጀመር።
የበና ማኅበረሰብ ገላቸው በልብስ ተሸፍኖ። በምሽት፣ መስክ ላይ በሚያነዱት እሳት ዙሪያ ተሰባስበው፣ በርኮታቸው ላይ ቁጢጥ እንዳሉ፣ አረቄያቸውን እየተጎነጩ ሲጨዋወቱ . . .
ጨረቃ ፍልቅልቅ ብላ ቁልቁል ስታስተውላቸው...
እሷ እና ቶማስ ጎን ለጎን እንደተቀመጡ፣ እሳቱን እየሞቁ በሹክሹክታ ሲያወጉ. . .
የበናዋ ጉብል   ጠይሙ ፊቷን በፈገግታ አስጊጣ፣ በዘመናዊ የቆዳ ጃኬት የተሸፈኑ ውድር ሮኬቶችዋን በማስቀደም  ወደ ጋሻው
ስትርብ . . .
ጋሻውም በርኮታው ላይ ጉብ እንዳለ ፣በነበልባሉ ውስጥ አሻግሮ እየተመለከታት በነደደ ስሜት ሲጠብቃት. . .
ጨረቃም እየተቅለሰለች ደመናው እቅፍ ውስጥ ስትሸሸግ . . .

Read 4690 times