Saturday, 14 June 2014 11:53

‘ብር አምባር’ ያያችሁ፣ ወዴት አላችሁ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ሰኔ ቀደመ ሰኞ ተከተለ! ለነገሩ ‘ሰኔና ሰኞ’ በቋሚነት ከገጠመ ስንት ጊዜያችን!
ስሙኝማ…በታሪካዊቷና ‘ታሪከኛዋ’ ከተማችን አንድ ክፍል ነው አሉ፡፡ እናላችሁ… ዕድሜያቸው ወርቅ ኢዮቤልዩን ‘አስከንድቶ’ ያለፈ ሴቶች (ቤተሰብና ሥራ ያላቸው!)  በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአካባቢው ዘንጠው ይቆማሉ አሉ፡፡ እና ‘ፒክ የሚያደርጓቸው’ ደግሞ… አለ አይደል… አንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ‘ዘርፈ ብዙ አገልግሎት’ እንደሚሰጡ ካወቁ አንድ ክረምት ብቻ ያለፋቸው አይነት ናቸው አሉ!
እኔ የምለው…“የምፈልገው ኤስከፒሪየንስና ዊዝደም ያላትን ነው…” ምናምን የምትሉ ወዳጆቻችን…እንግዲህ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም፡፡ …ቂ…ቂ…ቂ…ግን ግርም አይላችሁም…ለጁኒየሮቹ የታሰበ ለሲኒየሮቹ! እንዴት ነው ነገሩ…ምስር ይሄን ያህል ረክሷል እንዴ! (ሀሳብ አለን…ምስርን የሚወራበትን ሁሉ እውነት ይሆን ሀሰት አጥንቶ ለልማት የሚውልበትን ዘዴ የሚያጠና ኮሚቴ ይቋቋምልንማ!)
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደው “ይህንን አልሰማም…” ማለት አቅቶን ነው እንጂ “ምነው ጆሮዬ ይህንን ባያሰማኝ!”  የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙብን ነው፡፡ እንዲሀ አየነት ጉዶች የምነሰማው ኔነ ሰኞ በቋመኺነት ስለገጠሙ ሊሆን ይችላል!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል ‘ፍሬሽ’ ነገር…(የሚሰበር ‘ብር አምባር’ አይነት ነገር ማለት ነው፡፡) ጠፋሳ! ልክ ነዋ… ‘ብር አምባር’ ያው ‘ያልተነካ ፍሬሽ’ ነገር አይደል! እናላችሁ… በብዙ ነገሮች “…ሰበረልዎ ሸጋው ልጅዎ!” የሚያሰኝ ‘ብር አምባር’ እየጠፋብን ተቸግረናል!
ስሙኝማ…ዘንድሮ “ልጃችሁን ለልጃችን…” ለማለት ሽማግሌዎች ሲላኩ…ልጃችን ልጅ አገረድ ነች…” ምናምን የሚል ፉከራ እየቀረ ነው ይባላል፡፡ እንደውም ዘንድሮ… አለ አይደል… “እሷ እኮ አንገቷን የደፋች፣ ጨዋ፣ ሰው ቀና ብላ የማታይ፡ ቀሚሷ ከመርዘሙ የተነሳ ቁርጭምጭሚቷን የሚሸፍን…” ምናምን ማለት መፎከሪያ መሆኑ ቀርቷል፡፡
እናላችሁ…እንደ ዘንድሮ ‘ፍልስፍናችን’ እንዲህ አይነቷ መሄድ ያለባት ወደ ባል ሳይሆን ወደ ስነ ልቦና አማካሪዎች ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ… ደግነቱ ቁጥሩ ‘የሚያሰጋ’ ስላልሆነ የስነ ልቦና አማካሪዎቸ አይጨናናቁም፡፡ አሀ…ሰዉ ሁሉ ጨርቁን ጥሎ በሄደበት ዘመን፣ የሱሪ ቀበቶ ማሰሪያ ጭን ድረስ በወረደበት…የምን ቁርጭምጭሚት መሸፈን ነው!
ስሙኝማ…አጭር ቀሚስ የሚለብሱ እንትናዬዎች አልበዙባችሁም፡፡ ወጣቶቹም፣ በዕድሜ የገፉትም ‘ሰበብ የምትፈልግ’ ሚኒስከርት እየለበሱ ያልተሟሉ አንድ ሺ አንድ አምሮቶች እያሉን ሌላ ‘አምሮት’ ለምን ይጨምሩብናል!
(እግረ መንገዴን አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ…“በፊት ጊዜ ማዶ ቤት እንጀራ ሲጋገር ወይ ሹሮ ሲንደከደክ ሽታው ያውደን ነበር፡፡ ዘንድሮ…ምጣዱና ምድጃው አጠገብ ብንሆንም አይደለም ሽታው ሊያውደን እንፋሎቱም እየጠፋ ነው፡፡”)
እኔ የምለው…እንዴት ነው እግር ምናምን የሚባል ነገር አለ አይደል! እንዲሁ ‘ማጋለጡ’ አሪፍ አይደለማ! የምር እንነጋገራ… አንዳንዶቹ እንትናዬዎች እግዜር በፈጠረላቸው እግሮች ሳይሆን ከእንትን ካፌ ጁስ መጠጫ በተሰጣቸው ‘ስትሮው’ ላይ የሚራመዱ ይመስላሉዋ! መሳቀቁስ! ከአሁን አሁን “…ቅንጥስ አለች፣” ብሎ የሚሰጋ ስንት ልቡ ገና ያለጠጠረ ሞልቷል!
እኔ የምለው…‘የብር አምባር’ ነገር ከተነሳ… አለ አይደል… ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… ሙሽሪትና ሙሸራ ጫጉላ ቤት ይገባሉ፡፡ እንዲሆን፣ እንዲሆን ይሆኑና ‘የጂብራልታር አለት’ አለ ተበሎ ይታሰብበት ከነበረው ቦታ ሌሊቱን ሙሉ ቢፈለግ ይጠፋና ሙሽራው ይጠይቃል፡፡
“ብር አምባሩ የታለ?”
“አምባሩን ሁሉ አወላልቄ ኮመዲኖው መሰቢያ ውስጥ ከትቸዋለሁ!”
“እሱን አይደለም ያልኩሽ፣ ዋናው ብር አምባር የታለ?”
“ውስኪው ነካ አደረገህ እንዴ! የምን ብር አምባር ነው የምታወራው?”
እናማ እሱዬው ስለ ብር አምባር ‘ታሪካዊ ዳራ’ ቂ…ቂ…ቂ… ስዕላዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡ እሷም አዳምጣ ምን የምትለው ይመስለኛል… “እንደ እሱ አይነት ነገር መኖሩን ገና አሁን ከአንተ መስማቴ ነው!” ልክ ነዋ…“እስቲ አምጣው የ…ሸማ፣ እንድንስማማ…” እየተባለ ሰፈር እንዳልተቀወጠ ሁሉም ፉርሽ ሆኖ የሰርግ ማግስት፣ በር የምንደበድብበት ዘፈን ባጣነበት ዘመን ምን ብላ ትወቀው!
‘ብር አምባር’ ያያችሁ፣ ወዴት አላችሁ!
እንደውም ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወላጆች ለልጆቻቸው…“በአገራችን ውስጥ ከዕለታት አንድ ቀን ‘ብር አምባር’ የሚባል ነገር ነበር…” የሚል ተረት የሚነግሩን ይመስለኛል። (ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ዘንድሮ ብዙ ወጣቶች ‘ገና ጫማቸውን ማሰር ሳይለምዱ’ መስመር ስተው ለመሄዳቸው በዋናነት ከሚጠየቁት መሀል ወላጆች ናቸው!)
እና አዲስ ሀሳብ አግኝተን.. “ብር አምባር ሰበረልዎ!” ማለት ናፍቆናል፡፡
በአዲስ ስሜት፣ በአዲስ ተስፋ “አንተ ትብስ አንቺ ተባብለን ‘ብር አምባር ሰበረልዎ!’ ማለት ናፍቆናል፡፡
ከዲስኩራችን፣ ከጽሁፋችን፣ ከጥናታዊ ፊልሞቻችን ወዘተ… ያልተመቸንን ሁሉ “አፈር ድሜ ብላ!” አይነት ስድብ የማንሰማበትና የማናነብበት አዲስ ቀን መጥቶ… “ብር አምባር ሰበረልዎ!” ማለት ናፍቆናል!
ኤፍ ኤሞች ላይ አዳዲስ፣ ያልተነካ ‘ፍሬሽ’ ሀሳብ… ‘ብር አምባር’ እንፈልጋለን፡፡
‘ብር አምባር’ ያያችሁ፣ ወዴት አላችሁ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ጥያቄ አለን፣ አንስተነው ከሆነም እንድገመው፡፡ የሬድዮ አድማጮች ስልክ የሚደውሉት በዋነኛነት በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ወይም በሌላ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን ለመግለጽ ይመስለናል፡፡ ያሉት ነገር ለእኛ የሚተላለፈውም ጠቃሚ ነው ተብሎ ይመስለናል፡፡ እናማ ግራ የገባን እዚህ ላይ ነው፡፡
“መሠረት ከመሳለሚያ እያዳመጥኳችሁ ነው ብላለች፡፡”
“እነ ጉልማ ከጉለሌ ሰብሰብ ብለን እየሰማናችሁ ነው ብለዋል፡፡”
“ቹቹ ከቺቺንያ ባንኮኒዬን እያጸዳሁ እያዳመጥኳችሁ ነው ብላለች፡፡”
…አይነት ነገሮች ‘ሀሳብ መግለጽ’ ይባላሉ እንዴ! ልክ ነዋ… እነሱ እያዳመጡ መሆናቸው እኛን ምነ ‘ይኮነስረናል’! (ብዙ ነገሮች እየተለወጡ እንደሆነ ‘ሀሳብ መስጠት’ የሚለው ነገር ትርጉሙ ያለ አዋጅ ተለውጦ ሊሆን ይችላላ!) በመቶ ሺዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያዳምጡት ፕሮግራም ላይ.. “አምሀ ከአሜሪካ ግቢ እያዳመጥኳችሁ ነው ብሏል…” ትንሽ አያስቸግርም! (እንደ ‘አየር ሰዓት መሙያ’ ካልተቆጠረ በስተቀር ማለት ነው!)
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በቀደም የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ፈተና መጨረሻ ዕለት ምን ሆነ መሰላችሁ…ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ፈተናቸውን ጨርሰው የወጡት ልጆች የፈተና ወረቀታቸውን በጫጭቀው መንገዱን ሁሉ ጨረቃ አስመሰሉት፡፡ (ድሮ እንኳን ‘ጨረቃ ሲመስል’ ኤሌትሪክ ገመድ ላይ ነበር የሚንጠለጠለው! ቂ…ቂ…ቂ…)  እናላችሁ… በአካባቢው ያይ የነበረው ሰው በጣም እያዘነ ነበር፡፡ ደግሞላችሁ ልክ እንደ ሰፈር ህጻናት እየጮሁ እየዘለሉ አካባቢውን አምሰውት ነበር፡፡
እናማ…ይህን ሁሉ አይታችሁ እነኚህ ልጆች ከአራት ወይም ከአምስት ወር በኋላ ‘የኮሌጅ ተማሪዎች’ እንደሚሆኑ ስታስቡት…በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሌሎች ትምህርት ቤቶች የአሥረኛ ክፍል ተማሪዎችም የፈተና ወረቀታቸውን ቀዳደው በትነውት ነበር፡፡ አንድዬ ይመልሰው እንጂ ምን ይባላል!
እናላችሁ… የተፈጥሮ ‘ብር አምባር’ ከማግኘት ጭድ ውስጥ መርፌ ማግገኘት እየቀለለ የመጣ ቢመስልም በብዙ ጉዳዮች ‘ፍሬሽ’ ነገር፣ ‘ያልተነካ’ ነገር፣ አዳዲስ ሀሳቦች…በአጠቃላይ ‘የምንሰብረው ብር አምባር’፣  እንፈለጋለን፡፡
‘ብር አምባር’ ያያችሁ፣ ወዴት አላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5137 times