Saturday, 14 June 2014 11:53

“እኛ ኢትዮጵያዊያን ነብር ነን!”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

          ነፍስ አውቀን ጡጦ ሣንጥል ጀምሮ የምንሰማውና እስከ መቃብር የሚከተለን አንድ ቃል “ሕዝብ” የሚለው ነው፡፡ አንዳንዴ ቅፅል ተጨምሮበት፣ ሌላ ጊዜ ሌጣውን ሕዝብ እየተባለ ይወራል፡፡ ታዲያ እኛ በአፀደ ሥጋ ሳለን ብቻ አይደለም፤ የቀደመውም ትውልድ ከኛ በፊት፣ ወደፊትም እኛ በሌለንበት “ሕዝብ” ሳይባል ተውሎ አይታደርም፡፡ ሕዝብ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ፖለቲከኛው ሕዝብ ይከተለኛል፣ ሕዝብ ይደግፈኛል ሲል፤ አርቲስቱ በሕዝቤ ድጋፍ እኮራለሁ፤ ሕዝብ ነው ሀብቴ ይላል፡፡ ይሄንንም ሕዝቡ ያደምጣል፡፡
በ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግ በጠራው የድጋፍ ሠልፍ ላይ እንደ ብቅል የተሰጣውን ሕዝብ ያዩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ “ሕዝባዊ ማዕበል” ሲሉ ነበር የገለፁት። ግና በማግስቱ ቅንጅት ፓርቲ በጠራው ስብሰባ ላይ ያው ሕዝብ ካናቴራውን ቀይሮ በመምጣቱ ብዙዎችን አስደነገጠ። መለዮውን ቀይሮ በየትኛው ቡድን እንደሚጫወት ግራ ያጋባቸው አንዳንድ ሰዎች፤ “እንዴት ያለ ሕዝብ ነው?!” ብለው አፋቸው ላይ እጃቸውን ጫኑ፡፡
በደርግ ዘመን ይህ ሕዝብ “ሠፊው” የሚል ቅጽል ተጨምሮለት “ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ” ሲባል ኖሯል፡፡ ገዢዎቹ አብዮታቸውንም “አብዮትህ” እያሉ የራሱ እንደሆነ እንዲሰማው በስም ደረጃ ሲያሸክሙት ኖረዋል፡፡ ያ ሕዝብ ግን በየቤቱ ሲገባ እኔና እናንተ ነን። በአንድ ላይ የታሠረ ዕቃ ሲበታተን እንደ ማለት ነው፡፡
የኛ ሀገር ብቻ አይደለም ሕዝብ የሚባለው። የአሜሪካና የሶማሊያ እንዲሁም የሌላው አገር ሕዝብም ሌላ ስም የለውም፣ ያው ሕዝብ እንጂ። ታዲያ አንዳንዱ ሕዝብ ደግ፣ አንዳንዱ ጨዋ፣ ሌላው አስመሳይና አድርባይ ሊሆን ይችላል፡፡ አድርባይነት ከጨቋኝ መሪዎች ጨካኝ እርምጃ የሚፈጠር ማንነትን ጭራ ሥር የመቆለፍ አባዜ ነው፡፡ በልማድ ይሁን በሌላ ባላውቅም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ፣ ደግና ርሁሩህ ተደርጐ ይወራል። ይሁንና ይህ እውነት ደግሞ ከአንደኛው የሀገሪቱ ክፍል ወደ ሌላው ሲኬድ ይለያያል።
ብቻ አንዳንዴ “ሕዝብ” ብለን ይህን ያገራችንን ሕዝብ ስናየው መልኩ ሺህ ይሆንብናል፡፡ “ጀግና ሕዝብ” እንለዋለን፡፡ ያው ሕዝብ ደግሞ ጀግንነቱን የሸጠ፣ ሀገሩን ከጠላት ጋር ተስማምቶ ያስጠቃ ሲባል እንሰማለን። አሁን በቅርቡ እንኳን “ሕዝቡ ጀግና ነው” ያልኩት ጋዜጠኛ ወዳጄ፤ “የቱ ሕዝብ?” ብሎኛል፡፡ “እንዴ፤ ሌላ ምን ሕዝብ አለ፤ የኛ ሕዝብ ነዋ! ያሁኑን ባላውቅም የያኔው ጀግና ነው” ስለው “ጥቂት ጀግኖች ነበሩን በል እንጂ ሕዝቡ ጀግና አይደለም” ብሎ አስደነገጠኝ። ወዲያው ቀጠለና “ይህ ሕዝብ የምትለው ጣሊያን ጦርነቱን አሸንፎ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ፣ ከበሮ ጠፍሮ እልልታውን ሲያቀልጥ የሚያሳይ ማስረጃ አለኝ” ሲል አፋጠጠኝ፡፡ ኪሎዬ ቀነሰ! እኔስ ምኔ ሞኝ ነው… ጀግና የሚባለው ሕዝብ ሳይሆን በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ናቸው…ስል አሠብኩ ወይስ ሕዝቡ እንደነብር ብዙ መልክ ያለው ነው? “ይህ ሕዝብ ነብር ነው” የሚሉን ሲሰድቡን ነው ብዬ ደመደምኩ፤ (ዥንጉርጉር ቀለም ነው ለማለት ነው)
እውነትም ሕዝብን ጀግና የሚያሰኙ፣ ክንፍ ሆነውላት ይዘውት የሚበርሩ አሉ፡፡ ናፖሊዮን ፈረንሳይን የጀግንነት ዘውድ እንዳስጫናት፡፡ እንግሊዝን ቸርችል እንደታደጋት፡፡  
ባለፈው ሰሞን ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ፅፎት፣ አርቲስት ግሩም ዘነበ አሣምሮ የተረከውን የመሐመድ ዑስማን (ሚግ) የሕይወት ታሪክ አጣጥሜ አዳምጨው ነበር፡፡ ታዲያ የተፈጠረብኝን መሣከር በቃላት መግለፅ ያቅተኛል፡፡ መሐመድ ዑስማን (ሚግ) ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ቡድናችን ተመርጦ የመጣ ጐበዝ የእግር ኳስ ተጫዋች ነበር፡፡
የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ማለት ደግሞ የሀገር መልክ ነው፡፡ ላቡን ለሀገር ስም የሚያፈስስ፣ የወገን መጠሪያ ነው፡፡ ግን መሐመድ ያሳለፈው የመከራ መዐትና ስቃይ አንድ ሀገሩን የወከለ ሰው፣ በገዛ ሀገሩ ሊቀበለው የሚገባ አልነበረም። ደግ የሚባል ሕዝብ ባለበት፤ ያገር ልጅ መሀል የሚፈጠር ሰቆቃ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ያንን የመሰለ ጀግና የሚበላው ሲያጣ፣ የቤት ኪራይ መክፈል ሲያቅተውና ሲራብ፣ ኳስ ሜዳ ሲያዩት የሚያጨበጭቡ እጆች ለዳቦ እንኳ አልተፈቱለትም፡፡
እናም በሚያሳዝን ሁኔታ ዘንቢል እየተሸከመ መራራ ሕይወት ገፍቷል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንም ለዝቀተኛ ሥራ እንኳ ፊት አልሰጠውም፡፡ መሐመድ ዑስማን (ሚግ) “ደጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ” ሲባል፤ የሚስቅበት ጥርስ ቢኖረው እንዴት ይሆን የሚሳለቅበት? (ነብሩ ሕዝብ!)
ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ የስፖርት ጋዜጠኛው ንዋይ ይመር አቅርቦ አይቻለሁ።  በ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የብሔራዊ እግር ኳስ ቡድናችን ጐል ጠባቂ የነበረ ሰው፤ በችግር ምክንያት ስቴዲየም ገብቶ ኳስ የሚያይበት ዕድል ሲያጣ፣ እንኳ ትኬት የቆረጠለት የለም፡፡ እንደ ሸንኮራ መጥጠን ተፍተነዋል፡፡ ታዲያ የት ጋ ይሆን ደግነታችን? (ይሄ ሕዝብ አንዳንዴም እንዲህ ጨካኝ ነው፡፡)
ይህንን ተመጥጦ መጣልን ያዩ ሰዎች፤ ገንዘባቸውን ጠንቀቅ አድርገው ቢይዙ “ቋጣሪ” እያልን ቅጽል ስም ስንሰጣቸው ጆሮ ዳቦ የሚሉን ለዚህ ይሆን? ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ነገ የኔ ቢጤ ሆነን ከሚስቁብንና ከሚያባርሩን ዛሬ ጥሪታችንን ብንጠብቅ ይሻላል ብለው ሊሆን ይችላል፡፡
ይሄ ሕዝብ ስለዴሞክራሲ ያወራል፣ ዴሞክራሲን ይፈልጋል፣ ግን ራሱስ ዴሞክራት ነው? ብለን ስንፈትሽ ደግሞ ያንን ተፈጥሮ ውስጡ አናገኘውም፤ ብዙው አምባገነንነት ተጠናውቶት እናያለን፡፡ ራሱ የሚፈልገውን ውሸት፣ ከማይፈልገው እውነት ይልቅ ያፈቅረዋል።
ከወደደ ምክንያት አይሰማም፣ ከጠላም ምክንያቱን አይነግርም፡፡ አይኑን ይጨፍናል፡፡ አያይም አይሰማም። ስለዚህ እርሱ የወደደውን ካልወደድክ አለቀልህ! ጠመንጃ ባይኖረውም ጠጅ ቤት ያድማል፣ ቡና ቤት ያድማል፣ ዕድር ቤት ያድማል፡፡ “አብራችሁት ቡና አትጠጡ! ልጁን አትቅበሩ! የቀብር ቦታ አትሥጡት!…ሠላም አትበሉት!” ከማለት አይመለስም፡፡
ቤቱ ውስጥ ዴሞክራሲን አያውቅም፤ ያላወቀውን ማን ይናፍቃል? ተረቶቹ ሁሉ ዴሞክራሲን ይቃረናሉ። ስለ ሥልጣን፣ ስለ ንግሥና መጣፈጥ ያወራል፡፡ ደሞ መልሶ ዴሞክራሲን በፉጨት ሊጠራ ይሞክራል። ዴሞክራሲ አሜሪካ ተወልዶ፣ ኢትዮጵያ እንዲኖር “ጉዲፈቻ” ይጋብዛል፡፡ “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” ይላል፡፡ ደሞ መልሶ ሙስናን እጠላለሁ ይላል፡፡ መልኩ አይታወቅም፤ ይህ ሕዝብ ነብር ነው!
ይህ ሕዝብ ጨዋ ነው፤ ብልግና አይወድድም፤ ፈጣሪውን ሲፈራ ልክ የለውም ይባላል፡፡ ይኸው ሕዝብ ግን ወሲብ ላይ የተፃፉ መጽሐፍትን ዋጋ ሳይከራከር፣ ሂሣብ ሳይሟገት ሸምቶ ሲሄድ ታያላችሁ። ብቻ ሰው አይየው! ጀንበር ዘቅዘቅ ስትል መጥቶ የወሲብ ፊልሟንና መጽሐፍዋን ጉያው ውሽቅ አድርጐ ይሄዳል፡፡ “ባለጌ” የሚለው ፊት ለፊት የሚናገረውንና የሚታየውን ብቻ ነው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ እንደ ደራሲ ስብሀት ገ/እግዚአብሔር ዓይነት ሰዎች ላይ መራራ ወቀሳ ይሰነዝራል፡፡ አይኑን አልይ ይላል፡፡ ግና ከዚያ የባሰውን እርሱ ያደርገዋል፡፡ ሰባኪዎቻችን ቁምነገር ያወራሉ፣ እግዜርን ፍሩ ይላሉ፡፡ ሕዝቡ እልል ይላል፡፡ ታዋቂ ሰዎች ጠንቋይ ቤት ታዩ ከተባለ ዓይናችሁ ላፈር ይልና ያወግዛል። አንገታቸውን ያስደፋል፣ መድረክ ላይ ሲያያቸው ያሸማቅቃል፡፡ ይጠቋቆምባቸዋል። እርሱ ግን ጠያቂ የለበትም፡፡ በቡድን ጨዋ ሆኖ ያየነው ሕዝብ በተናጠል ይባልጋል፡፡ ሰንደሉን ገዝቶ ጫቱን ታቅፎ፣ ሽቶውን አንጠልጥሎ ድቤ መቺ ቤት ይሄዳል፡፡ ያው አውጋዡ ሕዝብ ጫማውን አውልቆ ሲገባ ታገኙታላችሁ፡፡ አንዳንዴ ሕዝቡ የቱ ጋ ነው? መልኩ ምን ዓይነት ነው? ብላችሁ ስታስቡ ቀለሙ ይጠፋባችኋል፡፡ ዥንጉርጉር ነው - እንደነብር!
ቀበሌ ስብሰባ ላይ ስለልማት ሥሩ እየተገታተረ፣ ላቡ ጠብ እስኪል ድረስ ያወራው ሕዝብ መልሶ፣ ልማት ላይ ሲያሽሟጥጥ ታያላችሁ! ይኸው ሕዝብ የወለደው መንግሥትም ራሱን ሕዝቡን መስሎ ቁጭ ሲል፣ ያሳደገው ሕዝብ ራሱ መልሶ የራሱን ሕይወት ይረግማል፡፡ መንግሥት ከሰማይ አይመጣ! ጉያው ሥር በራሱ አምሣል የቀረፀው ይኸው የሚያማርረው ሕዝብ ነው፡፡
ሕዝቡ የፖሊስ ሠራዊት እስኪመስል ድረስ ሌቦችን ካላሳደድኩ ይላል፡፡ ራሱ ግን በየቢሮው ይሠርቃል፡፡ ስለ ሕዝብ ስናወራ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተፃፈው የእሥራኤል ሕዝብ፤ ተሟጋች፣ እምቢ ባይና ስልቹ ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በመሪው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ በማጉረምረሙ ምክንያት እግዚአብሔር ሊያጠፋው ወስኖ ነበር።  ሙሴ ይመራው ዘንድ ሌላ ሕዝብ ሊሰጠው ፈቅዶ ነበር፡፡ ምናልባትም ቀድሞ ጣዖታትን ከሚያመልኩት ሕዝቦች በአዲስ ቃል ኪዳን እንደገና የራሱ ሊያደርግ ሳያስብ አልቀረም፤ ግን ሙሴ ይህንን ሃሳብ በይቅርታ እንዲለወጥ ፈለገ፡፡ ደግም ሆነ ክፉ፣ ጠማማም ሆነ ቀና ሕዝቡን ከማጣት ይልቅ ራሱን ከሕይወት መዝገብ መደምሰስ እንደዋነኛ ምርጫ ወሰደ።
እውነት ለመናገር ከእሥራኤል ሕዝብ ውስጥ ዋነኛ ጀግና እርሱ ነበር፡፡ ከነዐንን ሊጐበኙ ከሄዱት አሥራ ሁለት ሰላዮች መካከል ከኢያሱና ከካሌብ በስተቀር ጀግና አልነበረም፡፡
“በእነርሱ ፊት እኛ እንደ አንበጣ ነን፣ አሉ፡፡ ያ ጀግና ሕዝብ ፈራ፡፡ ግና ጥሩ መሪዎች ስለነበሩት ወደ ኋላ አልተመለሱም፡፡ ወደ ሕልማቸው ገሰገሱ፡፡ ሙሴ ታላቁ መሪ ሞተ፡፡ ከዚያ ኢያሱ ተተካ፡፡ ሕዝቡ ኢያሱን ልክ እንደ ሙሴ እንታዘዝሃለን አሉት፡፡
መሪ በመሪ ይተካል፡፡ ሕዝብን በሕዝብ መተካት ግን ከባድ ነው፡፡ ከራሱ ሕዝቡን ከፈጠረው በቀር ሕዝብን ማፍረስ የሚችል የለም፡፡ ሕዝብ መንጋ ነው፤ የመንጋውን አስተሳሰብ የሚለውጡት የመገናኛ ብዙሀን፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ተቋማት ናቸው፡፡ ጀግና ሳይሆኑ ጀግና ነኝ ብሎ ማቅራራት፣ ደግ ሳይሆኑ ደግ ነኝ ብሎ አዋጅ ማስነገር  የትም አያደርስም…በተለይ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነብር ነን!  

Read 2027 times