Print this page
Saturday, 14 June 2014 12:00

የአዲስ አበባውና የኢየሩሳሌሙ የግንቦት 20 መታሰቢያ

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የዛሬ 30 ዓመት 4ሺ ቤተ እስራኤላውያን በሱዳን በረሃ አልቀዋል

    ባለፈው ወር ግንቦት 20 የደርግ ሥርዓት የተገረሰሰበትና የፖለቲካ ስርዓቱ የተለወጠበት 23ኛ ዓመት ብዙ ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪ በታደመበት በስቴዲየም ተከብሯል፡፡ በዚሁ ቀን በእስራኤል ኢየሩሳሌም ውስጥም ቤተ እስራኤላውያን ዕለቱን አክብረውት ውለዋል፡፡ በእርግጥ የእነሱ የድል በዓል አልነበረም፡፡ የሃዘንና የፀፀት ቀን እንጂ፡፡
የዛሬ ሰላሳ አመት፣ በዚሁ ወርና ቀን ነበር በአስር ሺ የሚገመቱ ቤተ እስራኤላውያን የሱዳንንና የግብጽን በረሀዎች አቆራርጠው “ቅድስቲቱና የተስፋዋ ሀገራችን” ወደሚሏት እስራኤል ለመግባት በባዶ እግራቸው ጉዞ የጀመሩት፡፡ ሆኖም ያሰቡት አልተሳካላቸውም፡፡ አራት ሺ ያህሉ በሱዳን የገዳሪፍ ከተማ ውስጥ በነበረው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በረሀብና በውሃ ጥም የሚደርስላቸው አጥተው እስከወዲያኛው አሸለቡ፡፡ አሳዛኝ እልቂት ነበር፡፡
ከእልቂቱ የተረፉትም ቢሆን ዓመት በባተና ግንቦት በመጣ ቁጥር ይሄን አሳኝ የወገን ህልፈት ክፉኛ በተሰበረ ልብና በተጐዳ አዕምሮ ያስታውሱታል፡፡ ለዚህ ነው በህይወት የተረፉትና በእስራኤል የሚኖሩት ቤተ እስራኤላዊያን፤ የእድሜ ልክ የአሊያህ ምኞታቸውን ለማሳካት በሱዳን በረሀ ሲንከራተቱ፣ በክፉ ረሀብና ጥም ያለቁ ምስኪን ወገኖቻቸውን ለማሰብ እየሩሳሌም አቅራቢያ በሚገኘው የኸርዝል ተራራ ላይ በተሰራላቸው ልዩ የመታሰቢያ ቦታ ላይ የተሰባሰቡት - ግንቦት 20 ቀን 2006 ዓ.ም፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝና ርዕሰ ብሔሩ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፤  በአዲስ አበባው ብሔራዊ ስታዲየም ተገኝተው እለቱን በማስመልከት ለታደመው ህዝብ ንግግር እያደረጉ በነበረበት ሰዓት፣ የእስራኤል አቻዎቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁና ርዕሰ ብሔሩ ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬዝም ቀኑን አስመልክተው በኸርዝል ተራራ ላይ ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር በማድረግ ላይ ነበሩ፡፡ የንግግራቸው ጭብጥ ለየቅል ቢሆንም፡፡  
እንደመታደል ሆኖ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ስቴዲየም የተገኙት የግንቦት 20ን የድል ቀን ለመዘከር ነው፡፡ ለእስራኤሉ ቤንጃሚን ኔታንያሁ ግን ቀኑ በረሃ ለበረሃ ሲንከራተቱ በረሀብና በውሃ ጥም የወደቁ ወገኖቻቸውን አሳዛኝ እልቂት መዘከርያ ነበር፡፡ የቁጭትና የሀዘን ቀን!
በኸርዝል ተራራ ላይ ወናውን በቀረ የኢትዮጵያ የገጠር መንደር አምሳያ በተሰራውና በወቅቱ ካለቁት 4ሺ ቤተ እስራኤላውያን መካከል የ1500ዎቹ ስም ዝርዝር በተቀረፀበት ልዩ መታሰቢያ ሃውልት ፊት ለፊት ቆመው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፤ የዛሬ 30 ዓመት በቤተ እስራኤላውያኑ ላይ በደረሰው እጅግ አስከፊና አሳዛኝ እጣ ስሜታቸው እንደተነካ በግልጽ ያስታውቅባቸው ነበር፡፡ በእርሳቸው ንግግር መሃል ግን ከእርሳቸው ድምፅ የላቀ የለቅሶ ሳግ በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ያንን በተደጋጋሚ ይሰማ የነበረውን የልቅሶ ሳግ በመጠኑም ቢሆን የሚያስታግስ ተጨማሪ ንግግር ማድረግ ያስፈለጋቸው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በባለሙያ ተሰናድቶ የተሰጣቸውን ንግግር የሰፈረበት ወረቀት አጣጥፈው በቃላቸው መናገር ቀጠሉ፤ “ያ እጅግ አስከፊ ፍዳና መከራ እስራኤል ከደረሳችሁ በኋላም እንኳ እንዳለቀቃችሁ አውቃለሁ፡፡ አንዳንዶቻችሁ የእስራኤል ህይወት ከፈጠረባችሁ ከፍተኛ ችግርና መከራ ጋር አሁንም ድረስ እየታገላችሁ እንዳላችሁና እዚህ የተወለዱት ልጆቻችሁ የተሻለ ሃገር እንዲገጥማቸው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኙም አውቃለሁ፡፡ ጊዜ የራሱን ስራ ሰርቶ ሁሉንም ነገር እንደሚያስረሳችሁ ጨርሶ አልጠራጠርም፡፡ አመታት ባለፉ ቁጥር ችግሮቻችሁ እየደበዘዙ፣ ተገቢ ያልሆኑና መቋቋም የማይቻሉ  የዘረኝነትና የመድልኦ  ድርጊቶች ሁሉ ይጠፋሉ፡፡ በእናንተ ላይ የሚደርሱ ዘረኝነትና መድልኦዎችን አብረን እንዋጋቸዋለን፡፡ ሁሉም እንዲወገዱና አንዳቸውም እንኳ እንዳይቀሩ አድርገን እናሸንፋቸዋለን፡፡ ስሜታችሁን፣ ህመማችሁንና ምኞታችሁን ሁሉ እንደምረዳላችሁ ማወቃችሁ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በሁሉም መስክ የተሻለ ነገር እንድታገኙ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰድን ነው፡፡ በመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በጦር ሀይሉ፣ በፓርላማው፣ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በጤና ጥበቃ፣ ምን አለፋችሁ… እናንተ ገብታችሁ ልትሰሩ የማትችሉበት አንዲትም ቦታ እንኳ አትኖርም፡፡ በዚህ እመኑኝ፡፡”
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በከፍተኛ ሀዘን ይናጡ የነበሩትን ቤተ እስራኤላውያንን ለማጽናናት አስበው ያደረጉት ንግግር ግቡን እንዳልመታ ያወቁት ንግግራቸውን ጨርሰው ገና ቁጭ እንኳ ሳይሉ ነበር፡፡ የቤተ እስራኤሉ ለቅሶና ሳግ ተባብሷል፡፡ ምን ያድርጉ? ማንም ማንንም ሊረዳ ባልቻለበት በዚያን ክፉ ጊዜ ልጅ አባቱን፣ ሚስት ባሏን፣ ወንድም እህቱን እዚያ የሱዳን በረሃ ላይ ተነጥቋል፡፡
ወገን ወገኑን አጥቷል - በረሃብና በውሃ ጥም። እኒህም ለማልቀስና ለመፀፀት የበቁት በ”ዘመቻ ሙሴ” አማካኝነት ከሞት አፋፍ ለትንሽ ተርፈው ነው፡፡ ከሞት ተርፈው የተስፋይቱ አገር ወደሚሏት አገረ እስራኤል ቢገቡም ግን ዛሬም ከ30 ዓመት በኋላ እስራኤል ተስፋ አልሆነቻቸውም፡፡
ከጎንደር የገጠር ቀበሌዎች ተነስተው እጅግ ዘመናዊና አውሮፓዊ በሆነችው እስራኤል ለከተሙት ቤተ እስራኤላውያን፤ አዲሱ የእስራኤል ህይወት እንዴት ፈታኝ እንደሚሆን መገመት አዳጋች አይደለም፡፡
አብዛኞቹ ቤተ እስራኤላውያን ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ ክፉኛ ቢፈትናቸውም በዚህ ተማረው አላለቀሱም፡፡ ልባቸውን በቀላሉ እንዳይጠገን አድርጎ እጅጉን የሰበረውና የብራ መብረቅ የሆነባቸው ጉዳይ ሌላ ነው፡፡ “የቃልኪዳኗና የተስፋዋ ሀገራችን” እያሉ እድሜ ልካቸውን ሲመኟትና ሲያልሟት በኖሩት እስራኤል ውስጥ እየደረሰባቸው ያለውን የዘረኝነትና መድልዎ ጥቃት ነው መቋቋም ያቃታቸው፡፡ ለ30 ዓመት አንዳችም መሻሻል ሳያሳይ የቀጠለው ዓይን ያወጣ የዘረኝነትና መድልዎ ጥቃት ነው ብሶትና ምሬታቸውን ያከበደው፡፡
ከዛሬ ሀያ ሶስት አመት በፊት በወርሀ ግንቦት በተከናወነው “ዘመቻ ሰሎሞን” አማካኝነት አሊያቸውን ከፈፀሙት ቤተ እስራኤላውያን ይልቅ የ “ዘመቻ ሙሴ” ተሳታፊዎች በትንሽ በትልቁ ቶሎ ሆድ ይብሳቸዋል፡፡ እነዚህኞቹ በተለየ ሆደ ባሻ ሆነው ግን አይደለም፡፡  ወደ እስራኤል ለመግባት የተቀበሉት ፍዳና መከራ ሳያንሳቸው፣ የተስፋይቱን ምድር ከረገጡም  በኋላ ከፍዳና ከመከራ ባለመላቀቃቸው እንጂ፡፡
የሆኖ ሆኖ ግንቦት 20 ቀን በአዲስ አበባና በእየሩሳሌም የተከናወነው የመታሰቢያ ስነስርአት የተጠናቀቀውም በተመሳሳይ ሰአት ነበር፡፡ የስነ-ስርአቱን ፍፃሜ በተመለከተ ልዩነት አለ ከተባለ በአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም የተገኙት ነዋሪዎች ስነ-ስርአቱ እንደተጠናቀቀ ስታዲየሙን ለቀው ሲወጡ፣ በኸርዝል ተራራ የተሰባሰቡት ቤተ እስራኤላውያን ግን የመታሰቢያ ስነስርአቱ እንደተጠናቀቀ ከተራራው አልወረዱም፡፡ ያንን እጅግ ክፉ የመከራ ጊዜና በዚያ የበረሃ አሸዋ ላይ እንደነገሩ ቀብረዋቸው የመጡትን ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እያስታወሱ በቀላሉ መጽናናት አልቻሉም፡፡ በእነሱ ብርቱ ትዝታ ክፉኛ እየተናጡ እርስ በርስ አንገት ለአንገት ተቃቅፈው የሰቀቀን እንባ እያነቡ ረጅም ሰአት ለማሳለፍ ተገደዱ፡፡

Read 3124 times