Saturday, 14 June 2014 12:13

“ሄሊኮፕተር በመስራት በአፍሪካ የመጀመሪያው መሆኔን አረጋግጫለሁ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(8 votes)

     ገብርኤሉ ተረፈ ይባላል፤ ትውልድና እድገቱ ጎጃም ደጀን አካባቢ ነው፡፡ በለጋ ዕድሜው ወላጆቹን በሞት ያጣው ገብርኤሉ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ገንዘብ ሊያስገኙ የሚችሉ ነገሮችን እየሰራ በመሸጥ ራሱን እያገዘ ኖሯል፡፡ የጫማ መስፊያ ወስፌ በመስራት የራሱን ገቢ ማግኘት የጀመረው የ32 ዓመቱ ወጣት፤ ለሆቴሎች የማስታወቂያ ፅሁፍ በመፃፍና ስዕል በመሳል ወደ ፈጠራ ጥበብ ማደጉን ይናገራል፡፡ ትምህርቱን ከዘጠነኛ ክፍል በማቆም ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ለባለፀግነት ያበቁትን የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ሲሰራ የቆዩ ሲሆን በቅርቡም ሄሊኮፕተር መስራቱን ይገልፃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ገብርኤሉ ተረፈ ጋር በህይወቱ፣  በፈጠራ አጀማመሩ፣ በሰራት ሄሊኮፕተርና በቀጣይ እቅዱ ዙሪያ ተከታዩን  ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

የፈጠራ ስራ ፍላጎት ያደረብህ መቼ ነው?
ከልጅነቴ ጀምሮ ነገሮችን በአትኩሮት ማየትና መመራመር እወድ ነበር፡፡ በእርግጥ እናቴ ደሀ ስለነበረች ጠላ እየሸጠች ነበር የምታስተምረኝ፡፡ እኔም ሳንቲም የሚያወጡ ትንንሽ ነገሮችን እየሰራሁ እሸጥ ነበር፡፡
ለምሳሌ ምን ትሸጥ ነበር?
ለምሳሌ ሊስትሮዎች ጫማ የሚሰፉበትን የጫማ ወስፌ እየሰራሁ እሸጣለሁ፡፡ እናቴ ያኔ ጠላ ሸጣ በ15 ቀን የማታገኘውን ገንዘብ እኔ በቀን አገኝ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ስዕል መሳል አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር እወዳለሁ፡፡ የጫማ ወስፌ ሰርቼ መሸጥ የጀመርኩት ገና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር። ከዚያ ከፍ ስል ስዕል ወደ መሳል ገባሁ። ስዕሉንም የገቢ ምንጭ አደረግሁት፡፡ በየሆቴሉ እየሄድኩ ግድግዳ ላይ ጥሩ ጥሩ ስዕሎችን መስራትና የሆቴል ማስታወቂዎችን መፃፍ ስራዬ ሆነ፡፡
ተወልደህ ያደግኸው ጎጃም ደጀን ውስጥ ነው፡፡ እንዴት ወደ አዲስ አበባ መጣህ?
ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በጣም ልጅ ሆኜ ከ20 ዓመት በፊት ነው፡፡ የመጣሁበትም ምክንያት እናቴ በመሞቷ ነው፡፡ አባቴ ህፃን ሆኜ በመሞቱ፣ እናቴ ነበረች የምታሳድገኝ፡፡ እሷ ስትሞት ሁሉንም ነገር ትቼ ወደዚህ መጣሁ፡፡ ከዚያም የሻይ ማፍያ ማሽኖችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ያኔ የሻይ ማፍያ ማሽን በጣም አዋጪ ስለነበር፣ ገንዘብ ማግኘት ጀመርኩኝ። ቤትም መኪናም እስከ መግዛት ደርሻለሁ፡፡
ቀደም ብለህ እንደነገርከኝ በኑሮ ጫና ምክንያት ትምህርትህን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጠሃል፡፡ ቴክኒክና ሙያ ሳትማር ወይም ቴክኖሎጂ ነክ እውቀት ሳይኖርህ እንዴት የፈጠራ ስራ ላይ ልታተኩር ቻልክ?
በዚህ በፈጠራ ስራ ላይ ለምን ፍቅር እንዳደረብኝ ለራሴም ግልፅ አይደለም፤ ነገር ግን ነገሮች ወደ አዕምሮዬ መጥተው ሲታዩኝ ወዲያው ወደ ተግባር ለመቀየር እጣደፋለሁ፡፡ ወደ አእምሮዬ የመጣን የትኛውንም ምስል በድፍረት መሞከር እወዳለሁ፡፡ በጣም ድፍረት አለኝ፡፡ ለምሳሌ አንድን አውሮፕላን እሰራለሁ ብለሽ ስታስቢ፣ መጀመሪያ በምናብሽ (አዕምሮሽ) ትስይዋለሽ፡፡ ሁሉ ነገር አዕምሮሽ ውስጥ ነው የሚያልቀው፡፡ ከዚያ አዕምሮሽ ውስጥ ያለውን ስዕል ወደ እውነታ ትቀይሪያለሽ። ይህ ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ አዕምሮ ውስጥ ማብላላትን ይጠይቃል፡፡ ለእኔ የፈጠራ ስራ የምመሰጥበት ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ትምህርቴ ከዘጠነኛ ክፍል የዘለለ አይደለም፤ ነገር ግን ብዙ የፈጠራ ስራዎች ወደ አዕምሮዬ ይመጣሉ፡፡ እሰራቸዋለሁ፡፡
እስካሁን ምን ያህል የሻይ ማፍያ ማሽኖችን ሰርተህ ሸጠሃል?
ከአንድ ሺህ በላይ ይሆናሉ፡፡
አንድ የሻይ ማሽን ለመስራት ምን ያህል ጊዜ ይፈጅብሃል? ከምን ከምን ዓይነት ቁሳቁሶች ነው የምትሰራው?
የተለያዩ ታንከሮችን፣ የብረት ቱቦዎችን፣ ላሜራዎችንና መሰል ቁሳቁሶችን እጠቀማለሁ፡፡ አንድ የሻይ ማሽን ለመስራት ቢበዛ ሳምንትና ከዚያ በታች ነው የሚወስድብኝ፡፡ አንዱን ማሽን የዛሬ ዘጠኝ አመት አካባቢ ከ7-9 ሺህ ብር እሸጠው ነበር።
አሁንስ?
አሁን ስራው ስለደከመ የሻይ ማሽን አልሰራም። ስራው የደከመበት ምክንያት እዚህ አገር የፈጠራ ስራ ስትሰሪ የሚያበረታታሽ የለም፡፡ የሻይ ማሽን የሚሸጡ ሰዎች የአገር ውስጥ ማሽኖችን አትግዙ ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የሻይ ማሽን ነጋዴዎች ከውጭ የደከሙ ማሽኖች ያስገቡና ውጭያቸውን እየቀየሩና ቴክኒካቸውን እያደሱ፣ ከአገር ውስጡ የሻይ ማሽን ከፍ ባለ፣ ከውጭው ዝቅ ባለ ዋጋ በመሸጥ፣ አገር ውስጥ እየሰራን የምንሸጠውን ከጨዋታ ውጭ አደረጉን፡፡ በዚህ የተነሳ ስራውን ለመተው ተገድጃለሁ፡፡
አሁን በቋሚነት የምትሰራው ምንድነው?
በአሁኑ ወቅት ምንም በቋሚነት የምሰራው ስራ የለኝም፡፡ ነገር ግን በአዕምሮዬ ውስጥ ብዙ የፈጠራ ስራዎች ስላሉኝ የት፣   ልሂድ የትም እነዚያን ነገሮች እውን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ የፈጠራ ክህሎቴንም የበለጠ የማሳደግ ህልም አለኝ፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነችውን ሄሊኮፕተር ሰርተሃል፡፡ እስቲ ስለ ሄሊኮፕተሯ በአዕምሮህ መጠንሰስ ከዚያም እንዴት ወደ እውነታው እንዳመጣሃት ንገረኝ…
የሄሊኮፕተሯ ጉዳይ በሀሳብ ደረጃ በአዕምሮዬ ለረጅም ጊዜ አርግዣት የቆየች ናት፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተርን ጉዳይ አስብ ነበር። በትንሹ አምስት አመትና ከዚያ በላይ በአዕምሮዬ ውስጥ የተጠነሰሰ ጉዳይ ነው፡፡ ሄሊኮፕሯን በተግባር ለመስራት ግን አንድ አመት ነው የፈጀብኝ፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ አንድ የፈጠራ ስራ ቀድሞ የሚያልቀው አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡
ሄሊኮፕተሯን ለመስራት ምን ግብአቶች ተጠቀምክ?
ከብረታ ብረት ነው የሰራኋት፡፡ ከላይ የሚሽከረከረውን ነገር ከፋይበርግላስ፣ ኢንጂኗን ከሞተር ሳይክል ነው የሰራሁት፡፡ ምን አለፋሽ… ከወዳደቁ ነገሮች ነው የሰራኋት ማለት እችላለሁ። እርግጥ ኢንጂኑን በትክክል ለማምጣት የተለያዩ ሞተር ሳይክሎችን እየገዛሁ ስሞክርና ስጥል ቆይቻለሁ፡፡
ከሁሉም የገረመኝ የሰራሃት ሄሊኮፕተር በሻንጣ ተጣጥፋ መያዝ የምትችል መሆኑን ስሰማ ነው፡፡ ይሄ እውነት ነው?
አዎ! ትያዛለች፡፡ የአሰራሯ ሁኔታ ነው ተጣጥፋ እንድትያዝ የሚያደርጋት፡፡ በዚህም ከሌሎች ትለያለች።
ሄሊኮፕተሯ ስትበር አሳይተሃል?
በደንብ በርራለች፡፡ ይህንን ሳላረጋግጥማ ሄሊኮፕተር ናት ብዬ ለመናገርም አልደፍርም፡፡
ሄሊኮፕተሯን ለመጎብኘት የመጣነው በዚህ “የምርታማነት ማሻሻያ ማዕከል” ውስጥ ነው፡፡ በዚህ  ወርክሾፕ ውስጥ ለመስራት እንዴት ተፈቀደልህ?
ስራው አመቺ ቦታ ይፈልጋል፡፡ ይህ ማዕከል ደግሞ ለሥራው ጥሩ ቦታ ነው፡፡ ወደ ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ገ/ኪዳን የመጣሁት በፈጠራ ስራ ላይ የሚተጉ ሰዎችን እንደሚያበረታቱ ስለማውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው አልነበሩም፡፡ “የሉም” ሲባል እቅዴ ላይሳካ ነው በሚል አዝኜ ነበር፡፡ ሌላ ማንን እንደማናግር ለሰዎች ሳማክር፣ የማዕከሉን ምክትል ዳይሬክተር አቶ በረከትን ማናገር እንደምችል ተጠቆምኩኝ። አቶ ዳዊት የሚባሉ የማዕከሉ ሰራተኛ ናቸው አቶ በረከትን አናግር ያሉኝ። አናገርኳቸው። ከጠበቅሁት በላይ ተባባሪና ለፈጠራ ስራ ትልቅ አክብሮት ያላቸው ሆነው አገኘኋቸው። ወዲያው አስፈቀዱልኝ፡፡ በዚህ ማዕከል ወርክሾፕ ውስጥ ነው ሄሊኮፕተሯን የሰራኋት። በነገርሽ ላይ እስከዛሬ ድረስ እንደ አቶ በረከት አይነት ቅንና ተባባሪ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
አሁን ለምንድነው ሄሊኮፕተሯን የፈታታሀት?
ሞተሯ የሚነሳው ገመድ በመሳብ አሊያም እንደሞተር ሳይክል በመረገጥ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ሌላውን አካሏን እንዳይጐዳብኝና ጥራቷ እንዳይቀንስ በሚል ልክ እንደመኪና በቁልፍ እንድትነሳ ለማድረግ፣ እሱን ሞዲፍኬሽን በመስራት ላይ ነኝ። አሁን እሱም እየተሳካ ነው፤ ጥቂት ነገር ብቻ ነው የቀረኝ፡፡
በቅርቡ በይፋ ልታስመርቃት እንደሆነ ሰምቻለሁ። ትክክለኛ መረጃ ነው?
እውነት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ በሁለትና በሶስት ሳምንት ውስጥ ህዝብ በተሰበሰበበት በይፋ አስመርቃታለሁ፡፡
በዓለም ላይ በየጊዜው በርካታ የፈጠራ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ሄሊኮፕተር በመስራት ሰው በአፍሪካ የመጀመሪያው መሆንህን በምን አረጋገጥክ?
ኢንተርኔት ገብቼ ለመፈተሽ ሞክሬያለሁ፡፡ እስካሁን አንድ አሜሪካዊና አንድ ጃፓናዊ ናቸው የሰሩት፡፡ የጃፓኑ “ጊነስ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ” ላይ ተመዝግቧል፡፡ በአፍሪካ ሄሊኮፕተር የሰራ ካለ ብዬ ብዙ ሰርች አድርጌያለሁ፤ የሰራ የለም፡፡ ለዚህ ነው እርግጠኛ ሆኜ የመጀመሪያው ነኝ ያልኩሽ፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያው ሄሊኮፕተር የሰራህ ሰው መሆንህን ስታስብ ምን ይሰማሃል?
ዋው! ልነግርሽ አልችልም፡፡ ለግል ዝናና ክብር አይደለም ይህን የምልሽ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን በሌላው ዓለም ፓስታ እንኳን መመገብ የማንችልና መስራት የማንሞክር ተደርገን ነው የምንታየው። በረሀብና በጦርነት ነው ስማችን ሲነሳ የኖረው። ይሄ በግሌ ይቆጨኛል፡፡ ሀበሾች ይህን ያህል መስራት የሚችል ጭንቅላት ባለቤት መሆናችንን ዓለም ቢያውቅ ደስ ይለኛል፡፡ በአትሌቲክሱ፣ በጠፈር ተመራማሪነት፣ በህክምና፣ በፈጠራና መሰል ዘርፎች ኢትዮጵያዊያን ትልቅ አቅም እንዳለን ዓለም እንዲያውቅ እፈልጋለሁ። ለዚህ አስተሳሰብ መለወጥ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማበርከቴን ስገነዘብ በሃሴት እሞላለሁ፡፡ ደስ የሚል ስሜት ይሰማኛል፡፡ እኔ በትምህርቴ ገፍቼ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልማርም፤ ቴክኒክና ሙያ ባልከታተልም፣ እድሜ ለኢንተርኔት የማላውቀው ነገር የለም፡፡ አስተማሪዬ ኢንተርኔት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአምስትና ለስድስት ሰዓት ኢንተርኔት ላይ ተመስጬ ቁጭ የምልበት ሰዓት ሁሉ አለ፡፡ ራሴን አስተምሬ ለዚህ ውጤት በመብቃቴም ሌላ የሚሰማኝ ተጨማሪ ደስታ አለ፡፡
በጠቀስካቸው የአሜሪካና ጃፓን ዜጎች የተሰሩት ሄሊኮፕተሮች አንተ ከሰራሃት ሄሊኮፕተር በምን ይለያሉ?
የጃፓኑ ሄሊኮፕተር አራት ፒስተን ኢንጂን ነው፤ ፎርስትሮክ ይባላል፡፡ በዚያ ላይ 80 የፈረስ ጉልበት ሀይል አለው፡፡ የአሜሪካኑ ደግሞ መጠኑ ትንሽ ሆኖ 40 የፈረስ ጉልበት ሀይል ሲኖረው ባለ አንድ ፒስተን ኢንጂን ነው፤ ፎርስትሮክ ይሁን ቱስትሮክ ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
የእኔ ከእነሱ የሚለይበት እኔ የተጠቀምኩት ኢንጂን የሞተር ሳይክል ነው። ያመሀ የተባለ ሞተር ሳይክል ኢንጂን ሲሆን 250 ሲሲ ነው፡፡ እኛ አገር የፈረስ ጉልበት ምን ያህል እንደሆነ መለካት ባይቻልም ስገምት ግን ከ40 በላይ የፈረስ ጉልበት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከ42-45 የፈረስ ጉልበት ይሆናል ሀይሏ፡፡
የሄሊኮፕተሯን እሽክርክሪት ከፋይበር ግላስ የመስራት ሃሳብ እንዴት መጣልህ? ከዚያ በፊት የሞከርከው ሌላ ማቴሪያል ነበር?
ክንፉን ለመስራት ብዙ ዓይነት ማቴሪያል ተጠቅሜያለሁ:: ብዙ ብርም አውጥቻለሁ፤ ግን አልተሳካልኝም ነበር፡፡ ለምሳሌ “አቢቲ” የሚባል የእንጨት አይነት አለ፤ በጣም ውድ እንጨት ነው። ብዙ ጊዜ እየገዛሁ ሞክሬዋለሁ፤ ግን አልሆነም። ከሁሉም እሽክርክሪቱ በጣም ፈትኖኛል፡፡ መጨረሻ ላይ ሄሊኮፕተሯ እንድትነሳ ትልቁን ሚና የተጫወተው ፋይበር ግላሱ ነው፡፡ እንደምታዩት ፋይበር ግላሱ ስስ ይመስላል፤ በኬሚካል ሲጣበቅ ግን ለጥንካሬው ወደር የለውም፤ እናም ክንፉ ከፋይበር ግላስ ተሰርቶ ፈታኝነቱ አብቅቷል፡፡
አሜሪካዊው እና ጃፓናዊው ከሰሯቸው ሄሊኮፕተሮች ያንተ የምትሻልበት ነገር አለ?
አዎ! አንደኛ የእኔ ባለ አንድ ፒስተን ናት፡፡
ፒስተን ምን ማለት ነው?
ፒስተን ማለት የሄሊኮፕተሩ ማስነሻ ሀይል (እሳት የሚነሳበት ክፍል) ማለት ነው፡፡ አንድ ፒስተን ሁለት ፒስተን፣ ሶስት፣ አራት እያለ ይቀጥላል፡፡ የጃፓኑ ባለ አራት ፒስተን ነው ብየሻለሁ፡፡
የአሜሪካኑ ባለ አንድ ፒስተን ቢሆንም በጣም አነስተኛ ናት፤ በጭንቅላቱ ተሸክሟት ይሄዳል፡፡ የእኔ ባለ አንድ ፒስተን ናት፤ የራሷ ወንበር አላት፤ ቀበቶ አስረሽ መብረር ትችያለሽ፤ ስለዚህ የእኔ በብዙ መንገድ ትሻላለች፡፡
አንተ ራስህ በትክክል አብርረሃታል?
ምን መሰለሽ… የእኔ የኢንጂን ሲስተሙ የሄሊኮፕተር ሳይሆን የሞተር ሳይክል በመሆኑ ካንዴላ ሲስተም ነው፡፡ ኢንጂኑ በተፈጥሮው አንድ ክር ሲነቀል ሾርት ካደረገ ልትፈጠፈጪ ትችያለሽ፤ ስለዚህ እኔ በኢንጂኑ ስለማልተማመን አደጋ እንዳይመጣ ከመሬት አንድና ሁለት ሜትር ከፍታ ላይ እያስነሳሁ እሞክራታለሁ፡፡ እናም መነሳት መቻሏ ኢንጂኑ የሄሊኮፕተር ቢሆን ፐርፌክት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ሁሉ ነገር ተሟልቶላት በብዛት ብትፈበረክ በዋናነት ለምን አገልግሎት ልትውል ትችላለች?
አሪፍ ጥያቄ አመጣሽ! ለመከላከያ ሰራዊት ትጠቅማለች፡፡ ለፖሊስም ታገለግላለች፡፡ ለምሳሌ ፖሊስ ሰርቆ ያመለጠን ሌባ፣ አደጋ አድርሶ የሚፈረጥጥን መኪናና አሽከርካሪ አሳዶ ለመያዝ ከፍተኛ ጥቅም ትሰጣለች፡፡
ሄሊኮፕተሯን ከወዳደቁ ብረቶችና መሰል ቁሳቁሶች እንደሰራሃት ነግረኸኛል፡፡ ግን በጠቅላላ ለስራው ከ200 ሺህ ብር በላይ ማውጣትህን ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ይህን ሁሉ ወጪ ልታወጣ ቻልክ?   
ለጥናት እሄዳለሁ፣ ስሄድ የነዳጅ እና ሌሎች ወጪዎች አወጣለሁ፡፡ ማሽን ቤት፣ ብየዳ ቤት ሄደሽ ታሰሪያለሽ፡፡ አንድ እቃ ገዝተሸ ስትሰሪ፣ ያ ይበላሽና በሌላ ትቀይሪዋለሽ፡፡ ለምሳሌ ተሽከርካሪ ክንፏን ለመስራት አቢቲ የሚባለውን ውድ እንጨት በተደጋጋሚ በውድ ዋጋ ገዝቻለሁ በመጨረሻ ግን  ፋይበርግላስ መቀየሬን ነግሬሻለሁ። የሚገጣጠሙትን ጥርሶች ገዝተሸ አንዱ ከአንዱ አልግባባ ሲል ሌላ ትቀይሪያለሽ፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢንጂኑን በምፈልገው መጠን ለማምጣት የተለያዩ ሞተር ሳይክሎችን ለመግዛት ተገድጃለሁ፡፡ መጀመሪያ የገዛሁት ሞተር ሳይክል ኢንጂን አቅሙ ሲደክም ሌላ ገዛሁ፡፡ ከዚያም ሌላ ሞተር ሳይክል ገዛሁ፡፡ ሞተር ሳይክል እንደየአቅሙና ሁኔታው ከ7 ሺህ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር ይሸጣል፡፡ ይሄ ሁሉ ተደምሮ ከ200 ሺህ ብር በላይ ወጥቶበታል። በዚህ ላይ ደግሞ ጊዜና የጉልበቱን ነገር መዘንጋት የለብሽም፡፡
የፈጠራ ባለቤትነት መብት (Patent right) ማግኘትህን ሰምቻለሁ….
በትክክል! የፈጠራ ባለቤትነት መብት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ አግኝቻለሁ፡፡ ተቃዋሚ ይኖር እንደሆነ በሚል በጋዜጣ ከታወጀ በኋላ የፈጠራ መብቴ ተከብሮልኛል፡፡
በአዕምሮዬ የሚጉላሉ በርካታ የፈጠራ ስራዎች አሉኝ ብለሀል፡፡ ወደፊት ልትሰራ ካሰብከው አንድ ሁለቱን ልትነግረኝ ትችላለህ?
ስራው በምስጢር የሚቆይ ነው፤ ነገር ግን ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት ቀላል የሚያደርግ ነው፡፡ ምን እንደሆነ ለመናገር አልፈልግም፤ ሰርቼ ስጨርስ… ልክ እንደ ሄሊኮፕተሯ እውን ሳደርግ… ያን ጊዜ አብረን ብናየው ይሻላል፡፡
የፈጠራ ሥራዎችህን በትምህርት ለመደገፍ አላሰብክም?
ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ አስተማሪ ፊትለፊቴ ቆሞ አያስተምረኝ እንጂ እኔ ሁሌም ራሴን እንዳስተማርኩት ነው፡፡ ለምሳሌ ስለኮምፒዩተር ኪ-ቦርድ አሰራር ማወቅ ብፈልግ ኢንተርኔት ውስጥ እገባለሁ፡፡ አስተማሪ ከሚያስረዳኝ አምስት እጥፍ በላይ ኢንተርኔት ያስተምረኛል፡፡ ከዚያ ቤቴ ሄጄ ያንን ለመስራት ሙከራ አደርጋለሁ፤ ስለዚህ እኔ ራሴን እያስተማርኩ ነኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡
በመጨረሻ የምትለው ነገር ካለህ …  
የአንድን አገር መልካም ገፅታ ለመፍጠር ሁሉም በየዘርፉ ድርሻ አለው፡፡ አንቺ በጋዜጠኝነትሽ ስትበረቺ፣ እኔ በፈጠራዬ ስገፋ፣ መምህሩ በርትቶ ሲያስተምር፣ መሪዎች በአግባቡ ሀላፊነታቸውን ሲወጡ አገር መልካም ምስል ትይዛለች፡፡ ምሳሌ ልንገርሽ… ፎቶ ስታነሺ ወይም ስትነሺ አንቺ የምታይው ሙሉ ምስልሽን ነው፡፡ ነገር ግን ሜጋ ፒክሰሱ ትንንሽ ነጥቦችን ገጣጥሞ ነው ሙሉ ምስል ላንቺ የሚያሳይሽ። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የሚለውን ሙሉ ምስል ለማምጣት የሁሉም ሰው ድርሻ (ትንንሽ ነጥቦች) መገጣጠም ስላለበት፣ መንግስት ለየትኛውም ሙያ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፉን ቢቀጥል፣ ሙሉ የኢትዮጵያን ምስል ማየት እንችላለን፡፡ ሁሉም የድርሻውን ይወጣ። ሌላው በአገራችን ምርት ማመንና መኩራት አለብን። እኛ የሻይ ማሽን እየሰራን፣ ነጋዴዎች ከውጭ ያስገባሉ። ያገር ውስጥ ማሽን እንዳይገዛ እንቅፋት ይፈጥራሉ። መንግስት በእነዚህ ላይ ከፍተኛ ቀረጥ እየጣለ፣ በአገራቸው ምርት እንዲኮሩና የውጭ ምንዛሬ ያለአግባብ እንዳይባክን ማድረግ አለበት የሚል መልዕክት አለኝ። አመሰግናለሁ፡፡  

Read 6877 times